ይድረስ ለምሁሩ ወዳጄ!!
ይድረስ የኑሮ ውድነት ላነተበህ፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ከሰውነት ተራ ላወጣህ ምሁሩ ወዳጄ!… ያቺ ከልደታ ባዕታ የማታደርስህን ገቢ ለመሸሸህ ከግማሽ እድሜህ በላይ ቆርሰህ እስከፒ.ኤ.ቺ.ዲ ዲግሪ ድረስ ተማርክ፤ ለፋህ፣ ደከምክ፡፡ እነሆ ተምረህ ስታበቃ የደመወዝህ ስኬል እንደአሮጌ የባቡር ፉርጎ እየተጎተተ 15 ሺ ብር ላይ ቆመ፡፡ ከዚህ ላይ መንግስት 35 በመቶ ታክስ ሲያነሳለት፣የጡረታ ፣የአባይ ግድብ መዋጮ ሲቀነጫጨብለት.. ከዚያም ከዚህም የቃረምካቸው የቅሌት መዝገቦች(ብድሮች) ሲወራረዱ…ጠላትህ ክው ይበል፤ ክው የሚያደርግ ፍራንክ ይዘህ ወደሚስትና ልጆችህ ትነጉዳለህ፡፡
አማኝ ነህና ለዚህም ተመስገን ትላለህ…“ተመስገን፤ ይኸንንም አታሳጣኝ!..ይኸንንም ያጡ ብዙዎች አሉና አንተ በቸርነትህ ጎብኛቸው… አስባቸው!” እያልክ ነግቶ በመሸ ቁጥር ለብቻህ ታጉተመትማለህ፡፡ ይቅርታ፤ ትጸልያለህ፡፡
ጮሌዎቹ ባልንጀሮችህ “መንገዱን እወቅበት!” እያሉ ጠዋት ማታ ይጎተጉቱሃል፡፡ እነሱን እያቸው!…መንግስትን ደመወዝ ጨምርልኝ ከማለት ይልቅ “ይህ ልማታዊ መንግስታችን ባዶ ካዝና ነው የተረከበው፤ የገቢያችን ማነስ ድህነታችን የፈጠረው ችግር ነው!…ችግሩ በልማታዊ መንግስታችን ጥረት ይፈታል!…”ተረረም..ተረረረም..በማለት በየመለኪያ ቤቶች ጭምር ዲስኩራቸውን እየነፉ፤ ግን ቀብረር…ሞልቀቅ ያለ ኑሮአቸውን ያጣጥማሉ፡፡ ከየት አምጥተው ይመስልሃል ወዳጄ?!…ዕድሜ ለልማታዊ መንግስታችን!.. የአንተን ኪስ በጥሩ ደመወዝ መሙላት ቢያቅተውም፤ የሁነኛ ወጃጆቹን ቀዳዳ ኪስና ከርስ ለመሙላት ላቡን መዝራት አልተሳነውም፡፡
ለአንተና ለመሰሎችህ ግን በየቴሌቪዥኑ መስኮት፣ በየስብሰባ አዳራሹ ቋቅ እስኪልህ ድረስ “ዋንኛው ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው!” ሲል ዲስኩሩን ይግታቹሃል፡፡ አንተም ምስኪኑ…አንዳንዴ የሰማኸው ሁሉ እውነት እየመሰለህ ይህንኑ በየሄድክበት እንደበቀቀን ስትደግም ትውላለህ፤ “ዋንኛው ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው!…ኪራይ ሰብሳቢነት የሥርዓቱ አደጋ ነውና በተባበረ ክንድ እናጥፋው!…..ተረረረም..ተረረም…”
ያ አብሮ አደግህ ዶ/ር እንቶኔ 10 ሺ ብር የማትሞላ ወርሃዊ ደመወዝ ይዞ ግራውንድ ፕላስ ዋን ቤት ሰርቷል፡፡ ልጆቹን ለንደን ፣ አሜሪካ ልኮ ዶላር እየመነዘረ ያስተምራል፡፡ ያኛው (ስሙን ቄስ ይጥራውና!)… ከካድሬው በላይ ካድሬ ነኝ የሚለው….፤ መሽቶ በነጋ ቁጥር በፓርቲው እየማለና እየተገዘተ ራሱን ወደንዑስ ከበርቴ መደብ ከፍ ካደረገ ሰንብቷል፡፡ አንተ ግን በፈሪሃ እግዚአብሄር ተሞልተህ… ባዶ ኪስህን…ባዶ ሆድህን…ባዶ ቤትህን ይዘህ ትናውዛለህ፡፡
ለልጆችህ ወርሃዊ ክፍያ አጥተህ ስንቱን ስትቧጥጥ እንደምትኖር የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡…ደግሞ ይኸቺ ባዶነትህ ውስጥ የተሰካች ኩራትህ አናትህ ላይ ወጥታ ስትጨፍር ወግ ነውና ኮራ..ጀነን ትላለህ፡፡ ሰው እናድርግህ! ያሉህን “ልማታዊዋን” እየሸሸህ…እየሸሸህ፤ እነሆ በማትሸሸው ድህነት ማጥ ውስጥ ቦክተህ….ሐሩር እንደመታው ቄጤማ ከነቤተሰብህ ጠውልገህ ትኖራለህ፡፡
ደሃ ነህ!…ገና ጠግበህ መብላት የምትመኝ ነህ!…እናም በስርቆት ከደረጁት ጋር ተሰልፈህ ዛሬም ባልበላ አንጀትህ “ዋንኛው ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው!” እያልክ ትዘምራለህ፡፡ ሌላው መንገድ ያንተ አይደለምና ምን ምርጫ አለህ? ንጹህነትህን የሚጠየፉ ሌቦችን ከማጀብ ውጪስ ምን ተስፋ አለህ?…ግን ይኸ ጽዱ ኢትዮጵያዊ ንጽህናህ!…ደግነትህ!…ጨዋነትህ! የት ድረስ ያዘልቅህ ይሆን?…እንጃ?!….አንድዬ ይታደግህ አቦ!…
(እሱባለው ካሳ- ነሐሴ 2005 …በድጋሚ የቀረበ)