Connect with us

ሀገር የኾነው በየዘመናቱ የገጠመንን ዛቻ፣ ሴራና ማዕቀብ አልፈን ነው…

ሀገር የኾነው በየዘመናቱ የገጠመንን ዛቻ፣ ሴራና ማዕቀብ አልፈን ነው፡፡ ይህ ትውልድም ይህን ዘመን አልፎ ሀገር ያሻግራል
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ሀገር የኾነው በየዘመናቱ የገጠመንን ዛቻ፣ ሴራና ማዕቀብ አልፈን ነው…

ሀገር የኾነው በየዘመናቱ የገጠመንን ዛቻ፣ ሴራና ማዕቀብ አልፈን ነው፡፡ ይህ ትውልድም ይህን ዘመን አልፎ ሀገር ያሻግራል

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

ከግድቡ ሙሌት በፊት ከብዙ ነገር ሊያጎድሉን ነበር፡፡ እንደ ትናንቱ በቋንቋ ልዩነታችን እንዳንደማመጥ ወጥመድ ዘርግተውብናል፡፡ ዓለም ፊት አንሰን እንድንታይ በጉባኤው አሲረውብናል፡፡ አቅም የላቸውም ብለው አቅም ካለው ጎን ቆመውብናል፡፡ ግን ድምጽን በድምጽ ከሚባለው ወገን ያልሆነ ፈጣሪ ከእኛ ጋር የሆነ ህዝቦች ስለሆንን ድምጻችን ተሰምቷል፡፡

ግብጽን ለመብለጥ የምናስብ ዜጎች አይደለንም፡፡

ከግብጽ እኩል ስለመሆን የፉክክር መንፈስም አልተጠናወተንም፡፡ እኛ መከራችንን ድል ለማድረግ ውሃችንን የተመለከትን ደሃ ህዝቦች ነን፡፡ አምባሳደሩ እንዳሉት ተስፋ ግን ያለን፡፡

ተስፋችንን ለማጨንገፍ ሞክረዋል፡፡ ራሳችን ራሳችን ላይ እንድንነሳ ገዝተውናል፡፡ አበሳችን ዓለም እየሰማው አበቃለት የተባለ ግድብ ዳግም ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት እውን አድርገናል፡፡

የዛቱብን ብዙ የሚተማመኑበት መሳሪያ ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ሀብታምና ጎተራቸው ሙሉም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የረሱት ግን ፈጣሪ ከተራበው ጎን መቆሙን ነው፡፡ እኛ ጨለማ ለመግፈፍ ያለንን ጥሪት የገፈፍንበት ፕሮጀክት መሆኑ አልጠፋቸውም፤ ትዕቢት ግን ብዙ ቦታ አደረሳቸው፡፡

ትናንት እንዲህ ያለ ነገር ደጋግሞ ገጥሞናል፡፡ ተወረን የዓለም መንግስት ከወራሪያችን እኩል አይቶን ያውቃል፡፡ ተበድለን በደላችንን የሰማን አልነበረም፤ ይልቁንም እንድንጠፋ ተሲሮብናል፡፡ ያን ሁሉ አልፋ ዛሬ የደረሰች ሀገር ዜጎች ነን፡፡ ሚሳኤላችን ሰማይ የተቀመጠ፤ ሃይላችን በፈጣሪ ክንድ የሚታመን ህዝቦች ነን፡፡ ከማንም እንበልጣለን ስለማንል ከማንም አላሳነሰንም፡፡ ማንም ትንሽ አድርጎ አይቶን ትልቅ ሆኖ ስሙ አልተነሳም፡፡ ተራሮቻችን ምስክሮች ናቸው፡፡ የነጻነት ምልክት ሆነን ኖረናል፡፡

ይሄ ትውልድ ይሄንን ያልፋል፡፡ መከራው ታሪክ ይሆናል፡፡ ግድቡ እንዳይሞላ በየምክንያቱ መተከል፣ ማይካድራ፣ ጉራ ፈርዳ፣ አጣዬ ብዙ ቦታ የጎደሉ አሉን እነሱ እንደ አሽዋ እንደ ጠጠሩ ስውር የህዳሴው ግድብ ሰማዕታት ናቸው፡፡

ሰላም ማጣትን፣ ድህነትን፣ አድማን፣ እርስ በእርስ ጦርነትን ሁሉ ገብረን እውን ያደረግነው ግድብ መሆኑን ለልጆቻችን እንተርከዋለን፡፡ ባልጀመርነው አላልንም፤ እንጨርሰዋለን በሚል ዛሬም ወገን ዋጋ እየከፈለ ነው፡፡ ድምር ውጤቱ ከድምር ኪሳራው በላይ እንደሆነ የእኔ ትውልድ አደዋ ነው ከሚለው የዚህ ዘመን ወኔ ማየት ይቻላል፡፡

አባይ አንሶ አይደለም፡፡ 

አባይን የሚጨርስ የስስት መንፈስ የለብንም፡፡ አባይ ሳይበቃን ሳይሆን አይገባቸውም የሚለው መንፈስ አይሎ ብዙ ዋጋ ከፍለናል፡፡ ዓለም ዛሬ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ላይ እንደሆነን ከግብጽ ሰምቷል፡፡ ለግብጽ ነግረናታል፡፡ የሰወርናት ነገር የለም፡፡ ሸፍጥ ሳይሆን አብሮ መልማት የሚፈልገው መሻታችን አንዳች ጥፋት ሳይኖርበት ብዙ ደባ ተፈጽሞበታል፡፡

ማን ያውቃል አንድ ቀን ግድቡ ራሱን ይጠብቅ ይሆናል፡፡ 

ያኔ ስለግድባችን ደህንነታችን የሚያሳስባቸው ሀገራት ይበዙ ይሆናል፡፡ ያኔም ቢሆን ግን በፈጣሪ የምንታመን ህዝቦች እንጂ ወቅት አነሳን ብለን ሌላ ስም እንዲወጣልን እንደማንሻ ዓለም ዳግም ያረጋግጣል፡፡

እዚያ የጉባ በርሃ ውስጥ ከአይቻልም ጋር ትግል ላይ ሆነው ሌት ተቀን ተአምር የሚሰሩ ጀግኖች በየነፍሳችን ክብራቸው ታትሞ ይኖራል፡፡ ለትውልድ ከምናወርሰው ታላቅ ገድል ጋር የማይጠፋ ውለታቸው አብሮ ይሻገራል፡፡ ይህ ትውልድ ይሄንንም ያልፋልና፤

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top