Connect with us

ከድል-ኪሳራ ( ፒሪክ ድል) እንጠንቀቅ!!

ወገን እንቁረጥ?!
Social media

ነፃ ሃሳብ

ከድል-ኪሳራ ( ፒሪክ ድል) እንጠንቀቅ!!

ከድል-ኪሳራ ( ፒሪክ ድል) እንጠንቀቅ!!
(ፋሲል የኔዓለም)

ጦርነቱ እያስከተለ ያለው ጉዳት እንቅልፍ የነሳቸው አንዳንድ ወገኖች “ ጦርነቱ መቼ ይሆን የሚያበቃው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ወያኔ በፍጥነት ተደምስሶ ማየት የሚጓጉትም እንዲሁ “መንግስት መቼ ይሆን ፈጣን እርምጃ የሚወስደው?”ይላሉ ። የመንግስት እና የግል ጋዜጠኞችም የህዝቡን ስሜት እያነበቡ፣ ወታደራዊ አዛዦችን “መቼ ነው ወደ ማጥቃት የምትሸጋግሩት?” እያሉ ደጋግመው ይጠይቋቸዋል።

ወታደራዊ አዛዦችም የህዝቡን ጉጉት እያዩ “ ዝግጅታችንን ጨርሰናል፤ በቅርቡ የምናበስረው ድል ይኖራል ወዘተ” እያሉ፣ ምላሽ ይሰጣሉ። እውነት ለመናገር ሁላችንም ጦርነቱ ቶሎ እንዲያልቅ እንፈልጋለን። ከእኛ በላይ ደግሞ መንግስት ይፈልጋል። ከመንግስት በላይ ደግሞ ህወሃት ይፈልጋል ምክንያቱም በንጽጽር ስናየው በጦርነቱ መራዘም ከሁሉም በላይ የሚጎዳው ህወሃት ነውና።

የሁሉም ምኞት ፈጣን የሆነ ድል ማግኘት ነው። ነገር ግን አንዳንዱ ድል ፈጥኖ ይገኛል፤ ሌላው ደግሞ ዘግይቶ ይመጣል። በፍጥነት መሃል ኪሳራ፣ በመዘግየት መሃል ደግሞ ድል ይኖራል፤ ወይም በተቀራኒው። ፍጥነትና ድል ሲጣመሩ ተመራጭ ነው። ይህ እንዴት ይገኛል የሚለውን መመለስ የሚችለው ግን የነገን የማወቅ ሃይል ያለው እሱና እሱ ብቻ ነው።

የሰው ልጅ ማድረግ የሚችለው በደንብ አስቦ፣ አቅዶና በሁሉም ነገር ተዘጋጅቶች ወደ ስራ መግባት ብቻ ነው። በዚህ ሁሉ መሃልም ቢሆን ያልታሰቡ ነገሮች ( black swan) ሊከሰት ይችላል። ነገን በማወቅ በኩል አንድ የከብት እረኛና አንድ ፕሮፌሰር እኩል ናቸው። ሁለቱም ስለነገ በትክክል መናገር አይችሉም። ፕሮፌሰሩ ከእረኛው የተሻለ ስለነገ መናገር ይቻላል ቢባል እንኳን ” ነገ ጸሃይ ትወጣለች” ከሚል አይዘልም።

አንድ ነገር ግን ልብ ማለት ይገባል። ከራሳችን እቅድ ውጭ፣ በሌሎች ውጫዊ ወይም ውስጣዊ ጫናዎች ተገፋፍተን ፈጣን ወይም በደንብ ያልተዘጋጁበት እርምጃ ከመውሰድ መጠንቀቅ አለብን። በጫና ብዛት በተወሰደ እርምጃ የተነሳ ድል እንኳን ቢገኝ፣ ያ ድል ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል እርግጠኛ መሆን ይቻላል። እንዲያው የረጅም ጊዜ ውጤቱ አክሳሪ ሁሉ ሊሆን ይችላል።

በብዙ ኪሳራ የሚገኝን የጦር ሜዳ ድል የታሪክ ጸሃፊዎች ፒሪክ ድል (pyrrhic victory) ይሉታል። ታሸንፋለህ፣ የምታሸንፈው ግን ብዙ ኪሳራ ደርሶብህ ነው ማለት ነው። ፒሪክ ድልን ድሳራ ( ድል+ኪሳራ) ልንለው እንችላለን።

የፒሪክ ድል ታሪካዊ አመጣጡ እንዲህ ነው። ፒረስ የሚባል የኢፒረስ ( ግሪክ) ንጉስ ነበር። ከ 280 ዓዓ በፊት ከሮማውያን ጋር ተዋግቶ ሁለት ጊዜ ድል አደረገ።

ፒረስ ድሉን ያገኘው ወታደሮቹ ሁሉ ክፉኛ ከተጎዱ በኋላ ስለነበር፣ በቀላሉ ሰው መተካት በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ራሱን አገኘው። “ ለሶስተኛ ጊዜ ተዋግቼ ድል ባደርግ ኖሮ፣ በእርግጠኝነት ያከትምልኝ ነበር” ብሎ መናገሩን ፕሉታርክ ጽፏል።

ህወሃት ጥቅምት 24፣ 2013 ዓም በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ እርምጃ ሲወስድ፣ መከላከያ ሰራዊቲ በቂ ዝግጅት ሳያደርግ የአጸፋ እርምጃ ወስዶ ድል አደረገ። የኋላ ኋላ እንዳየነው ግን ድሉ ፒሪክ ድል ( ድስራ) ነበር። ያንን ድል ለማግኘት ሰራዊቱ ብዙ ዋጋ ከፍሏልና።

የመልሶ ማደራጀት ዋና ተልዕኮውም ከዚሁ ጋር የተያያዝ መሆኑን መካድ አይቻልም። ሰራዊቱ ሳይዘጋጅበት የገባበት ስለነበር አይፈረድም።

ህወሃት ከሰኔ በኋላ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ገብቶ ያገኘው ድልም እንዲሁ ፒሪክ ድል ነው። ህወሃት እነዚህን ቦታዎች ለመቆጣጠር ከፍተኛ የሰው ህይወት ገብሯል።

እንዲያውም ከደባርቅ ውጊያ በኋላ አንድ ሁለት ዙር ማጥቃት ቢያደርግ ኖሮ፣ እስካሁን ተንኮታኩቶ ታሪክ ይሆን ነበር። ህወሃት ጥቃቱን አቁሞ የያዘውን ይዞ ለመደራደር የሚሞክረው፣ ድል በሚለው ውስጥ ተሸንቁሮ ያገኘው ኪሳራ የሚሸከመው ሳልሆነ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለሁለተኛ ዙር ጥቃት ሲዘጋጅ የፒሪክ ድል ሰለባ እንዳይሆን በደንብ ማሰብ አለበት። የጦር አመራሮቹ ከውጭ የሚመጡ ጫናዎችን ተቋቁመው፣ እነሱ ባመኑበት ሰዓትና ቦታ ብቻ እርምጃ እንዲወሰዱ ነጻነቱ ሊሰጣቸው ይገባል ። ይገባኛል!የህዝቡ ስቃይ እንቅልፍ የሚነሳ ነው።

በተለይ በህወሃት በተወረሩ ቦታዎች ላይ ያሉ ሰዎችን ስቃይ ስናይ፣ መከላከያ መቼ በገባና በገላገላቸው የሚያስብል ነው። እኔም በእነሱ ቦታ ላይ ብሆን፣ መከላከያ የሚመጣበትን ቀን ስቆጥር ውዬ እንደ ማድር እርግጥ ነው።

የመንግስት ባለስልጣናት ፈጣን ድል አግኝተው ለህዝባቸው ማሳየትና ፊታቸውን ወደሌሎች ጉዳዮች ማዞር ይፈልጋሉ። ነገር ግን ዘላቂ ድል ይገኝ ከተባለ፣ ከጫና ነጻ ሆኖ ማሰብንና መዘጋጀትን ይጠይቃል። በተለይ ጋዜጠኞች በመከላከያ አዛዦች ላይ አላስፈላጊ ጫና ከመፍጠር ቢቆጠሩ፣ ጥሩ መስሎ ይታየኛል።

የህዝቡን ስቃይ ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት መቀጠል አለበት። ነገር ግን “ህዝቡ እየተሰቃየ ነውና ቶሎ እርምጃ ውሰዱ” የሚለው ውትወታ፣ ድስራ ( የድል ኪሳራ) ውስጥ እንዳይከተን እሰጋለሁ።

ወታደራዊ የሆኑትን ነገሮች መኮንኖች በራሳቸው የጊዜ ማእቀፍ እንዲፈጽሙ እድሉን እንስጣቸው። ይህ ሲባል እነሱም ዝም ብለው አላስፈላጊ ጊዜ ይውሰዱ ማለት አይደለም። ጊዜ እንውሰድ ቢሉም እንኳን ጊዜው ጊዜ አይሰጣቸውም። ከእኛ በላይ የሁኔታውን አስከፊነት እነሱ ይረዳሉ።

የእኔ ምክር ውስጣዊ ወይም ውጫዊ ግፊት እያደረግን ወታደራዊ አዛዦቹ ካስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ ውጭ ፈጥነው እርምጃ በመውሰድ፣ የድል ኪሳራ ውስጥ እንዳንገባ ጥንቃቄ ይደረግ የሚል ነው።

በተለይ ጋዜጠኞቻችንና አክቲቪስቶቻችን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የመልሶ ማጥቃቅ እንቅስቃሴ፣ በአነስተኛ ዋጋ ትልቅ ድል እያስመዘገበ በመሆኑ፣ ይህንኑ እያባዙና እያሳደጉ መሄዱ አዋጪ ስትራቴጂ ነው።

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top