Connect with us

የኢትዮጵያ አየርመንገድ ፡ የአፍሪካ አዲሱ መንፈስ

Social media

ነፃ ሃሳብ

የኢትዮጵያ አየርመንገድ ፡ የአፍሪካ አዲሱ መንፈስ

የኢትዮጵያ አየርመንገድ ፡ የአፍሪካ አዲሱ መንፈስ
(እስክንድር ከበደ – ድሬቲዩብ)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ሰማይ ነገሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ብሎም የአፍሪካ ህብረት መፈጠር ለአየር መንገዱ የበኩሉን ድርሻ የፈጠረለት ቢሆንም፤ብዙ ወጀቦችን አልፎ እስከ ፈታኙ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዘመን ደርሷል፡፡
እ.ኤ.አ በታህሳስ 21 ቀን 1945 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሰረተ ሲሆን ፤በአመቱ በሚያዚያ ወር ስራ እንደጀመረ ይነገራል፡፡ አየርመንገዱ እ.ኤ.አ በ1951 አመተ ምህረት አለም አቀፍ የበረራ መስመሮቹን እያሰፋ የመጣበት ጊዜ ነው፡፡ ከ14 አመታት በኃላ የሼር ኩባኒያ ሲሆን፤ የአለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማህበር አባል ሆነ፡፡
እ.ኤ.አ 1968 አመተ ምህረት ጀመሮ የአፍሪካ አየርመንገዶች ማህበር አባል ነው፡፡ የስታር አሊያንስ አባል አየር መንገድ የሆነው፤የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያን ወይም “ኢትዮጵያዊ ” መጠሪያና ባንዲራዋን ተሸካሚ በመሆን ይታወቃል፡፡

የኩባንያው አዲሱ መለያ መፈክር ደግሞ The New Spirit of Africa. ወይም የአፍሪካ አዲስ መንፈስ አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡
ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ዋና ማአከሉን ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፤በቶጎና በማላዊ ሁለተኛ ደረጃ ማእከሎቸ ፈጥሯል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ባለው መረጃ 127 የአለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች፣23 የሀገር ውስጥ በረራ መደረሻዎችና በ44 መዳረሻዎች የአየር ትራንስፖርት የእቃ ማጓጓዣ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ከአፍሪካ የአየር መንገዶች በተጓዥ ብዛት፣በመዳረሻ ቁጥር ፣በበረራ መጠን እና በገቢው ቀዳሚ የአየር መንገድ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዓለም የአየርመንገዶች ደግሞ በሚያገልግላቸው ሀገራት ብዛት በአራተኛ ደረጃ የሚጠቀስ አየርመንገድ ነው፡፡
የአየር መንገዱ ታላቅነት የሚጀምረው ከመነሻው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ወረራ ነጻ ከወጣች በኃላ እ.ኤ.አ በ1940ዎቹ መባቻ አካባቢ ቀዳማዊ ንጉሰ ነገስት ኃይለስላሴ ሀገሪቱን ለማዘመን ከወሰዷቸው እርምጃዎች አንዱ የኢትዮጵያ አየርመንገድ እንዲመሰረት ያደረጉት ጥረት ይጠቀሳል፡፡ ንጉሡ የአሜሪካ፣ የብሪታኒያና የፈረንሳይመንግስታት የአየርመንገዱን ለማቋቋም ድጋፍ ጠየቁ፡፡ ንጉሱ ኃያላኑን የኢትዮጵያን ድህነት ምስል የሚቀይር ብሄራዊ አየርመንገድ እንዲመሰርቱላቸው ፍላጎት ነበራቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከትራንስኮንቲኔንታል ኤየር ትራንስፖርትእና ዌስተርን ኤየር ኤክስፕረስ (ቲ ደብሊዩ ኤ) ጋር በመደራደር አሜሪካዊው የታሪክና የውጭ ጉዳይ አማካሪው ጆን ኤች ስፔንሰር የንግድ አየርመንገድ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመሰረት ሆነ፡፡ አየርመንገዱ ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ወጪ በዘመኑ በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በ25ሺ ሼር ወይም ድርሻ እንዲመሰረት ሆነ፡፡
በምስረታው ወቅት አየርመንገዱ በኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ወጪ ቢቋቋምም፤የሚታደደረው በቲ ደብሊዩ ኤ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሚታደደር ነበር፡፡ አሜሪካዊ ፓይለቶች፣ቴክኒሻኖቸ፣አስተዳደሪዎች እና ሂሳብ ሰራተኞቹ እንዲሁም ማናጀሮች የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡
የሥራና መገናኛ ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ታደሰ ሀብቴ የመጀመሪያው የአየርመንገዱ ፕሬዚዳንትና ሰብሳቢ እና በትራንስ ወርልድ ኤርላይንስ (ቲ ደብሊዩ ኤ) በኩል የተመደቡት አሜሪካዊው ዋና ሥራስኪያጅ ኤች ኤች ሆሎዌይ እ.ኤ.አ በ1945 አመተምህረት ባደረጉት የቦርድ ስብሰባ ቁልፍ አጀንዳው 75 ሺህ ዶላር በካይሮ ባንክ የተቀመጠ ሲሆን፤ ገንዘቡ ለአውሮፕላኖችና መለዋወጫዎች መግዣ ነበር፡፡ከጥቂት ጊዜ በኃላ አየርመንገዱ በኤደን፣በግብጽ፣በፈረንሳይ ሱማሌላንድ ፣ሳኡዲ አረቢያና ሱዳን የማረፊያ ፍቃድ በመደራደር ዳግላስ አምስት ሲ 47 አውሮፕላኖች እ.ኤ.አ በየካቲት ወር 1946 በማብረር ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ወደ ጄት ዘመን የገባው እ.ኤ.አ 1960ዎቹ እስከ 1970ዎቹ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአየርመንገዱ ወደ ጄት ዘመን እንዲገባ ልኡል ራስ መንገሻ ሥዩም ያደረጉትን አስገራሚ ትግል የትውልድ አደራ በሚለው ግለ ታሪክ መጽሀፋቸው ይተርካሉ፡፡
ልዑል ራስ መንገሻ የሥራና መገናኛ ሚኒስትር በነበሩበት ዘመን የአየርመንገዱም የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ይሰራሉ፡፡ ሚኒስትሩ ገና አየርመንገዱን እያጠኑ ባሉበት ጊዜ ጃፓን በሚካሄደው የኢንተርናሽናል አቬሽን ስብሰባ የመታደም እድል ገጠማቸው፡፡ በስብሰባው የሚቀርቡት ጥናቶች ሁሉ የጄትና የጄት በረራ ጉዳይ ሆነ፡፡ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተጓዙት በDC6 B አውሮፕላን የፕሮፔለር ኢንጂኖች (ሞተሮች) ነው፡፡ የሚባል ወሬ ሰምተው የማያውቁት ሚኒስትሩ ፤የኢትዮጵያ አየርመንገድን ከምስረታ ጀምሮ ለ15 አመታት የሚያማክረውን የትራነስ ወርልድ ኤየር ሰዎችም በስብሰባው ነበሩ፡፡ ራስ መንገሻ ዋና አማካሪውን 15 አመታት ሲያማክሯቸው ለምን ስለ ጄት እንዳላማከሯቸው ይጠይቃሉ፡፡
በፕሎፔለር ሞተሮችና በጄት ሞተሮች መካከል ከፍተኛ ልዩነት ነበር፡፡ የጄት ሞተሮች ያላቸው አውሮፕላኖች 50 በመቶ እንደተሻሉ የተረዱት ራስ መንገሻ ፤ዋና አማካሪውን ይሞግታሉ፡፡
አማካሪው ለጄት ዘመን ቴክኖሎጂ ሀገሪቱ ገና መሆኗ ቢገለጽላቸውም ፤ሚኒስትሩ እንዲጠናላቸው በመጎትጎት አማካሪው ጥናቱን ሰርቶ ያቀርባል፡፡
በጥናቱ የሁለት አውሮፕላኖች ግምት 45 ሚሊየን ዶላር ሆነ፡፡ 45 ሚሊየን ዶላር እንዲፈቀድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቀረቡ፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት መረጃው አፈትልኮ ወጥቷል፡፡
ሚኒስቴሮች ምክርቤት እንደቀረበ የገንዘብ ሚኒስትሩ ይልማ ደሬሳ ጥያቄውን ወዲያው አጣጣሉት፡፡ በቅርቡ በ28 ሚሊየን ዶላር ያወጡ ፤ሦስት DV6 B አውሮፕላኖች ተገዝቶ ለኢትዮጵያ አየር መንገዱ መሰጠቱን በመግለጽ አቶ ይልማ “አይቻልም” በሚል ይደመድማሉ፡፡
ይህን ውሳኔ በይግባኝ እስከ ንጉሡ የወሰዱት ራስ መንገሻ ፤ገንዘብ ሚኒስትሩን ወክለው እንዲደራደሩ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የቦይንግ ኩባንያ ሄዱ፡፡ ገና ናችሁ ተብለው ክርክር ቢገጥማቸውም ፤ በኃላ 45 ሚሊየን ዶላሩ ተፈቀደ፡፡
በኃላ ያልታሰበ የባለሙያዎች ስልጠና ደግሞ አሜሪካኖቹን በመጠየቅ ከሁለት አመት ተኩል በኃላ ለሚረከቧቸው ቦይንግ አውሮፕላኖች አብራሪዎችና ቴክኒሻኖች 5 ሚሊየን ዶላር እንዲሰጣቸው ጠይቀው አገኙ፡፡ ልዑል ራስ መንገሻ ካፒቴን አዳሙና ካፒቴን አለማየሁ አበበን ከፓይለቶች ፤ስድስት ሜካኒኮች ልከው ፤ያው ጄቶቹ ተሠርተው የመጀመሪያው በራራ ሊጀምር እንደቻለ ይናገራሉ፡፡
የልደታ አየር ማረፊያ የቦይንግ 720 ዎቹን አውሮፕላኖች ሊሸከም አይችልም በሚል የቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን እንዲሰራ መደረጉ ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ በታህሳስ 1962 አመተ ምህረት የ720ዎቹን የቦይንግ አውሮፓላኖች በመረከብ ወደ ጄት ዘመን መግባቱ ተበሰረ፡፡
በአመቱ እነዚህ አውሮፕላኖች ወደ ናይሮቢ መብረር የጀመሩ ሲሆን፤ በቀጣይ ወደ ስፔን መዲና ማድሪድ በረራ ቀጠሉ፡፡በጄት ዘመን ቴክኖሎጂ የፍራንክፈርት አየርን መቅዘፍ ጀመረ፡፡ በዛው ወር የቀድሞ DC-6B አውሮፕላንን በመተካት ከአዲስ አበባ ወደ አቴንስ መስመር በረራውን ቀጠለ፡፡የምእራብ አፍሪካ ኮሪደርም በዚህ አዲስ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ አየርመንገድ በ25ኛው ምስረታ አመት በኃላ ማኔጅመንቱን ጨምሮ አብራሪዎች፣ቴክኒሻኖችና አጠቃላይ የባለሙያዎች ስራዎችን የውጭ ዜጎችን በመተካት ኢትዮጵያውያን እንዲረከቡት አደረገ፡፡
እንደ ቢቢሲ የ2019 ዘገባ ከሆነ፤ እ.ኤ.አ 2018 የኢትዮጵያ አየርመንገድ በአፍሪካ ቀደሚው የአየርመንገድ መሆኑን ድምጽ አግኝቷል፡፡ ለአየርመንገዱ እንደ ድል የተቆጠረለት ተመጣጣኝ የአየር ትኬቶች ዋጋ፣ብቁ የአገልግሎት አሰጣጡ፣ የእቃዎች ደህንነት ሪኮርዱ እና ሰፊ የበረራ አውታሮቹ ይጠቀሳሉ፡፡

ዘገባው የኢትዮጵያ አየርመንገድ እ.ኤ.አ በ2011 የስታር አላይንስ አውታር አባል መሆኑ ፤በዓለምአቀፍ የአየርመንገዶች አውታሮች ተደራሽ እንዲሆንና ከበርካታ አየርመንገዶች ጋር በአጋርነት እንዲሰራ እድል ፈጥሮለታል ይላል፡፡
በአፍሪካ ጉዙፉ የአየርመንገድ መሆኑን የሚገልጸው ቢቢሲ፤በአፍሪካ ከሚገኙ አትራፊ ጥቂት አየርመንገዶች አንዱ መሆኑን ያትታል፡፡
ለአብነት በ2017/2018 አመት የኢትዮጵያ አየርመንገድ 245 ሚሊየን ዶላር ወይም 187 ሚሊየን ፓውንድ አትራፊ እንደሆነ ይህው ዘገባ ይጠቅሳል፡፡በዚሁ አመት 10 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎችን አጓጉዟል፡፡

በአፍሪካ በመንገደኛ አውሮፕላኖች ብዛትም ሆነ ፤ በአለም አቀፍ የበረራ ተደራሽነት በአህጉሩ የሚስተካከለው አየርመንገድ አይገኝም፡፡ 106 የዓለማቀፍና 23 የሀገርውስጥ በረራ መደራሻዎች አሉት፡፡
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ቦይንግ 787 ድሪምላይን እና 757 የእቃ ማጓጓዣ አውሮፕላን የተረከበ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየርመንገድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየርመንገድ ከራሱ አልፎ ሌሎች የአፍሪካ አየርመንገዶች በመርዳት የመሪነት ሚናውን ይጫወታል፡፡ አየርመንገዱ የማላዊን አየርመንገድ እንዲያንሰራራ 49 በመቶ ድርሻ ገዝቶ አብሮ በአጋርነት እየሰራ ይገኛል፡፡ በዛምቢያ አየርመንገድ ደግሞ 45 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ የሞዛምቢክ አየርመንገድንም ጋር አብሮ እየሰራ ይገኛል ፡፡ ከአህጉሪቱ አነስተኛ አየርመንገዶች እንዲያንሰራሩ እየሰራ መሆኑም ይነገራል፡፡
ከጂቡቲ፣ቻድ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ አየርመንገዶች ጋር ምክክሮች መጀመሩ ይሰማል፡፡
የፍላይት ግሎባል የተሰኘችው አቬሽን መጽሄት ጸሀፊ ማክስ ጆን ለቢቢሲ እንደነገረው ፤አየርመንገዱን በአፍሪካ ስራ ያቆሙ አየርመንገዶች እንዲያነሰራሩ የሚከተለው ስትራቴጂ የሚደነቅ መሆኑና የበረራ መስመሩን ከማስፋት ባሻገር መዳረሻዎቹን ይበልጥ ይጨምርለታል፡፡

የአየርመንገዱ 75 አመት ያስቆጠረ ሲሆን፤111 አውሮፕላኖች አሉት፡፡ በድምሩ 127 የበረራ መዳረሻዎችን የአለምአቀፍ ሚዲያዎች ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ አቬሽን ኢንዱስትሪ በአፍሪካ ተደራሽነቱን ይበልጥ ያጎለብትለታል እየተባለ ነው፡፡ይህም በአመት 22 ሚሊየን መንገደኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን፤የደቡብ አፍሪካው ጆሀንስበርግ የሚገኘውን የኦአር ታምቦ አለምአቀፍ አውሮፕላን የሚቀድም ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የራሱ የአውሮፕላን አብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምሕርት ቤት ሲኖረው የግል አብራሪ እና የንግድ አውሮፕላን አብራሪ ፈቃድ በመስጠት የሀገር ልጆችንም ሆነ የውጭ ዜጎችን በማሰልጠን የበርካታ አመታት ልምድ አለው። እንዲሁም ለብዙ የአፍሪካ ሀገር ብሔራዊ አየር መንገዶችና የግል አውሮፕላኖች የጥገና አገልግሎት ይሰጣል።
ቻይናዊው የጃክ ማና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢኒሼቲቭ በተባለው ለ54 አፍሪካ ሀገራት እንዲያደርስ ከቻይና የተላኩትን የኮሮና መከላከያቁሳቁሶች ከጥቂት ሀገራት በስተቀር አብዛኛዎቹን የአፍሪካ ሀገራት ሳምንት ባለሞላ ጊዜ አዳርሶ ማጠናቀቁ አቅሙን ያሳየበት አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ለአፍሪካ ሀገራት ለሚያደርገው ድጋፍ አየርመንገዱን መምረጡ ይታወሳል፡፡
ይህንን ግዙፍ ተቋም ወደ አልባዋ ሀገርን “ወደባችን” ብላ በመሪዋ አማካኝነት እንድታሞግሰው ያደረገ የአፍሪካ ተጽኖ ፈጣሪ አየርመንገድ ነው፡፡ ይህም ሆኖ የተፎካካሪዎቹ አየርመንገዶች ፤የምእራባውያኑ ሳይቀሩ በግልጽም ሆነ በስውር የሚፈትኑት ፤ ዝነኝነቱ የሚፈትኑ የጠለሹ ዘመቻዎች ከመስተናገድ አልቦዘነም፡፡
በቅርቡ በወደቀው የቦይንግ አውሮፕላን ቦይንግ ማምለጫ ለመፈለግ ስህተቱን ወደ ፓይለቱ ሊያላክክ ሲል ፤በመልካም ዝናው መገዳደር የቻለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በወደቀው ቦይንግ ሳቢያ በመላ አለም የሚገኙ ተመሳሳይ የቦይንግ አውሮፕላኖች ለጊዜው ከመብረር እንዲታገዱ የሆኑት ፤የኢትዮጵያ አየርመንገድ ሰመ ገናናነት አስተዋጽኦ አለው የሚሉ አሉ፡፡
በዛው ሰሞን የኬኒያ ብሄራዊ እግርኳስ ቡድን ጥቂት ተጫዋቾች በአየርመንገዱ ላለመሳፈር ማንገራገራቸው፤በእርግጥም በተደጋጋሚ አደጋ የሚታወቅ አየርመንገድ ሆኖ ሳይሆን የኬኒያ ኤይርዌይስ ስውር ግፊት አለ የሚሉትን ላለማመን ይቸግራል፡፡ የኢትዮጵያ አየርመንገድ የጃክ ማን ድጋፍ በራሳችን የአየርመንገድ እንውሰድ ማለታቸው፤አየርመንገዱ የሚዘመትበት የውስጥ ችግሮቹ ብቻ ሳይሆን የተፎካካሪዎቹ ፍላጻንም በጥንቃቄ ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡
በተለይ በአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ስምምነት እንዴት ይጠቅመኛል ብሎ ማስለት ቀጣይ የቤት ስራው ይሆናል፡፡መንግስት አንድ ሰሞን በከፊል ወደ ግል ይዛወራሉ ብሎ ከዘረዘራቸው ግዙፉ የመንግስት ኩባንያዎች ነበር፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በሦስት ወራት ከወጪ ንግድ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት አየር መንገድን በከፊል የመሸጥ ውሳኔ እንዲዘገይ መደረጉን ተናግረው ነበር፡፡
ሚኒስትሩ ስለኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳይ ተጠይቀው እንዳስታወቁት፣ አየር መንገዱን በከፊል ወደ ግል የማዛወሩ ውሳኔ ተፈጻሚነት እንዲዘገይ ተወስኗል ብለዋል።

አየር መንገዱ የሚገኝበት የተወዳዳሪነት አቅምና ብቃት፣ የኮሮና ተፅዕኖን በመቋቋም ያስመዘገበው ውጤት፣ ሠራተኞቹን ሳይበትን በካርጎ ትራንስፖርት ያካካሰበት የተቀዛቀዘው የመንገደኞች ትራንስፖርት ውጤታማነቱንና ጠንካራ አመራሩን ያረጋገጡ ማሳያዎች እንደሆኑ ተጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት አስቀድሞ አየር መንገዱን በከፊል ወደ ግል ለማዛወር ያሳለፈውን ውሳኔ ለወደፊቱ በይደር እንዳቆየው ምክንያቶችን ጠቅሰዋል፡፡
በአፍሪካ አንድ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በአህጉር ደረጃ መመስረቱ ሁለት ሀገራት የሁለትዮሽ ስምምነት ሲፈጽሙ በአየር መንገዶች ላይ ሲቀመጥ የነበረውን ገደብም ያስቀራል፡፡ የስምምነቱ ሌላ ጠቀሜታ አፍሪካውያን አየር መንገዶች ከአህጉሪቱ ውጭ ባሉ ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎች የተወሰደባቸውን የገበያ ድርሻ የማስመለስ ዕድል መስጠቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአህጉሪቱ ካለው የአየር ትራንስፖርት የገበያ ድርሻ ውስጥ 80 በመቶው የተያዘው የአፍሪካ ባልሆኑ አየር መንገዶች ነው፡፡ ኮሎኔል ወሰንየለህ ስምምነቱ በዚህ ረገድ የሚያመጣቸውን ለውጦች ይዘረዝራሉ፡፡

የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት እነዚህ ሁሉ ጠቀሜታዎች አሉት ቢባልም የተቃወሙት አፍሪቃውያን ግን አልጠፉም፡፡
መከራከሪያቸው ደግሞ ስምምነቱ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኬንያ ኤርዌይስ ፣ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ያሉትን ትልልቅ ኩባንያዎች ይበልጥ ጡንቻቸውን የሚያፈረጥም እንጂ ሌሎቹን የሚያዳክም ነው የሚል ነው፡፡ በስምምነቱ አነስተኛ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጨርሰው ይጠፋሉ ሲሉ የሚሞግቱም አሉ፡፡
አንድ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት በ30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይፋ ይደረግ እንጂ ጥንሰሱ ረጅም ጊዜ ቆይቷል፡፡ የአሁኑ ስምምነት እ.ኤ.አ 1999 የአፍሪካ መሪዎች ያማሳኩሩ ላይ ከተስማሙበት የሚመነጭ ነው፡፡ ይሄ እንደመነሻ ተወስዶ በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2000 ዓ.ም የአፍሪካ መሪዎች ቶጎ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ አንድ የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ እንዲኖር ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት ደግሞ ገበያው እንዲጀምር ኢትዮጵያን ጨምሮ የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት እሺታቸውን በፊርማቸው ገልጸዋል፡፡ ይህንን ነጻ ገበያ ምንነት ከአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲሁም የኢትዮጵያ አየርመንገድ ለመጠቀም ያለውን ምቹ ሁኔታዎችና ተያያዥ ነጥቦችን በሌላ ጊዜ የምንዳስሰው ይሆናል፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top