Connect with us

ህወሓት ስትሆን ‹‹ወልዲያ እና መቄት ላይ ተወረርኩ›› ብለህ ማልቀስ ይቻልኻል!

ህወሓት ስትሆን ‹‹ወልዲያ እና መቄት ላይ ተወረርኩ›› ብለህ ማልቀስ ይቻልኻል!
Photo: Social media

ማህበራዊ

ህወሓት ስትሆን ‹‹ወልዲያ እና መቄት ላይ ተወረርኩ›› ብለህ ማልቀስ ይቻልኻል!

ህወሓት ስትሆን ‹‹ወልዲያ እና መቄት ላይ ተወረርኩ›› ብለህ ማልቀስ ይቻልኻል!

(አሳዬ ደርቤ ~ለድሬ ቲዩብ)

የተናጠል ተኩስ አቁሙን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከከሸፈው የአፋር ወረራ በተጨማሪ ላለፉት ሦስት ወራት ሦስት የአማራ ዞኖችን ወርሮ የጋሊኮማን ሕጻናት የጨፈጨፈው፣ የአጋምሳ መንደርን ከነ ነዋሪዎቿ በከባድ መሣሪያ ያወደመው፣ ጪና ተክለ ሃይማኖት ላይ ንጹሐንን የረሸነው፣ በቦዛ እና በቆቦ ዙሪያ በርካታ ዜጎችን የቀጠፈው ‹‹ወራሪ›› ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ሠራዊት በትር ወገቡን ሲዳብሰው፡-

‹‹የጋሊኮማን ግፍ- የአጋምሳን ጭፍጨፋ

የጪናን ግድያ- የራያን ዘረፋ

ወደ ደቡብ ወሎ- ሳማትር ላስፋፋ

በወረርኩት ምድር- ድንገት ተወርሬ

መጥፋቴ ነውና- ወሎ ተቀብሬ

እናት አሜሪካ- ሁሉ የሚቻልሽ

ወሎን ለህውሓት- ሰጥቻለሁ ብለሽ

በብሊንከን በኩል- ታደጊኝ እባክሽ›› እያለ መነፋረቅ ጀምሯል፡፡

‹‹አራት ኪሎን እቆጻጸራለሁ›› የሚል ግብ አስቀምጦ፣ ሕዝባዊ የሚለውን ጦር እየመራ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወረራ ፈጽሞ መጠነ ሰፊ ውድመት ሲፈጽም የከረመው አሸባሪ የኢትዮጵያ አፈሙዝ ገና ከመነሳቱ፡-

‹‹የአራት ኪሎን እልፍኝ ፥ መቆጣጠር ሳስብ

ገብቻለሁና- ከኢትዮጵያ መረብ

በፈርጣማ ክንዷ ፥ ደቁሳ ሳትቀብረኝ

እባክህ ጆ ባይደን ፥ ፈጥነህ ድረስልኝ››…… የሚል እሪታውን ማቅለጥ ጀምሯል፡፡

የ120 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችን አገር እንደ እቃቃና ጨረቃ ቤት በመቁጠር ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ እንጦሮጦስ ድረስ እወርዳለሁ›› በሚል ፉከራ የፍርሰት ዘመቻውን ከጀመረ በኋላ ጎንደርና አፋር ምድር ላይ ያልታሰበ ቅጣት ሲያጋጥመው፣ በሌላ መልኩ ግን ለባለፉት ሦስት ወራቶች ሰሜን ወሎን ተቆጣጥሮ ከሊጥ እስከ ዱቄት፣ ከባንክ ቤት እስከ መኖሪያ ቤት፣ ከሕብረት ስራ ማሕበር እስከ መንግሥት መሥሪያ ቤት፣ ከዩኒቨርስቲ እስከ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ሲዘርፍ የከረመው የሽብር ቡድን ‹‹አሻንጉሊት›› የሚል ሥም የሠጣት የብረት ወፍ በአናቱ ላይ መፈንጨት ስትጀምር፡-

የዓድዋን ታሪክ- ይደገማል ዛሬም- መባሉን ሰምቼ

ጎራዴና ጋሻ- የያዘ ጦር ስቃኝ- ክላሼን አንግቼ

ኢትዮጵያን አፍርሼ- አደርጋታለሁ ስል- እንኩትኳች፣ አመድ

በአሻንጉሊት ጥቃት- እቅዴን ሰርዤ- እንጦሮጦስ ሳልወርድ

ተ.መ.ድ ሆይ መላ አምጣ- በአየር ነይ አየርላንድ››…… እያለ ይማጸን ይዟል፡፡

‹‹የትግራይ ገበሬዎች የእርሻ ወቅት እንዳያልፋቸው›› በሚል ውሳኔ ከመቀሌ ለቅቆ የወጣውን መከላከያ ሠራዊት ተከትሎ የአማራ አርሶ አደሮች ላይ ወረራ በመፈጸም ማረሻ በሚጨብጡበት የከሰብ ወቅት ክላሽ እንዲያነሱ ያስገደደው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ጎጇቸውን ጥለው እንዲፈናቀሉ ያደረገው፣ ተነግሮ የማያልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደረሰው… አረመኔ ቡድን በዚህ ሁለት ቀን በወገን ጦር ጎኑ ሲደቆስ… 

‹‹የወሎን አዝመራ- ሰብስቤ ልወስድ

ሳጓጉዝ ከረሜ- ጆንያና ማጭድ

ባላሰብኩት ጊዜ- ድንገት ከተፍ ብለው

ሊወቁኝ ነውና- እንደ ሰብል አጭደው

ዛሬ ነገ ሳትል…

ጸጥታው ምክር ቤት- መንግሥትን ገዝተው›› እያለ የአዞ እንባውን ማፍሰስ ጀምሯል፡፡

ጩኸቱን ጠቅለል ስናደርገው…

 በህወሓት ዘንድ ኅሊና እና ልቦና፣ ማሰብና ማገናዘብ የሚባሉ ነገሮች ከነጠፉ ቆዩ፡፡ በመሆኑም ምድርህን የሽብር ሜዳ አድርጎ ቤተ-እምነትን ሲያቃጥል፣ ዜጎችን ሲገድል፣ ከተሞችን ሲያወድም… ከከረመ በኋላ ወገቡን ያዝ ሲደረግ በደሉን አስረክቦህ ኀዘንህን ይቀማህና ‹‹ወልድያና መቄት ላይ ወረራ ተፈጸመብኝ›› በሚል እሪታው ያደነቁርኻል፡፡

ስትሸሸው ለዳግም ወረራ ተከትሎህ ይመጣና ‹‹ትግራይ ትስዕር›› እያለ ንጹሐን ደረት ላይ ይተኩሳል፡፡ አገሩ ላይ የሚሰነዝረው ዛቻ አልበቃው ብሎ ሰማዩን እና ደብሩን በእርሳስ እየቦዳደሰ እግዜሩ ላይ ይፎክርበታል፡፡ ጭራውን ሲያዝ ደግሞ ያለምንም ሼም ‹‹በወረርኩት መሬት ላይ ተወረርኩ›› እያለ የአዞ እንባውን ያንጠባጥባል፡፡ 

የዚህ ሁሉ ድንቁርና ምንጭ ታዲያ ህወሓት ‹‹በዓለም ላይ ያሉ አእምሮዎች ሁሉ እኔ የማስበውን ብቻ የሚያስቡ እንጂ ሐቅን እና ቅጥፈትን የሚያገናዝቡ አይደሉም›› የሚል ብቸኛ መረጃ የተጫነበት ጭንቅላት ባለቤት መሆኑ ሲሆን… በዚህ ዘመቻም እንደ ቀድሞው ጅራቱን ሳይሆን ጭንቅላቱን ተመትቶ አገራችን ሰላም ታገኝ ዘንድ እመኛለሁ፡፡

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top