Connect with us

አርባ ዓመት ወደ ኋላ የተመለሰው የሃገራችን መሠረተ ልማት 

አርባ ዓመት ወደ ኋላ የተመለሰው የሃገራችን መሠረተ ልማት
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

አርባ ዓመት ወደ ኋላ የተመለሰው የሃገራችን መሠረተ ልማት 

አርባ ዓመት ወደ ኋላ የተመለሰው የሃገራችን መሠረተ ልማት 

(ፍቱን ታደሰ – ለድሬቲዩብ)

የሃገራችን የመሠረተ ልማት እድገት አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ የደረሰው በትውልድ ቅብብሎሽ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የየራሱን አሻራ አሳርፎበት መሆኑ እሙን ነው፡፡ አውራ ጎዳናዎች፣ ግዙፍ ድልድዮች፣ ህንጻዎች፣ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወዘተ. ዛሬ የሚገኙበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በየትውልዱ ያለፉ ኢትዮጵያውያን እውቀት፣ ሃብትና ጉልበት ተከፍሎባቸዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ታዳጊ አገር የመሠረተ ልማት ግንባታ ዋጋው ብዙ ነው፡፡ ት/ቤቶችን ከገጠር እስከ ከተማ ገንብቶ ለማዳረስ አልቻልንም፡፡ ዛሬም ተማሪዎች በዳስ ውስጥ የሚማሩባቸው ዝቅተኛ የሚባለውን መስፈርት (Standard) እንኳን የማያሟሉ የገጠር ት/ቤቶች በርካታ ናቸው፡፡ የህክምና ተቋማትም በአገራችን ዘመናዊ ህክምና ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ባለው ሂደት ውስጥ የህክምና ተቋማት የደረሱበት የእድገት ደረጃ እጅግ በጣም አዝጋሚና የህዝቡን ፍላጎት የሚያሟሉ አይደሉም፡፡ 

እንዲህ በአዝጋሚ እድገት እዚህ የደረሰውን መሰረተ ልማት ወያኔ በእብሪትና በዘረኝነት ታውሮ በጀመረው ጦርነት የራሱን ክልል ጨምሮ በአማራና በአፋር ክልሎች በት/ቤቶች፣ በጤና ተቋማት፣ በኤርፖርቶች፣ በመንገዶችና በድልድዮች ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡ የመሠረተ ልማት አውታሮቹ የወደሙት በጦርነቱ ሳይሆን የትግራይ ወራሪ ሠራዊት በተቆጣጠራቸው የአፋርና የአማራ አካባቢዎች በተለይ ት/ቤቶችንና የጤና ተቋማትን አስቦና አቅዶ በከባድ መሳሪያ እየደበደበ አፍርሷቸዋል፡፡ 

የሆስፒታል መገልገያ እቃዎችን፣ በውድ ዋጋ የተገዙ የህክምና መሳሪያዎችን መድሃኒቶችን ዘርፎ የወሰደ ሲሆን የደሴ ሪፈራል ሆስፒታልን ጨምሮ 40 ሆስፒታሎችን፣ 453 የጤና ጣቢያዎች፣ 1,850 የጤና ኬላዎች፣ 416 የግል ጤና ተቋማትን በድምሩ 2,759 የጤና ተቋማትን የሚችለውን ዘርፎ ቀሪውን አውድሟል፡፡

በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመትም እጅግ በጣም የከፋ ነው፡፡ ወራሪው ኃይል በአማራና በአፋር ክልል በያዛቸው አካባቢዎች ት/ቤቶችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል፡፡ በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ላይ ጥቃት ለማድረስ በሌሊት በፈፀመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ በመቶዎች የሚቆጠሩትን ሰዎች ሲገድል ትምህርት ቤቱን ደግሞ ሙሉ በሙሉ አውድሞታል፡፡ 

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት የትግራይ ወራሪ ኃይል በክልሉ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ4ሺህ በላይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አውድሟል፡፡ በሰሜንና በደቡብ ወሎ የሚገኙት ዩኒቨርስቲዎች ላይም ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ደሴና ኮምቦልቻ ካምፓስ፣ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ወልዲያና መርሳ ካምፓስ፣ መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መቅደላና መካነ ሰላም ካምፓስ ላይ የሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በሙሉ ከዘረፉ በኋላ ህንጻዎቻቸውን በመድፍ ደብድበው አፈራርሰዋቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መጠነኛ ሊባል የሚችል ጉዳት የደረሰበት የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የመካነ ሰላም ካምፓስ ብቻ ነው፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው የትግራይ ወራሪ ኃይል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በት/ቤቶች ላይ ባደረሰው ውድመት ምክንያት ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ ሆነዋል፡፡

በመንግስት እንደተገለጸው ከሆነ የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ብቻውን ለሰሜንና ለደቡብ ወሎ፣ ለሰሜን ሸዋ፣ ለአፋርና ለትግራይ በአጠቃላይ በአመት ለ10 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ግዙፍ የህክምና ተቋም ነበር፡፡ ይህ ተቋም ዛሬ በወራሪዎቹ ወድሟል፡፡ አንድ የደሴ ከተማ ነዋሪ እንደተናገረው መከላከያ ደሴን ለማስለቀቅ ባካሄደው ውጊያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የወራሪው ኃይል አባላት ሲገደሉ በርካቶች ቆስለው በየመንገዱ ወድቀው ነበር፡፡ 

የደሴ ህዝብ ምንም ያህል ቢበድሉት እንኳን ሰብአዊነት ተሰምቶት የቆሰሉትን እየተሸከመ ወደ ጤና ተቋማት ቢወስዳቸውም የቁስል ማከሚያ አልኮልና ፋሻ ሳይቀር ዘርፈው በመውሰዳቸው የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ እንኳን ሊያገኙ ባለመቻላቸው ብዙዎቹ ህይወታቸው አልፏል፡፡ በጦርነት ጊዜ ተዋጊ ኃይሎች ትምህርት ቤቶችን፣ የህክምና ተቋማትንና የኃይማኖት ተቋማትን እንዳይነኩ አለም አቀፍ ህግ ይደነግጋል፡፡ ይህንን ተላልፎ የሚገኝ አካል በጦር ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ወራሪው ኃይል በራሱም ክልል የአክሱም ኤርፖርትን በግሬደር ቆፋፍሮ አገልግሎት እንዳይሰጥ በማድረግ፣ የተከዜ ድልድይን በማፍረስና የሃይል ማመንጫውን በማፈንዳት ከፍተኛ ውድመት ፈጽሟል፡፡   

የትምህርትና የጤና ተቋማትን በአዲስ መልክ ከገጠር እስከ ከተማ ለማስፋፋት መሪ እቅድ ተይዞ ወደ ትግበራ የተገባው ከ40 ዓመት በፊት በ1973 ዓ.ም ነበር፡፡ በ40 ዓመታት ውስጥ በየገጠር ቀበሌዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ በወረዳ ደረጃ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በብዛት ተገንብተዋል፡፡ በእድሜያቸው ወደ ት/ቤት የሚገቡ ህጻናት ቁጥርም ከፍተኛ መሻሻል ታይቶበታል፡፡ ከአንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች መስፋፋት አልፎም በጣት ይቆጠሩ የነበሩት ዩኒቨርሲቲዎች በየክልሉ ተደራሽ መሆን ችለዋል፡፡ 

ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከፍሎበታል፡፡ ዛሬ በዘረኝነት የታወረው የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራ ክልል ብቻ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ3ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችንና 2,759 የጤና ተቋማትን አውድሟል፡፡ በርካታ ፋብሪካዎችንም ከጥቅም ውጭ አድርጓል፡፡ የትግራይ ወራሪ በትውልድ ቅብብሎሽ ተገነባውን መሠረተ ልማት ዘርፎና አውድሞ የአገራችንን የመሠረተ ልማት እድገት አርባ ዓመት ወደ ኋላ መልሶታል፡፡ ይህ ድርጊት ከአሸባሪነትም በላይ በአለም አቀፍ ህግ መሠረት የጦር ወንጀልም ነው፡፡ 

ምዕራባውያን ይህንን ወንጀል እያዩ እንዳላየ መሆንን መርጠዋል፡፡ በህዝብና በሃገር ላይ የሽብርተኝነትና የጦር ወንጀል የፈጸመ በህግ መጠየቅ ሲኖርበት “ተደራደሩ” የሚል ስላቅ በተለይ ከፍተኛ በደል ለደረሰበት የኢትዮጵያ ህዝብ ትርጉም አይሰጥም፡፡  

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top