አባይ በልኩ ተቋም ይሰፋለት ….
(እስክንድር ከበደ- ድሬቲዩብ)
“ናይል ሪቨር ሪሰርች ኢንስቲትዩት ” (የአባይ ወንዝ ምርምር ተቋም ) በግብጽ ብሔራዊ የውሀ ሀብት ምርምርና ጥናት ማአከል (National water Research Center -NWRC ) ከሚገኙ 12 የምርምርና ጥናት ተቋማት አንዱ ነው። ብሔራዊ የውሀ ሀብት ምርምርና ጥናት ማአከሉ በሀገሪቱ የውሀ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር ስር የሚገኝ ግዙፍ የዘርፉ የሙያ ክንፍ ነው።
ካይሮ 12 የውሀና የመስኖ የጥናትና ምርምር ተቋማት ያላት ሲሆን፤ ግዙፉ ማአከል ደግሞ የአባይ ጥናትና ምርምር ተቋም ይጠቀሳል።
የናይል ምርምር ተቋም እ.እ.ኤ በ1990 አጋማሽ የአሁኑን ስያሜ ቢሰጠውም ፤ለብዙ አመታት በተለያዩ ስያሜ ሲጠራ ቆይቷል። ይህ ወሳኝ ኢንስቲትዩቱ እ.ኤ.አ በ1992 መሰረታዊ እድገት ያሳየበትና እውቅና የተሰጠው ወቅት ነበር። ተቋሙ ለግብጽ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለውና ስለ ታላቁ የአባይ ወንዝ እንዲታወቅ የላቀ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
የተቋሙ ዋና የተግባር ምርምር በማድረግ ለግብጽ የውሀ ሀብቶች አስተዳደርና ልማት በከፍተኛ ደረጃ ለፖሊሲ አውጪዎች ድጋፍ የሚያደርግና የሚሰራ ነው።የተቋሙ ግብ የአባይ ወንዝንና የናስር ሀይቅን በዘላቂነትና በሳይንሳዊ ምክንያታዊ መንገድ መጠበቅና ማልማት እንደሆነ በተቋሙ ድረገጽ ተገልጿል።አላማዎቹ ደግሞ :
በባለሞያዎች፣በተመሳሳይ ተቋማትና በግብጽ የሚገኙ ባለድርሻ ድርጅቶች መካከል ወንዙን በተመለከተ ሳይንሳዊና ቴክኒካዊ መረጃዎችና እውቀቶችን መለዋወጥ ዘዴዎችን እንዲሻሻሉ የማድረግ አላማ አለው፡፡ ፍላጎት ላላቸው ድርጅቶች የተቀናጀ የትብብር ጥናትና ምርምር ማቅረብ ፣የምክር አገልግሎቶች፣የአቅም ግንባታ እና የመስክ ምርመራዎች ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ተቋሙ ወንዙን በተመለከተ በሔራዊ ፕሮጀክቶች ዙሪያ የምህንድስና ስነህይወታዊ የማስተባበርና የማካሄድ እንደ አላማ የያዘ ነው፡፡
የጥናትና ምርምሩ አራት ዋና ዋና መምሪያዎች አሉት፡፡ 1) የወንዝ ምህንድስና መምሪያ 2) የውሃ ጥራት መምሪያ 3) ሀይድሮሊክ ጥበቃ መምሪያ 4) የናስር ሐይቅ መምሪያ ናቸው፡፡ ተቋሙ ሦስት ዘመናዊ ላብራቶሪዎችና ፣ ዘመናዊ የዳታ መሰብሰቢያና ማሰራጫ ቴክኖሎጂና ዘመናዊ የተደራጀ የመረጃ ቋት ማአከል ወዘተ ይዟል፡፡
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ የጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ያስፈልጋልታል ሲባል እንደዋዛ የሚወስዱት ይኖራሉ። አንድ ሀገር ተቋም ስላቋቋመች ሳይሆን ተቋማቱን እንዴት እንደምትጠቀምባቸው ማሰቡ ይጠቅማል። አስፈላጊነቱን ከሌሎች ልምድ መውሰድ ያስፈልጋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክር ቤቶች እየተባሉ በፌደራልና በክልል ደረጃ አደረጃጀት እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ምክር ቤቶች የፖለቲካ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠሉ የትርፍ ጊዜ ተቋማት ይመስላሉ። ለግድቡ ስራ የፋይናንስ ድጋፍ የቅስቀሳ ምክር ቤቶች ከመሆን ያለፈ ሚና አይኖራቸውም ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ አጠቃላይ የጥቁር አባይ ተፋሰስ ሳይንሳዊና ቴክኒካዊ የትምህርት፣የስልጠና ምርምር ስራዎችን በባለቤትነት የሚያስተባብር ግዙፍ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ድንበር ተሸጋሪ ወንዞችንና የተለያዩ የውሀ ሀብቶቻችን የእውቀትና የመረጃ ዘላቂ ተቋማትን መፍጠር ይጠይቃል። አጠቃላይ በተፋሰሱ ዙሪያ ምርምሮችና ጥናቶች የሚያደርግና በውሀ ሀብታችን ዙሪያ የእውቀት ማአከል ያስፈልገናል ። መሪዎችና የቴክኒክ ኃላፊዎች በተለዋወጡ ቁጥር “በግምገማ” ስራን ለመለየት መሞከር ዋጋ ያስከፍላል። የማይናወጥ ተቋማዊ አሰራር ማማተር ይጠቅማል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ስለህዳሴ ግድቡ ለማጥናት 8 ወራት ፈጀብን በማለት የመንግስታቸውን ጥረት ለማሳየት ባደረጉት ማብራሪያ ውስጥ ሀገሬን አሰብኳት-ለግዙፍ ፕሮጀክትና ለዘላቂው ታላቅ ወንዛችን የሚመጥኑ ተቋማት አለመኖራቸውን ነው።
አሁን ትኩረታችን የግድቡ ሁለተኛው ሙሌት ዙሪያ ነው፡፡ ከወዲሁ የግድቡ አስተዳደርና አመራር ብሎም በልኩ የተሰፋ ግዙፍ ሳይንሳዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች በጥልቀት የሚሰራ ተቋም ያሸናል፡፡ ህዳሴ ግድብ አንዱ ትልቅ አደረጃጀት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ፤ በግድቡ ውሃ የሚፈጠረው ትልቅ ሐይቅ በራሱ ግዙፍ የቤትስራ መጠየቁ አይቀርም፡፡
ግብጽና ሱዳን የግድቡ አስገዳጅ ስምምነት ይፈረም የሚሉት ግድቡን ብቻ ሳይሆን መላ ወንዙ ላይ ኢትዮጵያ የምትሰራውን በቅርበት ለመመርመርና ለማሰናከል የሚረዳቸውን ክፍተት ለመፍጠር ነው፡፡ ይህ ስምምነት አሁን በጥሩ ሁኔታ የተሰራው ግድብ ለተፈለገው አገልግሎት በሙሉ አቅሙ እንዳይውል የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡