Connect with us

የ ዶክተር ዐብይ ዘመቻ

የ ዶክተር ዐብይ ዘመቻ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የ ዶክተር ዐብይ ዘመቻ

የ ዶክተር ዐብይ ዘመቻ

(ኘሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ)

የጥንት የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥታት መሪዎች ሀገር በጠላቶች ጦር ስትወረር መዝመት ልማዳቸው ነበር። በተለይ ጦርነቱ የኢትዮጵያን ልዕልና ከተዳፈረ።

የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር በግንባር ቀደም ከተዋጉት ውስጥ አንዳንድ የቅርቦቹን ለመጥቀስ፣ የጀግኖቹ ጀግና አጼ አምደጽዮን፣ አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሀንስ፣ አጼ ምንይልክ እና አጼ ኀይለሥላሤ ይገኙባቸዋል።

አጼ አምደጽዮን፣ ታሞ ተኝቶ ሳለ አረቦችና ቱርኮች በ ኢትዮጵያውያን ሱማሌዎች እና አዳሎች እየታገዙ ኢትዮጵያን ወረሩ። አምደጵዮን ታሞ በተኛበት ቦታ ጥቂት ወታደሮች፣ ሴቶች፣ እና ህጻናት ብቻ ነበሩ።

አምደጽዮን በህመሙ ምክንያት አቅም ስላነሰው ድንኳን ውስጥ ተኝቼ ከምሞት ለሀገሬ ክብር እየተዋጋሁ እሰዋለሁ፣ የጦር ልብሴን አልብሱኝ እና ፈረሴ ላይ  አውጡኝ ብሎ አልብሰው አወጡት።

“ከኔ ጋራ ለመሞት የሚሻ ይከተለኝ። ዛሬ  ለሀገሬ ለኢትዮጵያ እንዴት እንደምሞትላት ይታያል፣” ብሎ ሰይፉን መዞ ወደፊት ሸመጠጠ። በሰይፉም በድፍረት ብቻውን የህልቆ መሳፍርቱን ቱርኮችና አረቦች አንገት ቀላ። አረቦቹም ምን ዐይነት ደፋር ነው? ሰይፉ ከሰማይ የወረደ መሆን አለበት፣ እያሉ በፍርሀት ርደው ሸሹ። ጥቂቶች የነበሩት የአጼ አምደጽዮን ወታደሮችም በእሱ ጀብድ ተነሳስተው የቻሉትን ያህል ወራሪ እያሳደዱ ጨረሱ። አጼ አምደጽዮ በድል አድራጊነት ወደ ድንኳኑ ተመለሠ። የጠላቱ ደም እሰይፉ እጀታ ላይ  ላይ ደርቆ፣ የንጉሡ ጣቶች ከሰይፉ በመከራ ተላቀቁ።

አፄ ቴዎድሮስም መቅደላ ሆነው ከእንግሊዝ ወራሪዎች ተፋልመው እሳቸው ተማርከው ኢትዮጵያ እና እሳቸው እንዳይዋረዱ ብለው እራሳቸውን አጥፍተዋል።

ደርቡሾች፣ ወይም ሱዳኖች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ አጼ ዮሀንስ ተዋግተው ካሳደዳቸው እና ካሸነፏቸው በኋላ በተባራሪ ጥይት አንገታቸውን ተመተው ወደቁ። ይህን ሲሰሙ፣ ይሸሹ የነበሩት ሱዳኖች ተመልሰው እራሳቸውን ቆርጠው ይዘው ሄዱ።

ቀደም ሲል ግን ከጦር አበጋዛቸው ከራስ አሉላ አባ ነጋ ጋራ ሆነው ከቱርኮች እና ከግብጾች ጋራ ተጋድለው ደጋግመው ድል አድርገዋል።

እንደሚታወቀው አጼ ምንይልክ አድዋ ላይ በጦር መሪነት ዘምተው ጣልያንን ማሸነፋቸው፣ የነጭን የበላይነት መደምሰሳቸው እና የጥቁርን ዘር የማኩራታቸው ዜና በወቅቱ በዐለም ተሰራጭቶ ነበር።

አጼ ኃይለሥላሴም በማይጨው ጦርነት ከፋሺስት ጣልያኖች ጋራ ገጥመው በግላቸው እይሮፕላን ጥለዋል። እሳቸው በተክለሰውነታቸው የጦር ሰው ባይሆኑም እና የአእምሮ እና የመጽሀፍ ሰው ቢሆኑም፣ ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን፣ ተዋግተው ከአንድ ኢትዮጵያዊ መሪ የሚጠበቀውን ግዳጅ ተወጥተዋል።

ዶክተር ዐብይም አሁን ሊያደርጉ የተነሱት ይህንኑ ነው። እኚህ ሰው የኢትዮጵያ መሪ ሆነው የተከሰቱት በኢትዮጵያ ቀውጢ ቀን እና እጅግ የተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ ነው። እንደ የኢትዮጵያ ጦር አዛዥነታቸው እሷ እጅግ በምትፈልጋቸው ስአት ነው የደረሱላት። እንደ መልካም እድል ሆኖ፣ እሳቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የውትድርና ስልጠና እና የጦርነት ተሞክሮ ስላላቸው እፊታቸው ለተደቀነው ተግባር ብቁ ናቸው። ይህም ሆኖ፣ በዙሪያቸው ያሉት የውስጥ እና የውጪ ጠላት በርካታ ስለሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። በተረፈ እስከ አሁን ያቆያቸው እግዚአብሄር ይጠብቃቸው። ለድልም ያብቃቸው። የእሳቸው ድል የኢትዮጰያ ነውና።

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

To Top