Connect with us

በአዲስ የአዲስ አበባ መሬት ምዝበራ 120 ኃላፊዎች ታገዱ

Social media

ማህበራዊ

በአዲስ የአዲስ አበባ መሬት ምዝበራ 120 ኃላፊዎች ታገዱ

በአዲስ የአዲስ አበባ መሬት ምዝበራ 120 ኃላፊዎች ታገዱ

(WZ news/ወዝ ኒውስ)

የ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ ዝንባሌ ያላቸው ባለሙያዎችን በማሰማራት በ 11ዱም ክፍላተ ከተማ ባካሄደው ጥናት በተለይ በአቃቂ ቃሊቲ ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ፣ በለሚ ኩራ፣ በየካ እና በቦሌ ክፍለከተሞች ከፍተኛ የመሬት ምዝበራ መካሄዱ ተመለከተ።

በጥናቱ ግኝት መሠረት አስተዳደሩ ፣ቀደም ሲል አምስቱን ክፍላተ ከተሞች ይመሩ የነበሩ ስራ አስፈፃሚዎች ፣ የወረዳ አመራሮችን እና የመሬት ተቋማት 120 ኃላፊዎች ከስልጣን በማንሳት በዕግድ እንዲቆዩ ተደርጓል።
በከተማዋ በተለይ በማስፋፊያ አካባቢዎች ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ጎልቶ መታየቱ ተመልክቷል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ አርብ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ካርታ ከወጣላቸው 2,170 ይዞታዎች ውስጥ በተደረገ ማጣራት 497 ቦታዎች ወይም 207ሺህ ካሬ ሜትር (20.7 ሄክታር) ቦታ ከመመሪያ ውጪ ለሌላ አካል በህገወጥ መንገድ ተላልፎ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

‘’በ2013 ዓ.ም መጀመሪያ የከተማ አስተዳደሩ ባደረገው የማጥራት ስራ ከአንድ ሽህ ሄክታር በላይ የመንግስት ቦታዎች ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ቢያደርግም 383.3 ሄክታር መሬት በድጋሚ መብት በሌላቸው አካላት መያዙ በመረጋገጡ በድጋሚ የማስመለስ ስራ ተሰርቷል’’ በማለት አቶ ጥራቱ ገልፀዋል ።

በተጨማሪም ለአረንጓዴ ልማት ከተለዩ 252 ቦታዎች 35 ቦታዎች በግለሠቦች መታጠራቸውና ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ በሰራው የማጣራት ስራ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ማድረጉንም አቶ ጥራቱ ተናግረዋል።

እንዲሁም ለኃይማኖት ተቋማት እና ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲውሉ ውሳኔ ከተላለፈባቸው 70 ቦታዎች መካከል 39ኙ በውሳኔው መሰረት አለመተላለፋቸውን ፣ ከነዚህም ውስጥ በ19 ቦታዎች ላይ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የከተማውን ካቤኔ ውሳኔ አለመተግበሩን ጭምር አቶ ጥራቱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የመንግስት መሬት በህገወጥ መንገድ ሲያዝ በቸልተኝነት ፣ በጥቅም ትስስር መሬት እንዲወረር ያደረጉ አመራሮች ፣ባለሙያዎች እና ሌሎች አካላት ተለይተው በየደረጃው ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ስራ መጀመሩን አቶ ጥራቱ ተናግረዋል፡፡

ከመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አመራሮች ጀምሮ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ድረስ በብልሹ አሰራር ውስጥ የተሳተፉ ፣ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ከ120 በላይ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተለይተው ከስራ ታግደው በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ጥራቱ አብራርተዋል፡፡

በተመራጯ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው ካቢኔ፣ ጥፋት ፈፅመዎል ተብለው ከሹመት በተገለሉት የቀድሞ አመራሮች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እርምጃ እንዲወሰድ ወስኗል ።

ቀደም ሲል ጥፋት አለባቸው ለተባሉ ባለስልጣናት በድጋሚ ሹመት ሲሰጥ ለቆየው የከተማው አስተዳደር ይህ አዲስ የጀመረው ያለመሾም እርምጃ በልዩነት ተመዝግቦለታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካና ከፍተኛ የመሬት ስሪት ሙያ ያላቸውን ከ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ፣ ከግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን እና ከፕላን ኮምሽን አወጣጥቶ ባዋቀረው ቡድን ፓለቲካዊና ቴክኒካዊ ጥናቶች ተካሂደዋል።

በአዲስ አበባ አስተዳደራዊ ክልል ውስጥ በሚገኙ 11 ክፍላተ ከተሞች ላይ በተካሄደው ጥናት በተለይ በአምስቱ ክፍላተ ከተሞች የመሬትና መሬት ነክ ሙስና ጎልቶ ወጥቷል ተብሏል። በነዚህ ክፍላተ ከተሞች አርሷደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም እየተካሄደ በሚገኘው ፕሮጀክት ለማይገባቸው መሬት በመስጠት፣ተደጋጋሚ የካሳ ክፍያ በመስጠት ከፍተኛ ምዝበራ ተፈፅሟል ።

በዝርዝር ሪፖርቱ አርሷደር ሳይሆኑ አርሷደር እየተባሉ መሬት የተሠጣቸው ፣ ተደጋጋሚ ካሳ ክፍያ የተሠጣቸው መኖራቸው ፣የካቢኔ ውሳኔ የማያከብሩ መኖራቸው በአጠቃላይ ህገወጥ ተግባራት ውስጥ የተዘፈቁ አካላት በርካታ መሆናቸው መረጋገጡ ታውቋል።

የታገዱት የክፍለ ከተማ አመራሮች ከአጥኝ ቡድኑ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። አመራሮቹ በሰጡት ምላሽ ይህን ያደረጉት ፣ከበላይ አካል አቅጣጫ እየተሰጣቸው እንደሆነ ገልፀዋል።
ነገር ግን የአመራሮቹ መከራከሪያ በከንቲባ አዳነች ካቢኔ ተቀባይነት እንዳላገኘ ታውቋል።የአመራሮቹ መከራከሪያ ተቀባይነት ያላገኘው አመራሮቹ፣ ቦታው ላይ የተሠየሙት ህግን ተንተርሰው አገልግሎት እንዲሰጡ እንጂ ያልተገባ ትዕዛዝ ተቀብለው እንዲፈፅሙ አይደለም በሚል መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top