እነ የታምራት ላይኔን የኔ ብለን ከሰማን ከህወኃት በምን ተለየን? እነሱስ ምን ለይቷቸው ከእነሱ ሊያስማሙን መጡ?
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ሰው እንዴት የገዛ ወገኑ እንዲህ ያለ የመከራ ቀንበር ይሆናል? አሁን ደግ ልቡ ሁሉን ያስረሳው ሆኖ እንጂ ቁጭ ብለን የሆነውን ከቆጠርን በታምራት ላይኔና በስብሐት ነጋ መካከል አማራን በመጥላት በመበደልና በማሳደድ ምን ልዩነት አለ?
ወልቃይትንና ራያን አሳልፎ የሰጠ የፖለቲካ ሹም ዛሬ ወልቃይትና ራያን አማራን አጥፍቼ እወስዳለሁ ከሚል ሃይል ጋር ላነጋግራችሁ የሚለን ሁለቴ እንዲገድለን እድል መስጠት የምንችል መስሎት እንጂ ስራው ጠፍቶት አይደለም።
ታምራት ላይኔ ከህወሃት ካነጋገረን አንድ ፊቱኑ ለምን ራሱ ዶክተር ደብረፅዮን አያስማማንም። ግን ጉዳዩ ሌላ ነው። እንደ ያሬድ ጥበቡ ስዬ አብርሃና ታምራት ላይኔ ያሉ ሽማግሌዎች የበደሉን ፅዋ የሞሉ የሀገር ጠላቶች ናቸው።
አቶ ታምራት አማራ እንዲሰደድ ዛሬ ማቅናት ያቃተንን ፍቅር ያጠመሙ የጥላቻው ፖለቲካ መሃንዲስ ናቸው። ያሬድ ጥበቡም የህወሓት ሀገር የማፍረስ መንፈስ ገና በጠዋቱ በርሃ ላይ የለከፈው ሰው ነው።
ስዬ አብሮ ቢሆንም እንደ እነሱ ትንሽ ሀሳብ የሌለው የሚሰራውን የሚያውቅ ወገኔ ለሚለው የትግራይ ህዝብ ድል አድራጊነትና አማራን እናንበረክካለን ባይነት በትጋት የሚሰራ ነው።
በኢትዮጵያ ትልቁ የሀገር ጥቅም ሲፈርስ የኖረው እና የሚያምን ለጉዳት የተዳረገው በዳይ ሽማግሌ እየሆነ ነው። ሽማግሌ ሊባል የሚበቃ ሰው አንተም ተው አንተም ተው ማለቱን አንጠላውም። ነውርም አይደለም። ጦርነት እንዲቆም ጦርነቱ ይነሳ ዘንድ ምክንያት የሆኑ ሰዎች እውነት ስታሸንፍ ሽማግሌ መስለው ሲመጡ ግን ስላቅ ነው።
የህወሃት ሰዎች ነውር ዘር ውስጥ ተሸጉጦ ሀገር ለመከራ ሲዳርግ አይተናል። ለምን? የኔ ዘር ነው በሚል የራስ ቋንቋ ተናጋሪ ሌባን ገዳይና ሀገር አጥፊን የትግራይ ህዝብ ያስጠጋዋል? ብለን ሞግተናል።
ዛሬ ደግሞ ያሬድና ታምራት ላይኔ ከስዬ አብርሃ መክረው አማራን እንደ ትናንቱ ያንተ ነን ብለው ለእሱ የማይሆን ምክር መለገስ ሊጀምሩ እንደሆነ ሰማን። ሽፋኑ ደግሞ ሽምግልና ነው።
ያዋጋን እና ለውጊያ ምክንያት የሆነን የጥላቻ አባት አሁን ሰላም ልስበካችሁ ቢለን ሰላም ከሚለው ቃል ጀርባ ያደባ ሴራ እንዳለ እንረዳለን።
አሁንም ጦርነት እንዲቆም መንግስት ላይ ነፍጥ ያነሳ እጁን ሰብስቦ ሀገር ማፍረስ ዓላማዬ ነው ያለ ቡድን ለፍትሕ ቀርቦ እንጂ ወንበዴ ማጣፊያው ሲያጥረው እድሜ መግዣ ደባ ሽምግልና አይደለም። ሠላምም አያመጣም።