Connect with us

” ግድቡ የኔ ነው !”  ይህ  የኢትዮጵያውያን የአንድነት መልክ ነው፡፡

” ግድቡ የኔ ነው !” ይህ የኢትዮጵያውያን የአንድነት መልክ ነው፡፡
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

” ግድቡ የኔ ነው !”  ይህ  የኢትዮጵያውያን የአንድነት መልክ ነው፡፡

” ግድቡ የኔ ነው !”  ይህ  የኢትዮጵያውያን የአንድነት መልክ ነው፡፡

           ( እስክንድር ከበደ  – ለድሬ ቲዩብ)

በሱዳን የእርሰበእርስ ጦርነት በተለይ የሁለተኛውን የሱዳን እርስ በእርስ ጦርነት የመሩት ዶክተር ጆን ጋራንግ ” አዲሲቷ ሱዳን ” የሁሉም ሱዳናውያን መሆን አለባት የሚል ፍልስፍና ነበራቸው፡፡ ጆን ጋራንግ እ.ኤ.አ 1983  እስከ  2005 የሱዳን ህዝብ ነጻነት ጦር ለ22 አመታት መርተዋል፡፡  እ.ኤ.አ በጁላይ 30፣ 2005 ከኡጋንዳ ሲመለሱ በውል ባልታወቀ ምክንያት የተሳፈሩበት ሂሊኮፕተር  ተከስክሶ  ለሞት ተዳረጉ፡፡  አሟሟታቸው ዛሬም ሚስጥር ነው፡፡ 

ዶክተር ጆን ጋራንግ ይመኙ የነበሩት  ለሱዳን መከፋፈል ሳይሆን ሁሉም የሚከባበርባት አዲሷ  አንዲት ሱዳን መፍጠርን  ያለመ ፍልስፍና ነበራቸው፡፡  እ.ኤ.አ በ2005  በመንግስትና በአማጺያኑ  መካከል  የተካሄደውን የሰላም ስምምነትን ተከትሎ ፤  ለ3 ሳምንታት ብቻ   የሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው  አገልግለዋል፡፡  

ቀደም ብለው የተደረጉትና በ2005  መንግስትና አማጺያኑ ያካሄዱት ስምምነቶች  የመሪዎች ሚስጥር  ብቻ  ሆነው  መቅረት የለባቸውም  ፤ ህዝብ ሊያውቃቸውና የራሱ  ሊያደርጋቸው ይገባል  በሚል ንግግር አድርገው ነበር፡፡

ጆንጋራንግ በዚሁ ንግግራቸው ፤” ሱዳን አረባዊ ብቻ አይደለችም ፤ ሱዳን የጥቁር አፍሪካዊያንም  ሀገር ብቻ አይገልጻትም…የእስላማዊ ሀገር ወይም የክርስቲያን አገር ብቻ ብያኔ የሚሰጣትም  የአንድ ወገን አገር አድርጎ መውስድ ተገቢ አይደለችም ” ብለው ነበር፤  ”  ዜጎች  የሁሉንም  የሱዳን ባህሎች አቅፈው እንደራሳቸው መገለጫ  አድርገው ሊወስዷቸው ይገባል” ብለዋል፡፡  እያንዳንዷ የሱዳን የባህል ቅንጣት  የሱዳውያን የወል ባህል መሆኗን አና ሱዳናውያንን የሚገልጽ የላቀና የሚጋሩት ከፍ  ብሎ  በአንድነት  የሚያስተሳስራቸው “ሱዳናዊ  ” መሆናቸውን ነበር የተናገሩት፡፡ አረባዊነት የባህሌ አካል ነው ፡፡ 

ክርስቲያን እምነት ቢኖረኝም እስልምናም ሱዳንን የሰራት የባሕሌ አካል  ነው ፡፡ ሱዳን  ልሙጥ አይደለችም ያሉት ጆን ጋራንግ ፤ አገሪቱን ያዋቀሯት  ልዩ ልዩ ምሶሶዎች ፣ እምነቶችና  የብሄረሰቦቿ  ባህሎች  የሱዳን የጋራ ሀብቶችና ባህሎች በመሆናቸው  እንደ ሱዳናዊ የሁላችንም ናቸው የሚል “ሱዳኒዝም “ፍልስፍና ይከተሉ ነበር፡፡ እኚህ ታላቅ የሱዳንና የአፍሪካ መሪ ያቀነቅኑ የነበረውን “ሱዳኒዝም”ን በአግባቡ ለመረመረ የሀገሬ ሰው  ብዙ ይማርበታል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም ቅርስ ተብለው የተመዘገቡ በርካታ ቅርሶች አሉ፡፡ የክርስትና ወይም የእስልምና ኃይማኖት አሻራዎች ያረፈባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የዓለምና ብሄራዊ  ባህላዊ፣ተፈጥሯዊ፣ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ቅርሶች ያሏት ሀገር ናት፡፡ ከላሊበላ እስከ ሀረር፤ ከጎንደር እስከ ኮንሶ፤ከቤንሻንጉል ጉሙዝ እስከ  ሱማሌ ፤ ከጋምቤላ እስከ አክሱም እንዲሁም በመላ ሀገራችን የሚገኙ ቅርሶችንን የጥንታውያነ ኢትዮጵያውያን አሻራዎች ገዝፈው የሚታዩባቸው ብርቅዬ   ሀብቶቻችን ናቸው፡፡ 

ከቅርሶቹ ውስጥ ተሸጉጠው ያሉ ጥንታዊ የምህድስና ጥበቦች፣ ሳይንስ፣ቴክኖሎጂና በርካታ አገር በቀል እውቀቶች  መገኛ ናቸው፡፡  ቅርሶቻችን ከእምነት አሻራቸው  በላይ የተገነቡ የላቀ እሴቶቻችን  ማሳያ ናቸው፡፡ የአንድ እምነት ተከታዮች የሚቆረቆሩለት ሌለው እንደ ባይተዋር የሚያዩት አይደለም፡፡

የሀገራችን  እስልምና እምነት  ተከታዮች በመስቀል አደባባይ ባካሄዱት የአፍጥር ፕሮግራም ብሎም የኢድ አከባበር ስነስርአት  ላይ ያካሄዷቸው የጋራ ስግደት ውስጥ  የእስልምና ሀይማኖታዊ ሥነስርአት የመከወን ብቻ አልነበሩም ፡፡ ” ግድቡ  የኔ  ነው !” በማለት ድምጻቸውን በአንድነት ያሰሙበት ታሪካዊ  ሁነት እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ታሪካዊ ሁነት ያስተባበሩ የእምነቱ መሪዎች ወይም ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በአርአያነታቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

እስሌማን አባይ በፌስቡክ ገጹ እንዲህ አለ ” እኛ ፣ እንዲህ ነበርን ፤  እንዲህም ፣ አደረግን ፡፡  ስለዓባይ አገራዊ ድምጻችንን  በዒድ ሶላት ላይ እንዲስተጋባ ከአጋሮቼ ጋር ስንዘጋጅበት  የነበረው ፕሮጀክት በድምቀትና በስኬት ተከናወነ፡፡  ጋዜጠኛ ዘካርያ መሀመድ እና መሀመድ ካሳ አሊ ፕሮጀክቱ ራሶች  እንደነበሩ ልብ እንድትሉልኝ ፡፡ አልሐምዱሊላህ የዓባይ ልጅ ”

አዎ  የማህበረሰብ መሪዎች ሀገርንና የህዝብን መንፈስ በቀና መልኩ የመምራት ኃላፊነታቸውን እንዲህ ሲወጡ ያስደስታል፡፡

ይህ  አዎንታዊ ድምጽ በጅማም የተስተጋባ መሆኑንና ግብጽ ድረስ የተሰማ የአንድነት ድምጽ መሆኑን እስሌማን  አጋርቶናል፡፡ ከልዩነት ይልቅ እንዲህ አንድነትን የሚያበረቱ ዜናዎች  እንዲበዙልን ብዬ እኔም ይህን ከተብኩላችሁ፡፡

የሆነው ሁሉ የኢትዮጵያውያንን የአንድነት መልክ የሚሳይ  ነው፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top