Connect with us

ጋሼና ምሽጉ ፥ እንደ ገል ሲሰበር…

ጋሼና ምሽጉ ፥ እንደ ገል ሲሰበር ባንዳ ሲነፋረቅ ፥ አገር ስትስቅ ነበር
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ጋሼና ምሽጉ ፥ እንደ ገል ሲሰበር…

ጋሼና ምሽጉ ፥ እንደ ገል ሲሰበር

ባንዳ ሲነፋረቅ ፥ አገር ስትስቅ ነበር

(አሳዬ ደርቤ ~ ለድሬ ቲዩብ)

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ጋሼና ማዶ ስንደርስ ጠላት የሚመካበትን ምሽግ ሰባብረው እናት አገራቸውን አሸናፊ ለማድረግ የቋመጡ ጀግኖች፡-

‹‹የእናት ኢትዮጵያ ፥የድል ማዕረግ

ይታያልና፥ ጋሸና ምሽግ

እባክህ ጋሼ ፥ አገረ ገዢው

በል ሸኘኝና ፥ ልምጣ ፈንግየው›› በሚል ሽለላ ነበር የተቀበሉን፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ጠላትን ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ ውስጥ ግንባር ቀደም በመሆናቸው የሚታወቁት አቶ ወርቁ አይተነውና በላይነህ ክንዴ ከመላው ሠራዊትና አብረዋቸው ከተሰለፉ ታዋቂ ሰዎች መካከል ቆመው እንዲህ እያሉ ጦሩን ያበረታታሉ፡፡

‹‹የከሃዲን ክንድ- የባንዳን ምሽግ

መስበር ካልቻለ ፥ ሀብት ምን ሊያደርግ?

አሞሌ እስኪሆን ፥  ጠላቷ ሟሙቶ

ለነፍስ አንሳሳም ፥ ለሃብት ቀርቶ››

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከባለሃብቶቹ ጋር የጦር መሪዎችን እና ታዋቂ ሰዎችን ሰላምታ ከሰጡ በኋላ የጦር መነጽራቸውን ዓይናቸው ላይ ሰክተው ጠላት ያደፈጠበትን ምሽግ እየተመለከቱ ‹‹አዋጊያቸው ማን ነው›› ብለው ሲጠይቁ ከጎናቸው የቆመው ጄኔራል ‹‹ጻድቃን ይባላል›› የሚል መልስ ሰጣቸው፡፡

እሳቸውም ጊዜ ወስደው ከጦር መሪዎቻቸው ጋር ከተመካከሩ በኋላ ‹‹ጻድቃንንም ሆነ ሠራዊቱን ኮንናችሁ ወደ ሲዖል ሸኟቸው›› በማለት አዘዙ፡፡

ይህቺ ቀን ደርሳ አገራቸውንና እኅቶቻቸውን የደፈረውን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያፈናቀለውን፣ ከባድ የሰብዓዊ ጥቃት ያደረሰውንና በግማሽ ምዕተ ዓመት የማይተካ ሐብት ያወደመውን አሸባሪ የሚደቁሱበትን እለት በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩ ጀግኖችም፡-

‹‹የዘረፈንን- ማስቀመጫ ያጣ

ሒሳብ ላወራርድ፥ ብሎ ከመጣ

እዳውን ሳይከፍል ሾልኮ እንዳይወጣ

ዙሪያውን ከብበህ- እርሳስ አጠጣ›› እየተባባሉ አፈሙዛቸውን ሲያንፈቀፍቁት…. የጠላት ሠራዊትን የሚመራው ጄኔራልም በተጠለፈው ስልኩ ውስጥ ‹‹ቶኩስ ቶኩስ ቶኩስ›› የሚል ትዕዛዝ ለመንጋው ከሰጠ በኋላ በሳተላይት ስልኩ ጌታቸው ረዳ ጋር ደውሎ ‹‹ብዛት ያለው ጦር ወደ ምሽጋችን እየተንደረደረ ነውና ባፋጣኝ ተጨማሪ ሃይል ይላክልን›› ብሎ ሲናገር ተሰማ፡፡ ጌቾም ‹‹የሚረዳህ ጦር እየመጣልህ ስለሆነ የምንኮራበት ምሽግ እንዳይሰበር ጠንክረህ ተዋጋ›› ብሎ ሲመልስለት ‹‹ከከበበን ብርቱ ሠራዊት ጋር ጠንክሮ መዋጋት CNN ላይ ቀርቦ እንደማውጋት ቀላል አይደለም›› ብሎት ስልኩን ዘጋው፡፡

ከዚያ በኋላም፣ ዐይኔን ወደ ወገን ጦር ስመልሰው ያየሁት ትዕይንት በቃላት ለማብራራት ቀርቶ በካሜራ ለማስቀረት የሚመች አልነበረም፡፡ ብቻ ግን ‹‹ሌላ እናት አገር የለኝም›› በሚል ውሳኔ የሚተምመው የወገን ጦር ‹‹እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም›› እየተባባለ በእርሳስ ካፊያ መሃከል ሲገሰግስ ጥይት የማይበሳው ሰውነት ወይም ደግሞ ተተኪ ሕይወት ያለው ይመስል ነበረ፡፡ ወራሪውን መንጋ ለመቅበርና ምሽጉን ለመቆጣጠር ያሰቡ ጀግኖች ሞትን እንደ ተራ ክስተት ቆጥረው በእሳት ነዲድ መሃከል በጀግንነት ሲረማመዱ ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና ለጁንታው ያላቸው የመረረ ጥላቻ ፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ሠራዊት ጀግንነት ከፍተኛ ፍርሐት የተሰማው ወራሪ ጦርም የደመ ነፍስ ተኩሱን ቢያበረታውም በፍርሐት የሚንቀጠቀጥ እጁ ግን ዒላማውን መምታት አላስቻለውም፡፡ ሲኩራራበት የከረመው የኮንክሪት ምሽግ የጦሩ መቃብር እየሆነ መምጣቱን የተረዳው ጄኔራል ጻድቃንም፤ በድጋሜ ኣይተ ጌታቸው ጋር ደውሎ ‹‹የከበበን ጠላት በሚገርም ፍጥነት ወደ ምሽጉ እየተቃረበ ነው›› በማለት ሲነግረው ‹‹የከበበህን ጠላት ከብቦ ያጭድልህ ዘንድ የላክንህ ሠራዊት በደቂቃ ውስጥ ስለሚደርስ በጽናት ተከላከል›› የሚል አጭር መልስ ሰጠው፡፡

እናም እንዳይሮጥ በተቆጡ አናብስቶች ዙሪያውን የተከበበው፣ ጠንክሮ እንዳይዋጋ የፈሪ ተኩሱ ዋጋ እንደሌለው የተረዳው የሽብር ሠራዊትም ደረቱን ተመትቶ ምድር ላይ ከመፈጥፈጡ በፊት መሳሪያውን እየጣለ ታንክን በክላሽ አሸንፈው ወደ ምሽጉ መግባት ለጀመሩት ጀግኖች እጁን ይሰጥ ጀመር፡፡ ይሄንንም አስገራሚ ትዕይንት ከርቀት ሆኖ ሲከታተል የቆየው ጄኔራል ወደ ጌታቸው ረዳ ጋር ለሦስተኛ ጊዜ ደውሎ ‹‹ከላክልኝ ሠራዊት በፊት ጠላት ከምሽጉ ደርሶ የመጨረሻውን ሳቅ እየሳቀ ነው?›› የሚል መረጃ ሲሰጠው ጌቾ ታዲያ ከእሱ ውጭ ምን አይነት ሠራዊት እንዲደርስልህ ፈልገህ ነበር?›› ብሎ በለሆሳስ ካወራ በኋላ እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቶት ስልኩን ዘጋው፡፡

‹‹ማነህ ጻድቃን የክልሉ ወጣት ሁሉ ዘምቶ ባለቀበት ሁኔታ እኔ ጌታቸው ተዋጊ ሮቦት ሰርቼ ልታደግህ ስለማልችል የምታምነው አምላክ ካለ መላዕክትም ሆነ አጋንንት ልኮ ይታደግ ዘንድ ቀና ብለህ ለምነው››

በዚህም የጌታቸው ረዳ ስላቅ የተበሳጨው ጄኔራል ‹‹ሲኦል ውስጥ አገኝኻለሁ›› ብሎ ሊዝትበት አስቦ መልሶ ሲደውል ‹‹የደወሉላቸው ደንበኛ ስልካቸውን አጥፍተው እራሳቸውን ስለማጥፋት እያሰቡ ስለሆነ ቆይተው ይደውሉ›› የሚል ድምጽ ሰማ፡፡ እናም ጋሼናን ተቆጣጥሮ የመጨረሻውን ሳቅ በመሳቅ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሠራዊት አሻግሮ እያዬ በሳተላይት እየመሩ ወደ ጋሸና ያስገቡትን ሃይሎች ‹‹በጥበባችሁ አውጡኝ›› ብሎ ሊጠይቃቸው አስቦ በተለመደው አድራሻ ሲደውል የተሰጠው መልስ ‹‹የደወሉላቸው ደንበኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ደውለው ‘ከጎንህ ነን’ የሚል ድጋፋቸውን እየገለጹ ስለሆነ እባክዎን መስመር ላይ ይጠብቁ›› የሚል ነበረ፡፡

ከዚህም ንግግር የአሰላለፍ ለውጥ መደረጉን የተረዳው ጄኔራል በሳተላይት መርተው ወደ ጋሼና ያስገቡት ተለዋዋጭ ሃይሎች ያለበትን ቦታ ጠቁመው ሳያስገድሉት በፊት እንዲህ እያለ ወደማያዉቀው አቅጣጫ ይፈረጥጥ ጀመር፡፡

‹‹ለእኛ ስለወጣ- የድሉ ፈረቃ

አልደራደርም፥ ብዬ ሳላበቃ

የምኮራበት ጦር

ከምን ጊዜው ታጭዶ- ከምኔው ተወቃ?››

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top