Connect with us

ይድረስ ለሱዳን …. ከኢትዮጵያ

ይድረስ ለሱዳን .... ከኢትዮጵያ
እንዴት ከርመሻል? ሰውም ምድሩም ሐቢቢ ነው ወይ? ክረምቱስ እንዴት አለፈ? ከዓባይ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሊት ጋር ተያይዞ ሊያጋጥመኝ ይችላል ብለሽ የገመትሽው የውሃ ጥም እንዴት አደረገሽ? እነ ግብጽና አሜሪካስ እንዴት ናቸው?

ባህልና ታሪክ

ይድረስ ለሱዳን …. ከኢትዮጵያ

ይድረስ ለሱዳን
ከኢትዮጵያ

(አሳዬ ደርቤ ከድሬቲዩብ)

እንዴት ከርመሻል? ሰውም ምድሩም ሐቢቢ ነው ወይ? ክረምቱስ እንዴት አለፈ? ከዓባይ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሊት ጋር ተያይዞ ሊያጋጥመኝ ይችላል ብለሽ የገመትሽው የውሃ ጥም እንዴት አደረገሽ? እነ ግብጽና አሜሪካስ እንዴት ናቸው?
ሱዳንዬ፡- ‹‹እንኳን አደረሰሽ›› ባትይኝም ይሄን ደብዳቤ የምጽፍልሽ አሮጌውን ዓመት ጨርሼ አዲስ ዓመቴን በተቀበልኩ ማግስት ነው፡፡ እናም አዲሱ ዓመት ላይ ሆኜ ያለፈውን ዓመት ሳስበው የኔ ሳይሆን ያንቺ ዘመን ሆኖ ማለፉን እረዳለሁ፡፡

ምስራቅ አፍሪካ ላይ የምገኝ የምዕራቡ ዓለም ቁራጭ ነኝ›› በሚል አስተሳሰብ እራስሽን ከእነ አሜሪካ ተርታ መድበሽ ስትጠብሪብኝ መክረምሽን አስታውሳለሁ፡፡በእድሜም ሆነ በአስተሳሰብ ታላቅሽ ስለሆንኩ የጦርነት ግብዣሽን በትዕግስት አለፍኩት እንጂ ቀላል አልተሳፈጥሺኝም፡፡

ቆይ እኔ እምለው ኑቢያዬ፡- ልማት ይመስል የጦርነት አምሮት ሊደፋሽ የነበረው ከፈርዖኖቹ ምን አይነት ጽንስ ቢታረግዥ ነው? ከምሬ እኮ ነው! ‹‹ዓባይ ተገደበብኝ›› በሚል ሰበብ ጠብ ስትፈልጊኝ መክረምሽ አንሶ ‹‹የኔና ያንቺ ግንኙነት ስላበቃለት ወንዝሽን ሰብስበሽ ያዥልኝ›› በሚል ምክንያት ጦርነት ልትገጥሚኝ ትንሽ ነበር እኮ የቀረሽ፡፡ በጎንደር በኩል ያለ መሬቴን መውረርሽ አልበቃሽ ብሎ ‹‹ቅኝ ግዛት ልገዛሽ እፈልጋለሁ›› ልትይኝ እያሟሟቅሽ ነበር እኮ፡፡ ‹‹በመተማ በኩል ሱዳን ላይ ወረራ የፈጸምኩት እኔ እሆን እንዴ?›› ብዬ እስካስብ ድረስ ‹‹ግጠሚኝ›› እያልሽ ስትለምኒኝ ነበር እኮ፡፡ የኣላህ ጌታዬ!

ቆይ ግን ሱዳንዬ በዚህ ልክ ጥጋብ የነፋፋሽ ምን አይነት ሺሻ እየነፋሽ ነው? የየት አገር ሩዝ ቀቅለሽ ብትበይ ነው? ከመጠን በላይ የፈነዳሺብኝ ምዕራባውያኑ ምን አይነት ልብ ቢገጥሙልሽ ነው? በዚያ ልክ ጦርነት ያማረሽ ኤክስፓየርድ ከማድረጉ በፊት ጥቅም ላይ መዋል ያለበት ስንት አቶሚክ ቦንብ አበልጽገሽ ነው? እንዴት እንደታዘብኩሽ አትጠይቂኝ፡፡

ደርቡሽዬ፡- በእነዚያ ጊዜያትም የፈጸምብሽኝን ግፍና ክህዴት ሳስበው ምን እንደማደርግ ታዉቂያለሽ?ወደ ብር ሸለቆ ማሰልጠኛ ጣቢያ ሄጄ የልጆቼን የእድገት ደረጃ በመገምገም ብስጭቴን አበርዳለሁ፡፡

በስደተኞች ሥም የተቀበልሻቸውን ልጆቼን እያስታጠቅሽ ስትልኪልኝ መክረምሽን ሳስታውሰው ባጠባኋቸው ልጆች የተነከሰ ጡቴን ጨብጬ ወደ ሁርሶ በመጓዝ ደም መላሽ ልጆቼን ስቆጥር እውላለሁ፡፡ ድንበሬን ደፍረሽ የሠራሽውን ድልድይና የዘራሽውን ሰብል ስመለከት ወደ ቱርክ ሄጄ ድሮን ስጎበኝ እውላለሁ፡፡

የምዕራባውያን እና የፈርዖን ፈረስ ሆነሽ ስትፈነጭብኝ መሰንበትሽ ትዝ ሲለኝ ዓባይ ዳር ቁጭ ብዬ ሳለቅስ እውልና ወደ ቤቴ ተመልሼ ቲቪዬን ስከፍተው ለጎርፍ ጥቃት ተጋላጭ መሆንሽን እሰማለሁ፡፡ ያ ጎርፍ ግን ውሃ እንዳይመስልሽ! እንባ እንጂ
ዓመቱን ሙሉ በፈጸምሽው የፍንዳታ ሥራ ሽማግሌ ፈልገሽ ይቅርታ ልትጠይቂኝ ሲገባ ‹‹ሽማግሌ ሆኜ የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግር እፈታለሁኝ›› ማለትሽን ስሰማ ብሔራዊ ቲያትር ገብቼ፡-

‹‹ማን እንደበደለኝ ማን እንደደፈረኝ
ጠያቂ አጣሁ እንጂ መልስማ ነበረኝ›› የሚለውን የአንድ ሰው ቲያትር ስመለከት አመሻለሁኝ፡፡
‹‹ችግር እና ስቃይ፥ ተውሳክ እየላከ፥ ጤናዬን ያሳጣ
ዋነኛው ሕመሜ ፥ ሐኪም ሆኖ መጣ›› የሚል ስንኝ በመጻፍ ብስጭቴን እገልጻለሁኝ፡፡

 

ሱዳንዬ፡- እንደ ላኪዎችሽና እንዳንቺ እቅድ ሳይሆን እንደ ፈጣሪ ፍቃድ ሆኖ ከአሮጌው ዓመት ጋር ብዙ ችግሮቼ አልፈዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት ደግሞ ቀሪ ውስጣዊ ችግሮቼን እቀርፍና ወደ ድንበሬ የምታስጠጊያቸውን የምሥር ታንኮች የምጎበኝልሽ ይሆናል፡፡ ‹‹እንበር ተጋዳላይ›› እያለ የሚያቅራራውን ካሴት ደምስሼ ስጨርስ ‹‹ኡዛዛ አሌና›› በሚል ካሴትሽ ላይ እንዲህ የሚል ሙዚቃ የምቀዳበት ይሆናል፡፡

አንቺ ጎረቤቴ፥ ውሃ ተቀብለሽ እንባ፥ የምትልኪ
እንደ መዥገራም በግ፥ አጥርና ድንበሬን፥ የምትታከኪ
ፍቅሬ ካልተመቸሽ፥ እጂሽን የሚቀስፍ፥ ወታደሬን እንኪ፡፡

የዚያ ሰው ይበለን ብቻ!
ያንቺው ኢትዮጵያ!

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top