Connect with us

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፤በኢትዮጵያ ሰማይ ስር …..

Social media

ነፃ ሃሳብ

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፤በኢትዮጵያ ሰማይ ስር …..

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፤በኢትዮጵያ ሰማይ ስር …..
(እስክንድር ከበደ ~ ድሬቲዩብ)

በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት መጀመሪያ አካባቢ ኢትዮጵያ ጥቂት የአሜሪካን ኤፍ ፋይቭ ጀቶች የነበሯት ሲሆን ፤ሶማሊያ ደግሞ የሶቭየት ፈጣን ሚግ ጄቶች ነበሯት፡፡ አውስትራሊያ ስሪት የሆነው ካምቤራ ሚባለው ግዙፍ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በድሬደዋ አየር ላይ ዝግ ብሎ ሲንሳፈፍ ከዚህ ግዙፍ ንሥር በላይ የሚያጅቡት የአሜሪካ ኤፍ ፋይቭ ጄቶች ነበሩ፡፡

ካምቤራ የሚያንጸባርቅ ብርማ ቀለም ያለው ሲሆን ግዝፈቱ የሚገርም ነው፡፡ ይህ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ጄቶቹ የሚያጅቡት ከላይ የጠላት ተዋጊ ጀቶች እንዳይመታ ነበር፡፡

የድሬደዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን የአየር ኃይል ምድብ ስለሆነ ፤ ጄቶቹ በድሬ ደዋ አየር ላይ በቡድን ወደ ምስራቅ ሲተሙ አየር ላይ የሚያሳዩት ትርኢት የሚገርም ነበር፡፡ ሶቭየት ህብረት ለ15 አመታት ሶማሊያን አስታጥቃ ነበር፡፡ ከፍጥነት አንጻር ሚግ 21 እና ሚግ 19 እጅግ ፈጣን በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያ የታጠቀቻቸው ኤፍ -5 ተዋጊ ጄቶች ብዙ ጊዜ ሚጎቹ ላይ አይደርሱባቸውም ነበር፡፡

ሁለቱ ሀገራት የነበራቸው የተዋጊ ጄቶች ብዛትም አይደራረሱም ነበር፡፡ ሱማሊያ ብዙ ተዋጊ ጄቶችን ታጥቃለች፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጥቂት ፓይለቶችና ውስን ተዋጊ ጀቶች ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶችን የታጠቀውን የሱማሊያ ጦር ሶማሊያ ድንበር ገብቶ ኢላማዎችን አደባይቶ ይመለስ ጀመረ፡፡ ይህ ኃይል የጦርነቱን ሚዛን የለወጠ ነበር፡፡ የሱማሊያ ሚግ ተዋጊ ጄቶች ድሬደዋ ሰማይ ድረስ ዘልቀው የአሜሪካ ስሪቶቹ ኤፍ ፋይቭ ጄቶች ተነስተው የሚያበሩበትና ከተማዋ መግቢያ ጋራ ላይ የተተከለው የአየር መቃወሚያ ተከታታይ ተኩስ ሰማዩ ረዥም ነጭ ጭስ ይፈጠራል፡፡

አጼ ኃይለስላሴ ከአሜሪካ ጋር የተፈራረሙትን የቃኛው ሻለቃ የጦር ሰፈር ስምምነት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም መሰረዛቸውን ተከትሎ ፤አሜሪካ የጦር መሳሪያ ግዥውን ሰረዘችው፡፡ ሁለቱ ኃያላን ቦታ ተለዋወጡ፡፡ ሶቭየት ህብረት አማካሪዎቿን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ ገባች፤አሜሪካም ሶማሊያን መርዳቱን ጀመረች፡፡
ለኢትዮጵያ አየር ኃይል የሱማሊያ የጦር ዲፖዎችና ጠቃሚ መረጃዎች ሶቭየት ኀብረት ባለሙያዎች
የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ በጻፉት ”ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ” በተሰኘ መጽሐፍ ከሶቭየት ኅብረት ወደ ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ እንዴት እንደተጓጓዘ ጽፈዋል፡፡ ” በታህሳስ 19 ቀን 1970 የሶቪየትኅብረት ግዙፍ እርዳታ ፤አንቶኖቭ 20 በተባሉ ግዙፍ አውሮፕላኖች ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መግባት ጀመረ ፡፡

አውሮፕላኖቹ ለሁለት ሳምንት ፤ያለማቋረጥ ከሞስኮ አዲስ አበባ እየበረሩ፤መሣሪያ አራገፉ፡፡ ቀላልና ከባድ መሣሪያዎች ፣ሚግ 21 እና ሚግ 19 ተዋጊ አውሮፕላኖች በብዛት ጭምር ፤እንዲሁም ሄሊኮፕተሮች ወላልቀው ፤በትላልቅ ሳጥን ታሽገው ፤ሦስት አራቱ በአንድ አውሮፕላን ይጓጓዛሉ፡፡በጣም ሚደንቀው አውሮፕላን በአውሮፕላን ተጭኖ እንደሚሄድ ብዙ ሰው አያውቅም ነበር፡፡”በማለት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጦርነት ወቅት እንዴት እንደታጠቀች ይተርካሉ፡፡

በዛ የኢትዮሶማሊያ ጦርነት እነዛ ምርጥ የጄት አብራሪዎች ሀገራቸውን ከውጭ ጠላት በሚገባ ተከላክለው የሀገርን ህልውና አድነዋል፡፡
አሁን ባለንበት ዘመን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፉት አራት አስርት አመታት በኋላ ዘመኑ ያፈራቸውን የጦር ጄቶች እስከ ድሮን መታጠቁ ይታወቃል፡፡

በቀድሞው አየር ኃይል እና በአሁኑ የአየር ኃይላችን የታጠቁት የየዘመናቸውን የጦር ጄቶች ልዩነት ቢኖርም ፤በየዘመኑ ጀግናና ምርጥ የጄት አብራሪዎች የሚያፈራ አየር ኃይል እንዳለን የሰሞኑ አየር ኃይሉ የፈጸመው ገድል ምስክር ነው፡፡
አየር ኃይላችን ሰሞኑን በመቀሌ ከተማ የተመረጡ ኢላማዎች ድብደባ ማካሄዱ ፤ ቡድኑን የመገናና አውታሮች ማማዎችና የጦር መሳሪያ ማምረቻና መጠገኛዎች ብሎም የማሰልጠኛ ካምፖች ማደባያቱ በላይ የሚያስተላልፈው መልእክት ኃያል ነው፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መታጠቁ አንድ ነገር ሆኖ፤ በህዝብ ከተሞላ ከተማ ውስጥ በንጹሀን ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ እጅግ በጥንቃቄ የተመረጡ ኢላማዎችን መደብደቡ አየር ኃይሉ አቅሙን ያሳየበት ነው፡፡ ቡድኑ ድበደባዎቹ ”ከተስፋ መቁረጥ ” ወይም ”ፋሽሽታዊ ” ድርጊት በማለት ደጋፊዎቻቸውን ለማጽናናት በፕሮፖጋንዳ ተጠምደዋል፡፡

በ1980ዎቹ ይጠቀሙበት የነበረውን ጊዜ ያለፈበት ወዥንበር የመፍጠር ብሎም የማወናበድ መላ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ደጋፊዎቻቸው ”ጠንካራ ኃይል ” ለመምሰል የሚያደርጉት እጅግ የተጋነነ ፕሮፖጋንዳ የአየር ኃይሉ ጥቃት በተግባር የቡድኑ አቅም ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለሁሉም በተግባር ያሳየበት ነው፡፡

በየጊዜው ከምእራባውያን እስከ ጎረቤታችን ሱዳን ጋር ወታደራዊ ልምምዶችን በማድረግ ወታደራዊ ጡንቻዋን በማሳየት የአካባቢው ”ኃያል ” እንደሆነች ምስል ለመፍጠር ለምትሞክረው ግብጽ በተግባር የተደገፈ ምሳሌ አሳይቷታል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በየትኛውም መንግስት በዚህ ያህል በፍቃደኝነት ወደ ውትድርና የተቀላቀሉ ወጣት ወታደሮች ወደ ማሰልጠኛ ማአከላት ከአቅም በላይ የገቡበት ጊዜ የለም፡፡ ከየትኛውም መንግስትና ዘመን በተሻለ መልኩ ብዝሀነት ያለው፤ በርካታ ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የተቀላቀሉበት አስገራሚ የምድር ጦር እየተፈጠረ ነው፡፡

ይህን የጦር ኃይል በዘር ዘመም ስብስብ ፍርስራሽ ላይ የተገነባ ጠንካራ ህብረበሔር ስብጥሩ ለማሸነፉ ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ታሸነፋለች !

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top