Connect with us

ላቡን እና ጥሪቱን ላፈሰሰላት አገሩ ደሙንም ሊሰጥ የተዘጋጀው አትሌት

ላቡን እና ጥሪቱን ላፈሰሰላት አገሩ ደሙንም ሊሰጥ የተዘጋጀው አትሌት
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ላቡን እና ጥሪቱን ላፈሰሰላት አገሩ ደሙንም ሊሰጥ የተዘጋጀው አትሌት

ላቡን እና ጥሪቱን ላፈሰሰላት አገሩ ደሙንም ሊሰጥ የተዘጋጀው አትሌት

(አሳዬ ደርቤ~ ለድሬ ቲዩብ)

ወጣት ሳለ ሽንፈት በማያውቁ እግሮቹ ኢትዮጵያን ወክሎ ባመጣቸው ሜዳሊያዎች መሪዎቿ ሥሟን ለመጥራት የሚጠየፏትን አገር በዓለም መድረክ ሲያስጠራት ኖረ፡፡ ከኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ እንዲደበዝዝና እንዲፋቅ የሚፈለገውን አገራዊ ስሜትም ነፍስ ሲዘራበት ኖሮ ጫማውን ሰቀለ፡፡ ላቡን አፍስሶ ያመጣውን ዶላርም ኢንቨስት በማድረግ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ቀዳሚ ያደረጋትን አገሩን የመዋዕለ-ንዋዩ ተጠቃሚ ማድረጉን ቀጠለ፡፡

መዋዕለ ንዋዩን ያፈሰሰው ደግሞ አብዛኛው ባለሃብት በሚሳተፍባቸውና በቀላሉ በሚበለጸግባቸው የሥራ መስኮች ሳይሆን ከፍተኛ ልፋትና ጥረት በሚጠይቁ ዘርፎች ነው። ለማስረጃም ያህል የሆቴል እና የቡና ልማቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት በመሆን እሱን መሰል አትሌቶች ለማፍራትና አገሩን የድል ባለቤት ለማድረግ ሲተጋ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከለውጡ በኋላ ታዲያ ጀግናውን አትሌት ሲያስከብራትና ስሟን ሲያስጠራት በነበረች አገሩ ውስጥ ያጋጠመው ነገር ሽልማትና አክብሮት ሳይሆን መጠነ ሰፊ ጥቃት ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ እንግዶችን የሚያስተናግድ ሪዞርቱን በእሳት የሚያቃጥልና የቡና ልማቱን ለአደጋ የሚጥል ድግስ ነበር የጠበቀው፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን የተለያዩ አገራት የክብር ዜግነት የተቸረውና ልበ ደንዳናው አትሌት አገሩን ‹‹አውፍ›› ከማለት ባለፈ ሊያኮርፋትና ሊቀየማት አልከጀለም፡፡ ይልቅስ ‹‹ኢትዮጵያ ካደረገችልኝ ውለታ ጋር ሲነጻጸር የተደረገብኝም ሆነ ያደረግኩላት ነገር ኢምንት ነው›› እያለ ምሥጋናውን ሲገልጽላት ነበር፡፡ ‹‹በመንጋ ጥቃት ከተቃጠለበት ሪዞርትና ጥሪት በላይም በበጎ አድራጎት ሥራ ተሰማርቶ በሰቆጣ አካባቢ ያስገነባውና በትሕነግ የሽብር ቡድን የወደመው ትምህርት ቤት በእጅጉ እንዳሳዘነው›› በሚዲያ ቀርቦ ሲናገር ነበር፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ በተለያዩ አገራዊ አበርክቶዎችና ሃላፊነቶች ላይ ‹‹ያገባኛል›› በሚል ስሜት መሳተፍ የሚወደው አትሌት ይህ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት እራሱን ከሀገር ሽማግሌዎች ተርታ አሰልፎ ልዩነቱን በንግግር ለመፍታት የተቻለውን ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ ጦርነቱን ማስቀረት ባይችልም፣ የአገርንም ሆነ የሰውን ክብር የማያውቁ ማፊያዎችን ‹‹ወደ ሰላም ጎዳና አመጣለሁ›› ብሎ ወደ መቀሌ ካመራ በኋላ ‹‹ደብረ ጽዮን›› የተባለ የሽብር ቡድን መሪ ለማግኘት እጁን ዘርግቶ ሲፈተሽና ሲበረበር ነበር፡፡

በእብሪተኛው ቡድን ተስበን ወደ ጦርነቱ ከገባን በኋላም ከአንድም ሁለት ጊዜ ወሎ ምድር ላይ ተገኝቶ በሚሊዮናት የሚገመት የእርዳታ ገንዘብ ‹‹ሰዎች ለሰዎች›› በተባለ ድርጅት አማካኝነት ሲለግስ የነበረ ከመሆኑም በላይ ‹‹የአገሬ ጉዳይ ይገደኛል›› በሚል አስተሳሰብ በተለያዩ ሚዲያዎች እየወጣም አሸባሪውን ሃይል በግልጽ ሲያወግዝና ለሚወዳት አገሩ ጥብቅና ሲቆም ነበር፡፡ እንደ አብዛኛው አዋቂና ታዋቂ ሰው ‹‹ምን አገባኝ›› በሚል እሳቤ ድምጹን አጥፍቶ ቢዝነሱን በመምራት ፈንታ አገር የመምራት ድርሻውን ወስዶ በንቃት ሲሳተፍ ነበረ፡፡

አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ‹‹የተከተሉኝ ጥሪ›› በመቀበልና አገሩ ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ሽንፈት በማያውቅ እግሩ የድል ሜዳሊያ ሲያጎናጽፋት፣ ዶላሩን ኢንቨስት ሲያደርግላትና የእርዳታ እጁን ሲዘረጋላት ለኖረች አገሩ በጦር ግንባር ተገኝቶ ሕይወቱን ሊገብርላት ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡ 

በአትሌትነቱ ላቡን አፍስሶ የድል ባለቤት ሲያደርጋት ለኖረች አገሩ በሻለቃነቱ ግንባር ድረስ ዘምቶ በደሙ አሸናፊ ሊያደርጋት መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡ ይሄን የሰሙ ኢትዮጵያውያንም ለሃይሌ አክብሮታቸውን፣ ለትሕነግ ደግሞ እንዲህ የሚል መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ፈይሳ በሸዋ ፥ ሃይሌ በአፋር ግንባር

ታጥቀው ከዘመቱ፥ አገር ለማስከበር

አይቻልምና ፥ አትሌት ቀድሞ ማምለጥ

ሊጥ መንታፊ እጅህን- ጁንታው ሆይ ቶሎ ስጥ፡፡

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top