Connect with us

መያዝ፣ ማጽናት፣ መጨመር

መያዝ፣ ማጽናት፣ መጨመር
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

መያዝ፣ ማጽናት፣ መጨመር

መያዝ፣ ማጽናት፣ መጨመር

(ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)

የማንኛውም ድል ጉዞ ይሄው ነው፡፡ መጀመሪያ የሚቻለውን ትግል ሁሉ አድርጎ ድሉን መጨበጥ ነው፡፡ ከማንኛውም ነገር ሁሉ ሀልዎት ይቀድማልና፡፡ በሌለ ነገር ላይ ምንም ማድረግ ስለማይቻል፡፡ የአንድ ነገር በትግልም ሆነ በዕድል መገኘት ለመቆየቱ ዋስትና አይይለም፡፡ አዳም ገነትን ያህል ቦታ ነበረው፡፡ ያቃተው ይዞ መቆየት ነው፡፡ ከማግኘት ባልተናነሰ ከባድ ትግልና መሥዋዕትነት የሚያስፈልገው አጽንቶ ለማቆየት ነው፡፡

 ኢትዮጵያውያን ነጻ ሕዝብ ለመሆን ከከፈልነው ዋጋ በላይ ነጻነታችን ይዘን ለመኖር የከፈልነው ዋጋ ይበልጣል፡፡ ለሺዎች ዘመናት የተከፈለው ዋጋ ነጻ ለመሆን ሳይሆን ነጻነትን አጽንቶ ለመቆየት ነው፡፡ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ከሺ ዘመናት በፊት እንደ እኛ ነጻ ሕዝቦች ነበሩ፡፡ በመካከል የተለያየነው ነጻነትን አጽንቶ በመያዝና ባለመያዝ ጉዳይ ነው፡፡

‹በቋንቋዎቻችን ውስጥ ‹maintain› ለሚለው ቃል መሳ ቃል የለውም ይባላል፡፡ ይህም ማለት እንደ ሐሳብ አልዳበረም ማለት ነው› የሚሉ ሊቃውንት አሉ፡፡: ይሄን ሐሳብ ለመግለጥ የምንጠቀመው ‹ጥገና› የሚለውን ቃል ነው፡፡ ጥገና ደግሞ ከፈረሰ ወይም ከተጎዳ በኋላ መልሶ መሥራትን የሚያመለክት እንጂ ‹ማንበርን› ወይም ይዞ ማቆየትን የሚያመለክት አይደለም ነው ክርክሩ፡፡ በታሪካችን ውስጥ ዘላቂነት አንዱ ፈተናችን ሆኖ ይታያል፡፡ ሥልጣኔዎቻችን ሲጀመሩ፣ ሲያብቡና ሲከስሙ ይታያሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ያገኘናቸውን ድሎች በተገቢው መንገድ አጠናቅቆ፣ ቋጭቶና ጠብቆ ወደ ሌላ ምእራፍ የማሸጋገር ፈተና ታይቶብናል፡፡ 

የአድዋ ዘመቻ፣ የአምስት ዓመቱ ወረራ መቀልበስ፣ የዚያድ ባሬ ወረራ መቀለበስ፣ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት፣ የጥቅምት 24ቱ የህልውና ዘመቻ በሚገባ ተጠብቀወና ተቋጭተው ወደ ሌላ ምዕራፍ ባለመሸጋገራቸው፣ ድሎቹ ከዕድል ይልቅ ፈተና ያስከትላሉ፡፡ ያገኘናቸውን ድሎች ቋጭተን ለዘለቄታው ይዘን ከማቆየት ይልቅ ነገር ዓለሙን የመተውና እንዳልተፈጠረ አድርጎ የመርሳት አባዜ አለብን፡፡

ድል ብቻውን ውጤት አይሆንም፡፡ አንድ ሰው የ12ኛ ክፍል ፈተናውን በጥሩ ውጤት ማለፉ ብቻ የነገውን ጉዞ አያቃናለትም፡፡ በውጤቱ መሠረት የሚገባበት ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብቶም የሚማርበት ዐቅም ያስፈልገዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል ውጤቱን ወደ ዩኒቨርሲቲ ዕድል ካልቀየረው፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጥሩ ውጤት ካላመጣው ተማሪ ጋር ኑሮው እኩል መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዲያውም ጥሩ ውጤት ካላመጣው ተማሪ ይልቅ፣ ጥሩ ውጤት አምጥቶ ባለበት የቆመው ተማሪ ንዴትና ብስጭቱ፣ ተስፋ መቁረጡም የባሰ ይሆናል፡፡ ድልም እንደዚህ ነው፡፡ የመገኘቱ ዋጋ እየጨመረ ካልሄደ እየወረደ ይሄዳል፡፡ እየወረደ ሲሄድ ደግሞ ጭቅጭቅና ንትርክ፣ ማናናቅና ማንኳሰስ ይከተላል፡፡

አሸባሪው ሕወሐት በተባበረው የኢትዮጵያውያን ክንድ ተመትቶ ከወረራቸው ቦታዎች እየወጣ ነው፡፡ የዛሬ ሁለት ሳምንት አካባቢ ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር ብቻ እንኳን ብናየው ያገኘነው ታላቅ ድል ነው፡፡ ይሄን ድል ግን መጀመሪያ ማግኘት፣ ቀጥሎም ማጽናት፣ በመጨረሻም ማብዛት ያስፈልጋል፡፡ የጦር ሜዳ ድል በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በትርክታዊ ድል ካልታገዘ በኮሜዲ ተጀምሮ በትራጄዲ ይጠናቀቃል፡፡ በ‹ሃይ› ተጀምሮ በ‹ዋይ› ያልቃል፡፡ ይሄንን በጁንታው ላይ ያገኘነውን ድል አጽንተን መያዝ አለብን፡፡ በምንም መልኩ ተመልሶ ከእጃችን እንዲወጣ ዕድል መስጠት የለብንም፡፡ 

ድል እንደ ጽዋ በየተራ መምጣት የለበትም፡፡ ሦስት ጊዜ እንደተበላ ዋንጫ እዚያው መቅረት አለበት እንጂ፡፡ ሦስት ጊዜ የተበላ ዋንጫም ቢሆን በአያያዝ ችግር ተወስዶ ያውቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብራዚል ምስክር ናት፡፡

ይሄ ድል የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንደ አርማታ አጠንክሮ፣ መከላከያችንን እንደ ካስማ ተክሎ፣ ኢኮኖሚያችንን ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆ፣ አሸባሪው ሕወሐት ሕግ፣ መዋቅርና አሠራር አድርጎ የተከላቸውን አረሞች ነቅሎ፣ በውስጣችን ያለውን ባንዳ አጽድቶ፣ የላይ ፈሪ የታች ፈሪ የሚሉትን ባለ ሥልጣናት ልክ አስገብቶ፣ የፖለቲካ ባህላችንን አቃንቶ፣ የኮሙኒኬሽን መንገዳችንን አስልቶ፣ ካልሄደ ‹ተወለደ – ሞተ› ይሆናል ታሪኩ፡፡ 

ድሉን ጠብቀን፣ እንደ ዶላር እየመነዘርን ከተጠቀምንበት፣ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረችውን አሜሪካ፣አፍሪካ ውስጥ እንድንፈጥር ዕድሉን ወለል አድርጎ ከፍቶልናል፡፡ካልሆነ ግን ‹ሰዶ ማሳደድ ካማረህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ› ነው፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top