Connect with us

ምሁር ኢየሱስ- የዓለም ጉዳይ የተናቀበት ዓለም

ምሁር ኢየሱስ- የዓለም ጉዳይ የተናቀበት ዓለም
ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

ምሁር ኢየሱስ- የዓለም ጉዳይ የተናቀበት ዓለም

ምሁር ኢየሱስ- የዓለም ጉዳይ የተናቀበት ዓለም

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ በታላቁ ገዳም ምሁር ኢየሱስ የነበረውን ቆይታ በተከታታይ ሲተርክል ነበር፡፡ ዛሬ የዓለም ጉዳይ የተናቀበት ዓለም ሲል የገዳሙን የተለያዩ ገጽታዎች ያስተዋውቀናል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

አባ ፍቅረ ሥላሴ የገዳሙ ቤተ መዘክር ኃላፊ ናቸው፡፡ ምሁር ኢየሱስ ሙዚየም ውስጥ ነኝ፡፡ ጠባብ ቢሆንም ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም አላቸው፡፡ ለዕይታ በተመቸ ስልጡን አደራደር ቅርሶቹ ተቀምጠዋል፡፡

የሙዚየሙ ቅርሶች የጥንቶቹና የአሁኖቹ ናቸው፡፡ የገዳሙ ክብርና ፍቅር ያሸነፋቸው ነገሥታት የሠጡትን ሥጦታ ተመለከትኩ፡፡ ቀደምት የብራና ጽሑፎችም አሉ፡፡ የቅዱሳን አባቶች መገልገያ ቁሳቁሶችም በክብር ለዕይታ በቅተዋል፡፡ ማንም ዜጋ እምነትና የመጣበት ሳያግደው መጎብኘት ይችላል፡፡ መግቢያ ክፍያና ህጋዊ መታወቂያ ይጠይቃሉ፡፡ የመግቢያ ክፍያው መጠን ከማነሱ የተነሳ እዚህ አልነግራችሁም፡፡ የምሁር አባቶች ትውልዱ ታሪክን ያውቅ ዘንድ ምሁርነታቸውን ያሳዩበት ሀሳብ እዚህ በክብር ተቀምጧል፡፡

መጋቢ አልሳ ወደ ሥዕል ቤቱ ወሰዱኝ፡፡ ምሁር ኢየሱስ ይሄ ጎደለ ሊሉት የሚከብድ ቤተ ጥበብ ነው፡፡ እውቀት ዋጋ አላት፡፡ እውነትም ስምና ግብር ያስብላል፡፡ ሥዕል ቤቱ በአንዲት ጥበበኛ ሰዓሊ መነኩሴ ይመራል፡፡

ዓላማው እንደ ቀደምቱ ኢትዮጵያውያን በሥዕል እምነትን፣ እውቀትን፣ ታሪክንና ውበት ማሻገር ነው፡፡ ቅዱሳት ሥዕላት ይዘጋጁበታል፡፡ ሥዕልን መማር ለሚፈልጉ ደግሞ ቤተ ሥዕሉ ያስተምራል፡፡ ምሁር ኢየሱስ፡፡

እዚህ ዋናው ነገር ለትምህርት የሚሰጠው ቦታ ነው፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቱ አለ፡፡ ከዚያ ጎን ተስፋ አበው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ሀገሬውን ጭምር እስከ ስምንተኛ ክፍል በነጻ ያስተምራል፡፡ ሊያውም የትምህርት ቁሳቁሶችን እየደገፈ፤

ደግሞ ሐዋርያት የምትባለው የወረዳው ከተማ ሸጋ አጸደ ሕጻናት አላቸው፡፡ ምሁር ኢየሱስ አስበውት የሚደክማቸው ነገር የለም፡፡ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ተጉዘው የዞኑ ከተማ ስመ መልካም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገንብተዋል፡፡ እዚህም አቅመ ደካሞችና መክፈል የማይችሉ ነጻ ይማራሉ፡፡

የምሁር የአብነት ትምህርት ቤት የተደራጀ ነው፡፡ የተማሪዎች መኖሪያ አለ፡፡ የሚመገቡት እዚያው ነው፡፡ የትምህርት አሰጣጡ ዲሲፕሊን ጠንከር ይላል፡፡ ሁሉም ጉባኤ ቤቶች አሉ፡፡ ሁሉም ጋር እንደ ልብ የሌለው ቤተ እንዚራ የተባለው በገና የሚያስተምር ቤት ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡

መምህር ሲሳይ ደምሴ በምሁር ኢየሱስ በገና ትምህርት ይወለድ ዘንድ ምክንያት ናቸው፡፡ ስማቸውን የገዳሙ አባቶች አንስተው አይጠግቡም፡፡ ዛሬ በእሳቸው ጥረት አንድ የሀገራችን ገዳም የበገና ትምህርት የሚሰጥ ለመሆን በቅቷል፡፡

የገዳሙ አባቶችና እናቶች በገና ይደረድራሉ፡፡ ምሁር ኢየሱስ የደብረ ዘይት እኩለ ጾም የደረሰ ተአምር ይመለከታል፡፡ እኔ የፍልሰታ ጾም ነው የመጣሁት፡፡ ምሁር የጥሞና ስፍራ ነው፡፡ አንዳች መንፈስን የሚያውክ ነገር አይሰማበትም፡፡ ዓለም ተንቃለች፡፡ አባቶቹ ወደ ፈጣሪ ለመቅረብ ከተራው ነገር ሁሉ አብልጠው የራቁ ናቸው፡፡ ያየኋቸው አበ ምኔትና ያደርኩባት ቤታቸው ብትጻፍ ኖሮ ብዙ በገለጽኩት ነበር፡፡ የጽድቅን ስራ ገበያ አላወጣውም፡፡

ምሁር ኢየሱስ መድረስ ብዙ ነገር ነው፡፡ ስትመጡ ከሬብን አሳዩን በሏቸው፡፡ በምሁር አክሊል ወረዳ ቆይታችሁ ከረዘመ መገራን ፏፏቴን ተመልከቱት፡፡ ከፈለጋችሁ ደግሞ እስከ ሀሰን ኢንጃሞ ቀዬ መሄድ ትችላላችሁ፡፡ ልመለስ ነው፡፡ ያንን ትሁትና ፍቅር ያልተለየው የገዳሙ ቤተሰብ መስተንግዶ መቼም አረሳውም፡፡ 

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top