በይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን በህግና ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው የሚገዙበት ረቂቅ መመሪያ ውይይት ተካሄደበት
የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን በህግና ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው የሚገዙበት ረቂቅ መመሪያ ዙሪያ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፣ በጠቅላይ አቃቢ ህግ እና በባለድርሻ አካለት መካከል ዛሬ በሳፋየር አዲስ ሆቴል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የበይነመረብ መገናኛ ብዙኃን ረቂቅ መመሪያና የጥቆማና ቅሬታ አቀራረብ ረቂቅ መመሪያ ቀርቧል፡፡ የውይይት መድረኩ ብዙ የዘርፉ ተዋናዮች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን በገለልተኛ አካል ለተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ግብዓት የሚሆን ሰፊ አስተያየት ለመሰብሰብ ያስቻለ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግራቸው ላይ እንዳብራሩት የበይ-ነመረብ ሚዲያው በተመዝጋቢነት ፍቃድ አጊኝቶ በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ቢሰራ ህጋዊነት የሚያጎናፅፋቸው እድሎችን መጠቀም ያስችለዋል፡፡
እንደማሳያም በቅርቡ የፀደቀው የሚዲያ ፖሊሲ የመገናኛ ብዙኃን ዘረፉ የኢንቨስትመንት ጥቅማ ጥቅም እንዲያገኝና ከውጭ የሚገቡ የሚዲያ የፓሮዳክሽን እቃዎች ላይም የቀረጥ ማስተካከያ እንዲደረግለት ጭምር እንደሚፈቅድ አብራርተዋል፡፡ “ግዴታን መወጣት መብትን በይተኛውም ልክ ማግኘት ያስችላል፡፡ ወደ ህጋዊነት ስትመጡ ባለሥልጣኑ እናንተን ለመደገፍ ሙሉ ትኩረት ይሰጣል” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በፀደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/13 መሰረት የመገናኛ ብዙኃን የህዝብን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ተነፃፃሪ መብቶችና ጥቅሞችን ባከበረ መልኩ በኃላፊነት መንቀሳቀሳቸውን ማረጋገጥና በህግ መሰረት እንዲሰሩ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍና ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ባረጋገጠ መልኩ በብሮድካስት አገልግሎት እና በበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ ፕሮግራሞችና ዜናዎች የሚመሩበትን ዝርዝር የስነ-ምግባር መመሪያ እንደሚያወጣ ይገልፃል፡፡ የእርስ በርስ ቁጥጥር ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን አደረጃጀቶችንም አስተያየት እንዲሰጡበትና አተገባበሩም ላይ እንዲሳተፉ እንደሚያደርግ ይደነግጋል፡፡
በዛሬዉ እለት እየተካሄደ ባለዉ የባለድርሻ አካላት የዉይይት መድረክም የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን እና የመገናኛ ብዙኃን ጥቆማና ቅሬታ አቀራረብ ረቂቅ መመሪያዎች ቀርበዉ ጠቃሚ ግብአት እየተሰበሰበባቸው ሲሆን በቀጣይ መመሪያዎቹን ለቦርድ አቅርቦ የሚያፀድቅ ይሆናል፡፡
የኢትዬጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ወደፊት በግልጽ በሚያወጣዉ ፕሮገራም መሰረት የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ምዝገባ፤ ፈቃድና እዉቅና የሚከናወን ይሆናል፡፡(የኢት መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን)