Connect with us

“የገዳዮች  ወንድማማችነት”

"የገዳዮች ወንድማማችነት"
አገኘሁ አዳነ ድልነሣሁ

ነፃ ሃሳብ

“የገዳዮች  ወንድማማችነት”

“የገዳዮች  ወንድማማችነት”

ሰዎች በተለያየ ርዕሰ ነገር ወይም አላማ ይወዳጃሉ:: የወዳጅነቱ አይነት የትየለሌ በመሆኑ ቆጥሬ አልዘልቀውም::  በጥቅሉ ግን ማህበራዊ ፋይዳው መልካም የሆነ ህብረት ሲሆን ያ ጓድ የለውጥ ሰራዊት/ሐዋርያት  “pioners of change”  የሚል ታሪካዊ ቅጽል  ያገኛል::

እንደሰንደቅ የሚውለበለብ ድል ባያቀዳጅም ዘወትራዊ ሕይወትን በድል የሚያሻግር መደበኛ ወንድማማችነትም ክብር ይገባዋል:: አላማው በጉልህ የማይታየው የፈንጠዝያ ውድጅትም ቢሆን የሚለካው አግኝቶ “ቢሰፍሩት” ዋጋው ከፍ ሳይል አይቀርም:: ዝንጋኤ እስካላስከተለ ድረስ አብሮነት ደግ ነው::

እኔን ግርም የሚለኝ የነፍሰ ገዳዮች “ወንድማማችነት” (Fraternity of  Assasins) ነው:: ይህ ውድጅት በተለያየ ምክንያት ይመሰረታል:: አንዳንዱ እጅግ እውቀታዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ፍልስፍናዊ መሠረት ያለው ይመስላል:: ይሁንና የዚህን ህብረት መሠረት ቢያናጉት ከሆድ ወይም ከግላዊ ጥቅም የዘለለ ጉዳይ አታገኙበትም:: 

ይህ ቡድን ለስሙ መጠርያ ተጨናቂ፣  ለቀለሙ ማማር ተብረቅራቂ፣ የሆዱን ጩኸት “በሕዝብ አለኝታነት” ደባቂ ነው:: ይህን መልከ ቀናነት ለመቀዳጀት የታቀደ “እውነት”የሚመስል ቅደም ተከተላዊና ፈር ያለው ስልት ያዘወትራል:: ይህ ውድጅት በነገረ ፆታ፣ በነገረ ወሲብ፣ በሐይማኖት፣ በብሔር፣ በፖለቲካዊ አቋም፣ በሙያ፣ በመሳሰለው ታላላቅ ስብዓዊ ጉዳይ ሁሉ ልታይ ልታይ ይላል::  ሀገር ያውካል:: ይህ አይነቱ ውድጅት “ይሉኝታ” ሲያልፍም አይነካው:: እንደደጎች ሁሉ የዚህን ቡድን ደቀ መዛሙርት  በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ::

  1. የጋራ የሆነችውን ሀገራችንን ጠፍጥፈው ዛሬ የሰሯት ይመስል: እኔ ብቻ አውቅልሻለሁ ይሏታል:: መሽቶ እስኪነጋ “አያምኗትም” ከቆሙበት ስፍራ በቀር ተጨማሪ ወይም የትየለሌ ግላዊም ቡድናዊም አንጻር/ምልከታ/አ ቋ ም ወዘተ. እንዳለ አይረዱም::

ቢረዱም ሌላው ሁሉ የማይረባና የተዋረደ ነው:: በጉልህ የሚታያቸው “ከሀገር የሚሰፋው ሆዳቸው” ነው:: ሀገር አፍ አውጥተሽ ተናገሪ ቢሏት ስለነዚህ ሰዎች ቃላት የሚያጥሯት ይመስለኛል::

በሌላ ወገን እኒህ ሰዎች በሰይፉ መታፈርያ ፍሬው አንዲት የግጥም አንጓ እንዲህ ይታዩኛል:-

“ይህ ዓለም ይህ ዓለም” ይላሉ:

ይህን ዓለም ሞልተው እንደኖሩ ሁሉ”

ሀገሩ የማናየው፣ የማናውቀው፣ የማንሰፍረው፣ የማንለካው ፣ የማንገምተው ጭምር ብዙ ጉዳይ አለው:: ዓለም ሰፊ ነው:: ይህን ሲያውቅ ሰው ትህትና ትዘልቀው ይመስለኛል::

  1. ጩኸት መቀማት አይነተኛ ጠባያቸው/ፍሬያቸው ነው:: በዚህ ጠባያቸው “ራሳቸው ገርፈው ራሳቸው አልቃሽ” በምሆን ከፊት ተሰላፊ ናቸው::
  2. ስለመቃወም መቃወም የሚያስገኘውን ትርፍ ያሰላሉ:: ጀብድ እንጂ ጀግንነት አያውቃችውም::
  3. ተቆርቋሪ ከሚመስለው የፊት ገፃቸው ባሻገር  ድብቁ ህልማቸው ሆድ መሙላት ወይም ጥቅም ማሳደድ በመሆኑ ያቀዱት ሲከሽፍ ካሸናፊው ጎን ለመሰለፍ እፍረት አታውቃቸውም:: የጠበቁት ጥቅም ካልተገኝ ጠላት ለመሆን እንዲሁ አይሰንፉም:: ይቸኩላሉ::
  4. በነሱ ዘንድ ወዳጅ ማለት ከጠባብ ሆዳቸው የመንጨ ደካማ ህልማቸውን የሚያገለግል እና ለሙት ህልማቸው ሕይወት መዝራት “ለምን? ” ሳይል የሚሰለፍ agent/object ነው::

እኒህ ሰዎች ውድጅት የሚያስፈልጋቸው የሰው ልጅ ለብቻው የማይገፋቸው በርካታ ሕይዎታዊ ጉዳዮች ስላሉት ነው:: ወዳጅነት ለብቻ የማይ’ገፋውን ለመግፋት የሚመሰርቱት ስልታዊ ኮንትራት ወይም strategic alliances ነው:: 

እንደተራራ የከበዳቸውን ሸክም ካራገፉ በኃላ ግን “ሆዳቸው አምላካቸው” ሆኖ ያርፈዋል::

በተለምዶ “ባንዳነት” ለፍርፋሪ ተገዝቶ ከውጭ ጠላት ጋር በግልፅ በመወገን ሀገርን መጉዳት/መክዳት ብቻ የሚመስለው ብዙ የዋህ አለ:: ነገር ግን ባንዳነት መጠነ ዙሪያው እጅግ ሰፊ ነው:: የሀገርን ህልም ለግል ሆድ መሸቀጫ ማድረግ መጠኑም ልኩም ካቅም በላይ ነው::

የገዳይ ወንድማማቾቹን መስፋፋት በማህበራዊ ድረ ገፆች፣ በቴሌቪዢን መስኮቶች፣ በሬዲዮና በመሰለው ሁሉ አዋጅ ነጋሪ ሆነው ማየት አዲስ አልሆን አለ:: ተለመደ:: የምናዋጣው ማንኛዋም “ቅንጣት” ነገ ለሚፈጠረው ሀገራዊ ግዙፍ ምስል አስተዋፅኦ ስላለው እየተስተዋለ ለማለት የተፃፈ::  ምክሩ መካሪውን እንዲጨምር ይሁን አሜን!

#አገኘሁ_አዳነ_ድልነሣሁ

***

ማስታወሻ:- አቶ አገኘሁ በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ፤ የአለ ፈለገ ሰላም የሥነጥበብ ት/ቤት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top