Connect with us

” ሂሳብ ማወራረድ! “

" ሂሳብ ማወራረድ! "
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

” ሂሳብ ማወራረድ! “

” ሂሳብ ማወራረድ! “

(ዶ/ር መሠረት ጀማነህ)

አዎ! ሂሳብማ መወራረድ አለበት፡፡ ግን ማን ሂሳብ  እንዳለበት፣ ማን   ማወራረድ እንደሚችል ማስረዳት ይገባል።

አሸባሪው ህወሃት  አማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎናል። “ እሳት አርፎ ቢተኛ ገለባ ጎበኘው” እንደሚባለው መሆኑ ነው ፡፡

የዚህን አሸባሪ ኃይል ታሪክና ማንነት ኢትዮጵያዊያን በደንብ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ብዙዎቻችን እኔንም ጨምሮ ብዙ ሚስጥር፣ ሸርና ሴራ ሳናውቅ አብረናቸው ቆይተናል። የወያኔ ትግል የጀመረው ትግራይን መገንጠል አላማ አድርጎ ነው፡፡ ይህ በደንብ መታወቅ አለበት። ይህንን ደብቆ ከኢህዴን ጋር የኢትዮጵያ የለውጥ ኃይል በመምሰል ግንባር ፈጠረ። ደርግ ከትግራይ እንዲወጣ ካደረጉ በኋላ የኛ አላማ ተሳክቷል፤ ትግራይን ነፃ አውጥተናል፤ እኛ ከዚህ አናልፍምና እናንተ ቀጥሉ ብለው  ትግራይ ወሰን ላይ ደርሰው መመለስ ጀምሩ። እንዴት ሊሆን ይችላል? ደርግን ከትግራይ ያስወጣነው አብረን አይደል እንዴ? አሏቸው።

ከዛም ከብዙ ክርክር በኋላ አብረው ደርግን ጥለው ህወሃት ለዘላለሙ መሪ እንደሚሆን በማሰብ ቀጠሉ። ደርግ ሲወድቅ ወያኔ መራሽ ግንባር እና መንግስት መስርተው ከፋፍለው እየገዙ ተጓዙ፡፡ ወያኔ እንደ ኢህአደግ ሲሆን ሰሙን፣ በራሱ ሳጥን ውስጥ ሲገባ ደግሞ ወርቁን  ሲቀኝና ሲያቀነቅን ቆየ። እንደ ኢትዮጵያም ቢሆን እኛ ከመራነው  አስከዛው  ጥሩ እድል ነው አሉና 27 አመት ገዙን፡፡ አንድ ቀን ግን መሸነፋችን ስለማይቀር በህገ መንግስት የታሰረ የከፋፍለህ ግዛው ዘዴን መከተል አለብን፡፡

እናም ለእኛ የሚመች ስርዓት እንፍጠር ብለው በሚስጥር ኪዳን አሰሩ። እናም አሁን እኛ ብቻ የምንመራት ኢትዮጵያ ትሆናለች፡፡በቃችሁ ስንባል ግን ትግራይን የመገንጠል  ህልማችንን እውን ለማድረግ  እዚያው ደደቢት ተመልሰን ትግራይን አገር እናደርጋለን፤ሌሎቹም ክልሎች እየተገነጣጠሉ ይወጣሉ፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያ የምትባል አገር ትፈርሳለች ብለው አቀዱ። ለዚህም እንድመች የሰሩትን ስራ  በአጭሩ እንመልከት።

1.ትግራይን ለመገንጠል ግዛት ማስፋፋት፣ኢኮኖሚ መፍጠር እና የትግራይን ክልል ከሱዳን ጋር ማገናኘት ዋና ስራ ሆነ። ይህንን ለማሳካት ወልቃይት ጠገደን በኃይል ከአማራ ክልል በመንጠቅ   ክልልሉን ከሱዳን ጋር እንዲዋሰን አደረጉ፡፡ በሌላ በኩል ከአማራ ክልል አሁንም ከወሎ ራያን በመውሰድ ግዛታቸውን አስፋፉ።  ወልቃይት ጠገዴን መያዝ ደግሞ የግዛት ማስፋፋት እና የኢኮኖሚ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ዋናው ጉዳይ ከሱዳን ጋር በመዋሰን ለመገንጠል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡

2.ሌላው መስራት የነበረባቸው ስራ የአማራ ህዝብ ርስቱን ተነጥቆ ዝም ሰለማይል እና ኢትዮጵያን የማፈራረስና የትግራይን የመገንጠል ሴራ ስለማይቀበል እሱን ማዳከም ከተቻለም  ማጥፋት የግድ  ነው የሚል ነበር፡፡ እናም ሊዘመትበት እና ሊዳከም ይገባል ብለው ቀሰቀሱ። በተግባርም  እነሱና መሰሎቻቸው ግፍ ፈጸሙበት፡፡

 ሌላው ህዝብም በአማራ ላይ ጥላቻ እንዲይዝ ሰሩ። ይህ ግን ጥቂት የነሱ ተቀፅላዎች ተቀብለው አደረጉት እንጂ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በአማራ ህዝብ ላይ ጥላቻ አላሳደሩም። ይችኛዋን ብቻ  አላሳኳትም እንጂ ሌላውን ሁሉ አሳክተዋል።

ይሄም ሁሉ ሆነና  እንደፈሩት ኢትዮጵያን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ጀምሮ በየደረጃው እስከ ቀበሌ ድረስ የያዙትን ስልጣን ይዘው የማይቀጥሉበት ጉዜ ላይ ደረሱ። ለውጥ ለውጥ የሸተታቸው የግንባሩ አባላት ስርአተ መንግስቱን ሲቀይሩት እነአጅሬ ይህማ ለኛ አይበጅም ብለው ሻንጣቸውን አንጠልጥለው መቀሌ ገቡና ያቺን የተነሱባትን የመገንጠል ሰነድ አቧራዋን አራግፈው ጠረጼዛ ላይ ዘረጓት እና  የመጨረሻ እድላቸውን ማስፈጸም ጀመሩ፡፡

አሁን ሃብት ሰብሰበዋል፣የአገሪቱን መከላከያ ትጥቅ ይዘዋል። ግን ባጠገባቸው ያለ  አንድ ሀይል ነበር እጅግ የሚፈሩት፤ እሱም የሰሜን እዝ ነው፡፡ እናም የመጀመሪያ ስራቸው እሱን መደምሰስ ነበር እና ጥቃት ሰነዘሩበት። ነገር  ግን አንድ የተሳሳቱት ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል መሰረተ- ሰፊ መሆኑንና አገር ሲፈርስ እያየ ዝም የሚል ህዝብም አለመኖሩን  አለማወቃቸው ነው፡፡ 

ከዚህ በኃላ መንግስት ህግ የማስከበር ተልዕኮ ውስጥ  መግባት የግድ ሆነ፡፡ በመንግስት እርምጃ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ አሸባሪው ሃይል ሙት፣ቁስለኛና ምርኮኛ ሆነ። የቀረውም ወደ የዋሻው ተሸጎጠ። የትግራይ ወገኖቻችን ልታስተውሉ ይገባል። ወያኔ ሀብት የሰበሰበው ለራሱ ነው እንጅ ለናንተ ጠብ ያለ ነገር የለም። እጣፋንታህም ጦርነት እንጅ ሰላምና ልማት አልሆነልህም። የነሱን ልጆች በውጭ ሀገር አስቀምጠው ያንተን ልጆች ጥይት መመከቻና የእሳትራት እያደረጉ ነው። ከኢትዮጵያን ወገኖችህ ሊነጥሉህም ወስነዋል። የፅሞና ጊዜው የተሰጠው ለዚህ ነበር። አሁንም አረፈደምና ወደውስጥህ ተመልከት።አንተን የሚወድ እንጅ የሚጠላህ ኢትዮጵያዊ የለም። ስለሆነም አሰላለፍህን እንደገና ፈትሸው።

 ኢትዮጵያን! ልብ እንበል፡፡ መንግስት ለህዝቡ የፅሞና ጊዜ እንስጠውና የሚበጀውን ይምረጥ፤ ወደ ርሻውም ይግባ ብሎ  የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ጦሩን ሲያወጣ እነሱ አሸንፈናል እያለ አፈር ልሰው በመነሳት  ህፃናትን አንገታቸው እስኪቆለመም ክላሽ አሸክመው ግንባር ላይ አሰልፈው ቀጠሉ። በወልቃይት ጠገዴና በራያ ግንባር ጥቃት ሰነዘሩ።

አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ በደንብ ልብ እንድል የምንፈልገው ነገር አለ። እነዚህ ሰዎች የዚህ ዘመን ፍጡራን ናቸው ለማለት ያስቸግራል። የዛሬ ሀምሳ እና አርባ አመት የነበረው የሀገራችን እና የአለም ፖለቲካዊ ሁኔታ ከአሁኑ ጋር  ልዩነት እንዳለው አይታያቸውም፡፡  ያኔ ደደቢት ሲገቡ ያዩት፣ የሰሙት እና አቋም የያዙበት ጉዳይ ዛሬም  ያው ነው ብለው  ያስባሉ። ማንም ምንም አለ ምን እኛ የምንለው እና የምንሰራው ሁሉ መቸም ቢሆን ትክክል ነው ብለው ያስባሉ። ከዳይናሚዝም ህግ ውጭ ናቸውና። እስቲ እነሱ ትክክል የሚሉትን ጥቂቶቹን  ልጥቀስ፡፡

1.የ3000ሺ ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት ማለታችን ትክክል ነው አሉ፡፡ 

2.የኛ መርህ ከፋፍሎ መግዛት፣ ብሔር ብሔረሰቦችን ማጋጨት፣  ማቃቃርና ማፈናቀል የሚል ሲሆን ጉልበተኛ ክልሎች እንጂ ጠንካራ ሃገረ መንግስት መኖር የለበትምና በዚህም እኛ ትክክል ነን ብለውናል፡፡

  1. የህወሃት የበላይነት እና መሪነትን በማረጋገጥ ሃብት በማሰባበብ ከሌላው ለመብለጥ  መስራት አለብን ይሉና ይህንንም በማድረጋችን እኛ ትክክል ነን ይላሉ፡፡

4.የአማራ ህዝብ ለኛም ለሌላውም ስጋት ነው፣ መዳከም አለበት! መጠላት አለበት።  ለዚህም ሰርተናል ይህን ማድረጋችንም ትክክል ነው ይሉናል።

  1. እኛ አገር ካልመራን የህዳሴ ግድቡ እንዲቆም፣ እንዲደናቀፍና እንዲመታም እንፈልጋለን። ለዚህም ለግብፅ እንወግናለን፣ የሱዳን ወረራም ተገቢነው ። በዚህም እኮ ትክክል ነን ይሉናል።

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች እና ክልሎቻችን! ነገሩ ከዚህም በላይ ነው።

 ነገር ግን እንዳው  በምን ህሊና ነው እነዚህ ሁሉ ነገሮች ትክክል ሊሆኑ የሚችሉት? ፍርዱ ለእናንተ ነው፡፡ በሀሺሽ አብደው ወጣቶችን በሀሺሽ እያሰከሩ በሬሳ ላይ ግፍ እየሰሩ አሁን የትግራይ ህዝብ ከነዚህ ምንድነው የሚጠብቀው? ነገሩ እንደዚህ ከሆነ ይህ አሸባሪ ቡድን ለትግራይ ህዝብም ለኢትዮጵያ ህዝብም እጅጉን የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም  በፍፁም ሊሆን አይችልም።

እናም ከዚህ የሻገተ፣ የደረቀ፣ እድሜልኩን ጠመንጃና ቦንብ ይዞ የሚሮጥ፣ በሳት የሚጫወት፣ ምንም ስልጣኔ የማይሸተው ፍጡር ጋር ተወያይቶም፣ ተሸማግሎም፣ መክሮም እንዲስተካከል ማድረግ በፍጹም አይቻልም፡፡ እናም ስለዚህ ያለው አማራጭ አንድ ብቻ  ነው፡፡ እሱም አቅምን አስተባብሮ ክልሉንና የኢትዮጵያን ነፃ ማውጣት  ነው። 

 መላው የኢትዮጵያ ህዝብ መከላከያን አና ልዩ ኃይሎቻችንን ባለ አቅም ሁሉ መደገፍ ይገባል። ይህ ደግሞ ለአገራችን ሰላምና እድገት አማራጭ የሌለው መፍትሔ  ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ግፈኛ ኃይል  የ27 አመት ያለበት እዳና ሂሳብ አሁን  መወራረድ አለበት፡፡ አመሰግናለሁ!!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top