Connect with us

የብሔራዊ ባንክ የሰነፍ ውሳኔ

የብሔራዊ ባንክ የሰነፍ ውሳኔ
ሲራራ

ነፃ ሃሳብ

የብሔራዊ ባንክ የሰነፍ ውሳኔ

የብሔራዊ ባንክ የሰነፍ ውሳኔ

(አብዱልመናን ሞሐመድ)

ከቀናት በፊት ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች በላከው መመሪያ ቤት፣ መኪና፣ ሕንጻ እንደ መያዣ ተጠቅመው ከባንክ ብድር ለሚወስዱ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ባንኮች ብድር እንዳይሰጡ አዟል፡፡ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አሻጥር መኖሩን አንስቶ ይህን ለመከላከል ሲባል ባንኮች ብድር መስጠት እንዲያቆሙ እንዳደረገ አስታውቋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህን መመሪያ ለማውጣት  የፈለገው ሰዎች ቤታቸውን፣ መኪናቸውን፣ ሕንጻቸውን አስይዘው ከባንክ ብር እየተበደሩ ዶላር እየገዙ ነው በሚል መረጃ ነው፡፡

በበኩሌ አንድ ጥያቄ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ቤት እና መኪና  ስላለ ብቻ ባንክ ቤት ብድር ይሰጣል ወይ? እኔ እስከምረዳው ድረስ፣ አንድ ባንክ ብድር ሲሰጥ የሚታይ የሥራ እንቅስቃሴ መኖር አለበት፡፡ ባንክ ቤቱም ቢሆን ብድሩን ለምን ፈለከው ብሎ መጠየቁ የማይቀር ነው፡፡ ዋስትና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ 

አንድ ተቀጣሪ መኪና ኖሮት ብድር ቢፈልግ ያለምንም የሥራ ዕቅድ ባንክ ቤት ብድር ሊሰጠው አይችልም፡፡ ሌላው እኔ እስከምረዳው ድረስ በእኛ አገር ከባንክ ብድር ማግኘት ረጅም ወራት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ ብድር ጠይቆ ነገ ተሰጥቶት ዶላር የሚገዛበትን ሁኔታ የሚፈጥር ሥርዓት በእኛ አገር የለም፡፡ በዚህ ምክንያት መኪና አስይዘው ዶላር ይገዛሉ የሚለው የብሔራዊ ባንክ ሐሳቡ ለእኔ ስሜት የማይሰጥ ነው፡፡ 

ከአጠቃላይ ብድር ፈላጊው ይህን ለማድረግ ያሰበው ምን ያህል መቶኛው ነው? ብሔራዊ ባንክ በዚህ መመሪያ ከባንክ ቤት ተበድረው ዶላር የሚገዙትን ተቆጣጠራቸው ብንል እንኳን፣ እጃቸው ላይ ካሽ ብር ያላቸውን ሰዎች በምን ለመቆጣጠር አስቧል?

ሌላው አንድ ሰው ዶላር የሚገዛው በአገሪቱ ባለው የዋጋ ንረት ምክንያት በእጁ ላይ ያለው  ብር  ዋጋ  እያጣበት ሲሄድ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ መኪና እና ቤት ዋጋቸው አብሮ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ፤ ቤት እና መኪና መግዛት ትልቁ የዋጋ ንረት መቋቋሚያ መንገድ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ በግሌ ይህን ንብረት አስይዞ ዶላር ለመግዛት የሚሯሯጥ ሰው አለ ብሎ ለመቀበል ይከብደኛል፡፡

በዚህ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ ኢኮኖሚ የለም፡፡ በዚህ ላይ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሲፈጠር፣ ኢኮኖሚውን ለመረበሽ ተራ አሉባልታ በቂ ነው፡፡ የምናስታውስ ከሆን በትንሽ አሉባልታ ሰው ጨው  በውድ ዋጋ በኩንታል እስከመግዛት ድረስ ደርሷል፡፡ ዛሬም ብሔራዊ ባንክ እንደ ተራ ነገር ባንኮችን አታበድሩ ብሎ የወሰነው ውሳኔ ነገ በገበያው ላይ ሌላ ምስቅልቅል ላለመፍጠሩ ምን ማረጋገጫ እንዳለው አናውቅም፡፡

በዚህ መመሪያ ሥራ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑ፣ በሒደት ላይ የነበሩ ብድሮች ሳይቀር በድንገት እንዲቆሙ እየተደረገ ነው፡፡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ኪሳራ ውስጥ የገቡ በብድር የሠራተኛ ደሞዝ የሚከፍሉ እቃ ከውጭ የሚያስመጡ በርካታ ድርጅቶች አሉ፡፡ የነዚህ ድርጅቶች እጣ-ፈንታ ምንድን ነው? ባንኮቹ በድር እንዳትሰጡ ሲባሉ አታትርፉ እንደተባለ መታሰብ  አለበት፡፡ ባንኮች የሚያተርፉት ከሚሰጡት ብድር  ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ችግሩን  አጥንቶ ጥፋተኛውን መቅጣት  ይችላል፡፡  አልያም ለባንኮች ኀላፊነት መስጠት ይችላል፡፡ ባንኮች ለሚሰጡት ቡድር ሪፖርት እንዲያደርጉ ማድረግ ይችላል፡፡ የሰጣችሁት ብድር ምን ላይ እንደዋለ ተከታትላችሁ ሪፖርት አድርጉልኝ ማለት ይችላል፡፡ ባንኮች ቀደም ሲልም የሰጡት ብድር ምን ላይ እየዋለ ነው? የሚለውን ይከታተላሉ፡፡ የማይከታተሉ ከሆነ ባንኮችን አስተማሪ ቅጣት መቅጣት  ይችላል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን ካላመናቸው ከዚህ ብር በላይ ብድር የሰጣችኋቸውን ሰዎች እና ተቋማት ስም ዝርዝር አሳውቁኝ ብሎ ናሙና ወስዶ ማጥናት ይችላል፡፡ ይህን የማድረግ ብሔራዊ ባንክ ሥልጣን አለው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህን ለማድረግ ለምን እንዳልፈለገ ግልጽ አይደለም፡፡ ለይቶ መቅጣት እየተቻለ በጅምላ ለመቅጣት የሚወሰን ውሳኔ የሰነፍ ውሳኔ ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ አንድ ሰፈር ውስጥ አንድ ጥፋት ሲጠፋ ያካባቢውን ሰው በሙሉ ይታሰር ከማለት ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡

የዶላር በዚህ ደረጃ ተፈላጊ እንዲሆን እና የጥቁር ገበያው በዚህ ልክ እንዲያይል የደረገው ማን ነው? የብሔራዊ ባንክ የብርን አቅም ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ማዳከሙ አይደለም ወይ?  ብር እየተዳከመ የዶላር ጉልበት  ሲጨምር በገበያው ላይ የዋጋ ንረት እየተባበሰ መጣ፡፡ ቀደሞ 8 እና 9 በመቶ የነመበረው የዋጋ ንረት አሁን 20 በመቶ እና ከዚያ በላይ ቆሚ መጠኑ እየሆነ ነው፡፡ 

ያለፈው ወር የምግብ ምርት የዋጋ ንረት 32 በመቶ ነው፡፡ ይህም ሆኖ  ብሔራዊ ባንክ ብር ከማዳከም ተግባሩ አልቆመም፡፡ ከዚህ ሰዓት ጉልበቱ እየጨመረ የመጣውን ዶላር ለማግኘት ሁሉም ቢሯሯጥ ምን የሚያስገርም ነገር አለው?

ከዚህ በፊት በነበረ የብር ሕትመት ያመጣ የዋጋ ንረት አለ፤ የፖለቲካ ቀውሱ እየፈጠረው ያለው የዋጋ ንረት አለ፤ የዶላር እጥረቱ ቀድሞ ከነበረው ተባብሷል፤ በዚህ የተጠራቀመ ችግር ላይ የብር መዳከም ሲጨመርበት፣ የጥቁር ገበያን ለማጦዝ ሐሜት በቂ ነው፡፡ ሁሉም አካል  በፍርሃት ውስጥ ሆኖ የሚያምነው ገበያ ያጣበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

መንግሥት ይሁን ብሔራዊ ባንክ በዚህ ሰዓት ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ስላለው ሁኔታ እና ስለሚወስነው ውሳኔ ጥልቀት ያለው ጥናት ማድረግ አለበት፡፡ የመንግሥት ኀላፊዎች የነጋዴውን ሥነ ልቦና የሚረዳ ስብዕና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከቁጥር መረጃዎች ባሻገር ሰው ምን እያሰበ ነው በሚል በመጠይቅ ዳሰሳ ጥናት ማድረግ መቻል አለባቸው፡፡

 በኢኮኖሚክስ ከቁጥር መረጃ ባሻገር የሰዎች ምልከታ እጅግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች የዜጎችን ሥነ ልቦና የተካተተበት ሊሆን ይገባል፡፡ ውሳኔዎች ያልተቸኮለባቸው ከብዙ አቅጣጫዎች የታዩ ብርካታ አካላት የሚሳተፉበት ሊሆን ይገባል፡፡

ኮምኒኬሽን በፖለቲካው ዘርፍ እጅግ ወሳኝ እንደሆነው ሁሉ በኢኮኖሚውም ዘርፍ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ውሳኔዎች ሲወሰኑ ለሕዝብ ሲደርስ ጥርት ባለ ቋንቋ መሆን አለበት፡፡ ውሳኔው ጊዜ የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ በአንደበት የሚነገረው እና የሚወሰደው እርምጃ የተጣጣመ መሆን መቻል ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ያለው ድንገት የሚወርደው ውሳኔ  ነው፡፡ ለውሳኔዎች የሰው አእምሮ ዝግጁ መሆን መቻል አለበት፡፡ ነጋዴው በመንግሥት ላይ እምነት ሊፈጥር ይገባል፡፡(ሲራራ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top