Connect with us

ቶሽካ”ሥውሩ” የበረሃ ፕሮጀክትን በጨረፍታ…

Social media

ነፃ ሃሳብ

ቶሽካ”ሥውሩ” የበረሃ ፕሮጀክትን በጨረፍታ…

ቶሽካ”ሥውሩ” የበረሃ ፕሮጀክትን በጨረፍታ…
( እስክንድር ከበደ – ለድሬ ቲዩብ)
የቀድሞው የግብፅ መሪ ሆስኒ ሙባረክ እ.ኤ.አ በ1997 “New Nile Valley Project” (የአዲሱ የናይል ሸለቆ ፕሮጀክት) በማለት ግዙፍ የሆነውን የሰሃራ በረሃን የማልማት ዕቅድ ነድፈው ነበር። ሙባረክ ለዕቅዱ ተግባራዊነት መንቅሳቅስ ጀምረው ነበር፡፡
ይህ ፕሮጀክት በዋናነት ሁለት ምዕራፎች ሲኖሩት አንደኛው በሰሜን ምሥራቅ ግብፅ የሚገኘው የአል ሰላም ቦይ (ካናል) ፕሮጀክት ነው፡፡ እሱም ውኃ ከዓባይ ግርጌ በመጥለፍ ወደ ሲና በረሃ ማሻገር ነው፡፡
ይህን በማድረግ ብዙ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት በማልማት 750 ሺሕ ግብፃውያንን ለማስፈር ያለመ ነው፡፡ ዋናውና ትልቁ ፕሮጀክት ግን የቶሽካ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይህም የደቡብ ምዕራብ ግብፅ በረሃን ለማልማት ያቀደ ፕሮጀክት ነው፡፡
በግብፃውያኑ ዘንድ ይህ ፕሮጀክት አሁን ባለው ሁኔታ እ.ኤ.አ. 2020 ያልቃል ተብሎ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ በዋናነት አዲስ ግብፅ በበረሃው ለመፍጠር ያቀደ ሲሆን፣ የተለያዩ በርካታ የውኃ ቦዮችንና የውኃ መምጠጫ ፓምፖዎችን በመገንባት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
ይህን በማደረግ በረሃውን በማልማት ወደ ሦስት ሚሊዮን ግብፃውያንን የማስፈር ዕቅድ አላቸው፡፡ እንደ ግብፃውያኑ ከሆነ ይህ ፕሮጀክት ውኃውን የሚያገኘው በናይል ላይ ከተሠራው የአስዋን ግድብ ጀርባ ከሚገኘው የናስር ሐይቅ ነው፡፡ ግብፃውያኑ ይህን ሥራ የትኞቹንም የላይኛውን የተፋሰስ አገሮች ሳያናግሩ ሲሠሩት ውኃውን ከየት እንደሚያመጡት ያውቃሉ፡፡
እነሱ እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር የተፈራረሙት በሌሎቹ አገሮች ውድቅ የተደረገው የቅኝ ግዛት ውሎች መሠረት አብዛኛውን የውኃ ድርሻ መድበው ጨርሰዋል።
እ.ኤ.አ. በ2005 መጋቢት ወር የፕሮጀክቱ ዕምብርት የሆነው የሙባረክ ውኃ ማሰራጫ ጣቢያ በይፋ ተመርቋል። የሙባረክ ውኃ መግፊያ ጣቢያ የዓባይን ውኃ ከናስር ሐይቅ ውስጥ ለውስጥ የሚገፋ ግዙፍ ማሰራቻ ነው። ከናስር ሐይቅ በስተስሜን 310 ኪሎ ሜትር የሚደርሰው ቦዩ እ.ኤ.አ. እስከ 2012 ድረስ 60 ኪሎ ሜትር ተሠርቶ ነበር።
በዚህ ፕሮጅክት ውኃውን 2340 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሽፍን ሲሆን፣ የዓባይን ሸለቆ በረሃ ወደ ምድረ ገነት የእርሻ መሬት የመለወጥ ዓላማ አለው። የቶሽካ ፕሮጀክት በፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ አማካይነት ዳግም እንዲያንሰራራ እየተደረገ ነው።
ግማሽ የሚሆነው መሬት ለኮሌጅ ተመራቂዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ ለእያንዳንዳቸው 4046.86 ካሬ ሜትር በመስጠት ‹‹ግብፅ ለዘለዓለም ትኑር ፈንድ›› ከሚባል ተቋም የገንዘብ ድጋፍ ምድረ በዳውን እንዲያለሙ ውጥን አለ።
የግብፅ ቶሽካ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 9 ቀን 1997 በቀድሞ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በተገኙበት መጀመሩ ተበሰረ፡፡ በፕሮጀክቱ ተመጋጋቢ ቦዮችን (ካናሎች) ከናስር ሐይቅ ወደ ግብፅ በረሃማ ሥፍራዎች ለመስኖ እርሻዎች የሚሆን ውኃ የሚያሻግር የመግፊያ ጣቢያ ተሠርቶለት ተጠናቋል።
እ.ኤ.አ. በ2020 ወደ ሦስት ሚሊዮን ነዋሪዎችን ማሥፈር የሚያስችል ሆኖ፣ የግብፅን የሚታረስ መሬት አሥር በመቶ የሚያሳድግ ግዙፍ የዓለማችን የውኃና የመስኖ ፕሮጀክት ነው:: ከግብፅ ሕዝብ 20 በመቶ የሚሆኑ ሰዎችን ማሥፈር የሚያስችል ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህም ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሰሃራ በረሃ በዘመናዊ ግብርና እንዲተዳደሩ፣ ብሎም ሌላ ካይሮን የምታህል ከተማ ለመገንባት ውጥን የተያዘበት ነው።
በቶሽካ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ የሙባረክ የውኃ መግፊያና ማሠራጫ ጣቢያ እ.ኤ.አ. በ2005 በ436 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው ተጠናቋል:: በአንድ ጊዜ 18 የውኃ መግፊያ መስመሮች የሚሠሩ ሲሆን፣ ሦስቱ ለጥገና ፍላጎት ሌሎች ሶስት ደግሞ እንደ መጠባባቂያ የሚያገለግሉ ናቸው:: የውኃ ማሠራጫ ጣቢያው 50 ሜትር በመሬት ጥልቅ ውኃ መግቢያ ቦይ የተፈጠረለት ነው፡፡
በሰዓት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይገፋል ፡፡ የካናሉ ውኃ ማስተላለፊያ ቱቦ 30 ሜትር ስፋት አለው:: የውኃ ማሠራጫና ማስተላለፊያ ካናሉ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መሪ ሼክ ዚያድ አል ናህያን ስም ተሰይሟል:: ቶሽካ ፕሮጀክት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራ በመሆኑ ነው በስማቸው የተሰየመው:: ከዚህ ግዙፍ የውኃ ማሠራጫ ጣቢያ የሚጀምሩና መሬት ለመሬት የተቀበሩ 24 የአግድሞሽ ውኃ መግፊያና ማሠራጫ ቱቦዎች በዋና ማከፋፈያ ጣቢያው ዳርና ዳር በሁለት ረድፍ ትይዩ ተሠርተው ተጠናቀዋል:: የውኃ ጫና መቆጣጠሪያና የፍጥነት ማስተካካያ ሥርዓትም ተበጅቶላቸዋል፡፡
የሙባረክ የውኃ መግፊያ (ማሠራጫ) ጣቢያ እ.ኤ.አ. በ2005 ሲጠናቀቅ በሲቪልና በሜካኒካል ምህንድስና ስኬቶቹ የተወደሰ ነው:: ሙሌቱ በብረት የተዋቀረ ሲሆን፣ የመሬት ርዕደትን መቋቋም እንዲችል ተደርጎ የተሠራ ነው:: ሆስኒ ሙባረክ እ.ኤ.አ. በ2011 በፀደይ አብዮት ከሥልጣን በመወገዳቸው የቶሽካ ፕሮጀክት ሒደትን እንደገታው ይነገራል፡፡
በአገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ ፕሮጀክቱ መቀዛቀዙ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
በቀጭን ክር ቶሽካንና ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ሼክ መሐመድ አል አሙዲን ማያያዝ ይቻላል። ‹‹ሳዑዲ ስታር አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመን›› ኩባንያ ባለቤት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሳዑዲ ዜጋ ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ናቸው፡፡ ኩባንያው በምዕራብ ጋምቤላ ወደ 10,000 ሔክታር መሬት የሚሸፍን እርሻ አለው።
ይህ ኩባንያ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ያፈስበታል ተብሎ ነበር። ይህ ፕሮጀክት ዋና ምርቱ ሩዝ ሲሆን፣ በዋናነትም ለውጭ ገበያ የሚቀርብ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሳዑዲ ስታር የተባለው የሼክ አል አሙዲ ኩባንያም ምርቱን በዋናነት ለሳዑዲ ዓረቢያ ሊያቀርብ የታሰበ ነበር፡፡
ባለሀብቱም ከሳዑዲ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ጋር ባላቸው መቀራረብ ተነጋግረው የተጀመረ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ ይነገራል። ይህ የሚያሳየን ሳዑዲ ዓረቢያ በአንድም በሌላም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የራሷ የሆነ የጥቅም ፍላጎት እንዳላት ነው፡፡ ጋምቤላ ውስጥ ያሉ ወንዞች የዓባይ ገባር መሆናቸውን ይታወቃል፡፡
የሳዑዲአረቢያ ሚና በዚህ ፕሮጀክት ላይ ምንድነው ስንል ታላቅ ኢንቨስትመንትን እናገኛለን፡፡ የሳዑዲው ልዑል አል ዋሊድ ቢን ጣላል ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑድ ‹‹ዘ ኪንግደም አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት›› የተሰኘ ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ፣ ግብፅ ውስጥ በጥቅሉ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያንቀሳቅሳሉ፡፡
በቶሽካ ፕሮጀክት ደግሞ ከአሥር ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ተረክበው የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለማምረት፣ ከግብፅ የውኃና የመስኖ ልማት ሚኒስቴር ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በየዓመቱም በሚሊዮኖች ለዚሁ የቶሽካ ፕሮጀክት አካል ለሆነው መሬት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈሱ ይነገራል፡፡
የቶሽካ ፕሮጀክት ሐሳብ አዲስ አይደለም፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጋማል አብደል ናስር በታላቁ የናስር ግድብ ጀምረውት፣ ግን እ.ኤ.አ. በ1964 የተቋረጠው ግዙፍ ዕቅድ አካል መሆኑ ይነገራል፡፡ የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦስቲን የዶክትሬት ተማሪዋ ኢማ በግብፅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ባካሄደችው ጥናት የቶሽካ ፕሮጀክት በጀት ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝብ የተሰወረ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡ ከግብፅ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም የተሰወረ ነው፡፡

ሳዑዲአረቢያ የኢትዮጵያ ስደተኞችን በገፍ የምታባርረው፤ በባዶእግራቸው ሳይቀር የምትልክን ያለምክንያት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በቀውስ እንድትዳከም ብሎም የታላቁ ህዳሴ ግድቡን ሙሌት ለማሰናከል ከወዳጇ ግብጽ የሚሰጣትን ስውር ተልኮ እየፈጸመች ነው፡፡ ምክንያቱም በአባይ ወንዝ ላይ ምን ያገናኛቸዋል ብንል- የቶሽካ ፕሮጀክት ይሆናል፡፡
በቅርቡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ላይ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አንድ መራር ሀቅ ጠቅሰዋል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የምንሰራው ከመካከለኛ ምስራቅ በባዶ እግራቸው የሚመለሱ ወጣት ስደተኞች በሀገራቸው ሰርተው እንዲኖሩ ማድረግ መሆኑን በዓለም ፊት ተናግረዋል፡፡
ዓለም ፊት የተፈጥሮ ሀብታችንና ጸጋችንን ተከራክረው ሊነጥቁን የማያፍሩት ቱጃሮቹ ሀገራት ፤ የእኛም ባልሰራንበት፤ እነሱ አስተዋጽኦ ባደረጉበት ድህነታችን እስከመቼ እንዲሳለቁብን እንፈቅድ ይሆን?

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

To Top