Connect with us

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር “ካጠፋን ቆንጥጡን” ብለዋል፤እያጠፋችኹ ያላችኹት ግን አርባ ግርፊያ የሚያንስበት ነው

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር "ካጠፋን ቆንጥጡን" ብለዋል፤ እያጠፋችኹ ያላችኹት ግን አርባ ግርፊያ የሚያንስበት ነው
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር “ካጠፋን ቆንጥጡን” ብለዋል፤እያጠፋችኹ ያላችኹት ግን አርባ ግርፊያ የሚያንስበት ነው

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር “ካጠፋን ቆንጥጡን” ብለዋል፤እያጠፋችኹ ያላችኹት ግን አርባ ግርፊያ የሚያንስበት ነው

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተስማሙ እንጂ ብልጽግናን ደፍሬ የጻፍኩት አይደለም፡፡ መሪው ካጠፋን ቆንጥጡን ብለዋል፡፡ እርግጥ የብልጽግና ጥፋት ከቁንጥጫ አልፏል፡፡ በርበሬ በሚያሳጥን ደረጃ የደረሰ ሆኗል፡፡ አርባ ግርፍያም ሲያንሰው ነው፡፡

አንድ መንግስት አንድ ከተማ ዓይኑ እያየ በታጣቂ ስትወድምና ስትቃጠል ምን ሰርቼ ውዬ አደርኩ ሊል ነው፡፡ የመንግስት ስራ ከተማን ከመቃጠል መታደግ እንጂ ከተቃጠለች ከተማ አመድ መጥረግ አይደለም፡፡ 

የኾነውን ስናስበው እጅግ አስፈሪ ነው፡፡ ዓለምን ድረሱልን ብለን ልንጠራ የሚገባን ፈተና ውስጥ ገብተናል፡፡ በገዳዩ ስምና ማንነት እየተከራከርን በአራቱም አቅጣጫ በቀን ሶስት ጊዜ ትበላለህ ተብሎ ቃል የተገባለት ህዝብ በቀን ብዙ ጊዜ እየተገደለ ነው፡፡

መንግስትነት ክብሩ የት ላይ ነው? የማይፈራ መንግስት እራሱን ብቻ አይደለም የሚያዋርደው ሀገር ያፈርሳል፡፡ እያንዳንዱ ደሃ እላዩ ላይ ቤቱ ሲፈርስ እኮ ሀገር ፈርሳለች፡፡ ቀባሪ ህዝብ ሆነናል፡፡ ተራና የእለት ኑሮን ተከልክለን እየተሰቃየን ነው፡፡ እየሞትን ያለነው ምክንያቱን ሳናውቅ ነው፡፡

ሰዎች በማንነታቸው ይሞታሉ፡፡ ገዳይ ተገዳይ ሆነው ሳለ እንኳን ስሙ ግጭት ይባላል፡፡ አማራ በወለጋ፣ በጉራፈርዳ፣ በመተከል፣ በአጣዬ ሟች ነው፡፡ በጠብ አይደለም የሞተው በተኛበት እየታረደ፣ በቤቱ እየተቃጠለ ነው፡፡ 

እንዲህ ያሉ ገድሎ የመፎከር ዘመቻዎች አድገው አድገው በአንድ ሀገር ውስጥ ብዙ መንግስት ተፈጥሯል፡፡ መንግስት ራሱ እያስገደለን ነው የሚለው የዜጎች ቁጥር አሁን ጨምሯል፡፡ መንግስቴ አስገደለኝ የሚል ሚሊዮን ህዝብ እንዴት ነው የሚበለጽገው?

ይኸ ሁሉ ቀውስ ሲፈጠር አመራሩ ምን ይሰራ ነበር? ከመንግስት ወገን ማን ነው ተጠያቂ? ከተማ ተቃጥሎ መንግስት ነኝ ብሎ ዝም ማለትስ ይቻላል ወይ? እስኪበለጽግ ሰላም የተነፈገው ህዝብ ሞቶ ካለቀ ማን ነው በብልጽግናው የሚያልፍለት?

ከቁንጥጫ በላይ ቅጣት የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡ መንግስት ሃላፊነቱን አልተወጣም፡፡ በተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ያደረጋቸው ሹመኞች የሉም፡፡ በየቀኑ በመንግስት በኩል አደራድሮ ቃል አሽሞንሙኖ መግለጫ አንጋግቶ በአንፈርስም አዝማቹ አጅቦ በየቀኑ ስንፈርስ ዝምታው አርባ ያስገርፍ ነበር የሚያስብለንም ለዚህ ነው፡፡

ትናንት ዶክተር አብይን የደገፈ ወጣት ዛሬ እያስገደሉኝ ያለው እሳቸው ናቸው ብሎ መጠራጠር ጀምሯል፡፡ ሰው በገዳዩ እንዴት ይበለጽጋል? መንግስት ገዳይ አለመሆኑን ለማሳየት በሟች ሞት ከመግለጫ ያለፈ ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግ አለበት፡፡

ኮስታራና መራራ መንግስት መኾን ያስፈልጋል፡፡ ማንም በአንድ ሀገር ሁለት መንግስት መሆን የለበትም፤ የተደራጀ ታጣቂው ሃይል ያሻውን እያደረገ ሀገር ሰላም አጥታ ስለ ብልጽግናና አንድነት ማውራት ቧልት ነው፡፡ ያጠፋንን የብሔር ፖለቲካ ስሙን ማጥፋት ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ በመንግስት ውስጥ የተሰገሰገውን ስውር የጥፋት ቡድን አጋልጦ ማውጣት፣ እርምጃ መውሰድና አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል፡፡ ሀገር ከሁሉም ትበልጣለች ካልን ለሁሉም እኩል ፍትሕ ማስፈንና ደሃ ሰላም ውሎ እንዲያድር ኮስተር ማለት ያስፈልጋል፡፡ በፈገግታ ሞት አይሸነፍም፡፡ በመግለጫ ሀገር አይረጋም፡፡ በምኞት የትም አይደረስም፡፡ 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top