Connect with us

ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በሰዎች የመነገድ ወንጀል የፈጸመው ኪዳኔ ዘካሪያስ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ
ፌ/ጠ/ዐቃቤ ህግ

ነፃ ሃሳብ

ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በትግራይ ክልል በአክሱም ከተማ በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እና የተከናወኑ የወንጀል ምርመራ ተግበራትን አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ላለፉት ሁለት ወራት ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከተውጣጡ አባላት በተቋቋመ የምርመራ ቡድን አማካኝነት ህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) በሀገሪቱ ላይ ያወጀውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በህዳር ወር 2013 ዓ.ም የተፈጸሙትን ወንጀሎች የመመርመር ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም በከተማዋ ውስጥ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ወታደሮች ተፈጽመዋል በሚል ለቀረበ ጥቆማ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የምርመራ ቡድኑ ወንጀል ተፈጽሟላ በተባለበት ስፍራ በአካል በመገኘት የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ስለመኖር ወይም አለመኖራቸው፤ እንዲሁም ተፈጽመውም እንደሆነ የወንጀል ፈጻሚዎችን ማንነት ለመለየት የሚያስችል የወንጀል ምርመራ እያካሄደ  ይገኛል፡፡

በከተማው ሞቱ ስለተባሉ ሰዎች በተደረገ የማጣራት ስራም በጦርነቱ መካከል ህገ-ወጡን ቡድን ኢላማ ያደረገ መድፍ ተተኩሶ ኢላማውን በመሳቱ እና በከተማዋ የሰዎች መኖሪያ ቤት እና ዩኒቨርስቲ አካባቢ በመውደቁ በመኖሪያ ስፍራው 4 እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው አካባቢ አንድ በድምሩ አምስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን በተጨማሪም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስፈጸም ሂደት ውስጥ ከሰዓት እላፊ ጋር በተገናኘ ሕግ በማስከበር ስራ ላይ ካሉ የፖሊስ አባላት ጋር በተፈጠረ እሰጥአገባ ሌላ ተጨማሪ አንድ ሰው በአጠቃላይ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡

በሌላ በኩል የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ከህዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሌላ ግዳጅ ከተማውን ለቆ እስከወጣበት እለት ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በአክሱም ከተማ ቆይቷል፡፡ ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም የመከላከያ ሰራዊቱ ለተጨማሪ ግዳጅ ከተማዋን ለቆ ሲወጣ የህወሀት ካድሬዎች ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ የኤርትራ ሰራዊት በሁለት ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ተራራማ ቦታ ላይ መጥቶ ሰፍሯል። የኤርትራ ሰራዊት ለመዋጋት ሳይሆን እጅ ለመስጠት ይፈልጋል በሚል አስወርተው አዴት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ያሉ የሕወሃት ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት በከተማዋ ውስጥ ካሉት 1500 የሚጠጉ የተኩስ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ጋር በመሆን ወደ አክሱም ከተማ ለመዋጋት ገብተዋል፡፡

በበረሀ የነበረው የቀድሞ የአክሱም ከተማ ከንቲባም ደብዳቤ ጽፎ ከሰሜን እዝ ላይ የተሰረቁትን ጨምሮ በአምስት ቦታዎች ላይ የተከማቹትን የጦር መሳሪያዎች በአክሱም ከተማ ከህዳር 01-09/2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ህወሃት የአንድ ቀን የመሳሪያ ተኩስ ስልጠና በመስጠት ለህገ-ወጥ ተግባር ላሰናዳቸው 1,500 ወጣቶች እንዲከፋፈል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህ ስለመሆኑ የምርመራ ቡድኑ የጦር መሳሪያ ከደረሳቸው እና ካልደረሳቸው ወጣቶች እንዲሁም ከልዩ ኃይል አባላት የምስክርነት ቃል ማረጋገጥ ችሏል፡፡ መሳሪያዎቹ በአምስት ቦታ የተከማቹ ሲሆኑ በአንዱ ማከማቻ ብቻ 400 መሳሪያ ወጪ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ አካላት ተባብረው ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ቀኑ 8 ሰዓት በቆየ ውጊያ ጥቃት ሲያደርሱ ውለው አጋዥ ሀይል በቦታው ሲደርስ ወደ ከተማዋ ሸሽተው መግባታቸውም በምርመራው ተረጋግጧል፡፡

በዚህም ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት በተደረገ ጥረት የ95 ሰዎችን የምስክርነት ቃል ለመቀበል የተቻለ ሲሆን በምርመራ ሂደቱም በጦርነቱ የ93 ሰዎች ሕይወት ማለፉ እና ሟቾቹም ወታደራዊ የደንብ ልብስ ባይለብሱም በአብዛኛው በጦርነቱ የተሳተፉ ሰዎች ስለመሆናቸውም በምርመራው የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡

የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን በተመለከለተ በአጠቃላይ 116 ተበዳዮች ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተከናወነ ምርመራም በወንጀሉ የተሳተፉ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተለይተው የፌደራል ፖሊስ አባላት ጉዳይ በክልሉ ዐቃቤ ሕግ እንዲመረመር እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወታደራዊ ግዳጅ ላይ እያሉ የፈጸሙት ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩ በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዲታይ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡

የአስገድዶ መድፈር ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎችን በቀረበው አቤቱታ ልክ ለመለየት ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ህወሃት አስቀድሞ በከባድ ወንጀል የተከሰሱ እና የተፈረደባቸው ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ እስረኞችን ከእስር ለቆ እና ለክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ  የኤርትራ ወታደሮችን ዩኒፎርም በማዘጋጀት እንዲሁም የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በሰነዘረበት ጊዜ ከገደላቸው እና ከያዛቸው የሰራዊቱ አባላት ላይ ወታደራዊ የደንብ ልብስ አውልቆ እና አስወልቆ ለራሱ ወታደሮች በማልበስ ይጠቀም የነበረ በመሆኑ የወንጀል ፈጻሚዎችን ማንነት የመለየት ስራውን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

በግድያውም ሆነ በአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ዙሪያ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በምርመራ ሊለዩ የሚገባቸው ቀሪ ጉዳዮች ቢኖሩም የድርጊቱን አፈጻጸም እና የፈጻሚዎችን ማንነት ለማረጋገጥ የሚረዱ የሰው፣ የሰነድ እና የገላጭ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል፡፡ አሁንም ምርመራው የቀጠለ ሲሆን ምስክሮች በመልክ የጠቆሟቸውን ተጠርጣሪዎች የመለየት ስራ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን በቤተክርስቲያን አካባቢም የእምነት አባቶች እና የቀብር አስፈጻሚዎችን  የምስክርነት ቃል የመቀበል እንዲሁም ከሆስፒታሎች የህክምና ማስረጃ የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም ከፌዴራል እና ክልል ፍትህ እና ጸጥታ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ጊዜ ይውስድ ይሆን እንጂ በሁሉም ወንጀሎች የተሳተፉ ሰዎች ሁሉ በፍትህ አደባባይ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በትጋት የሚሰራ መሆኑን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይገልጻል፡፡(የፌ/ጠ/ዐቃቤ ህግ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top