Connect with us

የግብጽ መልዕክተኛ ምልክቱ ኢትዮጵያን መጥላቱ!

የግብጽ መልዕክተኛ ምልክቱ ኢትዮጵያን መጥላቱ!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የግብጽ መልዕክተኛ ምልክቱ ኢትዮጵያን መጥላቱ!

የግብጽ መልዕክተኛ ምልክቱ ኢትዮጵያን መጥላቱ!

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ ድሬቲዩብ)

በግብጽ ተላላኪነት የሚታማው በዛ፤ ግብጽ የምትልከውን እናውቀዋለን፤ ምናችንን እንደምትጠላው እና ምን አይነት ተላላኪ እንደምትመርጥ የምናውቅ ህዝቦች ነን፡፡ ሰሞኑን “ለምን አማራ በማንነቱ ይገደላል?” የሚለውን የአማራ ክልል የተለያዩ ሰልፎች ወደ አንድ ፓርቲ ለመውሰድና ከአብን ጋር ለመለጠፍ የተደረገው ጥረት ከገዳዩ እኩል በንጹሁ ሟች የመጨከን ያህል ነው፡፡

ሰው በማንነቱ ሞቷል፣ ከተማ ወድሞ ዜጎች ሜዳ ላይ ወድቀዋል፡፡ መተከል ወለጋ አጣዬ የሆነውን ነገር ላሰበ ዜጋ ብሔር ሳይገድበው ለምን ማለት ይጠበቅበታል፡፡ በአማራ ክልል ከተሞች የተካሄዱ ሰልፎች ሌላ ዓላማ የላቸውም፡፡ ዓላማቸው ሞት ይቁም የሚል ነው፡፡ ሰልፈኞቹ ብሶትና ፍትህ ማጣት አደባባይ አስወጣቸው እንጂ አብንነት ወይም ብልጽግናነት እንዳልሆነ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

ስም ሲወጣለት የኖረ ቡድን ስም አውጪ ለመሆን ሲበቃ ቢሳሳት ምንም ላይሆን ይችል ይሆናል፤ ትናንት የኦሮሞ የፍትህ ጥያቄ ሁሉ ኦነግነት ነበር ስሙ፡፡ ወያኔ ሁሉንም የኦሮሞ የመብት ጥያቄ ኦነግ ከመሆን ጋር አስተሳስራ ስታሳድደው ኖራለች፡፡ መጨረሻዋን አሁን ለማንም የምንናገረው አይደለም፡፡

የኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች አማራ ምንም አይነት የፍትህ ጥያቄ ሲያነሳ ነፍጠኛ ብሎ ለማሸማቀቅና ስም ሰጥቶ አንገት ለማስደፋት ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ስም ወጥቶለት ለኖረ አንጃ ስም ማውጣት የተረኝነት ጉዳይ ካልመሰለው በቀር ከአለፈው ስህተት መማር መልካም ነበር፡፡

“ለምን አማራ ይሞታል?” የሚለውን ጥያቄ ከግብጽ ተላላኪነት ጋር ማገናኘቱ ያስተዛዝባል፡፡ ግብጽ አንድም ተላላኪ ማግኘት የሚቸግራት አማራ ፖለቲካ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ አማራ በማንነቱ የሚደርስበት ጥቃት ስደት ሞትና መከራ ግብጽ የሸረበችውና አማራን ካንበረከኩኝ የአባይ ጉዳይ ጣጣው ያልቃል የሚል ቅዠት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡

ግብጽ አክራሪ ኢትዮጵያዊነት ጠላቷ ነው፡፡ የመቶ አመት ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያ ማየት የምትፈልግ የፈረኦን ሀገር ናት፡፡ ለዚህ አክራሪ የኦነግ የፖለቲካ መንፈስ ምቹ ሜዳዋ ነው፡፡ ብሔራዊ ህብረትን፣ ታሪካዊ ክብርን፣ እንደ አድዋ ያሉ አኩሪ የአባቶቻችንን ጀግንነት የሚያኮስስ ፓርቲና ቡድን ትፈልጋለች፡፡

በግብጽ ተላላኪነት የምንከሰው ቡድን የለም፤ ራሱ መልእከተኛ ነኝ ያላችሁኝን አደርጋለሁ ብሎ በአደባባይ ሲምል ያየነው፣ ቃል ገብቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጫካ ሲገባ የተመለከትነው ቡድን አለ፡፡ ከግብጽ ማን እንደሚወግንና ግብጽ ምን አይነት ተላላኪ እንደምትፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ በአግባቡ የሚረዳ ነው፡፡

የሚበጀን ግን ጥፋትና እልቂትን አብረን በመኮነን የጋራ ሰላማዊ ሀገር እንዲኖረን ማድረግ ነው፡፡ ንጹሃንን የሚፈጅ የቱም ቡድን አላማው ምንም ቢሆን ሁላችንንም የሚያከስር እንደሆነ መተማመን አለብን፡፡ ለምን ሰው ይሞታል ለሚለው ስም እያወጣን ሩቅ አንሄድም፡፡ መገዳደል ስም አያስፈልገውም፡፡ ገዳይ ነውረኛና የሀገርም የፍጥረትም ጠላት ነው፡፡

በተረፈ አትግደሉኝ የሚለውን ግብጽ ልካህ ነው ብሎ መተርጎሙ ተልኬያለሁ ብሎ ሃላፊነት መሸከሙን በአደባባይ የነገረን አካል ስላለ ትዝብት ውስጥ ይጥለናል፡፡ ከመተዛዘብ መተዛዘኑ ይጠቅመናልና ማንም ማንንም የማይገድልባት፤ ከየቱም ወገን ቢሆን ገዳይ የሚወገዝበትና የገዳይን ክፉ ሀሳብ የምንገድልበት ህብረት ቢኖረን እንደ ሰው በተረጋጋ ሀገር እንኖራለን፡፡ መጠፋፋት የማንም ድል አይደለም፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

To Top