Connect with us

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ፣

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ዜና

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ፣

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ፣

~ “የሽብር ቡድኑ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የመንግስትን ትዕግስት የሚፈታተንና እስካሁን በተገበረው የተናጠል የተኩስ አቁም ምክንያት የተከተለውን የመከላከል አቋም ለመለወጥ የሚያስገድድ ነው።”
***
በመንግስት የተወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ የትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝና አርሶ አደሩም የጥይት ድምጽ ሳይሰማ ወደ እርሻ ተግባሩ እንዲሰማራ በማሰብ የተላለፈ ውሳኔ ነው። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የአሸባሪው ቡድን ተመሳሳይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ግጭትን መርጧል።

ቡድኑ ግጭቱን ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች በማስፋት ከ300 ሺህ ህዝብ በላይ ህዝብ ከቀዬው እንዲፈናቀልና በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ህይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓል።

በመንግስት በኩል ግን የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ጸንቶ መቆየቱ ልብ ሊባል የሚገባ ጉዳይ ነው። በመሆኑም የዓለም አቀፉ ማህብረሰብ የአሸባሪው ቡድን የሚያደርሰውን ግፍና በደል ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሊያልፈው አይገባል።

ምንም እንኳ መንግስት በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን መጠነ ሰፊ ጥረት ያደረገ ቢሆንም የሽብር ቡድኑ ግን ግጭቱን ወደ ጎረቤት ክልሎች በማስፋፋት አገሪቱ እንዳትረጋጋ በማድረግ ላይ ይገኛል።

መንግስት በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ተጨማሪ ጥቃት እንዲፈጸምና የህዝቦችን ኑሮ እንዲያመሰቃቅል ፈጽሞ አይፈቅድም። የሽብር ቡድኑ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የመንግስትን ትዕግስት የሚፈታተንና እስካሁን በተገበረው የተናጠል የተኩስ አቁም ምክንያት የተከተለውን የመከላከል አቋም ለመወጥ የሚያስገድድ ነው።

አሁን ጊዜው አካፋን አካፋ ብለን የምንጠራበት እና የሽብር ቡድኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን በጦርነቱ በማሰለፍ የጥይት ማብረጃ በማድረጉ ላሳየው ተግባር ተጠያቂ የሚሆንበት ላይ እንገኛለን።

የሰብዓዊ እርዳታን በተመለከተም መንግስት ለትግራይ እርዳታ ፈላጊዎች ተደራሽ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ሂደቱን በማፋጠን ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም ያረጋግጣል። የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ በቅርቡ በአሸባሪው ድርጅት ከአፋር እና አማራ ክልሎች የተፈናቀሉትንም የሚያካትት ይሆናል።

የሽብር ባለሟሉ የህወሓት ቡድን የሰብዓዊ እርዳታ
ተደራሽ እንዳይሆን በማድረግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛል። መንግስት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደጎን በመተው በሽብር ተግባሩ ላይ ተጠምዶ የሚገኘውን እኩይ ቡድን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ጥሪውን ያቀርባል።

በትግራይ የሚንቀሳቀሰው ህገ ወጡ ቡድን በግልጽና እና በድብቅ ከሚያካሂደው የሽብርና የወረራ ተግባር እንዲቆጠብ መንግስት ማሳሰብ ይፈልጋል።

በመከላከያ የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ስምሪት የሰጡ የሽብር ቡድኑ መሪዎች ተገቢው ፍርድ እንዲያገኙ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያሳውቃል። ከግጭቱ በፊትም በኃላ በየትኛው አካል ለተፈጸሙ ወንጀሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በህግ አግባብ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይሰራል።

መንግስት ዲሞክራሲ፣ አስተዳደርና ምርጫን በተመለከተ በአፍሪካ ህብረት ቻርተር ለተቀመጡትን የዲሞክራሲ መርሆዎችን ያለውን ተገዥነት እየገለጸ፤ ነገር ግን ከህግ መንግስታዊ ስርዓቱና ህዝብ በድምጹ ካረጋገጠው ፍላጎት በተቃረነ ሁኔታ የሚደርሱ የውጭ ተጽዕኖዎችን የማይቀበል መሆኑን ያሳውቃል።

ሰላምን በማረጋገጥ፣ ዲሞክራሲን ማጠናከር እንዲሁም አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ኢትዮጵያ በታሪኳ ነጻ፣ ግልጽ እና ተዓማኒ የሆነ ምርጫ አከናውናለች። ምርጫው የዲሞክራሲ ባህልን ከመገንባት አኳያ ትልቅ መሰረት ጥሎ ያለፈ መሆኑን ኢትዮጵያ አበክራ ታምናለች።

ተመራጩ መንግስትም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማካተት እንዲሁም በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ሁሉን አካታች ብሔራዊ የምክክር መድረክ በማጠናከር ዲሞክራሲን ለማጎልበትና ብሔራዊ መግባባትን ለማስፈን ይሰራል።

በአፋር እና አማራ ብሔራዊ ክልሎች አዲስ ግጭት በመቀስቀስ ጦር ናፋቂው የህወሓት ቡድን የሰላም አማራጮችን በማምከን ላይ ይገኛል። በመሆኑም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የአገሪቱን ልዑላዊነትና አገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ካለበት የሞራል፣ የህግና የፖለቲካ ግዴታ አንጻር የመከላከል አቅሙን ለመጠቀም እንደሚገደድ ማስገንዘብ ይወዳል።

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top