• አገሪቱን ለከፍተኛ ጥፋት እና ድህነት የሚዳርግ እጅግ አሳሳቢ ግጭት እየተስፋፋ ነው፤
• የጸጥታ ኀይሎች ቅድመ ግጭትን መሠረት ላደረገ መከላከል ትኩረት እንዲሰጡ ጠየቀ፤
• ሐሰተኛ ትርክቶች ለግጭት መንሥኤ ናቸው፤ ምሁራን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፤
• ሶሻል ሚዲያውን ለሰላም፣ አንድነትና ተግባቦት በመጠቀም ኹሉም የበኩሉን ይወጣ፤
በአገራችን እንኳንስ ሊደረጉ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጎሣንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በተለያዩ ክልሎች እየተስፋፉ መኾኑ በእጅጉ ያሳሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት ጸሎት እና ምሕላ እንዲደረግ ዐዋጀ፤ ከመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች አንሥቶ ኹሉም አካላት እና ዜጎች በየድርሻቸው ለአገራዊ ሰላም፣ አንድነት እና ተግባቦት የድርሻቸውን እንዲወጡ የሰላም ጥሪ አስተላለፈ፡፡
ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን በማካሔድ ላይ የሚገኘው ምልአተ ጉባኤው፣ የምሕላ ዐዋጁንና የሰላም ጥሪውን ያስተላለፈው፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ረፋድ፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ በሰጠው አስቸኳይ መግለጫው ነው፡፡
የበርካቶች ሕይወት ከጠፋባቸውና ንብረት ከወደመባቸው፣ ዜጎች ለከፋ እንግልትና እርዛት ከተዳረጉባቸው የቀደሙ ግጭቶች ባለመማር፣ አሁንም በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች እንዲሁም በሌሎችም ክልሎች፣ በአገራችን ላይ ከፍተኛ ጥፋትና ድህነት የሚያደርሱ መጠነ ሰፊ ግጭቶች መበራከታቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡
የአማራ እና የቅማንት፣ የአማራ እና የጉሙዝ፣ የአማራ እና የትግራይ፣ የሶማሌ እና የአፋር፣ የኦሮሞ እና የአማራ፣ ወዘተ. እየተባሉ የተደረጉ ግጭቶች ኹሉ፣ “ምክንያታዊ ባልኾኑ ጉዳዮች መነሻነት” የተከሠቱ እንደ ኾኑ ምልአተ ጉባኤው በመግለጫው አስፍሯል፡፡
ከእውነታ የራቁ፣ የሕዝቡን የአንድነት እና የአብሮነት ባህል የሚጎዱ፣ ታሪክን የሚያፋልሱ ሐሰተኛ ትርክቶች ለግጭቶች መንሥኤ እንደኾኑ ጠቅሶአል፤ የፖለቲካ ኀይሎች፣ የብዙኀን መገናኛዎች፣ የሶሻል ሚዲያው ተጠቃሚዎች እንዲሁም ምሁራንና የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላት ተቆጥበው፣ ከልዩነትና ግጭት ይልቅ ለሀገራዊ አንድነትና ተግባቦት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አስተላልፏአል፡፡
የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት፣ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ከመከሠታቸው በፊት፣ ቅድመ መከላከልን መሠረት ያደረገ የጸጥታ ሥራን በመተግበር የሰው ሕይወት መጥፋትንና የንብረት ውድመትን በማስቀረት የተጣለባቸውን ሓላፊነት እንዲወጡ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአስቸኳ መግለጫው ጠይቋል፡፡
ያለሀገር ሰላም እና አንድነት እንዲሁም ፍቅር እና ተግባቦት መኖር የማይቻል በመኾኑ፣ ኹሉም እንደየእምነቱ እና የሃይማኖቱ ሥርዐት፣ ከዛሬ ጥቅምት 13 ቀን ጀምሮ ለሦስት ቀናት ያህል በጸሎት እና በሐዘን፣ ስለ ሀገር ሰላም በአንድነት ለመናውን ለፈጣሪ ያቀርብ ዘንድ፣ ጸሎት እና ምሕላ እንዲያደርግ ማወጁን ምልአተ ጉባኤው በአስቸኳይ መግለጫው አስታውቋል፡፡
የአማራ እና የቅማንት፣ የአማራ እና የጉሙዝ፣ የአማራ እና የትግራይ፣ የሶማሌ እና የአፋር፣ የኦሮሞ እና የአማራ፣ ወዘተ. እየተባሉ የተደረጉ ግጭቶች ኹሉ፣ “ምክንያታዊ ባልኾኑ ጉዳዮች መነሻነት” የተከሠቴ እንደ ኾኑ ምልአተ ጉባኤው በመግለጫው አስፍሯል፡፡(ምንጭ ሐራ ተዋህዶ)