Connect with us

ከግብጽ ጎን ማንም ይቆማል፤ ከእኛ ጎን ግን ፈጣሪ ቆሟል፡፡

ከግብጽ ጎን ማንም ይቆማል፤ ከእኛ ጎን ግን ፈጣሪ ቆሟል፡፡
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከግብጽ ጎን ማንም ይቆማል፤ ከእኛ ጎን ግን ፈጣሪ ቆሟል፡፡

ከግብጽ ጎን ማንም ይቆማል፤ ከእኛ ጎን ግን ፈጣሪ ቆሟል፡፡

በእኛ ለመበደል ሳይሆን ከድህነት ነጻ ለመውጣት የምንባትል ነን!

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

የፀጥታው ምክር ቤት ስንት የደፈረሰ የዓለም ጉዳይ እያለ በደፈረሰ ውሃ ስለሚሞላ ግድብ ጉዳዬ ያለው የመከራውን ብዛት ያሳየናል፡፡ በየምክንያቱ ጉዞአችንን መንገድ ለማስቀረት የሚፈልጉት ጠላቶች ሲያተርፉ አላየንም፡፡

ኢንጅነር ስለሺ ከህዳሴው ግድብ ጋር አብረው ለዘለዓለም ከሚታወሱ ፋና ወጊ የሀገር ልጆች አንዱ ናቸው፡፡ ሰውዬው ዓለም መድረክ ሀሳባቸውን ሲገልጹ ጭንቀትም ፍርሃትም አልታየባቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኒውዮርክ የዘለቁት ሀቅ ይዘው ነው፡፡

ግብጽ የምትፈልገውን ዛሬም አላወቅንም፤ ሱዳን ግብጽ የምትፈልገውን ፍለጋ ላይ ሆኖ መንገዷን የቀየረች ሀገር ናት፡፡ ብዙ የተዶለተበት የጸጥታው ምክር ቤት ጉባኤ ግብጽ በምናቧ የደገሰችውን የበላችበት አልሆነም፡፡ ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡

ከግብጽ ጎን የቆሙ ሀገራት ቢበዙም፣ የግብጽ ካዝናዎች ቢሞሉም፣ የፈርዖኖቹ ጡንቻ ቢፈረጥምም፤ ሀቅ አለንና ፈጣሪ ከእኛ ጋር ነው፡፡

የመንደሮቻችንን አፈር ሩቅ ልከን የፈረዖናውያኑን ሀገር ስናለማ በእድገታቸው አንድም ቀን ዓይናችን ደም ያልለበሰ ከእነ አካቴው ልማታቸውና ግዝፈታቸው አጀንዳችን ያልሆነ ህዝቦች ነበርን፡፡

ያ ከየመንደሩ ያዋጣነው ውሃ እራትና መብራት ቢሆነን ስንልም የማንምም ጉሮሮ ስለመዝጋት ዶልተን አይደለም፡፡ ለሁላችን የሚበቃ የራሳችን ሀብት ላይ ጥቂት ቆንጥረን እፈሱ ስንላቸው መደፈር አድርገው ቆጠሩት።

የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ጉዳዩ ወደ ህብረቱ እንዲመለስ ወስነዋል፡፡ ግብጽ ያቀደችው አልሰመረም፡፡ ተሟጋቾቻችን ሀሳባቸው የምክር ቤቱን አባላት አሳምኗል፡፡

ነገ ከነገ ወዲያ ሌላ ምክንያት ሌላ መንገድና ሌላ መነታረኪያ እንጠብቃለን፡፡ የዘመናችን አድዋ ነውና ክተት ብለናል፡፡ መከራውን ስቃዩን ደባውን ድል እናደርገዋለን፡፡ አንዴ ህገ መንግስታችንን እናስከብርላችሁ ብለው፣ ሌላ ጊዜ የውስጥ ጉዳያችንን ጉዳይ አድርገው ምክንያተ ብዙ በሆነ ዘመቻ ብዙ ይሞክሩብናል፡፡ አብሮን ያለው ሃያል ሀገር ሳይሆን ፈጣሪ ነውና ድል እናደርጋለን፡፡

መቀነቷን የፈታችውና ግድቤ ያለችው እናት ግድቡ እንኳን እውን ቢሆን አይኗ በጢስ ጠፍቷል፡፡ እነኛ ለህዳሴው ግድብ ያልሆነ ብለው ሆ ያሉ ወጣቶች የጉብዝና ዘመናቸውን ተስፋ ጉርምስናቸው ሲደርስ የጠበቁ ናቸው፡፡ ከዳር ዳር ጉዳያችን የሆነ የእኛ ወንዝ ለእኛ ትንሽ ነገር ቢያደርግ እንጂ ግብጽ የምትባል ሀገር ብትከስር በሚል መንፈስ አይደለም፡፡ ያን ቀና መንፈሳችንን ፈጣሪ ይመለከታል፡፡ እናም እናሸንፋለን፡፡

ኢንጅነር ስለሺ በቀደሙት መንገድ ሄደዋል፡፡ እንደ ከተማ ይፍሩ እንደ አክሊሉ ሀብተወልድ የሀገር ሀሳብ ለዓለም ገልጸው ሀገር ጠቅመው መጥተዋል፡፡ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴም እረፍት አልባው የዲፕሎማሲ ጦርነት ሜዳ ላይ ናቸው፡፡

አንድ ከሆንን ዓለም በአንድ ድምጽ አሁንም ከእኛው ጋር እንዲቆም ማድረጉ ቀላል ነው፡፡ ብኩርናችንን ለምስር አሳልፈን ሸጠን በሀገር ጉዳይ ከሸቀጥን እንጠፋለን፡፡ ዛሬ እንደ ህዝብ አሁንም በአንድ መንፈስ አንድ ላይ ቆመናል፡፡ ያኮረፈውም ወደ ቆምንበት የጋራ ጉዳይ ቢመጣ መልካም ነው፡፡ ባይመጣ ድላችንን መካፈል ይቀርበታል እንጂ የሽንፈታችንንና የውድቀታችንን ዜና አይሰማም፡፡ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top