Connect with us

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የ፵ኛ ዓመት ጠቅላላ ዓለም አቀፍ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ስብሰባ የአቋም መግለጫ
© EOTC TV

ዜና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የ፵ኛ ዓመት ጠቅላላ ዓለም አቀፍ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ስብሰባ የአቋም መግለጫ

 1. ቤተ ክርስቲያናችን ባለፉት ፵ኛ ዓመታት በየደረጃው ባቋቋመቻቸው የሰበካ ጉባኤያት አያሌ ሥራዎች በታሪኳ ላይ ከማስመዝገቧም በላይ ለክርስቲያናዊ ዕድገትና ለሁለንተናዊ የካህናትና የምእመናን ተሳትፎን የገነባ ጠንካራ መሠረት ለመጣል የሚያስቸለንን አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በተለይም ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷ ይሣለጥ ዘንድ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደራዊ ሥርዓት መሠረት የየአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮን መሟላትና እውን መሆን በየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መሪነት ዐረፍተ ዘመን የገታቸው በልዩ ልዩ ዘርፍ የተወከለ ሓላፊዎች አገልጋይ ሠራተኞች ባደረጉት  ውጣ ውረድ የጎለበተና የታነጸ በመሆኑ በቀጣዩም የሥራ ዘመናችን እግዚአብሔር ቢፈቅድ የበለጠ ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የሚጠይቀውን አስፈላጊ መስዋዕትነት ሁሉ እንከፍላለን፡፡
 2. ባለፉት ፵ኛ ዓመታት በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ ተልእኮ ለማሟላት የቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ በየአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን ከዓላማውና ከተግባሩ በመነጨ አንድነት ከላይ እስከታች ባለው የሥራ መዋቅር በመናበብ በርካታ ሥራዎችን አከናውነናል፡፡ ለወደፊቱም በወሬ የማይፈታ ፈተናን የሚቋቋም ትውልድ በማነጽ ይህንኑ አንድነታችንን በማጠናከርና በማስተማር የቤተ ክርስቲያናችንን የሕልውና አንድነት ክብርና ልዕልና ለማስጠበቅ መንጋውን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአርቆ አሳቢነት በመሥራት አደራችንን እንወጣለን የቃለ ዐዋዲውም ሕግ በተጀመረው አግባብ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለሀገር ውስጥና ለውጭው ዓለም በበቂ ሁኔታ እንዲሠራጭ እየጠየቅን ቅዱስ ሲኖዶስም የቃለ ዐዋዲው መመሪያ በውጭው ሀገራት ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ እንዲውል  ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፣
 3. ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ ሀገረ ስብከት የተዘረጋውን ልዩ ልዩ ማስፈጻሚያ ተቋማት የየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ተግባራዊ ለማድረግ በየደረጃው ለሚገኙ ኃላፊዎች፣ የየወረዳው ሊቃነ ካህናት፣  የየአጥቢያዎቹ አስተዳዳሪዎችና አገልጋይ ካህናት የአጥቢያውን አብያተ ክርስቲያናት የመንፈሳዊ አገልግሎትና የመገልገያ ንዋያተ ቅድሳት በማሟላት ፣የአብነት ት/ቤቶችን በማቋቋምና በማደራጀት የመምህራንና የደቀ መዛሙርቱን መኖሪያ ቤት በመሥራት፣የሥልጠና ወጪ በመሸፈን በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ከሪፖርቶቹ ተረድተናል፡፡ ስለሆነም በመጪው በ2014/15 ዓ.ም ሕዝበ ክርስቲያኑንና የበጎ አድራጊ ወገኖች ተሳትፎ የበለጠ ዳብሮና ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችነን ጥረትና የማስተባበር ሥራ ለመሥራት ተስማምተናል፡፡
 4. በየደረጃው የሚገኘውን የቤተ ክርስቲያቱን ሀብትና ገንዘብ ካለው የሰው ኃይል ጋር በማቀናጀት በቁጠባና በማብቃቃት በመጠቀም ብኩንነትን የሚጋበዙ አሠራሮችን በማስወገድ ገንዘብና የቤተ ክርስቲያን መገልገያ ንዋያተ ቅድሳትን ከመዝባሪዎች የመከላከል አስፈላጊነቱ በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ጉባኤያት ተነስተው መመሪያ የተሰጠባቸው ቢሆንም አሁንም አልፎ አልፎ ምርመራ በተደረገባቸው ቦታዎች በዚህ ዘርፍ ያለው ችግር አለመቀረፉን የሚያሳይ ሪፖርት በንባብ ተሰምቷል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደራዊ ሓላፊነታችንን ከፍ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት በቆጣቢነት ለመጠቀምና ውሳኔና መመሪያን በማክበር በባለአድራነት ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡
 5. ሐዋርያዊትና ኩላዊት ቤተ ክርስቲያናችን በሀገራችን ሕዝብ ዘንድ በሚነገሩ ቋንቋዎች ለማስተማርና ለማገልገል በተጀመረው ጥረት በርካታ የአገልግሎት፣ የትምህርትና የመዝሙር መጻሕፍት ተተርጉመው ተሠራጭተዋል፡፡ የየቋንቋው ተናጋሪ ወጣቶችና ካህናት የአጫጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎች እየወሰዱ ምእመኑ የሚጠይቀውን በቋንቋ የመገልገልን ፍላጎት በማበርከት ላይ በመንግሥት ሚዲያዎች፣በእኛ ቤተ ክርስቲያን፣በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥንና በባለሀገሩ ቴሌቪዥን የመገናኛ ብዙኀን ሲተላለፉ የነበሩት መርሐ ግብሮች የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ ሐዋርያዊ ተልእኮ ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብና ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚያስተላልፈው መልእክት፣ ትምህርትና ጸሎት በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች በምልዓተ ክህነት ሲያገለግሉበትና ሲያስተምሩበት ከመገኘቱም በላይ በኮቪድ 19 ዐለማቀፋዊ ወረርሽኝ የተደናገጠውን ሕዝብ ቃለ እግዚአብሔር በመጥቀስ የማጽናኛ የማበረታቻ ትምህርት ሲሰጥ መታየቱ ቤተ ክርስቲያናችን ምን ያህል ዝግጁ መሆኗን የገለጠ ከመሆኑም በላይ ዓለም አቀፋዊ አድናቆትን አስገኝቷል፡፡ 

 

በአርያነት የሚጠቀስ ሆኖ በታሪክ የሚዘገብ ሥራ ሆኖ ይኖራል፡፡ ይኽንንም ሥራ ለማጠናከር በየአህጉረ ስብከቱ  ዜና ዘጋቢ የሰው ሓይል በቂ በጀት እንዲመደብ ቅዱስ ሲኖዶስ አጽንኦት ሰጥቶ አንዲመለከተው እንጠይቃለን፡፡

 1. የመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር ሲኖዶስ ተብሎ የላይ ፈሪና የታች ፈሪ ሲባባል ቆይቶ የቤተ ክርስቲያኗን ሲኖዶሳዊ አንድነት ለማስመለስ ብዙዎች ሊቃነ ጳጳሳት ሊቃውንትና ታዋቂ ሰዎች የደከሙበት ተግባር ቢሆንም ጊዜ ሲደርስ አምባ ይፍረስ እንዲሉ አበው ክቡር ጠቅይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በአግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸው በሄዱበት አውሮፕላን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን 4ኛ ፓትርያርክና በመላው ዓለም በሐዋርያዊ  አገልግሎት ላይ የነበሩ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በክብር ይዘው በመምጣት የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አንድነት ተመልሶ ቤተ ክርስቲያናችን ደስታዋን በቅዱስ ያሬድ ዝማሬ  በምእመናን  እልልታ በሚሊኒየም አዳራሽ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በማክበር ላይ ሳለች በዚን ዕለት የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የማይዋጥላቸው የውስጥና ውጪ ጠላቶች እንዲሁም ነጭ በጥቁር የመሸነፍ ምሥጢር የምሥጢሩ ባለቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሕዝቡን በአንድነት በሰላምና በፍቅር ገመድ አሥተሳስ ያቆየች መሆኗ እንደበደል ተቆጥሮባት ባሳደገቻቸው ልጆቿ በጠላትነት ተነስተው በጅግጅጋና በአካባቢው የሚገኝ አብያተ ክርስቲያናትን ካህናትና ምእመናን በእሳት ካቃጠሉ ንብረታቸው ተዘረፈው ጥለው እንዲሰደዱ ተደረገ መንግሥትም በጊዜው የጥፋት አመራር ሰጥተዋል የተባሉ ባለሥልጣናትንና ድርጊት ፈጻሚዎች ለሕግ ማቅረቡን ተመልክተናል፡፡ 

ከዚያ ወዲህ ግን እምነትንና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥፋት በቡራዩ ይኽን ተከትሎ በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ በሻሸመኔ በዝዋይ በመተከል በጉራ ፈርዳ ፣ምዕራብ አርሲ በባሌ፣በምዕራብ ሐረርጌ፣ድሬዳዋ ተከታታይ ጭካኔ የተሞላበት በተለያየ ቀን ጭፍጨፋ በመደረጉ ቤተክርስቲያኗን አሳዝኗል፡፡

 1. በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ማይካድራ ምዕራብ ጎንደር መተማ ሰሜን ጎንደር ጭና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ማእከላዊ ጎንደር በደቡብ ጎንደር ጨጨሆ መድኃኔዓለም ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዋግ ሕምራ ራያና ኮረም በጅማ በሊሙ ኮሳ በሊሙሰቃ ወረዳዎች ፤በሰሜን ሸዋ በአጣዬ በሸዋሮቢት በካራ ቆሬ በማጀቴ አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፡፡ የቤተ መቅደስ ካህናት ካህኑ ዘካርያስ በቤተ መቅደስ በተሰዋበት አምሳል በአገልግሎት እንዳሉ ጭምር ታርደዋል፡፡ 

ምእመናንና ምእመናት በሀገራችን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ፆታ ሳይለይ እመጫቶችን ነፍሰጡሮችን ግራና ቀኝ ፊትና ኋላ እሳትና ውኃ የማይለዩ ሕፃናት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉና ብዙዎች ሀብት ንብረታቸው ወድሞባቸው ለስደት እንዲዳረጉ ሆኗል፡፡ ለብዙ ዘመናት የተገነቡ ከተሞች የሕዝብና የሀገር ሀብት ወድሟል፡፡ 

የተቀጠፈው የሰው ሕይወት የወደመው የሐብት መጠን በውል ማወቅ ካልተቻለበት ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊተካ የማይችል ዘግናኝ ኪሳራ ደርሷል፡፡ ይኽ ክስተት በ3ኛው ምእት ዓመት ዘመነ ሰማዕታት ተብሎ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ ከምናነበው ታሪክ ጋር ተመሳሳይ የሚመሰልበት ክርስቲያኖች በዋሉበት እንዳያድሩ በአደሩበት እንዳይውሉ የተደረገበትን ታሪክ የሚያስተውልና የሚያረጋግጥ ቤተ ክርስቲያንን የሚፈትን በሰቆቃ የታጀበ አባቶችንና ሁላችንን ለዋርያዊ ለሰማዕትነት የሚያዘጋጅ ዘመን ነው፡፡ ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱ ክፉ ዘመን አሁን በምናየው የአህጉረ ስብከት የመተባበርና የመረዳዳት መንፈስ በመተጋገዝ በመተዛዘን እግዚአብሔር አምላክ የምሕረትና የሰላም እጁን ይልክ ዘንድ በጾም በጸሎት በስግደት ንጹሕ መሥዋዕትን በማቅረብ ምህረትን መጠየቅ ስለሚገባ በዚህ ዘርፍ ያለመታከት ጠንክረን ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

 1. ቤተ ክርስቲያናችን በመላው ትግራይ የሚገኙ አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች የገዳማትና አድባራት አገልጋይ ካህናትና ተገልጋይ ምእመናንን የምትመራና የምታስተዳድር መሆኗ ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ሕዝቡም በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር የክርስትና ምንጭ ንጹሕ አማኝ ፍጹም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ቤተ ክርስቲያናችን ታምናለች፡፡ መላው ሕዝባችንም ይኽኑ ያምናል፡፡ የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ነጻ እናወጣለዋለን የሚሉ የተለዩ ወገኖች አመለካከትና አስተሳሰብ ልጆቻቸውን ጭምር ሲገብሩና ጸዋትወ መከራ እንዲቀበል ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ 

ይሁንና ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቱን ይመራ በነበረው ፓርቲ ውስጥ በተደረገው የሥልጣን ሽግግር ሂደት ከተወሰነ በኋላ የትግራይን ክልል የሚመራው አካል ከማእከላዊው አመራር ጋር ልዩነት በመፈጠሩ ተግባብተውና ተመካክረው ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን በሰላም እንዲመሩ የሚያደርግ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ በተለያዩ ጊዜያት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ሓላፊ አባቶችና አባሎቻቸው እንዲሁም ከልዩ ልዩ ማኅበረሰብ የተውጣጡ ታዋቂና የተከበሩ የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምና ፍቅርና አንድነት እንዲመጣ እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሲያደርጉት የነበረውን ውጣውረድና መንገላታት ጉባኤው በታላቅ አክብሮት የሚያስታውሰው ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ባለው ችግር የተነሳ የሰሜን ወሎና የዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ተወካዮች በትግራይ ውስጥ የሚገኙ አህጉረ ስብከት ተወካዮች ሊቃነ ጳጳሳት የዚህ የ40ኛው ጉባኤ ተሳታፊ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ስለሆነም ከላይ በተጠቀሱ አካባቢዎች ለጠፋው ክቡር የሰው ሕይወት ለተቃጠሉ ገዳማትና አድባራት ለተፈናቀሉ ወገኖች ለወደመ ቅርስ ንብረት ልባዊ ኀዘናችንን እንገልጻለን፡፡ 

በይቀጥላልም ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበትና እየተነጋገረበት የሚገኝ መሆኑን ብንገነዘብም ለወደፊቱ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶበት የጥናት ቡድን በመሰየም ከመንግሥት ጋር በመነጋገር የወደመ ንብረት እንዲካስ ቤተሰቦቻቸቸውን በሞት ያጡ እንዲቋቋሙ የተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና የመኖር ዋስትና የሕግ ከለላ እንዲያገኙ ጥረት እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡ እኛም የጉባኤው ተሣታፊዎች የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

 1.   የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ በሚል ይንቀሳቀስ ከነበረው ክፍል ጋር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባለፈው ጥቅምት 2013 ዓ.ም ባካሄደው ጉባኤ ችግሩ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና እንደ አባቶቻችን ልማድ በውይይት እንዲፈታ በሳልና ጥበብ የተመላበት ውሳኔ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ 

ይሁን እንጂ ውይይቱና ውሳኔው በአህጉረ ስብከት በወረዳዎችና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተላልፎ ያልተቋጨና የተንጠለጠለ በመሆኑ አሁንም በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ውስጥ በወረዳዎችና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውዝግብ መኖሩን በሪፖርቱ ተደምጧል፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ውሳኔ አፈጻጸሙን እስከታች በማውረድ የሚታዩ ልዩነቶችን ሁሉ በውሳኔው መሠረት እንዲፈጸም እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

 1. በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የአብነት ት/ቤቶችና ገዳማትን ከማስፋፋት አንጻር በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከተመደበው የድጎማ በጀት በተጨማሪ በርካታ አህጉረ ስብከት ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ግንባታዎችን በራሳቸው ገቢ በመገንባትና ከኪራይ ከሚገኘው ገቢ ለአብነት ት/ቤት ለመምህራንና ለደቀ መዛሙርት በቅዳሴና በማሕሌት ለሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስት ቋሚ ወርኃዊና ዓመታዊ በጀት በመመደብ ቤተ ክርስቲያን እንድትገለገል እንዲሁም ካህናት በአካባቢው ቋንቋ እየሰለጠኑ ለወንጌል አገልግሎት ራሳቸውን እንዲያበቁ የካህናት ማሰልጠኛዎችን በማቋቋም በማጠናከር ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ከቀረቡ ሪፖርቶች መረዳት ተችሏል፡፡ ይህ ተግባር የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ በሚጠበቀው ልክ ለማከናወን አማራጭ የሌለው መፍትሔና ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ በቁጥርጠኝነት ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
 2. በየደረጃው ያሉ አህጉረ ስብከት የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሰበካ ጉባኤያት  በመንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማሟያ የገንዘብ ገቢ ያስገኙ ዘንድ በርካታ ሕንጻዎች ማስገንባታቸውን በየዓመቱ በሚቀርበው የሥራ ፍሬ ሪፖርት እየተገለጹ ይገኛሉ፡፡ ግንባታዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀጠላቸውን የሚያስመሰግን ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጉባኤው ተገንዝቧል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ቋሚ የቤተ ክርስቲያን ሀብቶች ተሰፍረውና ተቆጥረው ተመዝግበው የሚያስገኙት ገቢ ጭምር በግልጽ ታውቆ መረጃው እስከ ዋናው መ/ቤት እንዲደርስ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳነት ይዞና ተነጋግሮ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
 3. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በ2013 ዓ.ም በተለያዩ አርእስተ ትምህርት በተመረጡ ሊቃውንት በየአህጉረ ስብከቱ ለሚመለከታቸው የሥራ ሓላፊዎች የተሰጠው ትምህርታዊ ሴሚናር በከፍተኛ ደረጃ ያነቃቁ የተለያዩ ሐሳቦች የመነጩበት ነበር፡፡ ይህ ትምህርታዊ ሴሚናር ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት ክብርና ምሥጋና ይግባቸውና አባቶቻችን ቅዱሳን ፓትርያርኮች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሊቃውንት የጀመሩት የወጡበት የወረዱበት የደከሙበት ነገር ግን አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው እንዲሉ አበው በነርሱ ድካም እኛ የበረታንበት ያለደመወዝ ሠርተው እኛ ደመወዝ ተከፋይ የሆንበት አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያበቃው ይህ የሰበካ ጉባኤ ሥምሪት ነው፡፡ 

የ40ኛ ዓመት ጉዞ ስንል የ40 ዓመት ታሪክ በመድበል መጽሐፍ ታሪኩን ስናስቀምጥ የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ማለታችን ሳይሆን ለሰበካ ጉባኤ መጠናከር ሥምሪት የተደረገበትን ዓመት ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የሰበካ ጉባኤ ሥምሪት ውጤት ያስገኘ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በየደረጃው የሚገኙ ሓላፊዎችን የሚያገናኝ ሐሳብ ለሐሳብ የሚያለዋውጥና የሚያስተሳስር የሚያናብብ በአንድ ሐሳብ እንድራመድና እንድንፀና የሚያደርግ ወሳኝ መርሐ ግብር ስለሆነ ለወደፊቱም በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ትኩረት ተሰጥቶት እንዲቀጥል እንዲደረግ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

 1. በውጪ ዓለማት በሰሜናዊና ደቡብ አሜሪካና ካናዳ በአውሮፓና በአፍሪካ በአውስትራሊያ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚገኙ አህጉረ ስብከት በተመደቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የሥራ ሓላፊዎች አስተባባሪነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ቀኖናና ሥርዓተ አምልኮን መዋቅራዊ ሰንሰለትን በጠበቀ መልኩ በየአህጉሩ ለሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን አገልግሎት በመሥጠት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተከታታይ ትምህርተ ሃይማኖት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ ቀኖና ታሪክ ትውፊትና ባህል የአብነት ትምህርት እንዲያውቁ በማስተማር መሬት በመግዛት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን በመገንባት ቤተ ክርስቲያን በመግዛት ያሉትን በማደስ የሥራ መዋቅሩን በማጠናከር የሀገረ ስብከትና የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችን በመክፈት ስብከተ ወንጌልን ለምእመናን ለማድረስ እንደ የአካባቢው ሁኔታ በአካል በስልክና በኢሜል በማስተማር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በውጪው ዓለም ጎልታ እንድትታይ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ እንዲገለገሉ ጉልህ ሚና ከማበርከት በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በተከሠቱ ግጭቶች ለደረሰ ጉዳት ለችግሩ ተጠቂ ወጎኖች ለገዳማትና አድባራት ለአብነት ት/ቤቶች በገንዘብና በቁሳቁስ ያደረጉት አስተዋጽኦና እጅግ የሚያመሰግንና አለኝታነትን ያረጋገጠ ተግባር በመፈጸማቸው ጉባኤው ምስጋናና አድናቆቱን ገልጿል፡፡ 

ለወደፊትም ችግሩ ከሀገራችን እስከሚወገድ ድረስ የጀመሩትን ሃይማኖታዊና ወገናዊ አለኝታና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ከፍ ባለ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

 1. በውጭው ዓለም በተለይም በአውስትራሊያና በሰሜን አሜሪካ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑትን ኦርቶዶክሳውያን የትግራይና የሌላ ክፍለ ሀገር ተወላጆች በሚል እየከፋፈሉ ከሚገኙት መካከል አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል ከአውስትራሊያ አህጉረ ስብከት ከቀረበው ሪፖርት ጉባኤ ግንዛቤ አግኝቷል፡፡ በተከሰተውም ግጭት ምክንያት በውጭ ዓለም የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንና የውጭውን አህጉረ ስብከት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት የሚንድ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
 2. የምዕራቡ ዓለምና የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት እያደረሱ ያለውን ተጽእኖ ለሀገራችንና ለሕዝባችን አንድነት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትልና የተጠቀሱት ሀገራትም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ታሪካዊ ወዳጅነት የሚያሻክር መሆኑን በመረዳት በውጭው ያሉት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ነጩ ቤተ መንግሥት በመግባት ድምጻቸውን በማሰማታቸው ጉባኤው ያለውን አክብሮት እየገለጸ ቀጣዩ  የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የኢትዮጵያን እንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ያለውን አቋም ለዓለም ማኅበረሰብ እንዲያሳውቅ እንጠይቃለን፡፡
 3. በቤተ ክርስቲያኗ መዋቅራዊ አሠራር ውስጥ የሚከሰቱት የመልካዊ አስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሠራሮች የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አስተምህሮ የሚፈታተንና እናት ቤተ ክርስቲያን በምእመናን ልቡና ያላትን ተቀባይነት የሚያሳጣ በመሆኑ ይህ ችግር ተስተካክሎ በመልካም ዓርዓያነት ለመሥራት በቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚወሰኑ ውሳኔዎችን በመፈጸም የሚጠበቅብንን ድርሻ እንወጣለን፡፡
 4. በእንግሊዝና በመላው ዓለም ሀገር የሚገኙት ቅርሶች፣ ታቦታትና ልዩ ልዩ ንዋየ ቅድሳት ወደ ሀገራቸውና መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ የተጀመረው ያላሰለሰ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡
 5. የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሰበካ ጉባኤን ለማቋቋምና ለማጠናከር አባቶቻችን ለአርባ አመታት ሥምሪት በማድረግ ሥልጠናዎችን በማካሄድ በመውጣት በመውረድ በብዙ ድካም ለፍሬ የበቃበትን ዘመን ለማሰብ አርባኛ አመት ልዩ መርሐ ግብር ሲዘጋጅ ሙሉ ታሪኩን የሚገልጥ መድብለ መጽሐፍ በማዘጋጀትና በማሳተም የአርባ ዓመቱን ሙሉ ውጣ ውረድ ስብሰባዎች ሴሚናሮች ውይይቶች የፎቶግራፍ ዐውደ ርእይ በማደራጀትና ለእይታ በማብቃት ይህ መደበኛ ስብሰባ በልዩ ይዘትና ቅርጽ እንዲከናወን መምሪያው ያደረገውን አስተዋጽኦ ጉባኤው ልዩ ምስጋናና አክብሮቱን ይገልጻል፡፡ ለወደፊቱ የቤተክርስቲያኗን በሚገልጽና በሚመጥን መልኩ እንዲያስቀጥል አደራ እንላለን፡፡
 6. የ ፵ኛውን ዓመት ጠቅላላ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ስናደርግ ከእናት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር ሲነጻጸር በርካታ ትርጉም ቢኖረውም ለዚህ ጉባኤ ምሳሌ የሚሆን የእስራኤል ሕዝቦች በ40 ዓመት የበረሀ ጉዞ ወደ ቅድስት ሀገር እንደገቡ እኛም የቃለ ዐዋዲውን ሕግ በማስፈጸምና የቤተ ክርስቲያኗን መዋቅራዊ አሠራር ለማጠናከር በብዙ ውጣውረድ ቆይተንና የሰበካ ጉባኤን የሥራ እንቅስቃሴ አጠናክረን ለዚህ መድረሳችን እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ሲሆን ከዚህ በኋላ ከመጣንበት ተምረን የቤተ ክርስቲያኗን መዋቅራዊ አሠራር አጠናክረን ቤተ ክርስቲያናችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብላ እንድትታይ በመልካም አርአያነት ጠንክረን እንሠራለን፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

© EOTC TV

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top