Connect with us

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

EOTC TV

ዜና

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ፣ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወዐርባዕቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
– በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትገኙ፤
– ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤
– የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
– በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
– እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ
ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት

ሰማይንና ምድርን፣ በውስጣቸው የሚገኙ ፍጥረታትን የሚታዩትንና የማይታዩትን የፈጠረ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ 2013 ዓመተ ምሕረት ወደ ዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ 2014 ዓመተ ምሕረት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ፡፡

#ዘይሔድሳ ለምድር በበረከቱ$
‹እግዚአብሔር አምላክ ምድርን በበረከቱ ያድሳታል /ድጓ/›
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እኛም እንደምንገነዘበው እግዚአብሔር አምላክ በፍጡራን አእምሮ ሊመጠን በማይችል በረከቱ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ በማያቋርጥ ሒደት እያደሰ ይኖራል ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረታት እየታደሱ እንዲተካኩ በማድረጉ የቀደመው ሲያልፍ አዲሱ ሲተካ የሕይወት ጉዞ የማያቋርጥ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎአል ፡፡

ከጌታችን ከአምላካችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው አሮጌ ዘመን ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ በእርሱ መሥዋእትነት ሲያሳልፍ ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ያለውንም የምሕረት ዘመን ብሎ አድሶታል ፡፡

ወደፊትም በዳግም ምጽአቱ ሰማይንና ምድርን በማሳለፍ የተሻለ ሕይወት ለሰው ልጆች መስጠቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ከቅዱስ ወንጌል ተምረናል፡፡ (ማቴ. 24-25)
በመሆኑም ፍጥረታትን የማሳለፉ ተግባር የእግዚአብሔር ቀዋሚ ሥራ ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በባህርዩ ማርጀትና ኅልፈት የሌለበት ነው፤ በመጻኢው ዓለም ለሰው ልጆች ያዘጋጀው ሕይወትም ማርጀትና ኅልፈት የሌለበት፣ ሁል ጊዜ ሐዲስ ሆኖ የሚኖር ነው፡፡

የሃይማኖታችን ጽኑ ተስፋም በአዲሱ ዓለም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ይሁንና ወደ አዲሱ ዓለም ለመድረስ በየዘመኑ አዳዲስ ሥራዎችን በመሥራት እግዚአብሔርንና ፍጡራኑን በትጋት ማገልገል ያስፈለጋል፡፡

በዚህ ዓለም በፍጡራን ዓቅም ሊታደስ የማይችል ነገር ቢኖር ሃይማኖት ብቻ ነው፡፡ ከሃይማኖት በቀር ሌላው ሁሉ ለሰው ልጅ በሚጠቅም መንገድ ሊሻሻል፣ ሊስተካከልና ይበልጥ ሊጠቅም የሚችልበትን ዘዴ ተከትሎ ማሻሻል ተገቢ ይሆናል ፡፡
ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ አንሥቶ እስካሁን ባለበት ብቻ ቆሞ የኖረበት ዘመን የለም፤ በየጊዜው አዳዲስ የአሠራር ስልቶች እየተፈጠሩ፣ በቀጣይም በሌላ አዲስ ስልት እየተተኩ ይኖራሉ፤ ይህም ቀዋሚ የሆነ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው ፡፡

ከዚህ አኳያ በተሰናባቹ በ2013 ዓመተ ምሕረት ማብቂያና በአዲሱ 2014 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ቆም ብለን ልናስበው የሚገባ ነገር አለ ፡፡

ይኸውም በተሰናባቹ ዓመት የነበረንን አጠቃለይ ሥጋዊና መንፈሳዊ ተግባር መመርመር ሲሆን ያልሠራንባቸው አጋጣሚዎች ካሉም በአዲሱ ዘመን አካክሰን በመሥራት ያመለጠንን ሁሉ በእጥፍ ሠርቶ ለመተካት ጠንክሮ መሥራት ያስፈለጋል ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅድስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፦

አዲሱ ዓመት ሲመጣ የደስታና የተሐድሶ ልቡና ዘመን እንዲሆንልን ከመመኘቱ ጋር በብሩህ ተስፋ መቀበላችን መልካም ነው፤ ይሁንና የሰላምና የእድገት ምኞታችን ወደ ተጨባጭ ፍሬ ሊደርስ የሚችለው በሥራ ብቻ ነው ፡፡

በዓለማችን፣ እንዲሁም በአካባቢያችን የምናያቸው ውብና ድንቅ ነገሮች ሁሉ የሥራ ውጤት መሆናቸውን ለአንድ አፍታ እንኳ ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም ፡፡

እግዚአብሔር እኛን የፈጠረ ለሥራ እንጂ እንድንተኛ አይደለም፤ በሥራ ላይ ቸልተኛነትን የምናሳይ ከሆነ ኑሮአችን መመሰቃቀል ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት መክሊት ቀባሪ ተብሎ መጠየቅም እንዳለ ማሰብ ይገባናል ፡፡ እንደሚባለውም ‹‹ሰው ለመብላት አይኖርም፤ ለመኖር ይበላል እንጂ፤ እንዲሠራ፡፡››

ለሥራ ክብርን አለመስጠት፣ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረበትን ዓላማ እንደመዘንጋት የሚያስቆጥር ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ የሚበጅ አይደለም ፡፡ (ዘፍ. 1፡3)

እግዚአብሔር ከበረከቱ ያጎደለብን አንዳችም ነገር የለም፤ በየጊዜው አዲስ የሆነ ራዕይ፣ አዲስ የሆነ አሠራር፣ አዲስ የሆነ ጥበብ፣ አዲስ የሆነ ዘመን፣ አዲስ የሆነ ጤንነት ወዘተርፈ ከመስጠት ያቋረጠበት ጊዜ የለም ፡፡

ይሁንና እርሱ የሰጠንን አዲስ የዘመን ስጦታ በአዲስ አስተሳሰብና አሠራር ተቀብለን ካልተጠቀምንበት አዲስ ዘመን ማለቱ ብቻ ከምኞትና ከቃላት ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡

ዘመኑ አዲስ ሊሆን የሚችለው እኛ በምናበረክተው ሥራ እንጂ ዘመን በራሱ አዲስ ሊሆን አይችልምና እግዚአብሔር አምላክ የሚወዳችሁና እግዚአብሔርን የምትወዱ ልጆቻችንና ወገኖቻችን በሙሉ አዳዲስ ሥራዎችንና አሠራሮችን በመፍጠር አዲሱን ዓመት በሁለመናው አዲስ አድርገን እናክብረው ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በዓሉን የደስታና የጤና፣ዘመኑን የምሕረትና የሰላም ያድርግልን፡፡ ለሀገራችንና ለመላው ዓለም ሰላምን ይስጥልን፡፡ሕዝባችንን በፍቅርና በአንድነት ያጽናልን፡፡ የተዘራውን ዘር፣ የተተከለውን ተክል ይባርክልን፡፡የተወለዱትን ሕፃናት ያሳድግልን፡፡

መልካም የሥራ ዘመን ያድርግልን !!
እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top