Connect with us

አፍሪካዊ ነኝ ካልክ ይህን ጽሁፍ አንብብ !

(አፍሪካዊ ነኝ ካልክ ይህን ጽሁፍ አንብብ !)
Wendye Engida

ነፃ ሃሳብ

አፍሪካዊ ነኝ ካልክ ይህን ጽሁፍ አንብብ !

(አፍሪካዊ ነኝ ካልክ ይህን ጽሁፍ አንብብ !)

“Dr. Dambisa Moyo” ትባላለች! ብዙዎቻችሁ ላታውቋት ትችላላችሁ! እንደሷ ግን መታወቅ የነበረበት ከባድ ሚዛን አፍሪካዊ ሴት የለም! በትውልድ “ዛምብያዊ” ናት። እድሜ ለቤተሰቦቿ እዛች ደሃ ሃገር ውስጥ እንደምንም ተምራ ወደ አሜሪካ ለትምህርት ትሄዳለች። በመጀመርያ የኢኮኖሚክስ ማስተርሷን ከዕውቁ “Harvard University” ወሰደች። በዛ አላቆመችም!  ወደ እንግሊዝ ሃገር በመሄድ ከ”Oxford University” አራት አመት “ማይክሮ-ኢኮኖሚክስን” ቀጥቅጣ ተምራ ዶክትሬቷን ወሰደች።

 መቀመጫውን “New York” ባደረገው “Goldman Sachs” ለስምንት አመታት ወጥራ ሰራች! ቀላል መስሪያ ቤት እንዳይመስልህ ጌታዬ! “Goldman Sachs” መስራት ሎተሪ ነው! በአመት በቢልዮን ዶላሮች የሚያተርፍ ግዙፍ ባንክ እና የኢንቨስትመት አገልግሎት ሰጪ ስመጥር ተቋም ነው! ነጮቹ እራሱ ተፋልጠው ነው የሚገቡት! ሴትየዋ እዛ ብቻ አልሰራችም! ለሁለት አመታት “World Bank” ውስጥም ሰርታለች! አባዬ! ይችህ ሴት ይህንን ሁሉ ስታሳካ እድሜዋ ገና አርባዎቹ ውስጥ ነበር!

ከዛ ምን አደረገች መሰለህ?

ወደ 65 የሚጠጉ ደሃ ሃገራት በአካል በመሄድ “…..ለምን አንደማያድጉ? ለምን እንደሚለምኑ? ለምን እንደማያልፍላቸው?…” በደንብ አጠናች! የተማረችውን የኢኮኖሚክ ትምህርት እና በአካል የተመለከተቻቸውን ጥሬ ሃቆች በማሰባሰብ እ.ኤ.አ 2009 ላይ “Dead Aid-Why Aid is not working and How there is a better way for Africa?” የሚል ፀዴ መፅሃፍ አሳተመች! መፅሃፉ ከአንድ ሚልዮን ኮፒ በላይ ተሸጠ! ምዕራባዊያኑ ግን አበዱ፣ ተነጫነጩ፣ ወረዱባት፣ ተቿት፣ አጣጣሏት!

“Oxford University” ያስተማራት ነጭ ሼባ ፕሮፌሰር ሳይቀር አምርሮ ተቻት! “Bill Gates” “ሴጣን” ብሎ ሰደባት።

ለምን?

መፅሃፉ “….አፍሪካን ያቆረቆዛት የነጮቹ እርዳታ ነው! በፍጥነት መቆም አለበት!…” የሚል ስለሆነ!

ብርቱዋ “Dr. Dambisa Moyo” እንዲህ ትላለች!

“….ሶስት የእርዳታ(Aid) አይነቶች አሉ። የመጀመርያው “Humanitarian aid” ነው! ይህ ብዙ ግዜ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በጦርነት ለተፈናቀሉ /ለተጎዱ ሰዎች የሚሰጥ ነው! ይሄኛው እርዳታ ብዙም ችግር የለውም! ሁለተኛው እርዳታ ሃብታም ግለሰቦች ወይም ተቋማት የሆነን ማህበረሰብ ለመርዳት፣ ት/ቤቶችን ለማሰራት ወይም የጤና ተቋም ለመገንባት የሚሰጡት እርዳታ ነው! ይሄኛው እርዳታ ጥሩ ቢሆንም ለቁስለኛ የቁስል ማሸግያን ብቻ እንደመስጠት ነው! ለውጥ ያመጣል፣ ግን ዘላቂነት የለውም! ሶስተኛው፣ መጥፎው እና አፍሪካን ያቆረቆዛት የእርዳታ አይነት ደግሞ ከሃብታም ሃገራት ወይም ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ለደሓ ሃገራት የሚሰጥ እርዳታ ነው። 

የአፍሪካ ሃገራት ከቀኝ ገዢዎች ተላቀው እራሳቸውን ከቻሉ በኃላ ባሉት 50 አመታት ውስጥ ብቻ አፍሪካ ወደ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በእርዳታ መልክ ተለግሷታል! ነገር ግን እ.ኤ.አ 1970ዎቹ ላይ 10% ብቻ የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ ከአንድ ዶላር በታች የቀን ገቢ ነበረው! አሁን ላይ ግን ከ 70% በላይ የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ ከአንድ ዶላር በታች በቀን እንዲያገኝ ሆንዋል! አብዛኛው በእርዳታ መልክ የሚመጣው ገንዘብ የደሃውን ህይወት የቀየረ ሳይሆን አንባገነን መንግስታትን ያጠናከረ ነው! አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሃገር መሪዎች ይህንን ገንዘብ መዝብረዋል፣ ሰርቀዋል! “Aid model” የሚባለው አካሄድ የተጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጠረው አስከፊ ረሃብ በኃላ ነው!(የ 77ቱን ማለቷ ነው!) በወቅቱ እንደነ “Bob Geldof” እና “Bono”ን የመሳሰሉ ታዋቂ ነጭ ሙዚቀኞች “…አፍሪካ ተርባለች! እንድረስላት!…” በሚል የተሳሳተ መንገድ ብዙ የሙዚቃ ድግሶችን ለገቢ ማሰባሰቢያነት እያዘጋጁ ብዙ ሚልዮን ዶላሮችን ሰበሰቡ! ዝንብ ፊታቸውን የወረራቸው እና በጠኔ ለመሞት ጫፍ የደረሱ የቀነጨሩ ምስኪን የኢትዮጵያውያን ህፃናትን ፎቶ ለነጮቹ አሳዩ! የተሰበሰበው ያ ሁሉ ገንዘብ ግን በአብዛኛው በወቅቱ ለነበረው መንግስት የጦር መሳርያ መግዣነት ነበር የዋለው! ሙዚቃ ደጋሽ ነጮቹ ዝናን አተረፉበት፣ ብዙ ሽልማቶችን እና ክብሮችን አገኙበት! አፍሪካን ግን የረሃብ፣ የቸነፈር እና የሞት አህጉር ተደርጋ እስከወዲያኛው እንድትሳል አደረጉ!…”

ትቀጥላለች!

“….አፍሪካውያን በጠራራ ፀሃይ ወጥተው መሪዎቻቸውን የሚመርጡት የመረጧቸው መሪዎች ለሚሰሩት ስራ ሃላፊነትን እንዲወስዱ፣ ተጠያቂ እንዲሆን እና የሚመሩትን ህዝብ ሁለንተናዊ ህይወት እንዲያሻሽሉለት እንጂ ከአሜሪካ እና አውሮፓ ገንዘብ ለምነው እንዲቀልቡት አይደለም! የአፍሪካ መሪዎች መማር ያለባቸው የልመና ጥበብን ሳይሆን በራሳቸው መንገድ እንዴት ህዝባቸውን ከድህነት ማውጣት እንደሚችሉ ነው። የሚገርመው የአፍሪካን ችግር የሚያጠኑት ነጮቹ ናቸው! የአፍሪካ ኢኮኖሚ በምን መልክ መመራት እንዳለበት አቅጣጫ የሚሰጡን ነጮቹ ናቸው! ጥናታዊ ፅሁፍ የሚሰሩልን ነጮቹ ናቸው! ምን ያህል ገንዘብ እንደሚረዱንም የሚወስኑት እነሱ ናቸው! እርዳታ የአፍሪካ መሪዎች ዋነኛ ሃላፊነታቸውን እንዲዘነጉ እና እንዲሰንፉ አድርጓል! የአፍሪካ ሃገራት የእርዳታ ሱሰኛ እስኪሆኑ ዳርጓቸዋል። 

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሃገራት የአመት በጀታቸውን ሳይቀር የሚሸፍኑት ከእርዳታ በሚገኝ ገንዘብ ነው! ነጮቹ “…አፍሪካ በወባ በሽታ አለቀች!..” ብለው ብዙ ሚልዮን አጎበሮችን ገዝተው በእርዳታ ይሰጡናል! ነገር ግን ይህንን አጎበር በጥራት መስራት የሚችሉ የአፍሪካ የንግድ ተቋማት አሉ! ለምን ገንዘቡን ሰጥተዋቸው እነሱ እንዲያመርቱ አያደርጉም? ለምን የስራ እድል ለአፍሪካውያን አይፈጥሩም? አጎበሮቹን ግን የሚገዙት ከራሳቸው የንግድ ተቋማት ብዙ ሚልዮን ዶላሮችን ከፍለው ነው! ያ ገንዘብ አፍሪካ መጥቶ ገበያ ውስጥ ቢገባ ሁለንተናዊ ጥቅም ነበረው! ያንን ግን በጭራሽ አያደርጉም! የሚያሳዝነው በቀን ሶስት ሺህ እና በአመት 1 ሚልዮን አፍሪካውያን በወባ ምክንያት እስካሁን ያልቃሉ! ከዓለም 90% በወባ ምክንያት ሟቹ እዚሁ አፍሪካ ውስጥ ነው!

በአፍሪካ ትልቁ የደሓዎች መንደር ያለው የ”Kenya” ዋና ከተማ በሆነችው “Nairobi” ውስጥ “Kibira” የሚባል ቦታ ነው። እዚህ መንደር ውስጥ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ጥቅጥቅ ብለው የድህነት የመጨረሻ ጥጉን እያዩ ይኖራሉ! ሁሌም የሚደንቀኝ ከዚህ መንደር ትንሽ ርቀት ሄድ ስትል የ “United Nations Agency for Human Settlement” ዋና መቀመጫ ቢሮ ይገኛል! ይህ ተቋም የደሓዎችን ማህበራዊ ህይወት ለማሻሻል እና ሰዎች ምቹ መጠለያ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚሰራ ተቋም ነው፣ በየአመቱም በብዙ ሚልዮን ዶላሮች ፈሰስ ይደረጉለታል! ነገር ግን እዛው ከጎኑ ላሉት እንኳን ምንም አላደረገም! እርዳታ ደሓዎችን ይበልጥ ደሓ እያደረገ ነው! የአፍሪካ ሃገራት እድገት የተንቀረፈፈው በዋነኝነት በእርዳታ ምክንያት ነው! ረጂዎቹ ግን ተቃራኒውን እንድናስብ አድርገውናል። 

አፍሪካ በሙስና ብቻ ወደ 150 ቢልዮን ዶላር በአመት ታጣለች! 20% የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ በጠኔ ምክንያት የሞት አፋፍ ላይ ነው! 31% የሚሆኑ ከሰሃራ በታች የሚገኙ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አጥተው ቀንጭረዋል! ግማሽ ቢልዮን የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ አሁንም በመብራት እጦት ዳፈና ውስጥ ይኳትናል! 50% የሚሆነው አፍሪካዊ በኮሌራ እና ተቅማጥ የመያዝ እድሉ ሰፊ ነው። አንዲት አፍሪካዊ ሴት ከአሜሪካዊት ሴት ጋር ስትነፃፀር 231 እጥፍ በወሊድ ወቅት የመሞት እድል አላት!  25 ሚልዮኑ አፍሪካዊ የ “HIV” ታማሚ ነው። 600 ሚልዮኑ አፍሪካዊ ማንበብ እና መፅሃፍ የማይችል መሃይም ነው። ያልተረዳነው አፍሪካ የምትሻገረው በእርዳታ ሳይሆን በስራ ፈጠራ እና በካፒታል ነው።  ቻይና 850 ሚልዮን ህዝቧን ከደህነት አረንቋ ያወጣችው በእርዳታ ሳይሆን በራሷ ስራ ነው! በእርዳታ ያደገች/የበለፀገች አህጉር አይደለም ሃገር እንኳን የለችም! የሚገርመው አሜሪካ ከቻይና ገንዘብ ትበደራለች! ከዛ የተበደረችውን ደግሞ ለአፍሪካ በእርዳታ መልክ ትሰጣለች! አሜሪካ ምን ያህል ብታስብልን ነው ባክህ? የአፍሪካ ሃብት የሚመዘበረው በእርዳታ መጋረጃ ነው። 

ረጂዎቻችን “አፍሪካ እስከመቼ ትረዳ? ከዛስ ምን ትሁን?” የሚል ምንም እቅድ የላቸውም! ስለዚህ የአፍሪካ መሪዎች ለየሃገሮቻቸው የሚሰጠው እርዳታ ቋሚ እና መቼም የማይቆም አድርገው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል! የአፍሪካ መሪዎች የሃገራቸውን ኢኮኖሚ በምን መልኩ ፋይናንስ ማድረግ እንዳለበት አያውቁም! እርዳታ ቋሚ ገቢያቸው እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡ ተደርገዋል! ለምሳሌ አውሮፓም ሆነች አሜሪካ ለአፍሪካ ሃገራት እርዳታ ማድረግ የሚያቆሙበትን ቁርጥ ያለ የግዜ ገደብ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል! የአፍሪካ ሃገራት ከቀጣዮቹ አምስት አመታት በኃላ ምንም አይነት እርዳታ እንደማያገኙ ቢነገራቸው አህጉሪቷ ታድግ ነበር! ስራ ፈጠራ እና ኢንቨስትመት ላይ ታተኩር ነበር! ሃገራቱም እርዳታ ስለማያገኙ መውጫ እቅድ(Exit plan) አርቅቀው በግድ ይተገብሩ ነበር! ረጂዎቻችን ግን ይህንን መቼም አያደርጉም! መሪዎቻችንም ስለዚህ አያስቡም! “….10% አድጋችኃል! 12% አድጋችኃል!…” እያሉ ተቋሞቻቸውም አፍሪካን መሸወዳቸውን አያቆሙም!….” ትላለች “Dr. Dambisa Moyo”!

ጌታዬ! ከዚህ በላይ ከቀደድኩ ሙሉ መፅሃፉን መጨረሴ ነው! መፅሃፉን የማንበብ ፍላጎት ካላችሁ በውስጥ መስመር ለማቀበል ዝግጁ ነኝ! አንብብላት አትጎዳም ጌታዬ!

በመጨረሻም!

መፅሃፉን ካሳተመች በኃላ “Oxford” እያለች “Economics” ያስተማራት ያ ነጭ ሼባ ፕሮፌሰር እንዳብጠለጠላት ስትሰማ እንዲህ ነበር ያለችው!

“….ሃገራት የሚያድጉት በስራ ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና ገበያን መሰረት ባደረገ ፖሊሲ እንጂ በነጮች ምፅዋት፣ እርዳታ እና ችሮታ እንዳልሆነ ያስተማርከኝ አንተው መሆንህን ዘነጋኸው ወይ ውድ ፕሮፌሰር?….”

ጌታዬ! ልክ መፅሃፉ ሲጀምር እንዲህ ይላል!

“…..የተከበራችሁ የአውሮፓ መሪዎች እና ባለስልጣናት! አፍሪካ ውስጥ በጣም እየተሰቃየን ነው! እባካችሁ እርዱን! አፍሪካ ችግረኛ አህጉር ናት! ምንም መብት የለንም! ጦርነት እና ህመም አሰቃይቶናል! የሚላስ የሚቀመስ ነገር የለንም!… እናንተ ጋር መጥተን መማርና እንደ እናንተ መሆን አጥብቀን እንፈልጋለን!….”

ይህ ደብዳቤ የተገኘው ሁለት ህይወታቸው ያለፈ የ “ጊኒ” ዜግነት ያላቸው መጣቶች ኪስ ውስጥ ሲሆን ህይወታቸው ያለፈው ደግሞ ከ “ጊኒ” ተነስቶ ወደ አውሮፓ የሚሄድ የአንድ አውሮፕላንን ጎማ ተንጠልጥለው ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሲሞክሩ በመውደቃቸው ሳብያ ነው!

እና አያሳፍርም ወይ?

መልካም ምሽት፣ መልካም ቅዳሜ! ፍክት በሉ!

Wendye Engida  ገጽ የተወሰደ

ሄኖክ ሰጠኝ

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top