Connect with us

ጠላትን ማመን!

ጠላትን ማመን!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ጠላትን ማመን!

ጠላትን ማመን!

(ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)

በጦርነት ሂደት ውስጥ ተዋጊዎች ከሚፈጠርባቸው ወይም እንዲፈጠርባቸው ከሚደረጉ ሥነ ልቡናዊ ጫናዎች መካከል አንዱ ጠላትን ማመን ነው፡፡ የሚገድልህን፣ የሚያጠፋህንና የሚያወድምህን ጠላት መረጃዎች የመቀበልና የራስህን መረጃዎች የማጣጣል አባዜ፡፡ ጠላት በጦር መሣሪያዎቹ አማካኝነት ከሚያደርሳቸው ጉዳቶች በላይ ለጠላት የሚጠቅመው በሚጎዳቸው ወገኖች ዘንድ ለመታመን መቻሉ ነው፡፡

ጠላትን ማመን በሦስት ምእራፍ የሚዳብር አደገኛ ሥነ ልቡና ነው፡፡ የመጀመሪያው ምእራፍ ራስን መጠራጠር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጠላትን ማድነቅ ነው፡፡ ሁለቱ ተደምረው ጠላትን ወደ ማመን ያሻግሩናል፡፡ ራስን መጠራጠር የሁለት ነገሮች ውጤት ነው፡፡ የአፍራሽ ፕሮፓጋንዳ እና የተሳሳተ ግምገማ፡፡ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ከጠላት በኩል የሚሠነዘር ነው፡፡ በተደጋጋሚና ተጠየቃዊ በሆነ መልኩ የሚወርድ የፕሮፓጋንዳ ናዳ ሲሆን ዓላማው የቆሙበትን መሬት ማጠራጠር ነው፡፡

በተለይ ደግሞ ፍናፍንት ፕሮፓጋንዳ በጣም ጎጂ ነው፡፡ ፍናፍንት ፕሮፓጋንዳ ማለት በጥቂት እውነት ላይ የተመሠረተ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ይህ ፕሮፓጋንዳ ጠላትን ለማዳከምም ሆነ ወገንን ለመስለብ ሊውል የሚችል ነው፡፡ ሰይጣን ሔዋንን ‹ንግሥተ ሰማይ ወምድር› ብሎ ሲጠራት ከፊል እውነት ነበረው፡፡ ‹ንግሥተ ምድር› የሚለው እውነት ነው፡፡ ‹ንግሥተ ሰማይ› የሚለው ውሸት ነው፡፡: እርሷም የታለለችው በእውነቱ በኩል ውሸቱን አሾልኮ ስላስገባባት ነው፡፡ ፍናፍንት ፕሮፓጋንዳ በከፊል ወይም በጥቂት እውነት ላይ ተመርኩዞ የሚፈበረክ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ይሄንን ፕሮፓጋንዳ ራኬብም ተጠቅማበታለች፡፡ 

ራኬብ የኢያሪኮ ሰዎች ወደ ቤቷ መጥተው ‹ሁለቱ ሰላዮች ወደ ቤትሽ የታሉ?› ብለው ሲጠይቋት ‹አዎ ወደ ቤቴ ገብተው ነበር፤ ነገር ግን ወጥተው ሄዱ› አለቻቸው፡፡ የራኬብ ንግግር በከፊል እውነት ነው፡፡ ሰዎቹ ገብተው ነበር፡፡ ነገር ግን በላይኛው ደርብ ላይ በተልባ እግር ሥር ተሸሽገው ነበር እንጂ አልወጡም፡፡ የኢያሪኮ ሰዎች ግን ከፊል እውነት ስለነገረቻቸው ተቀብለዋት ወጥተው ሰዎቹን ሊያባርሩ ሄዱ፡፡

በሀገራችንም ወያኔ ከተጠቀመባቸው ፕሮፓጋንዳዎች አንዱ ፍናፍንት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ስለ መከላከያው፣ ስለ መንግሥት፣ ስለ ልዩ ኃይል፣ ስለ ፋኖ፣ ስለ ኤርትራ እና ስለ ራሱ ከሚነዛቸው ፕሮፓጋንዳዎች ብዙዎቹ በፍናፍንት ፕሮፓጋንዳ ስልት የተቀመሙ ናቸው፡፡ ወያኔ ሰዎችን ወደ ፕሮፓጋንዳ መረቡ የሚያስገባበት ጥቂት እውነታ ይይዛል፡፡ ልክ ዓሣ በብርብራ እንደ ማጥመድ፡፡ ብርብራው ለዓሣ ምግብ መሆኑ እውነት ነው፡፡ መቃጥኑ የተወረወረው ግን ዓሣውን ለመመገብ ሳይሆን ለማጥመድ ነው፡፡ 

ፍናፍንት ፕሮፓጋንዳም እንደዚሁ ነው፡፡ ወይም በወጥመድ አካባቢ ጥቂት ጥራጥሬ በትኖ ወፍ እንደ መያዝ ያለ፡፡ ‹በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ› የተባለው ለዚሁ ዓይነት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡

የኛ ሀገር የምግብ አቀራረብና የፈረንጆች ይለያያል፡፡ እኛ ዶሮ ወጥ ብለን ካቀረብን የምናቀርበው ዶሮ ወጥ ነው፡፡ ያውም ከነ ድስቱ፡፡ ቢበዛ አይብ ከጎኑ ይኖራል፡፡ ፈረንጅ ግን ዶሮ አሮስቶ ብሎ ካቀረበ፣ ግማሹ አትክልት፣ ግማሹ ድንች፣ ግማሹ ሩዝ፣ ቀሪው ነው ዶሮ፡፡ ስሙ ነው ዶሮ፡፡ ያውም አንዲት አጥንት፡፡ ፕሮፓጋንዳውም በዚሁ መልክ የሚቀናበር ነው፡፡ በፈረንጅ የዶሮ አቀራረብ፡፡

የዚህ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆነ አካል ራሱን ይጠራጠራል፡፡ ከራሱ ወገን የሚያገኛቸውን መረጃዎችና የራሱንም ጥንካሬ ይጠራጠረዋል፡፡ የቆመበትን መሬት ማመን ያቅተዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የባለ በጉ ታሪክ ነው፡፡ በግ ሊሸጥ እየጎተተ የሚሄደውን ሰው ለመቀማት የተስማሙ ሌቦች ራቅ ራቅ ብለው ጠበቁት፡፡ የመጀመሪያው ሌባ መንገድ ላይ አገኘውና ‹ምነው ውሻ ትጎትታለህ› አለው፡፡ በግ ሻጩም ተገርሞ ዝም ብሎ አለፈው፡፡ እልፍ እንዳለ ሌላው ሌባ አግኝቶት ያንኑ ጥያቄ ደገመለት፡፡ አሁን በግ ሻጩ ተጠራጠረ፡፡ በጉን በእጁ አሻሽቶ አረጋገጠ፡፡ እልፍ እንዳለ ደግሞ ሦስተኛው ሌባ አግኝቶት እየተደነቀ ‹ምነው እርስዎ ካልጠፋ ነገር ውሻ ወደ ገበያ ይጎትታሉ› አለው፡፡ ይሄኔ በግ ሻጩ ራሱን ተጠራጠረ፡፡ ‹እንዴት ሦስት ሰዎች አንድ ነገር ይነግሩኛል፤ ተሳስቼ በግ የያዝኩ መስሎኝ ውሻ አምጥቻለሁ ማለት ነው› ብሎ አመነ፡፡ ከዚያ ውሻውን ፈትቶ በግ ፍለጋ ተመለሰ፡፡ በጉም የሌቦች ሲሳይ ሆነ፡፡

ራስን መጠራጠር ማለት እንደዚህ ነው፡፡ ፍናፍንት ፕሮፓጋንዳ በድግግሞሹና በዒላማው ላይ አተኩሮ በመሥራቱ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት የቆምክበትን እውነት እንድትጠራጠረው ማድረግ ነው፡፡ እውነት ከክሥተት በላይ በመርሕ ላይ በመመርኮዝ የሚገኝ ነው፡፡ ለምሳሌ በጣልያን ወረራ ወቅት የኢትዮጵያ ጦር በጣልያን ጦር ተሸንፏል፡፡ ‹ኢትዮጵያ ተሸንፋለች› ወይም ‹ኢትዮጵያ አሸንፋለች› የሚለው ጉዳይ ግን የመርሕ ወይም የእምነት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተሸንፋለች ያሉ ለጣልያን አደሩ፡፡ 

ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ብለው ያመኑ ደግሞ መሣሪያቸውን ወልውለው በረሐ ገቡ፡፡ ከአምስት ዓመት ትግል በኋላም የኢትዮጵያን አሸናፊነት አረጋገጡ፡፡ ዐርበኞቹ እውነታቸውን እንዲጠራጠሩ ብዙ ፕሮፓጋንዳ በፋሽስት ጣልያን በኩል ተሠርቷል፡፡ አንዳንዶቹም በሂደት ተሸንፈው ተቀብለውት ከእውነታቸው ወድቀዋል፡፡ ሌሎቹ ግን ከሚያዩት ይልቅ የሚያምኑትን ተቀብለው አሸንፈዋል፡፡

ማሸነፍ የመርሕ ጉዳይ መሆኑን የሚያሳየን አንድ ጥሩ ምሳሌ የሰማዕታት ታሪክ ነው፡፡ ሰማዕታት በወደረኞቻቸው ፊት ቀርበው፤ በዓላማቸው ጸንተው፤ አንገታቸውን ሳይሰብሩ፣ ልባቸውን ሳይከፍሉ፣ የሞትን ጽዋ ጠጥተዋል፡፡ ያሸነፈው ማነው? የተሠዉት ሰማዕታት ወይስ ገዳዮቻቸው? ሰማዕታቱ በዓላማቸውና በመርሐቸው በመጽናታቸው የተነሣ ሞትን አሸንፈውታል፤ የጠላቶቻቸውን ዓላማም አክሽፈውታል፡፡ ሞትንም ክብር አድርገውታል፡፡ ለዚህም ነው የሰማዕታት ታሪክ የአሸናፊዎች ታሪክ የሚሆነው፡፡ 

በፍናፍንት ፕሮፓጋንዳ የተሰለበ እና ራሱን የተጠራጠረ ሰው መጨረሻው ክሥተት ተከትሎ ጠላቱን ማድነቅ ይሆናል፡፡ ለጠላትህ ተገቢው ቦታ መስጠት አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ጠላትን ማድነቅ ግን በሽታ ነው፡፡ ጠላትህን በራስህ መንገድ ማየት አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ራስህን በጠላትህ ዓይን ማየት ግን ራስን አውርዶ ጠላትን ማድነቅና ማግዘፍ ያስከትላል፡፡ ‹እነርሱ እንዲህ ሲያደርጉ እኛ ግን..› የሚል የተሰለበ ትንታኔ ውስጥ ይጥላል፡፡ ባዶ እጁን የቆመውን ጠላትህን አንተው በኅሊናህ መሣሪያ ታስጣቀዋለህ፤ ታጀግነዋለህ፤ ተአምር ፈጣሪ ታደርገዋለህ፡፡ አለቀልህ ሲልህ አለቀልኝ ትላለህ፤ ጨረስኩት ሲልህ አለቀ ትላለህ፤ ደረስኩ ሲልህ መጣ ትላለህ፤ በመጨረሻም ትፈራዋለህ፡፡ ከፈራኸው ደግሞ ፍርሃት ወደሚወልደው ደካማ እምነት ትገባለህ፡፡ ያም ጠላትን ማመን ነው፡፡

ጠላቱን ያመነ ሰው ራሱን በጠላቱ መመዘኛ ወደ መገምገም ይገባል፡፡ በጠላቱ ዕቅድ ይመራል፡፡ ስለራሱ ከጠላቱ ለመስማት ልቡን ይሰጣል፡፡ ‹ለምን እንዲህ ሆነ?› ብሎ ሲጠይቅ ለዚያ ሐሳቡ መነሻው የጠላቱ መረጃ ይሆናል፡፡ ነገሮችን የሚበይንለት ጠላቱ ይሆናል፡፡ በመጨረሻ ማሰቢያውን ጠላቱ ይቆጣጠረዋል፡፡ 

ነገሮችን የሚሰይመውና ቅርጽ የሚሰጠው ጠላት ይሆናል፤ በህልውና ዘመቻው ወቅት የጦርነቱን ባህሪይ፣ ውጤት፣ የአሸናፊነት መለኪያና ድል በተመለከተ በጠላት ብያኔና ስያሜ ለመተንተን የሚሞክሩ ወገኖች የዚህ ተጠቂ ነበሩ፡፡ አጠቃላይ የጦርነቱን መገለጫ ከቦታ መያዝና መለቀቅ አንጻር ብቻ እንዲታይ ያደረገው ይሄ በሽታ ነበር፡፡

አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎችን በተመለከተ አንዱ የገባንበት አረንቋ ይሄው ጠላትን የማመን በሽታ ነው፡፡ ከጠላቶቻችን ጋር መወገናቸውን እያወቅን እንኳን ልባችን ሊያምናቸው ይዳዳዋል፡፡ ተሰልበናልና፡፡ ጀግና ሕዝብ ግን የሚያምንበትን ይሠራል፤ የሚሠራውንም ያምናል፤ ራሱንም ያምናል፡፡ ጠላቱን ግን ይጠራጠራል፡፡ በክሥተት ሳይሆን በመርሕ ላይ አቋም ይይዛል፡፡

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top