Connect with us

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጣር የተሻሻለ መመሪያ ይፋ ተደረገ

ኘረዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

ዜና

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጣር የተሻሻለ መመሪያ ይፋ ተደረገ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጣር የተሻሻለ መመሪያ ይፋ ተደረገ

በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ ያለውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመግታት እና በስራ ላይ በነበረው መመርያ ቁጥር 30/2013 ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአዋጅ በተሰጣቸውን ስልጣን በመጠቀም ከነሀሴ13 ቀን/2013 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የሚያግዝ የተሻሻለ መመሪያ (መመሪያ ቁጥር 803/2013) አውጥተዋል፡፡

ይህንን አስመልክቶ መግለጫው የሰጡት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት ከፊታችን የተጋረጠብንን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲያልፍ፣ የጥንቃቄ መንገዶችን፣ ክልከላዎችና ግዴታዎች እያንዳንዱ ዜጋ፣ ተቋም፣ አመራር፣ የህግ አስከባሪ አካላት በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ በመተግበርና በማስፈፀም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን አካላትም በመመሪያው ዙሪያ ባለሞያዎችን በመጋበዝ ህብረተሰቡ መመሪያውን እንዲያውቀው በስፋት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንዲሰሩ እና እንደወትሮው ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የወጣው መመሪያ ቁጥር 803/2013 አስራአንድ ክፍሎችና ሰላሳ ሰባት አንቀፆች ያሉት ሲሆን በዚህ መመሪያ በዋናነት የተዳሰሱት ነጥቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል ፡፡

◾️የተከለከሉ ተግባራት እና የተጣሉ ግዴታዎች በተመለከተ

• ማንኛውም ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እያወቀ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት፣ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት የተከለከለ ነው፣

• ማንኛውም ሰው ለሰላምታና ሌላ ለማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ ወይም የእርስ በእርስ አካላዊ ንክኪ ማድረግ የተከለከለ ነው፣

• እድሜያቸው ከ6 አመት በታች ከሆኑ ህፃናት እና በማሰረጃ የተረጋገጠ የመተንፈሻ አካላት ወይም መሰል ችግር ካለባቸው ሰዎች በስተቀር በማንኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ መገኘት ወይም መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፣

• በማንኛውም መንግስታዊ እና ግል ተቋም ሰራተኞችና ተገልጋዮች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲሰጡ ወይም እንዲያገኙ ማድረግ ወይም በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ተገልጋዮች በላይ እንዲቀመጡ ማድረግ የተከለከለ ነው፣

• በክፍት ገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ወይም ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ርቀት መቆምም ሆነ መቀመጥ የተከለከለ ነው፣

• ማንኛውም የመንግስታዊ እና የግል ተቋማት ለሰራተኞች ስለ በሽታው አስፈላጊውን መረጃ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የማድረስ፣ በመግቢያና መውጫ በሮችና ሌሎች አስፈላጊ ቦታዎች በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮችን የማዘጋጀት፣ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡

◾️በቤት ውስጥ ማቆያ እናክብካቤ ወቅት መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ በተመለከተ

• ማንኛውም ከባድ ባልሆነ በኮቪድ-19 የተያዘ ታማሚ በቤት ውስጥ የኮቪድ 19 ህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል፣

• ከሌላው የቤተሰብ አባላት በ 2 የአዋቂ ርምጃ ርቀት መጠበቅ እንዲሁም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም፣ራስን ቢያንስለ 10 ተከታታይ ቀናት በመለየት መቆየት፣ በነዚህ ወቅቶች ከቤት አለመውጣት ይጠበቅበታል፡፡

◾️የኳራንቲን እና የድንበር ላይ ጤና ቁጥጥርን በተመለከተ

ከትራንዚት መንገደኛ በስተቀር በአገሪቱ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል የሚገባ ከአስር አመት ዕድሜ በላይ የሆነ ማንኛውም ተጓዥ ከ 120 ሰዓት ወይም አምስት ቀን በላይ ያልሆነው የተረጋገጠ የRT PCR ምርመራ ኔጌቲቭ ውጤት ይዞ መምጣት አለበት፣ አገር ውስጥ ከገባ በኋላም ለ7 ቀናት በቤቱ ራሱን ለይቶ የማቆየት ግዴታ አለበት፣
እራስን ለ7 ቀናት በቤት ውስጥ ለይቶ የማቆየት ግዴታ የሚከተሉትን አካላት አይመለከትም፡

• በ90 ቀናት ውስጥ ኮቪድ 19 ታመው ያገገሙ መሆናቸውን የሚግልጽ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ
• ዲፕሎማቶች
• የኮቪድ-19 ክትባትን በተሟላ ሁኔታ ወስደው ያጠናቀቁ ከሆነ
• ለኮንፈረንስ ለመሳተፍ የመጣ መንገደኛ ወይም ቱሪስት ወይም ለድንገተኛ አገራዊ ጉዳይ የመጣ መንገደኛ አገር ውስጥ ከገባ በሃላ ተጨማሪ የኮቪድ-19 ምርመራ ተሰርቶለት ዉጤቱ ኔጌቲቭ ከሆነ ለ 7 ቀናት ራስን ለይቶ ማቆየት አይጠበቅበትም፡፡

የኮሮና ቫይረስ ፖዘቲቭ የሆነ ማንኛውም ሰው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የተከለከለ ነው፡፡

◾️በአገሪቱ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል የሚያልፍ የትራንዚት መንገደኛን በተመለከተ

በአገሪቱ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል የሚገባ ማንኛውም የትራንዚት መንገደኛ አየር መንገዱን ለቆ ወይም በረራቸው እስኪደርስ ድረስ አየር መንገዱ ከለያቸው ሆቴሎች ውጪ ወደ ከተማ መግባት የለበትም ፡፡

◾️በአስክሬን ማስተካከል፣ ግነዛና ማጓጓዝ ወቅት ሊደረጉ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች በተመለከተ

ከቀብር በኋላ ለቅሶ መቀመጥ በድንኳን፣ በቤት ውስጥ ወይም ለዚሁ በተዘጋጀ ቦታ ላይ ሲደረግ ሀዘንተኛው እና የቤተሰቡ አባላት እና ለቅሶ የሚደርሰው ሰው ከ50 ሰው ሳይበልጥ እና ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀትን በመጠበቅና ባለመነካካት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ እና ሌሎችበአገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው ማንዋል ላይ የተቀመጡትን ጥንቃቄ ተፈጻሚ በማድረግ መሆን አለበት፡፡

◾️በስብሰባ ወቅት መወሰድ ስላለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች በተመለከተ

• የኮቪድ 19 ጥንቃቄዎችን ባማከለ መልኩ እስከ 50 ሰው መሰብሰብ ይቻላል፣
• ከ50 ሰው በላይ መሰብሰብ ግዴታ ሆኖ ከተገኘ ስብሰባው ሊደረግበት የታሰበበት አዳራሽን ጠቅላላ ስፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት አንድ አራተኛውን፣ በማይበልጥ ሰው ልዩ ፈቃድ ከሰላም ሚኒስቴር እና በተዋረድ ባሉ የክልል፣ ዞን እና ወረዳ የሰላም እና ፀጥታ መዋቅሮች አስቀድሞ በማኘት ሊከናወን ይችላል፣
• ስብሰባውን የጠራው እና መስተንግዶ ሰጪ አካል መሰረታዊ የመካላከያ ዘዴዎች መተግበራቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

◾️የሃይማኖት ስነስርዓቶችን አተገባበርን በተመለከተ

• ሀይማኖታዊ ስርዓት የሚፈጽሙ ሰዎች ሀይማኖታዊ ስርዓቱን በሚፈጽሙበት ወቅት ከሁለት የአዋቂ እርምጃዎች በታች ተጠጋግቶ ስርዓቱን መፈጸም የተከለከለ ነው፣
• የሀይማኖቱ ስርዓት የሚከናወንበት ህንፃ ውስጥ ህንፃው የሚሸፍነውን ጠቅላላ ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት አንድ አራተኛውን የማይበልጥ ሰው በመያዝ ስርዓቱን ማካሄድ ይኖርባቸዋል፣
• በእምነት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ የእምነቱ ተከታዮች የእምነት ስርዓቱን በሚፈስጽሙበት ወቅት ሲቆሙም ሆነ ሲቀመጡ የሁለት ሜትር ርቀት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው፣
• ማንኛውም ሰው የአፍእና አፍንጫ መሸፈኛ ሳይደረግ ወደእምነት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ መግባት የተከለከለ ነው፡፡

◾️የቤት ውስጥ ማህበራዊ ዝግጅቶችን በተመለከተ

• ለልደት፣ ምረቃ፣ማህበር፣ሀዘንን መሰረት የሚያደርጉ ዝግጅቶች (ከቀብር እና ከቀብር መልስ ያሉ ስነስርዓቶች ውጭ) እና መሰል በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ማህበራዊ በዓላት ከቤተሰብ አባላት ከሆኑ ውጭ ተጠራርቶ ማክበር የተከለከለ ነው፣

• ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ ማንኛውም ሰው ከ50 በላይ የማይበልጡ ሰዎች በመሆን እና ሁለት የአዋቂ እርምጃ (ሁለት ሜትር) ተራርቆ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ እና ተገቢውን የኮቪድ 19 መከላከያ የንጽህና እርምጃዎች በመተግበር የሰርግ ስነስርዓት ማካሄድ ይችላል፡፡

◾️የአደባባይ በዓላት አከባበርን በተመለከተ

• ህዝብን በብዛት የሚያሳትፉ የአደባባይ ላይ በዓላት የወረርሽኑ ስርጭት መረጋጋት እስኪጀምር ድረስ በታቸለ አቅም ባይደረጉ ይመከራል፣
• ማንኛውም በአደባባዮች ላይ የሚከበሩ በዓላትን የሚታደምም ሆነ አከባበሩን የሚያስተባበር ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የማድረግ እና በአከባበርም ወቅት ሁለት ሜትር ርቀትን ጠብቆ የመቆምና መቀመጥ ግዴታ አለበት፣
• ማንኛዉም በአደባባይ የሚከበሩ በዓላትን የሚያስተባብር አካል በዓላት የሚከበሩባቸው አደባባዮች የሚሸፍኑትን ጠቅላላ ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት አንድ አራተኛውን የማይበልጥ ሰው በመያዝ ስርዓቱን ማካሄድ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

◾️አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ካፌዎች፣ ባርና ሬስቶራንቶች፣መጠጥ ቤቶች፣ የመዝናኛ እና መጫዎቻ አገልግሎት የሚሰጡ ስፍራዎች በተመለከተ

• በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ሰው በላይ ማስተናገድ የተከለከለ ሲሆን በእያንዳንዱ ጠረጴዛ መካከል የሁለት ሜትር ርቀት ሊጠበቅ ይገባል፣
• አገልግሎትን የሚሰጡ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን የማድረግ ግዴታ አለባቸው፣
• የሚስተናገዱ ሰዎች ከሚመገቡበት እና ከሚጠጡበት ወቅት ውጭ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛን የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡

◾️ሲኒማ ቤቶች፣ ቲያትር ቤቶች እና የስዕል ጋላሪ ቤቶች በተመለከተ

አገልግሎቱ የሚሰጥበት አዳራሽ ወይም ስፍራ ስፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት አንድ አራተኛውን የማይበልጥ ሰው በመያዝ፣ ሁለት የአዋቂ እርምጃ (ሁለት ሜትር) በማራራቅ እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ በማስደረግ አገልግሎቱን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

◾️ስፖርታዊ ውድድሮች በተመለከተ

• ማንኛዉም የስፖርት ዉድድር የስፖርት ዉድድሩ ስፍራ የሚይዘው የታዳሚ ብዛት ታሳቢ በማድረግ ከአንድ አራተኛዉን ታዳሚ የማይበልጥ እንዲታደም በማድረግ ማከናወን ይቻላል፣
• እነዚህ ውድድሮች ወረርሽኙን ባገናዘበ መልኩ መከናወን መቻላቸውን በማረጋገጥ ፈቃድ የመስጠት እና በውድድር ወቅቶችም የጥንቃቄ እርምጃዎች የማይተገበሩ ከሆነ አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት አግባብ ባላቸው የመንግስት አካላት የሚፈጸም ይሆናል።
በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚገኙባቸው ተቋማት ላይ የተጣሉ ክልከላዎች እና መደረግ ያለባቸው

◾️የጥንቃቄ እርምጃዎች በተመለከተ

• የወረርሽኙ ስርጭት ያለበት ሁኔታ በየጊዜው እየታየ በሌላ መመሪያ እስኪወሰን ድረስ በሚከተሉት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በአካል መጠየቅ የተከለከለ ነው:: ነገር ግን እርዳታ ሰጭዎች ከተቋሙ አስተዳደር ድረስ በመቅረብ ማንኛውንም ድጋፍና መሰል ተግባራትን ማድረግ ይችላሉ
i. የአረጋዊያን መጦሪያዎች ስፍራዎች እና
ii. የማገገሚያ ማዕከላት
• በማረሚያ ቤቶች ላይ የሚደረግ የታራሚን በአካል የመጎብኘት ሂደት በታራሚው እና በጠያቂው መሀል ሁለት የአዋቂ እርምጃ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ፣ ታራሚውም ሆነ ጠያቂው የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ በማስደረግ፣ ጠያቂው ወደማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ከመግባቱም በፊት እና ሲወጣ እጁን በውሃ እና ሳሙና እንዲታጠብ ወይንም በሳኒታይዘር እንዲያጸዳ በማድረግ፣ እንዲሁም ሌሎች በዝርዝር በማንዋል የሚወጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡
ፎቶ:- ኘረዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top