Connect with us

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በረሃብ አድማ ምትክ ደም ሊለግሱ ነው

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በረሃብ አድማ ምትክ ደም ሊለግሱ ነው
Photo: Facebook

ዜና

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በረሃብ አድማ ምትክ ደም ሊለግሱ ነው

የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ባለፈዉ ዓመት ማብቂያ የፀደቀዉን የምርጫ አዋጅ በመቃወም የሁለት ቀን የረሃብ አድማ ለመምታት የያዙትን ዕቅድ ሰረዙ። አድማው የተሰረዘው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍቃድ ባለመገኘቱ ነው ተብሏል። ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በምትኩ በነገው ዕለት በሰሞኑ ሁከት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የደም ልገሳ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

አዲሱን የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የስነ ምግባር አዋጅን በመቃወም የረሃብ አድማ ለመምታት የወሰኑት የ71 የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች ነበሩ።ፓርቲዎቹ ለ48 ሰዓት የሚቆይ የረሃብ አድማ ለማድረግ የመረጡት በአዲስ አበባ የሚገኘውን የአራት ኪሎ አደባባይ ነበር። ይህንንም በመሰረቱት አስተባባሪ ኮሚቴ በኩል ለአዲስ አበባ አስተዳደር ማሳወቃቸውን የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበበ ተናግረዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሙሉጌታ “አድማውን ለማድረግ ፍቃድ አላገኘንም። ወይ ከልከናል የለም፤ ወይ ፈቅደናልም የለም፤ ከህጉ ውጪ ነው” ሲሉ የዛሬው መርኃ ግብር ያልተካሄደበትን ምክንያት አስረድተዋል። “እንዲህ አይነት በውጭ ለሚከናወኑ መርኃ ግብሮች ጥበቃ መመደብ ስለሚያስፈልግ በህጉ መሰረት ለአስተዳደሩ አሳውቀናል” የሚሉት አቶ ሙሉጌታ የፍቃድ ጉዳይ የሚመለከተው የአስተዳደሩ አካል ቢሮክራሲውን በመጠቀም ፓርቲዎቹን እንደገፋቸው ገልጸዋል።

“በመጀመሪያ ደረጃ ቦታ ቀይሩ የሚል ምላሽ በቃል ስጡን። ‘አይ! እኛ ቦታ አንቀይርም፤ በያዝነው ቦታ እና ፕሮግራም ነው የምናደርገው፣ ሊፈቀድልን ይገባል’ ስንል የሚፈቅዱት አካል ደብዳቤ ካስገባንበት ቀን ጀምሮ ቢሮ ገብተው እንደማያውቁ ጸሀፊያቸው ነገሩን” ሲሉ የአስተባባሪ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ያጋጠማቸውን ችግር አስረድተዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የረሃብ አድማ እቅዳቸውን አለመሰረዛቸውን የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ ከአስተዳደሩ ግልጽ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ብቻ እንዲዘገይ መደረጉን ገልጸዋል።

ሰባ አንዱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የስነ ምግባር አዋጅን ለመቃወም ከረሃብ አድማ ሌላ ሌሎችም የሰላማዊ የትግል ስልቶችን ለመጠቀም መስማማታቸውን አስታውቀዋል። የአዳራሽ ውይይት እና ሰላማዊ ሰልፍ ፓርቲዎቹ በትግል ስልትነት ከነደፏቸው ውስጥ ይገኙበታል። ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ለረሃብ አድማ ያነሳሳቸው አዋጅ “የዜጎችን የመደራጀት እና የመሰብሰብ መብት የሚከለክል እና የፓርቲዎችን ህልውና የጨፈለቀ ነው” ሲሉ አምርረው ይተቹታል።
(ምንጭ:-የጀርመን ድምፅ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top