Connect with us

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት ያስተላለፉት መልዕክት።

Social media

ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት ያስተላለፉት መልዕክት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት ያስተላለፉት መልዕክት።
እንኳን ለ2014 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!

ይሄን አዲስ ዓመት የምናከብረው በወሳኝ ሀገራዊ ፈተናና ተስፋ መካከል ሆነን ነው። ኢትዮጵያ በፈተና እና ተስፋ መካከል ሆና አዲስ ዓመት ስታከብር ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።

ምናልባትም የመጨረሻዋም አይሆንም። ኢትዮጵያውያን ፈተና የማያስበረግገን፣ ድልም የማያሰክረን ስለመሆናችን ዓለም ሁሉ ያውቃል። ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር ታሪክ ከሚያነሣቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ዐቅሙም አቋሙም አለን።

ኢትዮጵያን የሚፈትኗት ኢትዮጵያን የማያውቋት ናቸው። ኢትዮጵያ ለሺ ዓመታት በነጻነት ኖረች ሲባል ትርጉሙን አይረዱትም ማለት ነው። ጠላት አጥታ አይደለም ሺ ዘመን በነጻነት የኖረችው። ፈተና ረስቷት አይደለም የነጻነት ቀንዲሏ ሳይጠፋ እስከ ዛሬ ያለው።

ኃያላን ራርተውላት አይደለም ከከፍታዋ ያልወረደችው። ሁሉንም እንደ አመጣጣቸው አሸንፋ ብቻ ነው።

ታሪካችንን ሳያውቁ የሚገጥሙንን ታሪካችንን ዐውቀን እንጠብቃቸዋለን። ለወዳጃችን ወተት፣ ለጠላታችን ዕሬት መስጠት እንችልበታለን። ከቶም ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከማሸነፍ እንጂ ከመሸነፍ ጋራ ተጠርቶ አያውቅም። ከነጻነት እንጂ ከባርነት ጋራ ዝምድና የለውም። ኢትዮጵያ ተፈትና ታውቃለች። ተሸንፋ ግን አታውቅም። ቀጥና ታውቃለች፤ ተበጥሳ ግን አታውቅም። የዘመመች መስላ ታውቃለች፤ ወድቃ ግን አታውቅም።

ይህ አዲሱ ዓመት ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን የተጣባትን ፈተና የምንገላገልበት፣ አዲስ መንግሥት የምንመሠርትበት፣ ከደረሰብን ፈተና የምናገግምበትና ፊታችንን ወደ ኢትዮጵያ ብልጽግና የምናዞርበት እንደሚሆን እምነቴ ነው። አዲሱ ዓመት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሚጸናበት፣ ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶቻችን የሚጎለብቱበት፣ የጀመርነው ሪፎርም መልክ የሚይዝበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

ፈተናችን ከኋላ፣ ተስፋችን ከፊት ነው። በሀገር ፍቅር የነደደ፣ በማንነቱ የሚኮራ፣ አካባቢያዊ ማንነቱ ከሀገራዊ ማንነቱ ጋር የተስማማለት፤ አዳዲስ ፈጠራዎችን መሞከር የማይታክተው፤ ባልተሄደበት ለመጓዝ ድፍረትና ጽናት ያለው፣ ጋራ ሸንተረሩን በደንና በምርት ለመሸፈን የሚተጋ፣ አዲስ ትውልድ እየተፈጠረ ነው። ኢትዮጵያ በልጆቿ ተስፋዋን ሰንቃለች።

ለሀገራችንም ሆነ ለግል ሕይወታችን አዲስ ዓመት አዲስ ነገር ይዞ የሚመጣው ለአዲስ ለውጥ ራሳችንን ባዘጋጀንበት ልክ፣ ለመለወጥ ባለን መሻትና እሱን ለማሟላት በሚናሳየው ትጋት መጠን ነው። ለውጥን ከራሳችን ሳንጀምር የሀገራችንን መለወጥ የምንናፍቅ ከሆነ ዘመኑ እንጂ እኛ አልተቀየርም። በሀገር ጉዳይ ጣት ከመጠቆም ይልቅ “ከእኔስ ምን ይጠበቃል?” ማለት ካልጀመርን ዘመኑ አዲስ ቢሆንም እኛ አሮጌው ላይ ቆመን ቀርተናል።

እንደ ሀገር ወደ አዲሱ ዘመን የምናደርገው ሽግግር የሚጎዱንን አሮጌ ማንነቶች በመጣልና በአዲስ ጠቃሚ ማንነቶች በመተካት መሆን አለበት። በየግላችን ከምናደርገው ሩጫ ይልቅ ለጋራ ራዕይ ከተጋን፣ እርስ በእርስ መጓተቱን ትተን ለመተባበር ከቆረጥን፣ ጥላቻን ንቀን ፍቅርን ካነገስን ያኔ ለሀገራችን አዲስ ዘመን ይመጣል።

አዲስ ዓመት ተፈጥሯዊ ነው። አዲስ ዓመትን ሰዋዊ ማድረግ የሚቻለው እኛ በአዲስ ጎዳና ከተጓዝን ነው። ምንጊዜም ያለፈው መነሻችን ነው። የዛሬው መጓዣችን ነው። የነገው ደግሞ መድረሻችን። ትናንት የተጓዝንበትን መንገድ እንደ አዞ አናጠፋም። እንደ ፍየል ቀንድም ትናንትን ብቻ እያየን አንኖርም። ዛሬ ትልቁ ሀብታችን ነው። ዓመትን አዲስ ማድረግ የሚቻለው ዛሬን በመጠቀም ነው።

የ2013 የመጨረሻው ገጽ ጳጉሜን 5 ቀን ተጠናቅቋል። መቼም አይመለስም። የ2014 ዓ.ም አዲሱ ገጽ መስከረም 1 ይገለጣል። ማንም ምንም አልጻፈበትም። አዲሱ ዓመት ሁለት ነገሮችን ለመቀበል ዝግጁ ነው። በባዶው ገጽ ላይ የሚጽፍ ጀግና እና የሚጻፍበት ታሪክ። እኛ ዝም ብንል፣ ሌሎች የኛን ነገር በፈለጉት መንገድ ይጽፉበታል። እኛ ባንጽፍም የኛ ያልሆነ ነገር ይጻፍበታል።

አሁን ቁልፉ ጥያቄ አንድ ነው። በዚህ ለሁሉም ባዶ ሆኖ በቀረበው አዲሱ የዘመን መጽሐፍ ላይ እኛው ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ዕጣ ፈንታ እንጽፋለን? ወይስ ሌሎች እንዲጽፉልን አሳልፈን መጽሐፉን እንሰጣለን? አባቶቻችን የራሳችንን የዘመን አቆጣጠር ሲፈጥሩ የራሳችንን የዘመን መጽሐፍ እንድናዘጋጅና የራሳችንን ዕጣ ፈንታ እኛው ራሳችን እንድንጽፍ ያሰቡ ይመስለኛል።

እኛው ዐቅደን፣ እኛው ሠርተን፣ እኛው ችግሮቻችንን ፈትተን፣ እኛው ተነጋግረን፣ እኛው ተወያይተን፣ እኛው ዘምተን፣ እኛው አሸንፈን፣ እኛው አልምተን፣ እኛው ተጠቅመን፣ እኛው አምርተን፣ እኛው ረሐብ አሸንፈን – የእኛኑ ጉዳይ እኛው እንድንወስን ይመስለኛል። በአዲሱ መጽሐፍ ላይ መጻፍ ብቻ ሳይሆን አዲሱን መጽሐፍም ራሳችን እንድናዘጋጅ ያሰቡ ይመስለኛል።

በራሳችን ቁሳቁስ፣ በራሳችን ፈጠራ፣ በራሳችን መንገድ የራሳችንን የዘመን መጽሐፍ፣ ለእኛው በሚስማማ መንገድ፣ እኛው እንድናዘጋጀው ያሰቡ ይመስለኛል።

የዘመን መጽሐፉን የፈጠርን ሰዎች በዘመን መጽሐፉ ላይ በራሳችን መንገድ የራሳችን ዕጣ ፈንታ በእጆቻችን ለማሳረፍ የሚያቅተን ነገር የለም። ዕንቅፋቶቻችን እየተወገዱ ነው፤ ወደረኞቻችን ሁሉ ድል እየሆኑ ነው። ዘመኑ የኢትዮጵያ ነው።

አዲሱ ዓመት የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ በአዲሱ የዘመን መጽሐፍ ላይ አዲሱን የብልጽግና ጉዞዋን ትጽፍበታለች። ድሏንና አሸናፊነቷን ትጽፍበታለች። ክብሯንና ታላቅነቷን ትጽፍበታለች።

ሀገራችን ብልጽግናና ድሎቿን ለመጻፍ ስትነሳ መጻፊያ ብዕሯ እኛ ነን፡፡ ቀለሙም የሚቀዳው ከላብና ከደማችን ነው፡፡ ዜጎች ተደጋግፈው በጋራ ለማደግ ሊነሱ ኢትዮጵያ የጨበጠችው ብዕር በአግባቡ መሥራት ይጀምራል፡፡

ዜጎች እርስ በእርስ ሲተሳሰቡ ብዕሩ ትርጉም ያለው ገድል ይጽፋል፡፡ የሀገር ልጆች ልዩነታቸውን ጠብቀው በጋራ ጉዳይ አብረው መቆም ሲችሉ ያኔ ብዕሩ ድልን አድምቆ ይጽፋል።

በድጋሚ መልካም አዲስ ዓመት፣ ዘመኑ አዳዲስ ስኬቶችን የምናስመዘግብበት ይሁን!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጳጉሜን 5፣ 2013 ዓ.ም

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top