Connect with us

ምሁር ኢየሱስ-የምሁራን ሥፍራ፤ እውቀትና ጸሎት

ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

ምሁር ኢየሱስ-የምሁራን ሥፍራ፤ እውቀትና ጸሎት

ምሁር ኢየሱስ-የምሁራን ሥፍራ፤ እውቀትና ጸሎት

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በምሁር ኢየሱስ ገዳም እያደረገ ያለውን ቆይታ እየተረከልን ነው፡፡ ምሁር ኢየሱስ የምሁራን ሥፍራ ሲል የገዳሙን ገጽታ፣ ታሪክና በእውቀት ስሙ የሚነሳበትን ተግባር ይተርክልናል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

የአብነት ተማሪዎቹ ድምጽ ያስተጋባል፡፡ ከዚያ ውጪ የሚሰማው ድምጽ የወፍ ነው፡፡ ያለፈ ነገር ከተደመጠ ደግሞ የዛፍ ቅጠል ውዝዋዜ፡፡ ምሁር ኢየሱስ ገዳም ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ ቀደምቱ ነው፡፡ ቅደመ ዩዲት ዘመን ታሪኩን ይቆጥራል፡፡ በአቡነ ዜና ማርቆስ ተገደመ፡፡

ምሁር ኢየሱስ የተባለው የምሁራን ቦታ ስለሆነ ነው፡፡ እዚህ እውቀት ትልቅ ቦታ አላት፡፡ ጸሎት እና ትምህርት፡፡ የገዳሙ አበምኔት ትሁቱ ሰው አባ  ዘ ኢየሱስ ልክክ ያሉ መምህር ናቸው፡፡ ምሳሌ የሚሆኑ፤ ምሁር ኢየሱስ ስለመባሉ ጠየቅኋቸው፡፡ ተረኩልኝ፡፡ ቀደም ሲልም ስፍራው የትምህርት ማዕከል ነበር፡፡ በጉባኤ ቤቶቹ የሚታወቅ፡፡ ቢጠየቁ የሚመልሱ አባቶች ያሉበት፡፡ እናም ሀገሬው ምሁራኑ ጋር እንሂድ ይላል፤ ይመጣና ይጠይቃል፡፡ 

ከባድ ነገር የለም፡፡ መጻሕፍት የመለሱትን ምሁራኑ ይመልሱታል፡፡ እናም የገዳሙ መጣሪያ እውቀት ሆነ፡፡ የኢየሱስ ታቦት ሲጠራ ከፊቱ ምሁር ገባ፡፡ ምሁር ኢየሱስ፡፡ ታቦቱ የጥንት ነው፡፡ ከፊት ለፊቴ የምመለከተው ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ክብና ቀደም ያለ አሰራር አለው፡፡ ምናልባት ሁለት መቶ አመት ወይም ከዚያም በላይ፤ መጋቢ ኤልሳ ደስ የሚሉ አባት ናቸው፡፡ ዙሪያውን አስጎበኙኝ፤ አፌን ከፍቼ ሰማሁ፡፡

ታላቁ ስፍራ ዝም ብሎ የኖረባቸውና የተረሳ የመሰለባቸው ዘመናት ነበሩ፤ ዳግም ታላቅ ሰው ተነሱ፡፡ አቡነ መልከ ጸዴቅ፡፡ እሳቸው የጉራጌ ሀድያና ከንባታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሳሉ፤ የምሁር ታሪክ ዳግም ተነሳ፡፡ አዲስ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን እየተሰራ ነው፡፡ ግዙፍና በኖህ መርከብ ቅርጽ የተቀመጠ ነው፡፡

ብዙ ቤተሰብ ያለው ገዳም ነው፡፡ ስራ፣ ጸሎትና ትምህርት የገነነበት፡፡ ተደወለ፡፡ ሁሉም ወደ ስራ ተሰማራ፡፡

ምሁር ኢየሱስ እምነትና ታሪክ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮንም ጠብቋል፡፡ እዚህ የገዳሙን እድሜ የሚናገሩ፣ እንደ ሰው ዘመን ኖረው እንደ ፍጥረት ሸብተው፣ እንደ አዋቂ ሁሉን የሚናገሩ እድሜ ጠገብ እጽዋት አሉ፡፡ አንዱን ግንድ እንደ አደባባይ ብዞረው ስፋቱ የበዛ፤ መጠኑ የገዘፈ፤

በገዳሙ የተለያዩ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ ሁሉም ትጉህ ነው፡፡ እውቀትን ከስራ አጣምሮ የሚኖር፡፡ መነኮሳቱና መነኮሳይቱ ስራ ነፍሳቸው ነው፡፡ የገዳሙ ውበት፣ የቅጥሩ ማማር፣ የጥበበ ዕድ ቤቱ ውጤት ይናገራል፡፡ እምሰማውን አየዋለሁ፡፡

ነባሩ ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ነው፡፡ ዜና ማርቆስ ድርብ ታቦት ነበር፡፡ አሁን ራሱን ችሎ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል፡፡ የኮሬብ ወንዝን ተከትሎ ውብ ደን አየሁ፡፡ አሻግሬ የምመለከተው አለት ሥር ዋሻዎች መኖራቸውን ነገሩኝ፡፡

ቅጥሩ ሰፊ ነው፡፡ እያንዳንዱ ምዕራፍ ቆም ብሎ ብዙ ነገር ይታያል፡፡ ገና ወደ ገዳሙ ሙዚየም አብረን እንገባለን፡፡ ገና ሥዕል ቤት ትጎበኛላችሁ፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቱን የምሽት ድባብ በመጠኑ አሳያችኋለሁ፡፡ የተማሪዎች መኖሪያ እንወርዳለን፡፡ የበገና ቤቱን ተአምር ትሰማላችሁ፡፡

ምሁር የምሁራን ማፍሪያ ነው፡፡ በገዳሙ ጀርባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍቶ ሀገሬውን እውቀት ያስተምራል፡፡ ሐዋርያት ከተማ አጸደ ህጻናት አለው፡፡ ወልቂጤ ከተማ ስሙ የገነነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍቶ ያስተምራል፡፡ በሁለት በኩል የተሳሉ ሰይፎች ከእውቀት የሚሰሩበት ገዳም ነው፡፡ አልተመለስንም፡፡

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top