Connect with us

ታጣቂዎች እንዴት ከመንግሥት በላይ ሆኑ?

ታጣቂዎች እንዴት ከመንግሥት በላይ ሆኑ?
በኩር ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ዕትም

ነፃ ሃሳብ

ታጣቂዎች እንዴት ከመንግሥት በላይ ሆኑ?

ታጣቂዎች እንዴት ከመንግሥት በላይ ሆኑ?

ታጣቂ ቡድኖች እና የመንግሥት እርምጃ

ኢህአዴግ መቶ ከመቶ ምርጫዉን ባሸነፈበት ማግስት ህዝባዊ አመፆች በየአካባቢዉ ፈነዱ:: በምርጫ 2007 መቶ ከመቶ ማሸነፍ ለኢህአዴግ ህልውና የሚበጅ አልነበረም:: ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲዊ መብት ጥያቄዎች ለሠልፍ እና ለተቃውሞ መነሻ ሆነው ዘልቀው ነበር:: 

ሕዝባዊ አመፁ ኢህአዴግን ለውጥ እንዲያደርግ አስገደደው:: አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ለዶክተር ዐብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር አስረከቡ:: በሽብር የተከሰሱ ተፈቱ:: በኤርትራ ነፍጥ አንስተው የትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ እነ አዴሃን፣ ግንቦት ሰባት፣ ኦብነግ፣ ኦነግ ወ.ዘ.ተ  ከአሸባሪነት መዝገብ ተፍቀው ለሠላማዊ ትግል ወደ ሀገር ቤት ገቡ:: ብዙዎችም ከትጥቅ ትግል ወደ ሀሳባዊ ትግል ዙረው ለምርጫ ፖለቲካ ራሳቸውን አዘጋጅተዋል:: የትጥቅ ትግል የፖለቲካ ማስፈፀሚያነቱ በህዝባዊ የለውጥ ፍላጐቱ ያከተመ ቢመስልም፤ በሀገር ቤት ያሉ ታጣቂ  ቡድኖች ንፁሃን ሲጨፈጨፉ ዘግናኝ ወሬ መስማት የለውጡ እኩይ ገፅታዉ ሆኗል::

ኦነግ ሸኔ

በሲዳማ፣ በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ፣ በአማሮ  በደቡብዊ ኢትዮጵያ ኦነግ ሸኔ የሚባለዉ ታጣቂ ቡድን ረብሻ ፈጥሯል:: የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ህልውና በኦነግ ሸኔ ፈተና ውስጥ ወድቋል:: ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ሚያዚያ ሁለት ቀን 2013 ዓ.ም እንዳስነበበው መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሲዳማ ክልል ወዶንገነት ወረዳ የታጠቁ ሀይሎች በመከላከያ ሀይል ላይ ሳይቀር ጥቃት ከፍተው ነበር:: ከጥቃቱ ጀርባ የኦነግ ሸኔ ሀይል እንዳለ የሲዳማ  ክልል አሳውቋል:: በአማሮ ወረዳ የብልጽግና ፅህፈት ቤት  ሀላፊዉን ጨምሮ ስድስት አመራሮች በኦነግ ሸኔ ተገለዋል:: የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ  ጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም በአርባ ምንጭ  ውይይት አድርጐ ነበር:: በውይይቱም የጋሞ ዞን የኦነግ ሸኔ ሀይል ፓርኩ ውስጥ በመመሸጉ ፓርኩን ከህገወጦች ማዳን እንዳልተቻለ ገልጿል::

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ቸርነት ኃይለማሪያም በወቅቱ የነጭ ሳር ብሄራዊ ፖርክ በመሬት ወረራ እና በህገ ወጥ አደጋ ፈተና ውስጥ መግባቱን አረጋግጠው፤ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በምሥራቃዊ እና ምዕራባዊ የኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን ኦነግ ሸኔን በመስጋት መጐብኘት እንዳልተቻለ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ይፋ አድርጐ ነበር:: ታጠቂ ቡድኖች ታሪካዊ እና ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን ከማውደም እስከ ንፁሃን ጭፍጨፋ የዘለቀ ጥቃት እያደረሱ ነው::

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚሴና ዙሪያው፣ በደዋ ጨፋ፣ በአጣየ እና ሽዋሮቢት በዘመናዊ መንገድ የታጠቁ እና የተደራጀ  የኦነግ ሸኔ ሀይል ጥቃት ከፍቶ ንፁሃን እንደጨፈጨፈ የአማራ ክልል መንግሥት በወቅቱ ገልጾ ነበር:: በወለጋ እና በመተከል ካለው የአማራ ጭፍጨፋ ጀርባ ኦነግ ሸኔ እንዳለበት በተደጋጋሚ ይገለጻል::

በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሠብ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢ በተፈጠረ ግጭት 303 ንፁሃን እንደሞቱ እና 369 ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም መጋቢት 29 ቀን 2013 ይፋ አድርጓል:: የተፈናቀሉት ዜጐች ቁጥርም ከ50 ሺህ በላይ እንደሆነ ተቋሙ የገለፀ ሲሆን ጥቃቱን ያደረሡት ከባድ መሳሪያ የታጠቁ እና የተደራጁ  ታጣቂዎች ናቸው ብሏል::

ከመተከል እስከ አማሮ፣ ከነጭ ሳር እስከ አጣየ ባሉ ጥቃቶች ውስጥ የተደራጁ ታጣቂዎች ናቸው የሚል መግለጫ ይሰጣል:: እነዚህ ታጣቁዎች የመንግሥት ተቋማትን ያወድማሉ:: የሀገር መከላከያ ሀይሎችን እና ህዝባዊ ፖሊሶች ላይ ጥቃት ይፈፅማሉ:: እነዚህ ታጣቂ ሀይሎች በሚፈፅሙት ዘግናኝ ግድያ ተንቀሳቅሶ መስራት እና የመኖር ሰብዓዊ መብት በኢትዮጵያ አዳጋች ሆኗል:: መተከል ከመስከረም ጀምሮ ለሰባት ወራት ያህል በወታራዊ ሀይል ቢመራም መፈናቀል እና ሞቱ አልተቋረጠም:: አርሶ አደሩ የመኽሩን አዝመራ አልሰበሰበም:: ለክረምቱ የማሳ ዝግጅት ለማድረግም አካባቢዉ ሠላም አልሆነም:: አምራች አርሶ አደሮች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሆነው እጃቸውን ለእርዳታ ዘርግተዋል::

መሬት ጦም እያደረ ነው:: ታጣቂዎች በተደራጀ ሁኔታ በተለያዩ አካባቢዎች በሚያደርሱት ውድመት ዜጐች በልበ ሙሉነት ለመስራት ብሎም ለመኖር ጥርጣሬ ውስጥ ገብተዋል:: መፈናቀሉ በቀጠለ ቁጥር የኢትዮጵያ ሀገርነት ህልውና ጥያቄ ውስጥ እየገባ ታጣቂዎች የሚተራመሱባት የ19ኛው ክፍለ ዘመን መሳፍንታዊ ቅኝት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መምጣቱ ቅርብ ይመስላል::

ታጣቂዎች እንዴት ከመንግሥት በላይ ሆኑ?

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚደርሱ ጭፍጨፋወችን አስመልክቶ ባጠናከረዉ ዘገባ እንደገለፀው መንግሥታዊ ተቋማት የመፈፀም አቅም መዳከም የታጣቂዎች ጉልበት እንዲያንሠራራ አድርጓል:: ተቋሙ ለአብነት ሲያነሳ፤ በ2011 ዓ.ም በሰሜን ሽዋ እና በኦሮሞ ብሄረሠብ አስተዳደር ግጭት ተነስቶ ነበር:: ያ ግጭት ግን እንዳይደገም ተደርጐ መፍትሄ ስላልተሰጠዉ በ2013 ዓ.ም በተመሳሳይ ሁኔታ ደርሶ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል:: 

በመጋቢት መጀመሪያ 2013 ዓ.ም በተከፈተው ግጭት ተጠርጥረው የተያዙ 80 ያህል ተጠርጣሪዎች ያለምንም ማጠራት ከበላይ አካል የመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል እንደተፈቱ ተቋሙ ይፋ አድርጓል:: ሕግ በብሄር እና በፖለቲካ እሳቤ ስለሚመዘን ፍትሃዊ እርምት እየተሰጠ አይደለም:: የሀገሪቱ መንግሥታዊ ውቅርም ግጭቶችን ለማድረቅ ምቹነት እንደሌለው ተቋሙ ገልጿል:: በአስረጅነት የሠላም ሚኒስትር በስሩ ብሄራዊ ደህንነትን፣ የፀጥታ አካላትን ሁሉ አካቶ የያዘ ቢሆንም በያዘው አቅም ልክ ችግርን ቀድሞ ሲፈታ አይስተዋልም::

የሠላም ሚኒስትር የተግባር ተቃርኖ ያለበት ተቋምም ነው ሲል ግምገማውን ያስቀምጣል:: የሰላም ግንባታ  እና ጸጥታን ማስከበር ሁለት ተቃራኒ ጉዳቶች በመሆናቸው ብሄራዊ ደህንነቱ እና ፀጥታን ማስከበር በአንድ ተቋም  መምራት የተልኮ መዛነፍን እንደፈጠረ ገልጿል:: የፀጥታ መዋቅሩ በአንድ ተቋም፣ የሠላም ግንባታ ሂደቱ ደግሞ በሌላ ተቋም መመራት አለባቸው ሲል ምክር ሀሳቡን ያቀርባል::

የመንግሥት ተቋማት አፈፃፀም ደካማ መሆኑ ለግጭት በር ከፍቷል:: ለዚህም ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንደሚያደርስ፣ የቻግኒ የተፈናቃዩች የእህል መጋዘን ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል ቀድሜ ለመንግሥት ባሳውቅም መንግሥት እርምጃ ባለመውሰዱ ውድመቱ ደርሷል ሲል የመንግሥትን የመፈፀም አቅም ውስንነት ያነሳል::

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የፀጥታ ሀይሉ ምርጫዉ ተጠናቆ አዲስ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ የፀጥታ መዋቅሩ በአንድ ማዕከል ቢመራ የተሻለ ነው የሚል አማራጭ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህ ሀይል በፌዴራል ባለ መንግሥታዊ መዋቅር መመራት አለበት ሲልም ምክር ሀሳቡን ያጠናክራል:: ተቋሙ በተለይ የመተከልን ጉዳይ የመንግሥት ቸልተኝነት አለበት ሲል የገመገመ ሲሆን፣ ታጣቂዎች ትጥቅ ሳይፈቱ ድርድር መደረጉን በስህተትነት ወስዷል:: 

በመንግሥት በኩል ከ10 ሺህ በላይ ሚኒሻዎች እንዲሰለጥኑ ቢደረግም ትጥቅ አልቀረበላቸውም:: ኢመደበኛ ታጣቂዉ ሀይል ደግሞ በተደራጀ መንገድ ታጥቋል:: ይህ የሀይል አለመመጣጠን ለንፁሃን እልቂት መነሻ ሆኗል:: በወለጋም  የተደራጁ ሀይሎች ንፁሃን ከጨፈጨፉ በኋላ “ኦነግ ሸኔ ተደመሰሰ” እያሉ ዜና ማስነገር ሥህተት እንደሆነ ገምግሟል:: 

የኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ኦነግ ሸኔ ተደመሠሠ ቢልም፣ ኦነግ ሸኔ መስፋፋቱን እየቀጠለ እና የንፁሃን ሞትም እየበረከተ ከመምጣት አልታደገውም:: ኦነግ ሸኔ መዳረሻዉ ወለጋ አካባቢ ነው ቢባልም በአርሲ፣ በጉጅ የመሸገዉ ሀይል በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ፣ በአማሮ ወረዳ፣ በሲዳማ ክልል ጥቃት ሲፈፅም ይስተዋላል::

የኦነግ ሸኔ መሪ ነው ተብሎ የሚታሰበው በሌላ ስሙ ጃልመሮ “ኦነግን ሸኔን አላውቀውም:: ንፁሃንንም የኔ ሠራዊት ከጨፈጨፈ  ይረሸናል” ሲል ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ተናግሯል:: የኦሮሚያ ክልል ሠላም እና ደህንነት ቢሮ ሀላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል ከማል ገልቹ በበኩላቸው ኦነግ ሸኔ በመንግሥት ድጋፍ የሚደረግለት ሀይል ነው ሲሉ በ2011 ዓ.ም ለኤልቲቪ ቴሌቪዥን ተናግረው ነበር:: የኦሮሚያ ክልል ፖሊስም ከአንድ ሺህ በላይ መደበኛ የፀጥታ ሀይሎች ከሸኔው ሀይል ጋር ወግነው ስለተገኙ እርምጃ ወስጃለሁ ሲል ለኢትዮጵያ ቴሊቪዥን ተናግሮ ነበረ::

ከወለጋ የተፈናቀሉ ዜጐችም የሚያፈናቅለን እና የሚገድለን መንግሥታዊ መዋቅሩ ነው ሲሉ ይደመጣሉ:: በመተከልም የመንግሥት መዋቅሩ በማፈናቀል እና በመጨፍጨፍ እጁ እንዳለበት በመታመኑ የመተከል ዞን አስተዳዳሪ ሲታሰር፣ የተወሰኑ የምክር ቤት አባላትም ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ እንዲከሰሱ ሆነዋል::

በሽፍታው /በታጣቂ ሀይሎች/ እና በመንግሥት መዋቅር መካከል የሚና መደበላለቅ መኖሩ፣ መንግሥታዊ መዋቅሩ የግልፀኝነት እና የመጠያየቅ ባህሉ ዝቅተኛ መሆኑ፣  ተቋማት በገለልተኛነት የመፈፀም አቅማቸው ደካማ መሆኑ እና በጥላቻ ላይ የተመሠረተው ሀገር አፍራሽ ፖለቲካ ገዥ  ሆኖ መቀጠሉ ሀገሪቱን ታጣቁዎች እንደፈለጉ የሚፈነጩባት  ሊያደርጋት ይችላል::

በአማራ ክልል በ2011 ዓ.ም የበይነ መንግሥታት ግንኙነት የሚል ተቋም ከክልሉ ውጭ ያሉ አማራዎችን እና ከየክልል መንግሥታት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ተቋቁሟል::

በይነ መንግሥታት ቢሮ ምክትል ሃላፊዉ አቶ አሰማኸኝ  አስረስ እንደተናገሩት ‹‹የንጽሃን ጭፍጨፋ መንስኤው መዋቅራዊ ነው›› ሲሉ ይበይኑታል:: ዘመናዊ እና አዲስ መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎች መውጫ እና መግቢያውን በሚያውቅ የቅርብ አካል ካልተደገፉ ከየትም ሊያገኙት አይችሉም ሲሉም እይታቸውን ያስቀምጣሉ:: ብልጽግና ግንባር ድርጅቶችን ወደ ውህደት ሲያመጣ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ጥያቄዎች ነበሯቸው:: እነዚህ ጥያቄዎች በአንድ ማዕከል የጋራ መግባባት ስላልተደረሰባቸው የጋራ አቋም ለመያዝ እና ለማስፈጸም አስቸጋሪ ሆኗል ሲሉም የገዥ ድርጅቱን ድክመት ያነሳሉ::

 “አርሶ አደሮች ልንጨፈጨፍ ነው:: ድረሱልን ሲሉን ለሚመለከታቸው እናሳውቃለን:: ግን ምላሻቸው ንጽሃንን ከመጨፍጨፍ ያዳነ አይደለም” ሲሉም የመንግሥትን  ተቀናጅቶ እና ተናቦ ፈጣን ምላሽ  የመስጠት ውስንነት አንስተዋል::  መንግስት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ፤ለዚህም ተቋማትን ማደርጀት የመፍትሄ መንገድ አድርገው አቶ አሰማኸኝ ያነሳሉ:: በዘላቂነት ደግሞ የፖለቲካ ልሂቃን ድርድር እንዲሁም ነጣጣይ እና ስሁት  ትርክቶች ማረም ብሎም የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት መልክ በጋራ መቅረጽን መፍትሄ ናቸው ሲሉ ለበኩር ተናግረዋል::

በድሬድዋ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ በጸሎት አዲሱ እንደሚሉት  “ሽፍታ ወይም ታጣቂ ሃይሎች ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች አይደሉም:: መንግሥታዊ አደረጃጅቶች ናቸው ብለው ያምናሉ::” ለዚህ ሃሳባቸው ማሳያም ትጥቅ፣ ስንቅ እና መረጃ በመንግሥት ውስን አካላት ድጋፍ ባይደረግላቸዉ ኑሮ የጥፋት አድማሳቸው ይሄን ያህል አይሰፋም ነበር ይላሉ መምህሩ:: ስለዚህ እንደ አቶ በጸሎት የተደራጁ ታጣቂዎችን በምክር ቤት በሽብር መዝግቦ በሚረዷቸው ላይ ሁሉ የእርምት እርምጃ መውሰድ  ተገቢ ነው ይላሉ:: 

ፖለቲካዊ ማሻሻያም አስፈላጊ ነው:: ከፖለቲካዉ እኩል የጸጥታ መዋቅሩ  ማሻሻያ ያስፈልገዋል:: የፖለቲካ እና የጸጥታ መዋቅሩ  ገዳይ ቡድኖችን በአንድ ድምጽ ለማውገዝ እና ለማጥፋት ቢሰራ ታጣቂ ቡድኖች ክፋታቸው ያጥር ነበር:: በሌላ በኩል ታጣቂ ቡድኖች ጸረ ሰው ስለሆኑ ማን እንደሆኑ እና ምን እያደረጉ እንደሆነ በማሳወቅ ከሕዝቡ መነጠልም ተገቢ  ነው::

በኩር ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ዕትም

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top