Connect with us

የሕዳሴ ግድብ ወንድም ለሆነው የሱዳን ሕዝብ የስጋት ምንጭ ሊሆን አይችልም!

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወንድም ለሆነው የሱዳን ሕዝብ የስጋት ምንጭ ሊሆን አይችልም!
በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ

ዜና

የሕዳሴ ግድብ ወንድም ለሆነው የሱዳን ሕዝብ የስጋት ምንጭ ሊሆን አይችልም!

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወንድም ለሆነው የሱዳን ሕዝብ የስጋት ምንጭ ሊሆን አይችልም!

በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር  ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን ለሚገኙ ልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ይበልጣል በመግለጫቸው “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ እና ጉዳዩም ቴክኒካዊ ቢሆንም ከሚገባው በላይ የመነጋገሪያ እና የፖለቲካ ጉዳይ  እየሆነ  ስለመጣ ወንድም ለሆነው የሱዳን ህዝብ እውነታውን እንዲያውቅ ለማገዝ የተዘጋጀ ጋዜጣው መግለጫ ነው” ብለዋል።

የአባይ ተፋሰስ የኢትዮጵያን ሁለት-ሶስተኛ የውሃ ሀብት የሚሸፍን እንዲሁም የናይልን 86 በመቶ ኢትዮጵያ የምታበረክት ቢሆንም ሀብቱ እያለ እስካሁን ድረስ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በኤሌክትሪክ እጦት በጨለማ ውስጥ ይኖራሉ ያሉት አምባሳደሩ አባይን ማልማት ለኢትዮጵያ መብቷ እና ግዴታዋ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ስትጠቀም ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በመሆኑም በማንም ተጋሪ ሀገር ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማታደርስ ፣ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ሕግንና መርህን አክባሪ እንደሆነችና ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የፍትህና የእውነት አገር መሆኗንም ነብዩ መሃመድ እንደመሰከሩላት ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን፣ የጋራ ታሪክ ያላቸው ዕጣፈንታቸውም የተሳሰረ መሆኑን ያስረዱት አምባሳደር ይበልጣል በታሪክ እንደታየው አንዳቸው ለአንዳቸው ጋሻ ሆነው መቆየታቸውን አውስተዋል። ከዚህ አንጻር ሱዳን ለኢትዮጵያውያን የክፉ ቀን መጠጊያ እንደሆነችው ሁሉ ኢትዮጵያም ለሱዳን ሰላም፣ መረጋጋት እና አንድነት የቁርጥ ቀን ደራሽ መሆኗን  አስታውሰው፣ በ1972 (እ.ኤአ.) በሰሜን እና ደቡብ ሱዳን ኃይሎች የሠላም ስምምነት እንዲመጣ ከማድረግ ጀምሮ በምስራቅ አፍሪካ በይነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ስር በሠላም ሂደቱ ንቁ ሚና በመጫወት፣ እንዲሁም በዳርፉር እና በአብዬ የሠላም አስከባሪ በማሰማራት እስከ ህይወት መሰዋዕትነት በመክፈል እና አሁን በሱዳን ለተፈጠረው ሠላምና የሽግግር መንግስት ምስረታ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ሚና የሱዳን ሕዝብ የሚያውቀው እንደሆነ አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም ያለው በመሆኑም ሱዳናዊያን እና የሱዳን መንግስት ለግድቡ ግንባታ አስፈላጊውን የፖለቲካ፣ የማቴሪያልና የሞራል ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ ጠቅሰዋል፡፡  

ከዚህ አኳያ ግድቡ “የሱዳን ኃይል ማመንጫ ግድቦች ከዓመት እስከ ዓመትበሙሉ አቅማቸው ኃይል ለማመንጨት እንደሚረዳ፣ የአባይ ወንዝ ተመጣጣኝ ፍሰት ስለሚኖረው በዓመት ሶስት ጊዜ ለማምረትና ምርታማነትን እንደሚጨመር፣ ወንዙ በበጋ ወቅት ከነበረው ከሁለት እስከ አራት ሜትር ከፍ ስለሚል እና ዓመቱን ሙሉ የተመጠነ ፍሰት ስለሚኖረው ለመጓጓዣነት (navigation) የተሻለ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር፣ በወንዙ የውሃው ከፍታ ስለሚጨምር ለውሃ መሳቢያ ሞተሮች /pumps ወጪን እንደሚቀንስ፣ ወደ ሱዳን ግድቦች ይገባ የነበረውን 90 በመቶ ደለል በመቀነስ ሱዳን ለደለል ማስወገጃ በየዓመቱ የምታወጣውን 50 ሚሊዮን Euro እንደምታድን፣ ሱዳን በአነስተኛ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ማግኘት እንደምትችል፣ የጎርፍ አደጋ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ የህይወትና ንብረት ጥፋትን እንደሚታደጋት ገልጸዋል በጥቅሉ “ታላቁ የኢትየጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለ የሱዳን ግድብ ነው” ቢባል ማጋነን እንደማይሆን ጠቅሰዋል።

ግድቡ ለሱዳን የሚሰጠው ጥቅም አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን ጨምሮ በሱዳን ባለሙያዎች ጥናት የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ “ለ20 ሚሊዮን ሱዳናዊያን እና ለሱዳን ግድቦች አደጋ ነው” መባሉ ከእውነት የራቀ እንደሆነ፣ የግድቡን ደህንነት በተመለከተ  ግድቡ በወቅቱ ያለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ በጠንካራ የአለት መሰረት፣ ከምንም ዓይነት የመሬት እንቅስቃሴ ነፃ በሆነ አካባቢ፣ ሳይንሳዊ ደረጃውን በጠበቀ ዲዛይን፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ በርካታ ግድቦችን በመገንባት ስመጥር በሆነ ኩባንያ እየተገነባ ያለ አስተማማኝ ግድብ እንደሆነ እና የሱዳን የውሃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስም የግድቡ ደንነት በሱዳን እና ግብጽ ካሉ ግድቦች የተሻለ እንደሆነ መናገራቸው የዚሁ ማሳያ እንደሆነ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ገልጸዋል።

ከመረጃ ልውውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለማጋራት ዝግጁ ስትሆን የግድቡን ሙሌት በተመለከተ መቼ ምን ያክል ውሃ መያዝ እንዳለበት በሶስቱ ሀገራት ባለሙያዎች መግባባት የተደረሰበት እንደሆነ ጠቅሰዋል። አምባሳደሩ አያይዘውም 86 በመቶ የውሃ ሀብትን ለናይል የምታበርክትን ሀገር በራሷ ግዛት፣ በራሷ ገንዘብ እና የራሷን ፍትሐዊ የውሃ ድርሻ ተጠቅማ ለምትገነባው ግድብ ውሃ አትሙላ ማለት ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል። 

በሀገራት መካከል አንድን ጉዳይ በተመለከተ የሚደረስ ስምምነት በጉዳዩ ላይ አስገዳጅ እንደሚሆን አውስተው ሱዳን እና ግብጽ አስገዳጅ የሚሉት ስምምነት ደግሞ አግላይ የሆነ እና በግብጽ እና ሱዳን ብቻ የተደረገ ፍትሐዊ ያልሆነ የውሃ አጠቃቀምና ክፍፍል የሚያስቀጥል እና ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ላይ ያላትን መብት የሚሽር እና ወደፊት የልማት ስራ ከማከናወን የሚገድብ ተቀባይነት የሌለው ሃሳብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጉዳዩ በሶስቱ አገሮች መካከል በሚደረግ ድርድር የሚጠናቀቅ ሆኖ ሳለ፣ በሱዳን እና ግብጽ በኩል ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቅም መርሆዎች ባፈነገጠ መልኩ “የኢትየጵያን የውሃ የመጠቀም መብት ለመገደብ መሻታቸው፣ ቴክኒካዊ የሆነን የግድብ ጉዳይ የጸጥታ እና የፖለቲካ ጉዳይ ለማድረግ ቀን ከሌት እንደሚሰሩ፣ የዐረብ ሊግ አገራትን በማስተባበር በኢትጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እንደሚሞክሩ፣ ጉዳዩ ወደ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ለመውሰድ ሌት ተቀን በመስራት ጉዳዩን ዓለምአቀፋዊ ለማድረግ እንደሚጥሩ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ እምነት አላስፈላጊ ጫና ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል በአጽንኦት ገልፀዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር በሚደረገው ድርድር ሶስቱን አገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት መድረስ እንደሚቻል የጠቀሱት አምባሳደር ይበልጣል መጀመሪያ የግድቡ አሞላል ዙሪያ ሶስቱ ሀገራት የጋራ መግባባት የደረሱ በመሆኑ በመጀመሪያ ሙሌቱ ዙሪያ መስማማት እና በቀጣይ ድርድሩን በግድቡ ዓመታዊ የውሃ አለቃቅ(annual operation) ዙሪያ ማስቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል።(በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top