Connect with us

ከአባይ ወንዛ ወንዙ  እስከ ደሞ ለአባይ ….

ከአባይ ወንዛ ወንዙ እስከ ደሞ ለአባይ ….
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከአባይ ወንዛ ወንዙ  እስከ ደሞ ለአባይ ….

ከአባይ ወንዛ ወንዙ  እስከ ደሞ ለአባይ ….

 “የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና… “

 ( እስክንድር ከበደ)

ጆሴፍ ኮርቤል በዩናይትድ ስቴትስ ዴንቨር ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት በማስተማር ይታወቃሉ፡፡ ጆሴፍ ኮርቤል የአሜሪካንን ውጭ ጉዳይ በመግራትና ተጽኖ ፈጣሪ ተደርገው ከሚወሰዱ ሙህራን መካከል ቀዳሚውን ይይዛሉ፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ዴንቨር ዩኒቨርሲቲ ጆሴፍ ኮርቤል ስም የዓለምአቀፍ ጥናት ተቋም ሰይሟል፡፡ እኚህ ሰው የአሜሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ወጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት የማደሊን ኦልብራይት አባት ናቸው፡፡ 

ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ሦስት ሴቶች የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ሆነው አገልግለዋል፡፡ ማድሊን ኦልብራይት ፣ኮንዳሊዛ ራይዝና ሂላሪ ክሊንተን  ናቸው፡፡ጥቁር አሜሪካዊቷ  ኮንዳሊዛ ራይዝ ከልጅነት   ጀምሮ ፤ፒያኖ መጫወት ትወድ ነበር።በ15 አመቷ በዴንቨር ሲንፎኒ ሞዛርትን ተጫውታለች ።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ዘመኗም በዋይት ሀውስ የሚዘጋጁ በሙዚቃ መድረኮች  በሙዚቃ መሳሪያዎች የተቀነባበሩ  ዝግጅቶች ፒያኖን በመጫወት ትታወቃለች። በትላልቅ የዲፕሎማሲ መድረኮችና በኤምባሲዎች ፒያኖ የተጫወተቼ  ሲሆን፤ለንግሥት ኤልዛቤት ክብር   በተካሄደ ዝግጅት ተሳትፋለች።

በጆርጅ ቡሽ ዘመን  የውጭ ጉዳይ ሚንስትርና የሀገሪቱ የደህንነት አማካሪ የነበረችው  ኮንዳሊዛ ራይስ ጀርመን እንድትዋሃድ የበኩሏን ሚና ተጫውታለች፡፡ የቀደሞዋን ሶቬት ህብረት ደግሞ አብጠርጥራ ለማጥናት ሙዚቃና ፖለቲካዋን ቃኝታለች፡፡ ኮንዳሊዛ ራይስ የሶሻሊስቱን አለም አብጠርጥራ እንድታውቅ ያሰለጠኗት የማድሊን ኦልብራይት አባት ጆሴፍ ኮርቤል ናቸው፡፡ ኮንዳሊዛ ራይስ Music and Politics in Soviet Union ( ሙዚቃና ፖለቲካ በሶቬት ህብረት ) በሚል ጥናት አካሄዳ ነበር።የሶቬት ህብረት  ሙዚቃና ፖለቲካዋ በሚገባ ተጠንቶ የሆነውን እንተወው፡፡

ዶክተር ኮንዳሊዛ ራይስ የምስራቁን ጎራ በተለይ የቀድሞ ሶቬት ህብረትን አብጠርጥራ ለማወቋ አንዱ ምክንያት እንደአጉሊ መነጽር የተጠቀመችበትና ሩሲያን አጮልቃ ያየችው በሙዚቃ ነበር። የአሜሪካ የደህንነት አማካሪዋ ኮንዳሊዛ ራይስ   የሶሻሊስት ጎራን ማወቋ ፤ ሌሎች ገፊ ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆነው በኪነጥበብ በር በመግባት የቀዝቃዛው ጦርነትን ለማሸነፍ የሶቬትህበረት ህዝብ የሚያስበውን  በመተንተን ለአሜሪካ ጥቅም አውላለች፡፡  የሞስኮ ህዝብን ስነልቦና ለመመርመር  ”የሩሲያ አዝማሪ ምን ይላልʔ”  ብላ አጥንታለች፡፡

ሙዚቃ እንደአንድ ጥበብ መመዘኑ እንዳለ ፤ በአግባቡ ከተጠና  የዘመኑ እሳቤዎችና እሴቶችን የመንገር ሀይል አለው፡፡አባይና የአባይ ሙዚቃዎቻችንና የአባይ ፖለቲካን  በቀጭን ክር አገናኝተን እንድንፈትሽ ፈለኩ።   የሶስት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ዘፋኞች” አባይ” ዘፈኖችን በጨረፍታ መቃኘት ወደደኩ።በአንድ ሀገር ውስጥ ሥነጥበብ ከተጠና ከመዝናኛነቱ ባሻገር የሀገርንና ህዝብን አተያይና ነብስ እንደመስታወት የማሳየት ጉልበት አለው።

በቅድሚያ የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ)” አባይ” ዘፈን እንመልከት።  እጅጋየሁ ሽባባው የአባይ ወንዝ  የምትዘፍነው አንደ አብሮ አደግ  ውድ  ጓደኛዋ  እያቆላመጠች ነው፡፡ የጣናን ሀይቅ እያየች ማደጓ፤  ከልጅነቷ እስከ እውቀት  የፈጠረባትን ምስል ታጋራናለች፡፡

 ጂጂ  የወንዙን የዘመናት  ውበትና ፈሰት ከፍጥረት ጀምሮ የማያረጅ፣ የማይደርቅና የማያረጅ እያለች ታሞግሰዋለች።

የማያረጅ ውበት

የማያልቅ ቁንጅና

የማይደርቅ የማይነጥፍ

ለዘመናት  የጸና

የፈሰሰ ከውሀ

ፈልቆ ከገነት

የአገር ጸጋ  …የአገር ልብስ

ግርማ ሞገስ  አባይ አባይ አባይ…

ጂጂ  የአባይ ከሥነፍጥረት ጀምሮ  የማያረጅ ቁንጅናውና የማያልቅ ውበት በሚያምር ቅላጼዋ ታዜምለታለች።የአገር ጸጋና ግርማ ሞገስ ብላ ያቀነቀነችለት ይህ ወንዝ ፤ከአድናቆቷ ቀጥላ ቁጭት  በውስጧ እንዳጫረባት ወረድ ስንል  ስሜቷን እናጤናለን።   “የበረሃ ሲሳይ  ” የሚለውን ደጋግማ ታሰማናለች።አራቴ ትነግረናለች።

“ብነካው ተነኩ

አንቀጠቀጣቸው

መሆንህን ሳላውቅ

የሚበሉት ውሀ

የሚጠጡት ውሀ

አባይ ለጋሲ ነው

በዛ  በበረሀ  “

ኢትዮጵያ ውሀውን መጠቀም ብትፈልግ፤አትንኩብን የሚሉ መኖራቸውን ዘፈኑ ይተርካል። የሚበሉትም ሆነ የሚጠጡት ውሀ ብላ አባይ ሁለነገራቸው መሆኑን በዘፈኑ ጠቅሳ፤ጭው ባለ በረሀ ዘልቆ የአባይን  ለጋስነት ታሰማናለች። የግብጽን  የዘመናት ማስፈራራትና የእኛን ወራጅ ውሀውን ሳንሰራበት  ደጋግመን ብንጠራውም አለመስማቱን “ወንዙን ከግብጽ ጋር ፍቅር የወደቀ” አድርገን ስንወቅሰው በምጸት ጭራ ታለፈዋለች።

“አባይ የወንዝ ውሀ

አትሁን እንደሰው

ተራብን ተጠማን

ተቸገርን ብንለው

አንተ ወራጅ ውሀ

ቢጠሩህ አትሰማ

ምን አስቀምጠሀል

ከግብጾች ከተማ?”

ጂጂ  ወንዙን ጠይቃ  “አባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ” ብላ ትዘጋዋለች። “መዘዙ” ምንድነው? የሚለውን ባትነግረንም “ውሀው ሲነካ የሚያንቀጠቅጣቸው ” መኖራቸውን በውብ ዜማዋ የጫረችብንን  ደጋግመን እንድናስብ ትታን ትነጉዳለች።   (ይቀጥላል) 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top