ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርቲዎ እርስዎን ይዞ ሳይኾን እርስዎ ፓርቲዎን ይዘው ለድል በቅተዋል፤ እንኳን ደስ ያለዎት!!
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ብልጽግና ጠቅላይ ሚኒስትሩን አስመረጠ አንልም፤ ይልቁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲያቸውን ጭምር ይዘው ተሻገሩ፡፡ ዶክተር ዐብይ ባልተወዳደሩባቸው ቦታዎች ሳይቀር ሰዎች እሳቸውን ከመፈለግ እና በእሳቸው ተስፋ ከማድረግ የተነሳ ምርጫቸው ብልጽግና ሆኗል፡፡
ብልጽግናን ወክሎ ከተወዳዳረው ብዙ እጁ በራሱ ተክለ ቁመና የሚመረጥ አልነበረም። ግና ብረት መዝጊያ የሆነ የፓርቲ መሪ ታድሏል፡፡ በፓርቲ መሪው ምክንያት ድምጽ ያጣ እንዳለ ሁሉ ብልጽግናም በፓርቲው መሪ ሳቢያ ለድልና ለመንግስትነት በቅቷል፡፡
ብዙ ሰዎች ብልጽግናን ተጠራጥረው ለጠቅላዩ ልባቸውን የሰጡ ናቸው፡፡ ፓርቲው በየወረዳው ከአካባቢው ተመራጭ ተወዳዳሪ ፎቶ ጎን የዶክተር ዐብይን እየሰቀለ ቀስቅሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበሻሻን ያህል በድፍን ኢትዮጵያ ፎቶአቸው ለምርጫ ቅስቀሳ ውሏል፡፡ ብልጽግና ዛሬ የሚኮራባቸው ጸጋዎች በሙሉ በአንድም በሌላም የመሪው ገጸ በረከቶች ናቸው፡፡
ፓርቲው ከትናንቱ የወረሳቸው ዛሬም በየጎዳናው የለቀማቸው ብዙ ግሳንግሶች ቢኖሩትም አራግፎ በመቀጠል በኩል ከኢህአዴግ ፍጹም እንደሚለይ አሳይቷል፡፡ ኮተቱን አባብሎ አምባሳደር ሾሞ መደብ ቀይሮ ሀገር የሚጫን እንዳልሆነ ከእስከ አሁኑ ጉዞ ለመረዳት ይቻላል፡፡
ምርጫ ቦርድ ብልጽግና መንግስት መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ግን እውነቱ መንግስት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ በእኔ ግምት ፕሬዚዳንታዊ ቢሆን ምርጫው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚደርስ ሀገር አቀፋዊ ተወዳዳሪ መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡
ዶክተር ዐብይ ፓርላማቸው ጉራማይሌ እንዲሆን ፈልገው ነበር፤ አስቀድመው ድምጽ አትበትኑ አንድ ላይ ሁኑም ብለው መክረዋል፡፡ ምህዳሩን ጥሩ ለማድረግ የጣሩት ጥረትም የሚደነቅ ነው፡፡ እንጀራ ሆኖበት ላለመውደቅ በታገለ ካድሬ ምክንያት ምርጫው ጤንነት ላይ ጥያቄ ያስነሱ ችግሮች ቢፈጠሩም ተቃዋሚዎቹ ሳይቀር ያመሰገኑትም ምርጫ ቦርድ ማየት የቻልነው በብልጽግናው መሪ ቁርጠኛነት ነው፡፡
አሁን ዶክተር ዐብይ አሸንፈዋል፡፡ በሻሻ ብቻ ሳይሆን በድፍን ኢትዮጵያ ስማቸው ተስፋቸውና ምኞታቸው ምርጫ ተቀስቅሶበት እናቶች እሳቸውን አምነው፣ ወጣቶች ነገን ተስፋ አድርገው ፓርቲያቸውን ጭምር ለመታደግ፣ የወረዳውን ሰው ሳይቀር ለድል አብቅተዋል፡፡ እውነት ለመናገር ፓርቲያቸው እሳቸውን ይዞ ሳይሆን እሳቸው ፓርቲያቸውን ይዘው ለድል ስለበቁ እንኳን ደስ ያለዎት ሊባሉ ይገባል፡፡
ቀጣዩ ይሄንን አደራ በቁርጠኝነት መወጣት ነው፡፡ የመዋቅራቸው ዋስ እሳቸው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የመዋቅሩ ዋስ የአካባቢው ካድሬ ነበር። አሁን የአካባቢው ካድሬ ዋስ ጭምር ጠቅላዩ ናቸው። እናም ይሄንን ብሎ ድምጽ የሰጠውን መራጭና መንግስት ያደረጋቸውን ህዝብ ከምንም በማያስጥል ሰነፍ ካድሬ ቀይረውት ስሜቱን እንዳይሰበር ማድረግ አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ አሸንፋለች የሚለው መፈክር ሰርቷል፡፡ ሀገር ምንም ሳትከስር፣ ወገን ሳይናቆርና መንግስት ሳይታማ ምርጫው አልቆ ለፍሬ በቅቷል፡፡ መጪው ዘመን ቃል እንደተገባልን የብልጽግና ቢሆን ጥቅሙም ትርፉም የእኛው ነው፡፡
ከአምስት አመት በኋላ ጥቂቶቹ ፓርቲዎች በልዩ መንፈስ ብቃትና አቅም ዳግም ተደራጅተውና መሬት ረግጠው እንደሚመጡ አልጠራጠርም፡፡ ያ እንዲሆን ግን ቢያንስ ፓርቲውን ይዞ የሚሻገር ታማኝ መሪ የግድ ይላል፡፡