Connect with us

ጎንደር በአታ የአቋቋሟ ዩኒቨርሲቲ

ጎንደር በአታ የአቋቋሟ ዩኒቨርሲቲ
ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

ጎንደር በአታ የአቋቋሟ ዩኒቨርሲቲ

ጎንደር በአታ የአቋቋሟ ዩኒቨርሲቲ

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከአርባ አራቱ ታቦታት አንዷ የሆነችውና በቀድሟዋ መናገሻ መዲና ስለምትገኘዋ የጎንደሯ በአታ ማርያም የአቋቋማ ዩኒቨርሲቲ ሲል በተለይም በአብነት ትምህርት ብዙ ሊቃውንትን ያፈራችውን ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን አስመልክቶ ለዛሬ እንዲህ ያጋራናል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

ጎንደር በአታ፤ ደብረ ኃይል ወ ደብረ ጥበብ፣ እንደ ስሟ ናት፡፡ የተከሏት መናኔ መንግሥት ተክለሃይማኖት ናቸው፡፡ ዐጼ ተክለ ሃይማኖት ምንም እንኳን ዐጼ ተብለው ቢነግሡም ስልጣኑን ከጀርባ ይዘውሩት የነበረው ስኡል ሚካኤል ነበሩ፡፡ መንፈሳዊው ንጉሥ ዘመናቸው አበሳ ስልጣናቸው አልጸና ሲል በነገሡ በሁለተኛ አመታቸው በአታ ማርያምን ተከሉ፡፡

በ1765 ዓ.ም. ለተተከለችው በአታ የንጉሡ የቅርብ ሰውና መንፈሳዊ አባት አባ አውሴ ዋናው ባለታሪክ ናቸው፡፡ ጽላቷን ያስመጡት እሳቸው ሲሆኑ ቀድሞውኑም ቢተክሉ ብለው ምክር የሰጡ ናቸው ይሏቸዋል፡፡

ከዋልድባ አፈር አስጭነው በ1763 በአታን ማሳነጽ ጀመሩ፡፡ በ1765 ሥራው ተጠናቀቀ፡፡ የደብሩን አለቃ ስም መልአከ ኃይል አሉት፡፡ በወቅቱም 227 የብሉይ፣ የሐዲስ፣ የዜማ፣ የቅኔ መምህራን መደቡባት፡፡ በአታ ከጅምሯ የሊቃውንት ማእከል እና የእውቀት ቦታ ሆነች፡፡

ዛሬ ታህሳስ ሶስት ቀን ይህቺ ስፍራ ልዩ ናት፡፡ የሚገርመው ግን 250 አመት በዚህ መንፈስ ድባብ አለች፡፡ ገና ያኔ በመናኔ መንግሥት ተክለሃይማኖት ዘመን ታህሳስ ሶስት በአታ ከእሷ አልፎ የጎንደር ጌጥና ድምቀት ነበረች፡፡

እንድ ቀደምት ጥናቶች ከየሀገሩ ሊቃውንቱ አመት ጠብቀው ታህሳስ በገባ በሶስተኛው ቀን በአታ የሚመጡት ቃለ እግዚአብሔሩ ልዩ፣ መንፈሳዊ ሥርዓቱ ደማቅ፣ የሊቃውንቱ ቅኔና ዜማ የማይገኝ ስለነበረ ነው፡፡

በአታ የአቋቋም ዩኒቨርሲቲ ናት፡፡ ይህ የአቋቋም ትምህርት ቤት ከደብሯ ታሪክ ጋር እኩል ዘመን ያለው ቀደምት ተግባር ነው፡፡ ታምራት ወርቁ የተባለ ጸሐፊ ቀኝ ጌታ ዘርይሁንን ጠቅሶ እስከ 1845 ዓ.ም. አስራ አምስት መምህራን በአቋቋም ቤት ወንበሩ መተካካታቸውን ይነግረናል፡፡

ከበአታ መምህራን መካከል ሀገር ስማቸውን ገና ሲሰማ የሚያውቃቸው አንዱ ሰው አለቃ ገብረሃና ናቸው፡፡ ከዐጼ ቴዎድሮስ በኋላ ደግሞ አሁን እስከአሉት መምህር አስር ሊቃውንት የአቋቋም ቤት ወንበሩን ተተካክተውበታል፡፡

አሁን ያሉት መምህር መጋቢ አዕላፍ ሄኖክ ወልደ ሚካኤል ናቸው፡፡ በታች ቤት ዜማዋ የምትታወቀው በአታ ከዝማሜ፣ ቁም፣ መረግድ፣ ጽፋት፣ አመላለስና ወረብ ጋር ስሟ ገኖ፣ ክብሯ ከፍ ብሎ እየኖረ ነው፡፡

ደብረ ጠቢባን በሚል ስም የምትታወቀው የጠቢባኑ መቀመጫ ታላቋ ደብረ ኃይል በአታ ማርያም በፈዋሽ ጠበሏ ስሟ ገኗል፡፡ የጥንቱ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን መቅደስ ላይ ጥንታዊው የኢትዮጵያ የአሣሣል ጥበብ ያረፈባቸው ቅዱሳት ሥዕላት ይገኙበታል፡፡

የተጠቀምኩትን ፎቶ ያገኘሁት እዚሁ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ነው፡፡

 

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top