Connect with us

በጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በተሸለሙ ሰሞን ያረፉት አንጋፋው ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ

በጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በተሸለሙ ሰሞን ያረፉት አንጋፋው ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ
ሠርፀ ፍሬስብሐት

ነፃ ሃሳብ

በጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በተሸለሙ ሰሞን ያረፉት አንጋፋው ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ

በጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በተሸለሙ ሰሞን ያረፉት አንጋፋው ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ

ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ፤ ከአባታቸው ከአቶ ጽጌ ጉልች እና ከእናታቸው ከ ወ/ሮ አበበች መርሻ፣ በሸዋ ክፍለ ሀገር በመርኀ ቤቴ አውራጃ በ1927 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ፣ ከአጎታቸው መልአከ አርያም አለቃ ይትባረክ መርሻ ዘንድ፣ በደብረ ጽጌ የቅኔ ጉባኤ ቤት፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በተለይም የቅኔ ትምህርትን ተምረዋል፡፡

አጎታቸው ለሥራ ወደ አዲስ አበባ ሲዛወሩ፣ አብረው በመምጣት ዘመናዊ የቀለም ትምህርታቸውን በኮከበ ጽባህ እና ተስፋ ኮከብ ትምህት ቤት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህታቸውን በትጋት ጨርሰዋል፡፡

በነበራቸው ትልቅ የሥነ ጥበብ ፍቅር ምክንያት፣ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ በኾነው፣ [በአሁኑ አጠራሩ] አለ የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ በማዕረግ ተመርቀዋል፡፡

በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ፣ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ  ትምህርት ቤቱን እየጎበኙ በነበረበት ወቅት፣ በድንገት ባቀረቡት ታላቅ ቅኔ ንጉሠ ነገሥቱን ማስደነቅ ቻሉ። ንጉሠ ነገሥቱም፣ የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ስላመቻቹላቸው፣ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አውሮፓ ፖላንድ ሀገር በመሔድ በዋርሶ የሥነጥበብ ዩኒቨርሲቲ ለ7 አመታት ተምረው የማስተርስ ዲግሪ ባለ ማዕረግ ኾነው ተመርቀዋል፡፡

ከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው በመመለስም፣ ከ1960 – 1962 ዓ.ም. በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ከአገለገሉ በኋላ፣ በ1963 ዓ.ም. ወደ ለንደን ሔደው ለ2 ዓመታት የሥነ ጥበብ ማስተማር ሥነ ዘዴን ተከታትለው ተመልሰዋል፡፡ [ሳይጠቀስ የማይታለፈው]፣ በዚያ ቆይታቸው፣ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጓደኞቻቸው በተሻለ የንጉሣዊ ሰላምታ ሥርዓትን በልዩ ኹኔታ በማቅረባቸው ከእንግለዝ ንግሥት እጅ ልዩ ሽልማትን አግኝተዋል፡፡

ከ1964 እስከ 1968 ዓ.ም. በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከ”UNESCO” ጋር በመተባበር ከመጀመሪያዎ የዩኒቨርሲቲው መሥራቾች አንዱ ኾነው ዛሬ ላለበት ደረጃ እንዲደርስ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡ በዚሁ ዩኒቨርሲቲም በሌክቸረርነት ለ5 ዓመታት አገልግለዋል፡፡

በወቅቱ በነበረው የዕድገት በሕብረት የእናት አገር ጥሪ ላይ በሞያቸው በመሳተፍ ለሀገራቸው እንዲሁም ለወገናቸው አዝማች በመኾን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የ2 ዓመታት ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ለዚህም ከወታደራዊው መንግሥት ሸልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ፥ በትምህርት ሚኒስቴር መደበኛ ሠራተኛ ኾነው በአገሪቱ የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ላይ ሠርተዋል፡፡ በመቀጠልም፣ ወደ ባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀይረው በሥነ ጥበብ ዘርፍ በኃላፊነት ሠርተዋል፡፡

ከዚያም፥ እርሳቸው የመጀመሪያ የሥነ ጥበብ ትምህርታቸውን ወደ ተከታተሉበት፣ ለሀገሪቱም የመጀመሪያ በኾነው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት በመዘዋወር፣ በመምህርነት እና በሠዓሊነት ሙያቸው ለረጅም ዘመን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡

በሠዓሊነት ሙያ ዘመናቸው ብዙ የቅብ ሥራዎችን ያበረከቱ ሲኾን፣ ከእነዚህም መካከል በኹነኝነት፤

*”የጉልበት ብዝበዛ”

*”የቀረችው ጨርቅ” እና

*”ብሩኅ ተስፋ” ተጠቃሽ ሥራዎቻቸው ነበሩ።  እነዚህ የሥዕል ሥራዎች፤ በግለሰቦች እና በብሔራዊ ሙዚየም ይገኛሉ፡፡

በሀገር ውስጥ በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት፣ በሒልተን ሆቴል እና በአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴ የሥዕል ኤግዚቢሽን ያቀረቡ ሲኾን፣ በውጭ ሀገራት፥ በፖላንድና በቼኮዝላቫኪያ በቡድን ከሌሎች ሠዓልያን ጋር ኤግዚቢሽን ዐሳይተዋል፡፡

በሠዓሊነት ዘመናቸው “የኢምፕሬሽኒዝም” እና “የሪያሊዝምን” ቲክኒኮች ያደንቁ ነበር፡፡ በአሠራራቸው ላይም “ኢምፕሬሽኒዝምን” ዘይቤን ያዘወትሩ ነበር፡፡

ከመደበኛ ሥራቸው ውጪ፣ በሀገሪቷ ላይ በአንድ ወቅት በደረሰው ድርቅ ምክንያት በእርዳታ ማስታባበርያ ውስጥ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ እንዲያገኙ በመሳተፍ፣ የሀገር ሽማግሌ እና የቀበሌ ሊቀመንበር በመኾን በትጋት ወገኖቻቸውን አገልግለዋል። እንዲሁም በወረዳው ባሉ የልማት ሥራዎች በሙሉ ተሳትፈዋል፡፡

የቅዱስ እግዚአብሔር አብ አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ሲመሠረት ከሕንጻ ኮሚቴው ጋር በመኾን በሙያቸው ተሳትፈዋል፡፡ ኮሚቴው ለዚህ ተሳትፎዋቸው የምስጋና ምስክር ወረቀት አበርክቶላቸዋል፡፡

ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ ከጡረታ በኋላ በካበተ ሙያቸው በተለያዩ መስኮች ያገለገሉ ሲኾን፣ በዋናነት በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የፔዳጎጂ ክፍል ዋና ኃላፊ ኾነው ለዓመታት አገልግለዋል፡፡

***ለዘመናት በሥነ ጥበብ ሙያቸው ላበረከቱት አገልግሎት ከጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፥

   “ኢትዮጵያን ስላገለገላችሁ፣ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች!” በሚል ሚያዚያ  1 ቀን 2013 ዓ.ም. በተዘጋጀ መርኀ ግብር ላይ የክብር ሜዳልያ ተሸላሚ ነበሩ።

ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ በትዳር ከወ/ሮ ፀሐይ ጋረደው ጋር ለ47 ዓመታት በሥጋ ወደሙ ተወስነው እስከ ኅልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ኖረዋል፡፡ ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ በሕይወት ዘመናቸው 10 ልጆችን 15 የልጅ ልጆችን እንዲሁም 4 የልጅ ልጅ ልጆች አፍርተዋል፡፡ ሠዓሊ ኃይሉ ጽጌ ባደረባቸው ኅመም በተወለዱ በ86 ዓመታቸው ሚያዝያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

            በቀብራቸው ዕለት ከተነበበ የሕይወት ታሪካቸው   የተወሰደ።

(ምንጭ፡-ሠርፀ ፍሬስብሐት)

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top