Connect with us

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ

ክፍል 3 የመጨረሻው ክፍል

  1. ፍልስፍና ፍለጋ

ለምን ፍልስፍና አስፈለገን? አብይ ፍልስፍና ፍለጋ የገባው “ኢትዮጵያ ታማላች፤ ከህመሟ እንድትወጣ አንድ አይነት መፍትሄ ያስልጋታል። ይህም መፍትሄ ሃገራዊ ፍልስፍና መሆን አለበት” ብሎ በማሰቡ ነው። “የሃገር ህመሟ በድህነት፣ በርስ በርስ ግጭት፣ በሰላም እጦት፣ በህግ የበላይነት መጥፋት፣ በሞራል በስነምግባር መበስበስ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በመብት መገፈፍ፣ በፍትህ ማጣት በጥቅሉ በአንድ ሃገር ዜጎች ላይ ሊደርሱ በሚችሉ ስቃዮች የሚገለጹ ናቸው” ብሎ ያምናል። አይደሉም ብሎ የሚከራከረው አይኖርም።

ይህ የሃገር፣ በውርደትና በግፍ የተሞላ ወቅታዊ ሁኔታ በአብይ አእምሮ ውስጥ ቁጭትና ምሬት ፈጥሯል። ሌሎች ሃገሮችና ማህበረሰቦች እኛ ኢትዮጵያውያን ከምንሰቃይባቸው ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስቃዮች ከሞላ ጎደል ነጻ ሆነው የሚኖሩ መሆናቸው ቁጭቱን አበርትቶታል። ይህ ብቻ አይደለም ዛሬ ከኢትዮጵያ በላይ የተረጋጋና የበለጸገ ህይወት ያላቸው ሃገሮች፣ ቀደም ባሉት ዘመናት ስልጣኔያቸው፣ ታሪካቸውና ገናናነታቸው ከኢትዮጵያ በታች ወይም እኩል እንጂ የሚበልጡ ያልነበሩ መሆናቸው አብይን ከንክኖታል።

እንግዲህ የፍልስፍና ፍለጋ ምክንያቱ ይህ ከሆነ፤ እኛም እንደ ሃገርና ህዝብ ሌሎች ሀገሮች የተቀዳጁትን ዘመናዊነት፣ ሰላምና መረጋጋት እና የዘመነ ህይወት ለመቀዳጀት ከሆነ ፍላጎታችን፣ ወደ ፍልስፍናው የሚወስደን መንገድ አንድና አንድ ብቻ ጥያቄ በመጠይቅ ብቻ የሚጀምር መሆን ይኖርበታል። “እንዴት ነው በስልጣኔ እነዚህ ከእኛ እኩል ወይም ከኛ በታች የነበሩ ሃገሮች በአጭር ጊዜ ውሰጥ ሁሉ ነገራቸው የሞላላቸው መሆን የቻሉት?

ይህ ጥያቄ ሃገሮችን ለምና እንዴት በፍጥነት ወደ ዘመናዊነት ወደ ብልጽግና እንደ ተሸጋገሩ ወደ መመርመሩ ስራ ይወስደን ነበር። የዚህ የምርመራ ውጤት አንድና አንድ ብቻ ይሆን ነበር።ይህ የምርመራ ውጤት የሚቀጥሉትን ሃቆች ያስገነዝበን ነበር።

ዘመናዊ የሆኑ ሃገሮች በሙሉ፣ መሰረታዊ ማንነታቸውን ያልካዱ፣ የቆዩ ትወፊቶቻቸውን ባህሎቻቸውን ያልለቀቁ፣ ስልጣኔ ወይም ሃገር ማዘመን እነዚህን የኛ የሚሏቸውን ማንነቶች የፈጠሩትን፣ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን፣ ወጋቸውን፣ ትውፊቶቻቸውን ለማንበር ለማሰቀጠል የመንፈስ ጽናት ያላቸው ብቻ ናቸው። መዘመን የተለየ ማንነት ባህል ታሪክ ባላቸው ሌሎች የዘመኑ ሃይለኞች እንዳይወረሩ ወይም እዳይጨፈለቁ ለማድረግ ነው። ሳይንስን፣ ቴክኖሎጂን እና እምነትን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የቆየ ባህል የሚቃረኑ ሳይሆኑ አዲሱ የጥንቱን በማደስ በማንበር መስተጋብር ላይ ተመስርቶ የሚያድግ አድርጎ ከሚታይ እሳቤ ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው።

አብይ በምሳሌነትና በቁጭት መቀስቀሻነት የሚያነሳቸው፣ እነጃፓን፣ ኮሪያ፣ ቻይና የእስያ ሃገሮች ፈጣን የዘመናዊነት እንቅስቃሴ መሰረቱ ማንነትን ከሌሎች ሃይሎች ወረራ ለመከላከል፣ ለራስ ማንነትና ክብርና ኩራት ከሚሰጥ ትልቅ ትርጉም ጋር የተያያዘ ነው። ለጃፓንነት ለኮሪያዊነት ለቻይናዊነት ከሚሰጥ ብሄራዊ ክብር ጋር የተያያዘ ነው።

ጃፓን በፍጥነት ራሷን ያዘመነችው፣ ይህን ማድረግ ባትችል በዘመናዊ ኢንዱስትሪ እድገት የሚመረቱ አደገኛ የጦር መሳሪያዎች የታጠቁ ምእራባውያን፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ሊወሯት፣ ባህላቸውን፣ እምነታቸውን፣ ማንነታቸው ሊጭኑባት፣ እንደ ልዩ ሃገርና ህዝብ የነበራትን አለም አቀፋዊ ቦታ ሊገፏት እንደሚችሉ ከመገንዘብ ነው። መሪና ተመሪ አለቃና ምንዝር መላው የጃፓን ህዝብ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ከአሜሪካ በስተቀር ሌላውን አለም ያስከነዳ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ባለቤት ጃፓንን ያደረጋት ዋናው ምክንያት ይህ ነው። ሁሉም የእስያ ሀገሮች በፍጥነት የመልማት መኮርኮሪያቸው የመጣው ለብሄራዊ ማንነታቸው ለሚሰጡት ክብርና ኩራት እሱን ከየትኛውም ጥቃት በዘመናዊ እድገት ለመከላከል በማሰብ ነው።

ማህቀፉ ሌላ ቢሆንም የ”መደመርን ሃሳብ” አብይ በገለጸበት ገጽ ይህን ሃቅ በደንብ የተገነዘበው መሆኑን አሳይቶናል። “የሰው ልጅ ስጋዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ለስሙና ለነጻነቱ ቀናኢና ሟች ነው፡፡ የሰው ልጅ የክብሩና የነጻነቱ ፍላጎት ካልተሟላለት ለምግብ ቀርቶ በህይወት ለመኖር ምንም ፍላጎት እንደማይኖረው” አብይ ነግሮናል (መደመር ገጽ 6-7)። ይህን መልእክት ያስተላለፈው በአጠቃላይ የሀገራችንን የዜጎችንም ሆነ ከሃገራችን የማንነት ፖለቲካና ከዚህ ጋር ተያይዘው የተነሱ የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄዎችን ከምር እንድንወስድ ለማመላከት ነው።  እዚህ ላይ አብይ የነጻነትና የእኩልነት ቀበኞች አድርጎ የወሰዳቸው ሃገር በቀል ሃይሎችን ነው።

ሆኖም ግን የእኩልነት፣ የነጻነትና የክብር ቀበኞቹ የውጭ ሃይሎች ሆነው ሲታዩ የአንድን ሃገር ህዝብ ምን ያህል በአንድነት እንዲተባበርና ለከፍተኛ ክንዋኔ ሊያስነሳው እንደሚችል በተለይ በፍጥነት መዘመን መበልጸግ ከቻሉት ሃገሮች ታሪክ ጋር በማያያዝ አልቀረበም። አብይ በምሳሌነት የጠቀሳቸው ሃገሮች በሙሉ ለእድገትና ለዘመናዊነት እንዲነሱ ዋናው ነዳጃቸው ሃገራዊ ክብር፣ ነጻነትና እኩልነት ነው። 

አብይ ይህን ማሳየት ችሎ ቢሆን ኖሮ ከግለሰብ ወይም ከብሄር በላይ ተሻግረን እንደ አንድ ሃገር ህዝብ ከምግብ በላይ የምናያቸው የጋራ ጉዳዮች ምን ሊሆኑ እንደሚገባቸው ወደ መጠየቅ ያመራ ነበር። የተነጣጠሉ ግለሰቦችና ማህበረሰቦች የነጻነትና የክብር ጥያቄ ኢትዮጵያን በመሰለ ሃገር ውስጥ አጠቃላይ የሁሉንም ድቀት ሳያስከትል በምን መንገዱ ተፈቶ ጠንካራ የበለጸገ ሃገር መፍጠር እንችላለን ወደሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ይወስደን ነበር። አልሆነም። 

ሌላው ቀርቶ ወደ ዘመናዊ ስልጣኔ በኮምኒስት ርእዮእተ አለምና  ኮምኒስት መሪዎች የተሸጋገሩት ሃገሮች፣ የርእዮእተ አለም ፍለጋቸው ጠንካራ የሀገራዊ ብሄረተኛነት መነሻ ነበረው። የሩሲያ ብሄረተኛነት እንጂ የኮምኒስት ርእዮእተአለም አልነበረም የፈጣን እድገት የጥንካሬዋ ምንጭ። ሃገር ይቀይራል የተባለለት የኮምኒስት ርእዮእተ አለም ተቀባይነት ያገኘው ሩሲያኖች በሰለጠኑ፣ በዘመኑ ሃገሮች ከሚደርሳባቸው ጥቃት፣ ቁጭትና ውርደት የሚገላግል በመሆኑ ነው። የሃገራቸውን ኋላ ቀርነት ከሌሎች ከበለጸጉ ሃገሮች በንጽጽር ከማየት ከመጣ ቅናት ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው።

ሁሉም የግራ ርእዮተአለም እንቅስቃሴዎች መሰረት ሃገራዊ ብሄረተኛነት ነው። ይህ ሃቅ በሃገራችንም የፖለቲካ ታሪክ የተንጸባረቀ ነው። የኢትዮጵያ ምሁራን እና ተማሪዎች ከግራ ርእዮተአለም በፊት ለትግል ለለውጥ ያነሳሳቸው ኢትዮጵያ እንደሃገር የምትገኝበት ታሪኳን እና የቀድሞ ገናናነቷን የማይመጥን ከዘመናዊነት የራቀ አዋራጅ ሁኔታ ነው። ሃገራዊ ብሄረተኛነት ነበር።

እነ ቻይና እና ራሽያ ሌሎች በኮምኒስት ርእዮት በኩል ወደ ዘመናዊነትና ብልጽግና የተጓዙት ሃገሮች በራሳቸው የተለየ ሃገራዊ ሁኔታ ብሄራዊ ማንነታቸው ክብርና ኩራታቸውን እንደያዙ በመቅረታቸው የኮምኒስት ርእዮት በተዳከመበት የአለማችን ሁኔታ እነዚህ ሃገሮች ከምእራባውያኑ እንዳያንሱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፉክክር ወስጥ ገብተው የእድገትና የብልጽግና አሴት እያሰባሰቡ ነው።

የኢትዮጵያ ታላቁን የአድዋ ድል ተከትሎ የመጣው በሃገራዊ ብሄረተኛነት ላይ የተመሰረተውና በአብዮታዊ መንገድ የተሞከረው ሃገር የማዘመን ሙከራ ሲከሸፍ ቦታውን የተካው ከሃገራዊ ብሄረተኛነት ጋር ትልቅ ጠብ ያለው የዘውግ ብሄረተኛነት መሆኑ፣ ሃገሪቱ  ሌላ ሃገር የማዘመን ነዳጅ ሊሆን የሚችል ማህበራዊ የጋራ እሴት ማግኘት እንዳትችል ሆናለች። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ቁልቁል ወደታች እንጂ በፍጥነት በልማት እንደተመነደጉትና እሷም  እንደምትቀናባቸው የእስያ ሃገሮች ማደግ አልቻለችም።   

ምእራባውያንም ቢሆኑ የየሃገራቸውን ብሄራዊ ማንንነት፣ ከአጎራባች ሃገሮች ማንነት ለመከላከል፣ አንዱ የያዘውን የዘመነ መሳሪያና ዘመናዊ የአስተዳደርና የፖለቲካ ተቋምና መዋቅር፣ ሌላው በፍጥነት እየቀዳ፣ ጦርነትና ደም መፋሰስ ባላበት ፍክክር አልፈው ነው ከአለም ቀድመው ዘመናዊ ወደ ሆነው አለም የገቡት።

ሁሉም የአውሮፓ ሃገሮች ልዩ የሚያደርጋቸውን የማንንነት መለያዎች እንደያዙ ነው የሰለጠኑት። የቆዩ የዘመናት በእውነት ላይ የተመሰረቱና ያልተመሰረቱ  ታሪኮቻቸውንና ትርክቶቻቸውን ለጋራ ስነልቦና መገንቢያ አድርገው ነው የተነሱት።  ከእየአንዳንዱ የአውሮፓ ሃገር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለውን ጥንታዊ የግሪክና የሮም ስልጣኔ አቧራ ለብሶ ከነበረበት የታሪክ ትቢያ እያነሱና እያራገፉ የጨለማውን ዘመን ማለፊያ ሻማ አድርገው ተጠቅመውበታል። ለአዲሱ ዘመን የስልጣኔ መኮርኮሪያ በማድረግ ወደፊት ገስግሰውበታል።

በቅድሚያ አንድን ማህበርሰብ ለስልጣኔ/ዘመናዊነት ወደፊት የሚገፋው፣ ተባብሮና ተጋግዞ ከፍተኛ ስነስርአት ተላብሶና መስዋእትነት እየከፈለ ወደፊት እንዲገሰግስ የሚያደርገው ከዳቦ፣ ከልብስ፣ ከመጓጓዣ፣ ከመኖሪያ ቤትና ሌሎች ዘመናዊ ቁሳቁሶች ጋር የተያያዘ ፍቅር አይደለም። እነዚህ የስልጣኔ ትሩፋት እንጂ ለመሰልጠን የሚያስፈልጉ የሞራልና የመንፍሰ ስንቅ አይደሉም።

በዘመናዊነት ወደፊት ከገሰገሱት የምሰራቅና የምእራብ ሃገሮች መሃል የመዘመን ፍላጎቱ የራሱን የቀድሞ ስልጣኔ፣ ታሪክ ባህል ወግ ቋንቋ የአኗኗር ዘይቤ (way of life) ማትረፍን አላማው የሞራልና የመንፈስ ስንቁ አድርጎ ያልተነሳ ሃገር ማግኘት አይቻልም።

የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያም ችግር ይህ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኤክስፐርቶች ወደ ምእራብና ምስራቅ ሃገራት ልከን ብናሰለጥን፣ በሚሊዮኖች ነዋይ አፍስሰን የእነሱን የልማት ፖሊስና እቅድ ብንገለብጥ፣ በቢሊዮኖች አፍስሰን የእነሱን ዘመናዊ መሳሪያዎች አምጥተን ብንገጥም፣ አፍሪካ የበለጠ እየተዋርደች ከምትሄድበት የወርደት እስር ቤት አትወጣም። ኢትዮጵያም እንደዚሁ። ችግሩ የተፈጠሮ ሃብት አለመኖር አይደለም። ችግሩ ትምህርት ስልጠና፣ ዘመናዊ አሰራር ስልትና ቁሳቁስ ከምእራቡም ከምስራቁም የመግዛት አቅም ማጣት አይደለም። ይህ ካልሆነ ታዲያ ችግሩ ምን  ላይ ነው የሚል ጥያቄ መነሳት ይኖርበታል።

የአፍሪካ ምሁራን ተሰባሰበው ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። “የአፍሪካ ህልውና የአፍሪካ ስልጣኔ፣ የአፍሪካ ገናናነት አፍሪካዊ የፍልስፍና መሰረት ከሌለው እውን ሊሆን አይችልም። በነጮች ፍልስፍና አፍሪካን መገንባት አይቻልም።” ፍልስፍና ፍለጋ እየባዘኑ ናቸው። ይህን አፍሪካዊ ፍልስፍና ፈለጋ አይናቸው ወደ ኢትዮጵያ እያማተሩ ነው።

ዶ/ር አብይም ቀደም ብዬ እንደጠቀከስኩት እዚህ ልድገመውና “ከኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ስሪት የሚነሳ ችግሮቻችን ሊፈታ የሚችል፣ እኛው እያቃናነውና እያሟላነው የምንሄደው፣ ከአለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ፣ ሁላችንንም ሊያግባባና ሊያስተባብር የሚችል  አንዳች ሉአላዊና ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ያስፈለገናል”   ብሎናል።

አብይ ይህን ፍልስፍና ለማግኘት ብዙ ሞክሮ የተቸገረው ለምን እነእስራኤል፣ እነጃፓን እነቻይና ኮርያና ሌሎች ሃገሮች ተሳካላቸው እኛ አለተሳካልንም የሚለውን ጥያቄ መልሱን ቴክኒካል በሆነ መንገድ በመመለሱ ነው።

ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ፣ ዘመናዊነትን ለማምጣትና፣ ዘመናዊነትን ተከትለው የሚመጡ በሌሎች ሃገሮች የተከሰቱ በጎ ነገሮች በሃገራችን እንዲከሰቱ ለማድረግ የኛ የኢትዮጵያውያን የመንፈስ የሞራል ስንቅ መሰረት የሚሆኑ ከማንነታችን ከሰብአዊ ክብራችን ጋር የተያያዙ ከታሪካችን ከባህላችን ከተውፊታችን የምንመዛቸው እውነተኛ የሆኑ ያልሆኑም እኛ የምናምንባቸው ጉዳዮች  ምን ሊሆኑ ነው ወደሚለው ጥያቄ ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ ከዘመናዊ እድገት ምቹነት ጋር በተያይዘ የተለያዩ ሃገሮችን ተጭባጭ እውነታ በንጽጽር መልኩ ማየቱ ጠቃሚ ነው።

  1. የዘመናዊነት እድሎች፣ ፈተና፣ ድልና ሽነንፈት በአለም ዙሪያና በኢትዮጵያ

በታሪክ እንዳየነው ለፈጣን ዘመናዊ እድገት የተመቻቹ ሃገሮች በአንድ በኩል የተለያዩ ቋንቋዎችና ማንነቶች በመጨፍልቀ አንድ ወጥ ማንነት በሂደት በመፍጠር ውስጣዊ መረጋጋትና የዘመናዊነት መሰረት የጣሉ ናቸው። ብዙዎቹ የአውሮፓ ሃገሮች የዚህ ምሳሌ ናቸው። ጦርነት፣ ማስገበር፣ ፈጣን እና ዘመናዊ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ግስጋሴ ማድረግ፣ የተረጋጋ ማህበረሰብ መፍጠር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለፋታ የተከናወኑባቸው ሃገሮች ናቸው። የምእራብ አውሮፓ ሃገሮች።

በምስራቁ በኩልም የምናየው በፍጥነት ወደ እድገት የመጡት ሃገሮች በአብዛኛው፣ ከ90 በመቶ በላይ የሆነውን ህዝባቸው የአንድ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት ባለቤት የሆነባቸው ሃገሮች ናቸው።  እነዚህ ሃገሮች እራሳቸውን በማዘመን ማንነታቸውን ባህላቸውን ታሪካቸውን ለመከላከል መንቀሳቀስ ሲጀመሩ የተከፋፋሉ የወስጥ ማንነቶች፣ የታሪክ ሽሚያዎችና የባህል ሽኩቻዎች እንቅፋት ያልሆኑባቸው አገሮች ናቸው። 

እነዚህ ሃገሮች አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ሁሉንም የሃገራቸውን ህዝብ ለአንድ አላማ በተጠንቀቅ እንዲቆም፣ በአንድ ላይ በአንድ አቅጣጫ እንዲተም ማድረግ ይችላሉ።  አድርገውታልም። የታወቁት የጃፓን የአጥፍቶ ጠፊ (የካሚካዚ) ፓይለቶችና የጃፓን ወታደሮች የዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ተራራን በአካፋና ዶማ ንደው የሚደለድሉ፣ መከራ የማይበገራቸው የ1940 እና 1950ዎቹ የቻይናወ መሪ የማኦ ዜዱንግ ወጣት ተከታዮች ሌላ ምሳሌዎች ናቸው። 

ከዚህ ውጭ አንድ ባህል አንድ ቋንቋ አንድ እምነት የሚጋሩ ሆነው ወደ ዘመናዊነት የሚያደርጉት ጉዞ ከሽፎባቸው መከራቸውን የሚያዩት በርካታ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ናቸው። እንደ ሩቅ ምስራቅ ሃገሮች  የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች በፍጥነት ወደ ልማት መግባት የተሳናቸው የቀድሞ ስልጣኔና ማንነታቸው የሚመጥን እድገት ማስመዝገብ ያልቻሉት በምእራባውያን ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ የቅኝ አገዛዝ ስር በመውደቃቸው ነው። 

ቅኝ ገዥዎች  የመሃከለኛው ምስራቅ ሃገሮችን በጋራ የሚያስተሳስራቸው እሴቶች አውደመው ችግር ውስጥ እንዲወድቁ ያደረጓቸው ሃገሮች ናቸው። ዛሬ በዘመናዊነትና በባህላዊነት (modernization and tradition) መካካል በአረብ ሃገራት ወስጥ የሚታየው አውዳሚ ሽኩቻ የዚህ የምእራብ ሃገራት የቅኝ ተገዥነት ቅርስ ውጤት ነው።

በርካታዎቹ የአረብ ሃገራት በጃቸው ባለው የነዳጅ ሃብት ላይ የተመሰረተ የቀድሞውን የአረብና የእስልምና እምነት ስልጣኔ የሚመጣን በቴክኖሎጂና በሳይንስ ምእራባውያንን ሊያስከነዳ የሚችል ከራሳቸው ማንነት ጋር የተዋሃደና ያን ማንነት ለመከላከል ታቅዶ የተገነባ ዘመናዊ ስልጣኔ የሌላቸው የሆኑት ለዘመናዊነት የሚሆነው የሞራልና የመንፈስ ስንቃቸው በቅኝ ገዥዎች የተበላ በመሆኑ ነው።

አረቦች፣ አሜሪካኖችና እንግሊዞች እንዳሻቸው የሚያደርጓቸው ናቸው። የምእራባውያን የሸቀጥ ማራገፊያ ናቸው።  ከአረብ ህዝብ የሚዘረፍ ሃብት በምእራባውያን ሆቴሎች ካዚኖዎች ይጠፋል። ውድ ቤተመንግስቶች ይገነባበታል። ለምእራብ መንግስታት መሪዎችና ባላስልጣናት ውድ ስጦታ ይሰጠበታል። በየምእራብ ሃገሮች ባንኮች ታጭቆ ይገኛል።  አንድ አይነት ለአረብ መነቃቃት መሰረት የሚሆን የአረብ ፍልስፍና ሳይኖር አረቦች ከገቡበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ከሰላም ማጣት ከምእራባውያን አሻንጉሊትነት ነጻ መውጣት እንደማይችሉ ግልጽ ሆኗል። እኛም ከድህነት ጋር ከአረቦች የባሰ ሁኔታ ውስጥ የገባን እንዳውም የፈረንጆቹ ብቻ የእነዚህ አረቦች መጫወቻ መሆናችንን አንዘንጋ። 

ወደ አፍሪቃ ስንመጣ፣ የትኛውም ሃገር የአንድ ቋንቋ እምነትና ባህል ተላባሽ ሆኖ አናገኘውም። ሁሉም ሃገሮች ከኢትዮጵያ በስተቀር በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች የተፈጠሩ ናቸው። አፍሪካ ውስጥ  አንዱ ቁንቋ ባህል እምነት በአካባቢው የሚገኘውን ሌላ ቋንቋ እምነትት ባህል ጨፍልቆ አውሮፓውያኑ በሄዱበት መንገድ ተጉዞ ሃገር መፍጠር የቻለ የለም።

በአፍሪካ ውስጥ በአንድ ሃገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ የዘውግ ማህበረሰቦች መኖርና የርስበርስ መሳሳብ በአንድ ላይ መደረግ ለሚገባው የጋር የዘመናዊነት እንቅስቃሴ እንቅፋት እንደሚሆን የታወቀ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ትልቁ የአፍሪካ ሃገሮች ችግር የተለያዩ ብሄረሰቦች በአንድ ሃገር መገኘታቸው አይደለም።  እየአንዳንዱ ሃገር እንደ ምስራቅ ሃገራት ዘመናትን የተሻገረ ከማንነቱ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ሌሎች በሰልጣኔና እና በጉልበት እንዳይጨፈልቁት ሊከላከለው የሚሻው የጋራ የሚለው ሃገራዊ የባህልና እና የታሪክ እሴት የሌለው መሆኑ ነው።

ይህ ችግር በየአንዳንዱ አፍሪካ ሃገር ምእራባውያን ቅኝ ገዥዎች ተተውት ከሄዱት የራሳቸው የባህል፣ የቋንቋ፣ የታሪክ ተጽእኖ ጋር ተደምሮ የአፍሪካን ሃገሮች እንደ ምእራብና እንደ ምስራቁ ሃገሮች በፍጥነት ዘምነን፣ ምእራቡም ሆነ ምስራቁ ሊይሳደር የሚችለውን ተጽእኖ እንቁቋም የሚል የውስጥ ግፊት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። አፍሪቃውያን ሌላው ሁሉ ቀርቶ ፈጣሪ በሰጣቸው፣ ከሁሉም የሰው ዘር በፊት የነሱ ሃብት በነበረው ለነጩና ቢጫው ባስተላለፉት ሁሉን ቀዳሚ የሰው ልጅ የመልክ ቀለማቸው፣ የፊት ቅርጻቸውና ጸጉራቸው ሳይቀር የሚያፍሩ ፍጥረቶች እስከመሆን ደረሰዋል።

“አፍሪካውያን ወደ ዘመናዊነትና ገናናነት ለማምራት አንድ አይነት አፍሪቃዊ ፍልስፍና ያስፈለገናል፣ ይህን ፍልስፍና የህልውናችን ዋስትና አድረገን በመነሳት ብቻ ነው ከገባንበት ውርደትና ወደፊት ከሚያጋጥሙን አደጋዎች መትረፍ የምንችለው” የሚለው የአፍሪካ ምሁራን እሪታ የበረታው ለዚህ ነው።  

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ከምእራብ፣ ከምስራቅ፣ ከመካከለኛው ምስራቅና ከአፍሪካ የተለየ ሁኔታ እናገኛለን። ኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎች እምነቶች ለረጅም ዘመን በአንድ ላይ ከሞላ ጎደል በአንድ  ሃገር ውስጥ የተገኙባት ሃገር ናት። በዚህ ሃገር ውስጥ ማለቂያ የሌላቸው የመገበር የማስገበር የመውረና የመወረር ታሪኮች ቢኖሩም፣ የትኛውም  የቋንቋ የባህል የእምነት ማህበረሰብ ሌሎቹን ጨፍልቆ የአውሮፓ መንግስታት የፈጠሩትን አይነት የአንድን ቋንቋ፣ እምነትና ባህል ያለው ህዝብና ሃገር መፍጠር የቻለ የለም። 

አለመሆኑንም እያየነው ነው።  በጦርነትና በወረራ ማንነታቸውን ያጡ ጠቅለው የወደሙ ማህበረሰቦች የሉም ማለት አይደለም። ይህን ሆኖም የቋንቋ የእምነት ብዝሃነታችንን አለምም እኛም እናውቀዋለን።

“ለምን በየጊዜው የመጡ ሃይለኛ ነገስታት ባላባቶች ወይም ኤሚሮች የአውሮፓ መሪዎች እንዳደረጉት አንድ ወጥ የቋንቋን የባህልና የእመነት ሃገር መፍጠር አልቻሉም” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “በዋንኛነት የበላይነት ካገኙት ንጉሶች ወይም ባላባቶች ወይም ኤሚሮች የዘመናዊ መንግስት ምስረታ አቅም ጋር የተያያዘ ነው” የሚለው ነው። አውሮፓውያኖቹ ዘመናዊ ሃገር ምስርታ ወረራና ውጊያ ውስጥ ሲገቡ ከባላባታዊ የኢኮኖሚ፣ የአስተዳደርና የአመራረት እድገት ደርጃ እየወጡ የበሩበት ወቅት ሲሆን፣ የኛ ሃገር ምስረታ ከጥንት የጀመረ ፍጹም ባህላዊ በሆነ መንግስታዊ አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የተከናወነ መሆኑ ነው።

በኢትዮጵያ የተደረጉት የትኛዎቹም የግዛት ማስፋፋት ወረራዎች አውሮፓውያኖቹ ደርሰውበት በነበረው የማህበረስብ የእድገት ደረጃ በደረሱ የአካባቢው ሃይሎች ተከናውኖ ቢሆን ኖሮ ወረራውን ተከትሎ ይመጣ ይችል በነበረው ፈጣን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ለወጥ ዛሬ አብዛኛዎቹ ወይም ሁሉም ቋንቋዎች፣ ባህሎች ጠፍተው ኢትዮጵያ የአንድ ወጥ ቋንቋና ባህል ሃገር ትሆን ነበር። በፈረንሳይ፣ በጣሊያን በጀርመን በሌሎች የአውሮፓ ሃገሮች የሆነው ይህ ነው። በኢትዮጵያ ግን አልሆነም።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደሌሎች የመካከለኛው እና የአፍሪቃ ሃገሮች በቅኝ ባላመገዛቷ ከቅኝ ገዥዎች የተረከበችው ማንነትንም ባህልን የሚቦረቡር በፍጥነት የመዘመን ፍላጎት የሚያደናቅፉ  የመንፈስና የሞራል ስንቅ የተራበች ሃገር አይደለችም።

ይህም ሆኖ በዘመናዊነት እንደገነኑት ምእራባውያንና ምስራቃውያን ሃገሮች ተዘጋጀቶ የተቀመጠ፣ አንድ ቋንቋ ከሚናገር፣ አንድ ባህል እና እመነት ከሚጋራ ማህበረሰብ በቀላሉ ሊቀዳ የሚችል አንድ ወጥ የማንነት እሴት የላትም። በዚህ መንገድ የሚቀዳ እሴት የላትም ማለት አለማዊ ልዩ ተፈጥሯዋን የሚያንጸባርቅ የራሷ የሆነ እሴት የላትም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ የብዙ ባህል ቋንቋ እምነት ያሏቸው ማህበረሰቦች ሃገር መሆኗ አንድ ወጥ ሃገራዊ እሴታችን፣ አንድ ወጥ ብሄር እንዳለባቸው ማሀበረሰቦች ያለ ምንም ድካም ለሁሉም ፍንትው ብሎ ይታያል ማለት አይደለም።

እንግዲህ ከዚህ በላይ እንዳቀረብኩት ለፈጣን የዘመናዊ እድገት ሃገሮችን እንዲነሱ የሚኮረኩረው የአንድ ሃገር ህዝብ ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ትውፊቱን፣ እምነቱን  በጥቅሉ ማንነቱን ከሌሎች ሃይሎች ወረራና ጭፍለቃ ለመከላከል ነው ብያለሁ።  ይህ ሃቅ የበርካታ የዘመኑ ሃገሮች የመዘመን ግፊት ምክንያት እንደሆነ በተጨባጭ መረጋገጡ ላይ ጥያቄ የማናነሳ ከሆነ ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ የሚከተለው ይሆናል።

በፍጥነት የመዘመን ፍላጎትና ውስጣዊ ግፊት የሚመጣው ታሪክን፣ ባህልን፣ ቋንቋን፣ ተውፊትን፣ እምነትንና ማንነትን ለመከላከል ሲባል ከሆነ የብዝሃን ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ ይህ የመዘመን የእሽቅድድም ግፊት ከየት ልታመጣው ነው የሚል ነው። 

የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፣ አንድ ህዝብ በፍጥነት ለማደግ የሚተጋው ማንነቱን፣ ምንነቱን ባህሉን ቋንቋን ከሌሎች ወራሪዎች ለመከላከል ካለው ትልቅ የክብርና የኩራት ፍላጎት ጋር በተያያዘ ነው ካልን፣ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው የብዝሃን ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ የትኛውን ማንነት፣ የትኛውን ባህል፣ ቋናቋ፣ የትኛውን ክብርና ኩራት ለመከላከል ነው ህዝብ በህብረት በአንድነት ተባብሮ ዶ/ር አብይ እንደሚለው ተደምሮ ለዘመናዊነት ለብልጽገና ለሰለጠነ አስተዳደር የሚተጋው?

ባለፉት ጥቂት መስመሮች እንዳቀረብኩት የዘመናዊ ማህበረሰብ ግንባታ ፍላጎት የሚመመነጨው ቀጥተኛ ከሆነ ወይም ካልሆነ የባህል የማንነት ወረራና መጨፈለቅ ራስን ለመከላከል ከሆነ ቀጥሎ ደግሞ የሚነሳው ጥያቄ በኢትዮጵያ ወስጥ የሚገኙ የተለያዩ በባህል በቋንቋ በትውፊት ልዩነቶች ላይ የተመሰረቱ ማህበረሰቦች የየራሳቸውን ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ ትውፊትና እምነት በተናጠል ይዘው እሱን ለመከላከል ሲሉ ወደ ዘመናዊና ፈጣን እድገት መግባት ይችላሉ ወይ የሚለው ነው? ካልሆነስ እንዴት በጋራ ሆነው በፈጥነት ለዘመናዊ እድገት መነሳት ይችላሉ?

በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ እንደሃገር ማዘመን ካልተቻለ እንዴት ሆኖ ነው ሁሉም ባህልና ቋናቋ ተላባሾች በተናጠል እራሳቸውን ማዘመን የሚችሉት ? በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማህበረስቦች ራሳቸውን ወደ ተፋጠነ ዘመናዊ እድገት ለመምራት በቅድሚያ ራሳቸውን፣ አካባቢያቸው ከሚገኙ ሌሎች ቋንቋዎች ባህሎች ተላባሾች ለይተው የኔ የሚሉትን የተለየ ማንነት የያዘ ግዛት ሊያስፈልጋቸው ነው? 

በዚህ መንገድ ሄደው የተሳካላቸው ከ19መቶ ክፈለ ዘመን መባቻ ላይ ራሳቸውን ሃገር ማድረግ የቻሉ የአውሮፓ ሃገሮች ብቻ ናቸው። ያ ዘመን አልፏል። ባለንበት ዘመን ይህ አካሄድ በኢትዮጵያ ውስጥ መሳካት ይችለል ወይ?

የሃገሪቱ አፈጣጠር፣ የብዝሃነቷ ግዙፍነት፣ ህዝቡ በባህል፣ በእምነት፣ በደም፣ ከምስራቅ እስከ ምእራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ የተጋመደበት ሁኔታ፣ በባህል በእምነት የኔ ናቸው የሚላቸው እሴቶችና ቅርሶች በመላው ሃገሪቱ በተበተኑበት ሁኔታ፣ እነዚህን ቅርሶችና የሀገሪቱን የግዛት አንድነት ከወራሪዎች ለመከላከል ሁሉም ከየቀየው እየተመመ ከቀየው ውጭ ከተለያዩ የወጭ ወራሪዎች ጋር በተደረጉ ውጊያዎች ደሙን እያፈሰሰ የተከላከለበት ሁኔታ፣ ይህን በተለያዩ ማንነቶች ላይ  የተመሰረቱ የነፃ ግዛት ግንባታ ይፈቀዳል ወይ?

ከሰማኒያ በላይ የባህልና የቋንቋ አሃዶች አሉንና ከኢትዮጵያ ሰማንያ አገር ወጥቶ ሰማንያውም በከፍተኛ ፍጥነት የዘመነው አለም ላይ ለመድረስ የሚያስችል አቅምና እሴት ይኖራቸዋል ወይ? በየትኛውም አመክንዮ ይህ መንገድ ሙት መንገድ ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ብዙ ደጋፊ ሊኖረው የማይችለው ለዚህ ነው።

ታዲያ ሌላው አማራጭ ምን ሊሆን ነው? ኢትዮጵያ የአንድ ባህል ቋንቋ፣ እምነት፣ ትውፊት ተላባሽ ህዝብ ሃገር ካልሆነች፣ ሃያላን እና አስፈሪ የሆኑ ነጮችና ቢጫዎች የሚያሳድሩባትን ጫና ወደፊትም ሊያስከትሉባት የሚችሉትን  አደጋዎች ለመከላከል ለፈጣን እድገት በመኮርኮሪያነት የምትጠቀምበት፣ ማንነት፣ ትውፊት፣ ታሪክ፣ ባህል እምነት ምን ሊሆን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ የማያወላዳ ነው። “የብዝሃን ማንንነት ላይ የተመሰረተ” የሚል ከመሆን ውጭ ሌላ መሆን አይችለም።

ይህ ውስብስብ የሆነ የሚመስል  የብዝሃን ማንነት ራሱ ኢትዮጵያዊ ማንነት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ይህን ማንነት መሰባሰቢያ አድርጎ የሃገሪቱ ህዝብ በአንድነት መቆም ይችላል። ያለውን ጉልበት፣ አቅም፣ ሃብት፣ አሰባስቦ ሃገሪቱ እንደሃገር፣ ህዝቧ ከነብዝሃነቱ ወደፊት በዘመናዊ ስልጣኔ እንዲገሰግስ የሚያደርግ የመንፈስና የሞራል ስንቅ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ውስጥ ማግኘት ይችላል። ብዙዎች እንደሚሰጉት ይህ ስራ ከባድ ስራ አይደለም። 

ለዚህ ስራ መሰረት የሚሆነው መደላድል ለዘመናት በጋር ሲገነባ ስለነበር እንደሌሎች አፍሪካ ሃገሮች ከዜሮ አንነሳም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስፈሪ ቡርቦራ ቢካሄበትም ጠቅሎ አልወደመም። እኛ ማድረግ የሚገባን እንደ አውሮፓውያኖች ዳዋ እንዲለብስ አቧራ እንዲሸፍናቸው የተደረጉትን የቅርብና የሩቅ የጋራ ታሪኮቻችንን ዳዋና አቧራቸውን ገፈን የዘመናዊ እድገት ፍላጎታችን መኮርኮሪያ ማድረግ ብቻ ነው። 

በሌሎች የተለያዩ ማንነቶች ባሉባቸው አፍሪካ ሃገሮች እንዲህ አይነቱን ሃገራዊ ፍልስፍና እንገንባ ቢባል ሊያስቸግር ይችላል። ምክንያቱም ነጮች በጉልበት ማሰባሰቢያ ካደረጉት የቅኛ ተገዥነት ሙጫ ውጭ የየአንዳንዱን አፍሪካ ሃገር የተለያዩ ማህበረሰቦችን አንድ አድርጎ የሚያስተሳስራቸው የጋራ ታሪክ የላቸውምና። ብዙዎቹ ሃገሮች የጋራ መሰባሰቢያ የሚሆኑ ነገሮች ለማግኘት አበሳቸውን እያዩ ነው።  ለዚህ ነው የአፍሪቃ ምሁራን የናጀሪያ፣ የጋና፣ የደቡብ አፍሪቃና ውዘተ ፍልስፍና ሳይሆን እነዚህን ሃገሮች የሚሻገር  ሰው ሰራሽ የቅኝ ገዥዎችን ድንበር የሚንድ የአፍሪቃን ህዝብ አንደ አንድ ሰው ሊያስተሳስር የሚችል ፍልስፍና ያስፈልገናል ያሉት።

  1. ኢትዮጵያ ልዩ የሆነ ከራሷ አልፎ የአፍሪካ መዘመኛ የሚሆን ፍልስፍና ያላት ሃገር፤

ከሌሎች አፍሪካ ሃገሮች በተለየ ሁኔታ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ማህበረሰቦች ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ ትወፊት መትረፍ የቻለው ሁሉም በጋራ ይህን የየአንዳንዳቸውን ማንነት ሊያጠፋ ባህር አቋርጦ የመጣን ጠላትን በጋር በመመከታቸውና በጋራ ድል ማድረጋቸው መሆኑን ያውቁታል።

በጋራ ተከላክለን ያተረፈነው ብዝሃንነታችን ነው ስንል ትንሽ ከሚመስል ነገር ይጀመራል። ከቋንቋ ከባህል በታች ከሚወርድ ነገር።

ኢትዮጵያ ሁሉን አይነት የመልክ፣ የቀለም አይነቶች ያሏት ሃገር ናት። አዎ ሁላችንም ጥቁር ነን። ይህን አላጣሁትም። በራሳችን አይን ግን ነጭነት የሌለብን በጥቁርነት ወስጥ የሚገኙ የተለያዩ የቀለም ዝርያዎች ያቀፈ ዥንጉርጉር ህዝብ ነን።

የዛሬ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ ሶማሌነት፣ ጉራጌነትና ወዘተ የተረፈው አደዋ ምድር ላይ ኦሮሞ፣ አማራውም፣ ጉራጌው፣ ትግሬውና ወዘተ ደሙን በጋራ አፍሶ አጥንቱን ከስከሶ ነው።

የእምነት የቋንቋ የባህል ልዩነታችን የድክመታችን ምንጭ ሆኖ፣ አድዋ ላይ በጋራ ተሰባስበን ጣሊያንን ማሸነፍ ባንችል ኖሮ፣ ዛሬ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግራዋይነት፣ ሲዳማነት፣ የሚባል ነገር አይኖርም ነበር።

ክርስትና፣ እስልምና፣ ዋቄ ፈታ፣ አክሲዮም ጽዮን፣ ላሊበላ፣ አልነጃሺ፣ እሬቻ፣ ጨምበላላ፣ ገዳ፣ ቡሄ፣ አሽንዳ፣ አተቴ፣ ሌሎችም በተለያዩ ብሄር ብሄርሰቦች ወስጥ የሚገኙ ድንቅ የእምነት የባህል እሴቶችቻን አይኖሩም ነበር። የሺ ዘመናት እድሜ ያላቸው የተዋህዶ ክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት መትረፍ የቻሉት ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ ጎን ሙስሊሙ ከከርስቲያኑ ጎን አድዋ ላይ ወድቆ ነው።

እሬቻ የተረፈው፣ እሬቻ ዛሬ በአል ሆኖ የሚከበረው ኦሮሞና አማራ አንድ ላይ ከሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ጋር በጋራ ጣሊያንን ስለሰበሩት ብቻ ነው። የዘመኑ የኦሮሞ የዋህ ልሂቅ  እንደሚለው ኦሮሞው አማራውን ወይም አማራው ኦሮሞውን ሰብሮት ቢሆን ኖሮ እንኳን እሬቻ ሁላችንም አንኖርም ነበር። አማራና ትግሬ ብቻቸውን አድዋ ላይ ገጥመው ጣሊያንን ገጥመው ተሸነፈው ቢሆን ኦሮሞነት አይኖርም ነበር።

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በመቶ ሚሊዮኖች ተከታዮች ያሏቸው፣ ታሪክ የራሱን የዘመናት አሻራ ያሳረፋባቸው፣ ከማንነታችን ጋር የተጋመዱ የክርስትና እና የእስልምና ልዩ እምነቶች አሉን። አድዋ ላይ ተሸነፈን ቢሆን ኖሮ እምነቶቻችንም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ ወይም እስልምና ወይም ዋቄ ፈታ ወይም ሌላም ሃገራዊ እምነት መሆኑ ቀርቶ ጣሊያኖች የሚጭኑብን የጣሊያኖች እምነት ብቻ  ይሆን ነበር። 

ከዛም በታች ተዋርደን ሁሉም ቀርቶ “ደግሞ ለባሪያ የምን  እምነት” ተብለን እንደ ውሻ በቤተእምነት ደጃፍ ላይ እንዳንደርስ እንደረግ ነበር። 

የብዝሃነታችን ሚስጥር አንድነታችን ለመሆኑ ትንሽ ሰፋ አድርጎ ማሳየቱ ወደፊት ለማቀርበው የመደመር እይታ ጠቃሚ ስለሆነ ልቀጥል። 

ስማችን ኦኬሎና አርዬት፣ ለሜሳና ጫልቱ፣ ሃጎስና ሃዳስ፣ ሃሰንና ዘይነብ፣ ሃይለ ሚካኤልና ወለተማሪያ፣ አንበርብርና ተዋበች፣ ዘበርጋና ኬርየዢ፣ ኤራቶና መፋያት፣ በርገኖና ጫኪሴ፣ ገቲሶና ሚሸሜ፣ ግሽና እና አቸም፣ ወዘተ የሚል ሆኖ የምናገኘው አያቶቻችን በጋራ ብዝሃንነታችን ሲከላከሉ ደማቸውን በማፍሰሳቸው አጥንታቸውን በመከስከሳቸው ነው።

ቅደመ አያቶቻችን በጋራ ጣሊያንን መመከት ተስኗቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሁሉም የእዚህ ሃገር ወንድና ሴት በሙሉ ሰብአዊ ክብራችንን ገፎ በባርነት ሊገዛን ባህር አቋርጦ መጥቶ በነበረው በጣሊያን የባሪያ ገዥ ስም ነበር የምንጠራው። ወንዱን ከዚህ መልስ “ማሪዎ” ተብለሃል ሴቷን ደግሞ ከዚህ መለሰ “ማርገሪታ” ተብለሻል እየተባለ የጅምላ ስም ይታደለን ነበር። ለባርነት በተዳረጉ በሌሎች ሃገሮች ይህ የስም አሰጣጥ ተግባራዊ መደረጉን አንርሳ!

ልብሳችን፣ ምግባችን፣ ሙዚቃችን፣ ጭፈራችን፣ ቋንቋችንና ተውፊታችን እንደ ብዝሃነታችን የተዋበና ያማረ ሆኖ መትረፍ የቻለው በጋራ አድዋ ላይ የወደቁ የቅደመ አያቶቻችን የመስዋእትነት ልጆች ስለሆነን ብቻ ነው።

አድዋ ላይ ተሸንፈን ቢሆን  አለባበሳችንም አመጋገባችንም አንድ ወጥ የጣሊያን አለባበስና አመጋገብ፣ መልካችንም የጣሊያን ዲቃላ፣ ነጫጭባ፣ ሙላቶ ይሆን ነበር።

አድዋ ላይ ተዋርደን ቢሆን ኖሮ ሁላችንም የምንናገረውም ቋንቋ ጣሊያንኛ ይሆን ነበር። ወይም ከጣሊያን ጋር ተስማማተው ኢትዮጵያ ላይ የሰፈሩ አውሮፓውያን ጌቶቻችን ቋንቋ ይሆን ነበር።

ዛሬ የልዩነትና የመጋጫ ምክንያት አድርገን የምናቀርበው የዘውግ ማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የዘር ልዩነት ወድሞ፣ ተጨፍልቆ እንደሰው በኩራት ሳይሆን፣ ጣሊያን በፋብሪካው ከሚያመርተው ርካሽ የፋብሪካ እቃ ወይም በገመድ ጣሊያኖች አስረው በየፓርኩ ከሚጎትቷቸው ውሾች የተለየ ማንነት የማይኖረን፣ ከቢጫው ዘር በታች የተመደብን የመጨረሻው የተዋረድን የአለም ፍጥረቶች ሆነን እናርፈው ነበር። ያም እድለኞች ከሆንን እንጂ፣ እንዲህ አይነቱ እድል ላይገጥመን ይችል ነበር።

ኢትዮጵያ በብዝሃነት ያሸበረቀችው፣ የኢትዮጵያ ልጆች በቅኝ ከተገዙ የአለም ህዝቦች የተለየን ሆነን የተረፍነው፣ ነጭ ከኛ የተለየና የተሻለ ፍጡር ነው ብለን የማናምነው፣ በአለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን መራመድ የቻልነው፣   የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋና ሌሎችም ብዝሃነታችን የሚያንጸባርቁ እሴቶቻችን ማትረፍ የቻልነው፣ በጋራ የቆሙ በጋራ የወደቁ ቅድመ አያቶቻችን ልጆች ስለሆንን ነው። 

አማራውን የኦሮሞው ኦሮሞውን የአማራው ትግሬውን የጉራጌው ጉራጌውን የትግሬው፣ ሲዳማውን የሱማሌው ሱማሌውን የሲዳማው ልጅ የሚያደርገው የኛ ቅድመ አያቶች አንዳቸው ለአንዳችን መትረፍ ተያያዘው በጋራ መስዋእትነት በመክፈላቸው ነው።

ምኒሊክ ከመላው ኢትዮጵያ አድዋ ላይ እንዲሰባሰብ የጠራው ህዝብ ሳይገኝ ቀርቶ ቢሆን፣ ተገኝቶም በወኔና በጀግነት ሳይዋጋ ቀርቶ ቢሆን የዛሬው የየግላችን የማንነታችን መለያ አድረገን መናቆሪያ ያደረገነው ቋንቋችን፣ ባህላችን፣ እምነታችን፣ የኔ ነው አትድረሱብኝ የምንለው አሰፋፈራችን ያበቃለት ነበር።

በ19ኛው ምእተ አመት መጨረሻ፣ ነጮች ለጥቁር ዘር የደገሱት ድግስ ምን እንደሆነ በደንብ ለሚረዳ፣ የእኛ ቅደመ አያቶች አድዋ ላይ ተሸንፈው ቢሆን ኖሮ አገራችንን  ባህር አቋርጦ ለመጣ ጠላት ማስረከብ ብቻ ሳይሆን እንደሰው በዚች ምድር ላይ መኖራችንም አጣራጣሪ ነበር።

የነጮች ህልም በተፈጦሮ ሃብት፣ በመልካም አየር ጠባይና በመሬት ስፋት የታደለችውን አፍሪካ ከውስጧ ነባሩን የጥቁር ዘር  አጥፈተው እንደ አውስትራሊያና እንደ ሰሜን አሜሪካ የነጮች መፈንጫ ለማድረግ ነበር። አላማቸው ለአውሮፓ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ሃብት ከአፍሪካ መውሰድ አልነበረም። የቅኘ ግዛት አላማቸው ጥሬ እቃው ፍለጋ መሆኑ ቀርቶ ሰው ማስፈሪያ ፍለጋ ሆኖ ነበር።

ስለሆነም ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በአድዋ ድል ስንኮራ የሚያይ የጥቁር ዘር በሙሉ እኛም  የተረፍነው በእናንተ ቅድመ አያቶች መስዋእትነት ነው። ክብር ለአድዋ ሰማእታት” የሚለን።

አድዋ ላይ ቀደምቶቻችን ጣሊያንን ድል በመንሳት ያተረፉት ከብዝሃነታችን ጋር የተያያዙ የየአካባቢያችን ትውፊቶች፣ የታሪክ ቅርሶችና ቁንቋዎች ብቻ አይደለም። እነዚህ የየአካባቢውን እምነቶች፣ ተውፊቶች፣ የታሪክ ቅርሶች፣ የሁሉም የሃገሪቱ ህዝብ ሃብቶች እንዲሆኑ በማደረግ ጭምር ነው።

ለወላይታው ወጣት የአክሱም ሃውልት ትርጉም የሚሰጠው ያለ እሱ ቅድመ አያቶች የአድዋ ምድር መስዋእተነት አክሱም የጣሊያን እንጂ የትግሬ ሃገር አለመሆኗን፣ ሃውልቱም የኢምፔሪያል ጣሊያን የድል አድራጊንት ምልክት እንጂ የአንድ አፍሪካዊ ህዝብ የታላቅ ስልጣኔ ማስታወሻ እንደማይሆን ስለሚታወቅ ነው።  ሌሎችም ከደቡብ እስከ ስሜን ከምእራብ እስከ ምስራቅ ያሉ የታሪክ ቅርሶች በሙሉ የአካባቢው ሳይሆኑ የመላው የሃገሪቱ ዜጎች መኩሪያና መመኪያ ቅርሶች ተደርገው የሚታዩት በዚህ ሎጂክ ነው። ያለሁሉም መስዋእትነት አንዳቸውም አይተርፉምና ነበርና ነው።

አድዋ ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎችን ብቻ አይደለም ያተረፈው። የትግርኛ የአማርኛ፣ የግእዝ ቋንቋዎች የሚጻፍባቸውን ብቸኛውን የጥቁር ህዝብ የሳባ ፊደልንም ጭምር ነው ያተረፈው። ያለኦሮሞ፣ ያለከምባታ፣ ያለጉራጌ፣ ያለአፋርና ሌሎችም ህዝቦች ደም አማርኛ ብቻ ሳይሆን ቁንቋው የሚጻፍበትም ፊደል አይተርፍም ነበር። 

ለዚህ ነው “አንድ ኦሮሞ ይህን ብቸኛ የጥቁር ዘር የሳባ ፊደል የኔም ፊደል ነው። ለትግሬና ለአማራ ብቻ የሰጠው ማነው” ማለት የሚችለው። አፋሩም፤ ወላይታውም፣ ከንባታውም፣ ሱማሌውም፣ ሃድያውም፣ ሲዳማውም ይህን የማለት ሙሉ መበት አለው። ጋምቤላውና ቤንሻንጉሉ ሌሎችም በርካታ የደቡብ ብሄረሰቦች የኔ ነው ብለው እየተጠቀሙበት ነው። 

የጥቁር ዘር ብቸኛው ፊደል ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ደማቸውን ገብረው ያተረፉት ፊደል ነው። የትኛውንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝን ቋንቋ፣ ባህል፣ ተውፊትና ሌላውንም የታሪክ ቅርስ፣ በየትኛውም የሃገሪቱ ግዛት ውስጥ የሚኖር ዜጋ የኔ ጭምር ነው የማለት የሞራል ልእልና ያለው ለዚህ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል በነጻነት እንዳሻው የመኖር፣ ሁሉም ክልል ውስጥ የሚገኝ የከተማና የገጠር መሬት፣ በከርሰ ምድርና ከከርሰምድር በላይ የሚገኝ ሃብት የኔ ነው የማለት ሙሉ መብቱን የተጎናጸፈው የዚችን ሃገር መሬትና ሃብት የወጭ ወራሪዎች መሬትና ሃብት እንዳይሆን በጋራ ቅድመ አያቶቹ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ከየቀያቸው እየወጡ በጋራ ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የተከላከሉት በመሆኑ ነው። 

ማንኛውም ብሄር ወይም ብሄረሰብ ዛሬ የሚኖርበትን ክልል ለብቻው ከውጭ ወራሪ ተከላክሎ ባላዳነበት ሁኔታ “ይህ ክልል የኔ ብቻ ነው” አትድረሱብኝ የሚል ንግግር ምንም አይነት የታሪክም ሆነ የሞራል ቅቡልነት ሊኖረው አይችልም። 

ደግሞ ደጋግሞ በታሪክ እንደታየው፣ የታሪክ ጸሃፊዎችም እንደሚያስገነዝቡን ሀገራትን ሃገር ከሚያደርጋቸው ትልቁና ጠንካራ ኩነት ዋናው የአንድ ሃገር ህዝቦች ራሳቸውን ከወራሪ ጠላት በመከላከል በጋራ የከፈሉት መስዋእተነትና በጋራ የሚተዳጁት ድል ነው። አድዋ የዘመናዊት ኢትዮጵያ የሃገር መሰረት የሆነውም፣ ከመሆንም ውጭ አማራጭ እንዳይኖረን ያደረገው በዚህ ታሪካዊ ትርጉሙ የተነሳ ነው።

ሌላው ከአድዋ ድል ጋር ተያይዥነት ያለው፣ የዛ ድል ምልክት ወይም ምስል ሆኖ በመላው የጥቁር ዘርና በአለም ህዝብ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ነው።

በአድዋ ምድር ላይ የተሰለፉት ከመላው ሃገሪቱ የተሰባሰቡ ጀግኖች የኢትዮጵያዊነታቸው መለያ አድርገው ያውለበለቡት የኢትዮጵያን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለውን ስነደቅ አላማ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የብዙ መቶዎች አመታት እድሜ እንዳለው ይታወቃል። የሩቁን ዘመን ታሪክ እንተወው። ምክንያቱም በዛ ዘመን የኢትዮጵያ አካል አልነበርንምና የዛ ዘመን የሰንደቅ አላማ ታሪክ አይመለከተንም የሚሉ አሉና።

ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን በምንጠራት ሃገር ውስጥ ለረጅም ዘመን የሚታወቀው ሰንደቅ አላማ ይኼው የዛሬው ሰንደቅ አላማ ብቻ እስከሆነ ሌላ ተግደርዳሪ ሰንድቅ አላማ እስካልነበረ ድረስ በየትኛውም ወቅት የሃገሪቱ ህዝብ አካል የሆነ ህዝብ ይህን ሰንድቅ አላማ የራሱ አድርጎ ሊቀበለው የሚያስችለው ከሚገባው በላይ በቂ ምክንያት አለው። እንደሌላው ነገራችን የሰንደቅ አላማውም ታሪክ የተወሰነው አድዋ ላይ ነው። ስለሆነ ከአድዋ እጀምራለሁ።

ጣሊያን ድል አድራጊ እንደሚሆን ተማምኖ በአውደ ውጊያው ወቅት የሃገሩን መለያ የሆነውን  አረንጓዴ፣ ነጭና ቀይ  ባንዲራውን በኩራት አውለበለበ። ኢትዮጵያውያንም የሃገራቸው መለያ የሆነውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ  ሰንደቅ  አላማቸውን በኩራት አውለበለቡ። ኢትዮጵያውያን ድል ሲያደርጉ የጣሊያን ባንዲራ በአድዋ ምድር ላይ እንደ አልባሌ ነገር ወደቀ። የሽንፈትና የውርደት ምልክት ሆነ። በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ የተውለበለበው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ  ሆነ።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ  ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በዚህ ሰንደቅ አላማ  ስር የተሰለፈው ሁሉም ባለ እምነት ሁሉም ባለቋንቋ ሁሉም ባለ ባህል እንደሆነ ታሪክ ከትቦታል። ስለዚህም ነው ሰንደቅ አላማው ጥንታዊነትቱ አብቅቶ በኢትዮጵያ ህዝቦች የደም ጠበል ተነክሮ የሁሉም ማህበረስቦች ቋንቋዎች ባህልና እምነት ባለቤቶች ሰንደቅ አላማ የሆነው። 

ለዚህ ነው ይህን ሰነድቅ አላማ የትኛውም እምነት ተከታይ፣ የትኛውም ብሄር ወይም ብሄረሰብ የኔ ብቻ ነው ማለት የማይችለው። የኔ ብቻ ነው ለማለት ለብቻው ጣሊያንን መክቶ አላተረፈውምና ነው።

በአድዋ ምድር ከፍ ብሎ የተውለበለበውን ሰንደቅ አላማ ከውርደት ያዳኑት ሁሉም የሃገሪቱ ጀግኖች ልጆች ናቸው። ኦሮሞውም፣ አማራውም ትግራዋዩም፣ ጉራጌውም፣  ክርስቲያኑ ሙስሊሙም ናቸው። ለክርስትና እምነት መዳን በእዚህ ሰንደቅ አላማ ስር ተሰልፎ የወደቀው ሙስሊም ከፈለገ ይህን ሰንደቅ አላማ በቤተ መስጊዱ ላይ ማውለብለብ መበቱ ነው። 

ይህ ባንዲራ ከኔ እምነት ጋር ብቻ የተሳሰረ ነው ለሚለው የትኛውም አካል “እኔ ከጎንህ ባልቆም አንተም፣ እምነትህም ሰንደቅህም አይኖርንም ነበር” የሚል በሃቅ ላይ የተመሰረተ መልስ በለበ-ሙሉነት መመለስ ይችላል።

በሌላ በኩልም ይህን ሰንደቅ አላማ የሁለንተናቸው መገለጫ አድርገው የሚያዩ ዜጎችም ይህን የማድረግ ሙሉ መብት አላቸው። ማድረጋቸው ሊገርመን አይገባም። የሚያስገርመው ባያድርጉ ነበር። ምክንያቱም ባህላቸው፣ እምነታቸው ወይም ቋንቋቸው ብቻ ሳይሆን ህልውናቸውም ሳይቀር መትረፍ የቻለው ይህን ስነድቅ አላማ በሚያውለበልቡ የሃገሪቱ ልጆች መስዋእትነት ስለሆነ። 

ትልቁ ቁም ነገር የዚህ የሰነድቅ አላማ ባለቤት አንድ አካል ብቻ መሆን የማይችል መሆኑ ነው።። ይህን የማለት መብት ያለው ብቸኛ አካል በዚህ ሃገር ላይ እንደሌለ መረዳት ነው። የኛ ብቻ ነው ለሚሉ አካላት መልሳችን ያውላችሁ እንዳሻችሁት አድርጉት በማለት ቅድመ አያቶቻችን በደማቸው በአለም አደባባይ በኩራት እንዲውለበለብ ያደረጉትን ሰንደቅ አላማ ትተን ሌላ እሴት አላባ ሰንድቅ አላማ መፈለግ አይደለም። ይህን ማድረግ ለምን እንደማይገባን ተጨማሪ ምክንያት እነሆ፤

በአረንጓዴ ቀይና ቢጫው ሰንደቅ አላማ ስራ ቅድመ አያቶቻችን ተሰለፈው ያዳኑት ቋንቋችንን ትውፊታችን ብቻ ሳይሆን እንደሰው በዚች ምድር የመኖራችንን እድል ነው ያተረፉት። ከራሳቸው አልፈው፣ ከእኛ አልፈው፣ የጥቁር ዘርን በሙሉ ነው፣ ከዘላለማዊ ጥፋት ያዳኑት።

አባቶቻችን አድዋ ላይ ተሸንፈው፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ  ወድቆ የጣሊያን ሰንደቅ አላማ ተውሎብልቦ ቢሆን ኖሮ እኛን ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም የጥቁርን ዘር ከምድረ ገጽ የማጥፋቱ ሂደት ይጀመር የነበረው በሽንፈታችን ማግስት ይሆን ነበር።

አባቶቻችን ለነጻነቱ ያነሳሱት ጥቁርን ብቻ ሳይሆን የቢጫውንም ዘር እንደሆነ ከአድዋ ድል በኋላ እስያ ውስጥ የተቀጣጠለውን የነጻነት ትግል በዋቢነት በማጣቀስ የታሪክ ጸሃፊዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የአድዋ ድል የአለምን የታሪክ አቅጣጫ የቀየረ ታላቅ አለማቀፋዊ ኩነት ነው የሚባለው ለዚህ ነው። በዚህ የተነሳ መላው የጥቁር ዘር ኢትዮጵያውያን በጋራ አድዋ ላይ ያውለበለቡትን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማ  የጥቁርነቱና የነጻነቱ መለያ አድርጎ ወሰዶታል።

የጥቁር ዘር በሙሉ፣ “እነዚህ  አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት  የአንድነት፣ የቆራጥነት፣ የጀግንነትና የጽናት ምልክቶች ናቸው” አለ። “ከዚህ ሰንደቅ አላማ ጀርባ ያሉትን እሴቶች ከኢትዮጵያ ወስደን” አለ አፍሪካ “የአፍሪካን የተሃድሶ ፍልስፍና፣ ስሙን ኢትዮጵያዊነት ብለን ጠርተን፣ አህጉራችንን ትልቅ አህጉር እናደራጋለን” ብሎ ፎከረ።

አሜሪካኖች የቀድሞዎቹን የአሜሪካ ምድር ኗሪዎች አጥፍተው በጉልበት በያዙት ምድር ላይ የተከሉትን ባንዲራ በባርነት ቀንበር ተገፎ አሜሪካ የሄደ አፍሪካዊ ሳይቀር ባገኘው አጋጣሚ በኩራት የሚያውለበልብበትን ሁኔታ እያየን ነው። እኛ ቅድመአያቶቻችን በጋራ ነጭን በጀግንነት ያንበርከኩበትን የነጻነት የአልገዛም ባይ ምልክታችንን በተለያዩ ሰበብ አስባቦች የኔ አይደለም ወደሚል ሄደናል። 

ይህን የሚያዩ አፍሪካውያን፣ የአፍሪካ ማፈሪያ፣ የአፍሪካ ማድያት እያሉ እንደሚጠሩን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን?  

“የአፍሪካ ህልወና የአፍሪካ ስልጣኔ፣ የአፍሪካ ገናናነት አፍሪካዊ የፍልስፍና መሰረት ከሌለው እውን ሊሆን አይችልም። በነጮች ፍልስፍና አፍሪካን መገንባት አይቻልም።” ይህ የአፍሪካ ፍልስፍና፣ “ታሪክ አዋጭነቱን፣ ድል አድራጊነቱ በተግባር ያስመስከረው ኢትዮጵያዊነት ነው” በማለት አፍሪካውያን ወደ እኛ ሲያምትሩ እኛ ምን እያደረግን ነው?

አድዋ ሌላው የሰራው ነገር የኢትዮጵያን የሺዎች አመታታ የኋልኛዎቹ ቅድመ አድዋ ታሪካችንን የሁላችንን ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ የ3000 ዘመን ታሪክ ያላት ጥንታዊ ሃገር የሚል ትርክት አድዋ ላይ ተሸንፈን ቢሆን ኖሮ ያበቃለት ነበር። የ3000 አመት ታሪክ እኔን አይወክልም ለሚሉቱ ወገኖች ያ ታሪክ የእነሱ እንዲሆን አድዋ ላይ ቅድመ አያቶቻቸው መስዋእትነት ከፍለው ያዳኑት ታሪክ መሆኑን መገንዘብ ብቻ ይበቃቸዋል።

አድዋ የጥንቱን የሁላችንም እንዳደረግው ሁሉ ከአድዋ በኋላ የመጣውን ዘመን የሁላችን እንዲሆን አድርጎታል። ከአድዋ በኋላ በተድረጉ በርካታ አውደውጊያዎች ኢትዮጵያውን በጋራ መስዋእትነት እየከፈሉ ያቆይዋት ሃገር ናት ኢትዮጵያ።

መላው አፍሪካ ያልታደለው፣ በአለም ላይ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሃገሮችና ህዝቦች ያልታደሉትን እኛ ኢትዮጵያውያን በታሪክ አጋጣሚ ድንቅና  ልዩ ታሪክ ታድለናል። የውስጥ ችግራችን የፈለገውን ያህል ቁስል ይኑረው፣ በጋራ ራሳችንን እና መላውን የጥቁር ዘር ለማትረፍ የከፈልነው መስዋእትነት የትኛውንም የውሰጥ ቁስል እንዲሽር የሚያደርግ ትልቅ ድልና ትልቅ የጋራ እሴት ነው።

የወስጥ ችግራችን የፈለገውን ያህል ቁስል ይኑረው፣ በጋራ በቋንቋ በእምነት፣ በባህል፣ በትውፊት፣ በታሪክ ያሸበረቀ ብዝሃነታችን ለማትርፍ በጋራ የከፈልነው መስዋእትነትና የተቀዳጀነው ድል የትኛውንም የውሰጥ ቁስል እንዲሸር የሚያደርግ ትልቅ ድልና የጋራ እሴት ነው።

ፈጥነን ወደ ዘመናዊ እድገት እንድንሄድ የሚኮረኩረን፣ እኛም እንደ ጃፓኖች የራሳችን ማንነት ያለን የተለየን ህዝቦች ነን፣ በፍጥነት ለስልጣኔ ለእድገት ካልተጋን ይህን ኩሩ ማንነትታችን ከወራሪዎችና ከጨፍላቂዎች መከላከል አንችልም። ለእድገት የምንተጋው ብዙ ዳቦ የሚያመርት የዳቦ ፋብሪካ ለመገንባት አይደለም። ዘመናዊ መኖሪያ እና ቤት ለመስራት፣ በዘመናዊ መጓጓዣ ለመጓጓዝ አይደለም። እነዚህ የዘመናዊነት ትሩፋቶች ናቸው።

በፍጥነት ለእድገትና ለብልጽገና የምንነሳው ማንነታችን ለመከላከል። በሳይንስና በቴክኖሎጂ እየተራቀቁ ያሉ ከኛ እምነት ባህል ተውፊትና ማንነት ጋር የተለየ ማንነት ያላቸው ሁሌም በእኛ ኪሳራ የራሳቸውን ማንነት ማበልጸግ የሚፈልጉ ጉልበተኛ ሃገራትን ሴራ፣ ትንኮሳና ወረራ ለመመከት ነው። ከኛ አልፈን፣ መጪው ዘመን በጥቁር ዘር ላይ ይዞት የሚመጣውን አደጋ በጋራ ለመመከት ለአፍሪካም የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሳይንስና የነጻነት ብርሃን ለመሆን ነው። ከዚህ በላይ በጋራ እንድንነሳ ሊያደርገን የሚችል ራእይ ሊኖረን አይችልም።

  1. የመደመር ፍልስፍናን እውን ለማድረግ

ከዚህ በላይ የጻፍኩትን ሃተታ የሚያነብ ሰው በመጀመሪያ የሚጠይቀው ጥያቄ “እንዴት ሆነ ታዲያ ይህን የመሰለ ድንቅ የታሪክና የባህል እሴቶች ያለው ህዝብና ሃገር በልማትና እድገት የአለም ጭራ፣ በሰላም እጦት በድህነት የሚማቅቅ፣ የሰው ህይወት የረከሰበት፣ አድዋ ድረስ የራሰቸውን ስንቅ እና ትጥቅ ይዘው በባዶ እግራቸው ተጉዞው በጋራ ለማንነታቸው መከበር የወደቁ የአንድ ቅድመአያት ልጆች ዛሬ አንዱ ሌላውን በዘሩና በእምነቱ እየለየ በጭካኔ የሚያርድበት፣ የሚያፈናቅልበት ሁኔታ ውስጥ መውደቅ ቻለ?” የሚለው ይሆናል። 

ቀጥሎ የማመራው ለዚህ ጥያቄ መልስ በመስጠት የመደመር ፍልስፍና እውን አንዲሆን የሚያስችሉ ጥቆማዎች መስጠት ነው።

ቀደም ብሎ ሃገሮችን በፍጥነት ወደ ዘመናዊ እድገት የሚገፏቸውን ምክንያቶች በተመለከተ የቀረቡትን ነጥቦች እያስታወሰን ፊታችንን ወደ ኢትዮጵያ እናዙር።

በአድዋ ድል  የተንሳ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ እውቅና ያገኘች የአዲሱ ዘመን ሉአላዊ ሃገር ሆና ወጣች። የኢትዮጵያ ችግር የመነጨው ይህ ድል የተመዘገበው፣ ሃገሪቱ ባህላዊ በሆነ የፖለቲካ፣ የአስተዳደር፣የኢኮኖሚና የትምህርት ስርአት ወስጥ በነበረችበት ጸረ ዘመናዊነት ሁኔታ ውስጥ በመገኘቷ ነው።  የአድዋን ድል አስገራሚ የሚያደርገውም በጣም በዘመናዊ ስልጣኔ የገሰገሰ የተባለለትን ጣሊያንን የመሰለ ሃያል መንግስትና ሃገር በዘመናዊ ስልጣኔ ኋላ ቀርታለች በምትባል በኢትዮጵያ እጅ መሸነፉ ነው። 

በአድዋ ጦርነት የተነሳ ኢትዮጵያውያን ያዩትን የህልወና አደጋ፣ ከአደጋው ለመውጣት ያደረጉት ተጋድሎና ያጎናጸፋቸውን ድል ለፈጣን እና ለዘመናዊ እድገት መኮርኮሪያነት ተጠቅመው እንደ ምእራባውያንና የምስራቅ ሃገራት ሃገራቸውን ወደ ዘመናዊ ስልጣኔ ማስገባት አልቻሉም። 

በአድዋ ድል ማግስት የነበረው የፖለቲካ ስርአት ፍጹም ባህላዊ ነበር። በቡቃያ መልኩ እንኳን የዘመናዊነት እሸት የማያታይበት ነበር። ለዘመናዊነት የሚሟገት የሰው ሃይልና በዘመናዊነት የተቃኘ  ሃሳብ በትንሹም ቢሆን የማይገኝባት ሃገር ነበረች ኢትዮጵያ። የዚህ ውጤት፣ ሃገሪቱን ይገዙ የነበሩ ጥንታዊ ልሂቃን ሃገርን በፍጥነት ማዘመን ሳይሆን የተያያዙት በአድዋ ድል መኩራራት፣ በነበረው የመቀጠል ተደላዳይነት ነበር ።

ጣልያን ከአርባ አመት በኋላ የበለጠ ተደራጅቶ፣ የበለጠ ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ ለዳግም ወረራ ሲመጣ ኢትዮጵያ ራሷን ለማዘመን የሄደችበት እርቀት፣ ራሷን ከዳግም ወረራ ለመከላከል የገነባቸው አቅም ዜሮ እንደነበር ይታወቃል።

ጣሊያን ለአምስት አመትም ቢሆን ኢትዮጵያን መውረር መንግስቷን ማፍረስ የቻለበትን አሳዛኝ ሁኔታ የተፈጠረው በ40 አመት ወስጥ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ለማድረግ የተሞከረ ነገር አለመኖሩ ነው። የአድዋን ተመከሮ መንቂያ፣ የአድዋን ድል ለሌሎች ታላላቅ ድሎች መስፈንጠሪያ አድርገን ለመጠቀም ባላመቻላችን ዳግም የጣሊያን ወረራ መቋቋም እንዲያቅተን ሆንን። 

ሁለተኛውን የጣሊያንን ወረራ በድል አድራጊነት ተወጥተንም የኢትዮጵያ መንግስታዊ ፖለቲካዊ ማህበራዊ ስርአት ወደኋላ በሚመለከት ባህል የተቃኘ በመሆኑ ለሌላ 40 አመታት ሃገር በነበረችበት ስትረግጥ ቆየች።

የሃገሪቱ ሁለንተናዊ ኋላቀርነት፣ ሃገሪቱን ለውጭ ሃይሎች ጥቃትና ተጽእኖ ከማጋለጥ አልፎ በሃገር ውስጥ ዜጎች በዘመናዊው ዘመን ተቀባይነት ያገኙ የሰው ልጆች መብቶች ያልተሟሉሏቸው፣ የዘመናዊ ስልጣኔ የህይወት ቱሩፋቶች ያልተዳረሷቸው በመሆናቸው ራሳቸው የመንግስታዊና ፖለቲካ ስርአቱ ዋንኛው ተግደርዳሪ ሆነው ብቅ አሉ። ኢትዮጵያ፣ ጥንታዊው ልሂቋ እንደፈራው በውጭ ጥቃትና ተጽእኖ ሳይሆን በውስጥ ቅራኔ ፈነዳች።

የፖለቲካ ስርአቱ በተንጠባጠበ መልኩ ዘመናዊ ትምህርት እንዲቀስም ያደረገው አዲስ ትውልድ ባህላዊ በሆነ መንገድ ሃገሪቱን ሲመሩ ከነበሩት ሰዎች ቀድሞ፣ ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደ ዘመናዊ ሃገር ካልተሸጋገረች ለሃገሪቱም ሆነ ለህዝቧ የሚጠብቃቸው ውርደት መሆኑ ተረዳ።

ሃገሪቱን ለዘመናት የመራው ጥንታዊ ልሂቅ ሃገር እንዲሻሻል በየጊዜው ከዘመናዊ ልሂቁ የሚቀርብለትን የማሻሻያ ሃሳቦች የሚቀበል አልሆነም። ይህ የተማረ የሰው ሃይል ለአድዋ እና ቀጥሎም ኢትዮጵያውያን በተቀናጀ ትግላቸው በድጋሚ በጣሊያን ላይ ለተቀዳጁት ድል ቅርብ ስለነበረ ሃገር የማዘመን ፍላጎቱን የጀመረው የአድዋን እሴት መሰረቱ አድርጎ ነው።

በሁሉም መልኩ ሃገሪቱ ያሉባትን ችግሮች ሲተነትን መፍትሄ ሲያስቀመጥም የኢትዮጵያን ጥንታዊ ስልጣኔ እና ገናናነት፣ በአድዋ ላይ የተገኘው ህብረ ብሄራዊ ድል በአንድ ላይ ደምሮ እንዴት ይች ገናና እና የጀግኖች ሃገር ከየትኛውም የአለም ሃገራት በዘመናዊ ስልጣኔ ወደኋላ ትቀራለች በማለት ነበር ። ከግራ ርእዮተአለም በፊት በኢትዮጵያ ምሁራን አካባቢ ሃገር የማዘመን ግፊቱ የመነጨው ከጠንካራ የኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነት ስሜት ነው።

ይህ የብሄረተኛነት ግፊት “የሃገሪቱን የፖለቲካ የኢኮኖሚ የማህበራዊ ህጸጾች በሙሉ መንቀል፣ የተዛቡ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን፣ የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋ እኩልነትን፣ የፖለቲካና የሰብአብዊ መብቶችን ማረጋገጥ የማንችልበት ምክንያት አይኖረም” በሚል በከፍተኛ ተስፈኛነት የተነሳ ነበር። 

እንደሌሎች ከጥንታዊነት ወደ ዘመናዊነት መሸጋገር እንደቻሉት የኮምኒስት ሃገሮች የኢትዮጵያ ምሁራን የግራውን ርእዮተአለም የድርጊታቸው መቃኛ አድርገው ሲወስዱ በሃገራዊ ብሄረተኛነት ላይ የተገነባውን ሃገር ከሌሎች የሰለጠኑ ሃገሮች እኩል ማሳደጊያው የግራ ፖለቲካ ንድፈሃሳብ ነው በሚል እምነት ነበር።

በሃገራዊ ቁጭት ላይ የተመሰረተው ሃገር የመለወጥ የምሁሩ እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሞላ ጎደል ሁሉንም ምሁር አካተተ። በአለም ዙሪያ ለትምህርት ተልኮ የነበረውን ምሁርና ተማሪ፣ ሃገር ውስጥ ከነበረው ምሁርና ተማሪ ጋር አስተሳስሮ በአፍሪካ ምድር ታይቶ የማይታወቅ፣ አንድ ህዝብ በገዛ ሃገሩ መንግስትና የፖለቲካ ስርአት ላይ ያመጸበትን ሃገራዊ ሁኔታ ማመቻቸት ቻለ።

የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት በአፍሪቃ ምድር በየትኛውም ሃገር ታይቶ የማይታወቅ፣ አለም ላይ ከተካሄዱት የፈረንሳይ፣ የሩሲያና የቻይና  ከመሳሰሉት ትልልቅ አብዮቶች ጋር የተመደበ አብዮት ሆነ። የዚህ አይነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በትልቅ ተስፋ ሃገራቸውን ወደ ከፍተኛ የእድገት ማማ ማድረስ እንችላላን ብለው ከዳር እስከዳር እንደ አንድ ሰው የተንቀሳቅሱበት ፖለቲካዊ ንቅናቄ በአፍሪቃ ምድር ታይቶ አይታወቅም። 

እንዲህ አይነቱ ታሪካዊ የህዝብ መነሳሳት በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰት የቻለው ምሁሩና ህዝቡ በጋራ የተጋመዱበት የኢትዮጵያዊ የማንነት ድር እና ማግ ጠንካራ በመሆኑ ነበር። ሆኖም ግን የሃገሪቱ ምሁራን  ያሰቡትን ትልቅ ተስፋ እውን ለማድረግ የተከተሉት ሃገር በቀል ያልሆነ የባእድ ርእዮእተአለም የለውጡን እንቅስቃሴ  ችግር ላይ ጣለው።

በሃገራዊ ብሄረተኛነት ላይ ተመስርቶ በኮሚኒስት ርእዮተአለም እየተመራ ኢትዮጵያንን ወደ በለጸገችና የለማች ሃገር የመቀየር ሂደት የሃገሪቱን አጠቃላይ ልዩ ተፈጥሮ ግምት ውስጥ ያስገባ ባለመሆኑ ውርጃ ገጠመው።  ውርጃ የገጠመው ሃገር በፍጥነት ወደ ዘመናዊነት የመቀየር የምሁሩ ህልም ብቻ ሳይሆን ይህ ህልም የቆመበት ሃገራዊ ብሄረተኛነት ጭምር ሆነ። ይህ ውርጃ በአድዋ ድል ላይ ተገንብቶ የነበረውን የተጋመደ ህብረ ብሄራዊ ሃገር የተጋመደበትን ስፌት የሚበትን አቅጣጫ ያዘ።

ብዝሃነት የሃገሪቱ ጥንካሬ መሆኑ ቀርቶ የሃገሪቱ ድክመት ሆነ። የብዝሃነት አንድነት የነበረው ሃገር አንድነት የሌለው የብዝሃነት ሃገር ሆነ። ሃገራዊ ብዘሃነት የጥንካሬው ምንጭ አድርጎ የተነሳው የሃገሪቱ ምሁርና ተማሪ ከሃገራዊ ማንነት በላይ የራሳቸውን ማንነት የሚያራግቡ፣ የራሳቸውን ማንነት አግዝፈው በሚመለከቱ ጽንፈኛ ዘውጌ ብሄረተኛ ሃይሎች ተሸነፈ።  

ይህ ሽንፈት አድዋ የሰበሰበውንና የቋጠረውን ኢትዮጵያን እንደ ሃገር፣ ከሌሎች የለሙና የዘመኑ ሃገሮች ተርታ በፍጥነት እንድትሰለፍ የሚያስችላትን የሞራልና የመንፈስ ስንቅ መብላት ጀመረ።

“የአድዋን ድል እኛ ለብቻችን ያመጣነው ድል ነው። አማሮች ግን ድሉ የኛ ነው በማለት ታሪካችንን ቀምተውናል የሚለው የትግራይ ጽንፈኛ ብሄረተኛ ተፈጠረ። በሌላ በኩልም አድዋን ከሃዲ ኦሮሞዎች አማራን ከውርድት ያዳኑበት እንጂ ለኦሮሞ ምኑም አይደለም የሚሉ የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሄረተኞች ብቅ አሉ። 

መላው ህዝብ ከመላው ሃገሪቱ አድዋ ላይ ተሞ በጋራ መስዋእትነት ብዝሃነቱን ማትረፉ ተካደ። ይህ እውነታን የካደ አዲስ የሃሰት ትርክት ምንጩ ከየት ነው። በነማን መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍ ተሰጥቶት መስፋፋት ቻለ? በደንብ ሊመረመር የሚገባው ጉዳይ ነው።

ጽንፈኞች ያለ አድዋ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬና ወዘተ የሚባል ነገር ሊኖር ይችል እንዳልነበር ህዝብ እንዲረሳ ተግተው ሰሩ።  አድዋ ላይ በጋራ የተሰራ ኢትዮጵያዊነት እየተረተረ ኢትዮጵያ ምንም የሚያያዛቸው ክር የሌላቸው ከሰማኒያ በላይ ራሳቸውን የቻሉ፣ የራሳቸውን ሰንደቅ አላማ ማውለበለብና ነጻ ሃገራት መሆኑ የሚችሉ የማህበረሰቦች ስብስብ ሃገር ናት ተባለ። 

ይህ የፖለቲካ አመለካከትና ትርክት ሃገሩን በተቆጣጠሩት ጽንፈኛ ብሄረተኞች አማካይነት ህግ ጸደቀ። የሃገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መቅረጫ ሆነ። ፖሊሲውን ማስፈጸሚያ እቅድ ተዘጋጅቶለት፣በጀት ተይዞለለት ተግባር ላይ ዋለ።

በጋራ መስዋእትነት በተገነባ ሃገር በቋንቋ ላይ በተመሰረተ አንዱ ሌላውን በጎሪጥ የሚመለከትበት፣ የሃገሪቱ ዜጎች በገዛ ሃገራቸው በዘራቸው እየተለዩ ሁለተኛ ዜጋ እንዲሆኑ ያደረገ፣ በሂደት ዜጋ አይደላችሁም በሚል በመቶ ሽዎች የሚፈናቀሉበትንና የሚገደሉበትን አስተዳደራዊ መዋቅር በብሄር ብሄረሰቦች መብት ማስከበር ስም ተግባራዊ ተደረገ።

ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው የጥቁር ዘር የነጻነትና የጀግንነት ምስል ተደርጎ የተወሰደው ስነደቅ አላማ በተራ ጨርቅነት የሚገልጹ ግለሰቦች የሃገሪቱ መሪዎች ሆኑ። ከኢትዮጵያ ውጭ 15 የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ ገዥዎች ነጻ በወጡበት ወቅት በጉባኤ ተቀምጠው ሰንድቅ አላማችንን በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ  አምሳያ እንቀርጻለን ብለው ሰንደቅ አላማዎቻቸውን ሶስቱን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ  ቀለማት ያየያዙ እንዲሆኑ መወሰናቸው እየታወቀ፣ በኢትዮጵያ አንድም ክልል እነዚህን ሶስት ቀለሞች ወስዶ የክልሉ ሰንደቅ አላማ ያደረገ ጠፋ።

እያንዳንዱ ብሄረሰብ ለመላው የጥቁር ዘር የነጻነት  አርማ አድርጎ በመስዋእትነት ያስረከበውን ሰንደቅ አላማ እየሰረዘ የራሱን ከዚህ የጥቁር ዘር ስንደቅ አላማ ጋር ምንም አይነት መመሳሰል የሌለውን፣ ቢሳካላቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ወረው ባሪያቸው ያደርጉ የነበሩ የአውሮጳና የአረብ  ሃገሮች የሰነድቅ አላማ ቀለማት ያላቸው ባንዲራዎች በየክልሉ ማውለብለብ እንደ የብሄርሰብ እኩልነት ማሳያ አድርጎ ወሰደው።

አድዋ ላይ ሁሉም የሃገሪቱ ህዝቦች መስዋእተነት ከፍለው ከጥፋት ያዳኑት የሳባ ፊደል የሃገሪቱን የተለያዩ ቋንቋዎች መጻፊያ ፊደል በመሆን ለዘመናት በሃገራችን የኖረውን የቋንቋዎች መስተጋብር ማፋጠን የሚችል መሆኑ እየታወቀ፣ በርካታ ዜጎች በቀላሉ የበርካታ ቋንቋዎች ተናጋሪዎች መሆን የሚችሉበትን እድል የሚያሰፋ መሆን እየታወቀ፣ በርካታ ቋንቋዎችን ኦፊሲያሊያዊና ፌደራላዊ ቋንቋ የማድረግ እድላችንን የሚያሰፋ መሆኑ እየታወቀ፣ ፊደሎቹ ከየትኛዎቹም የአለም ፊደላት ይበልጥ ሃገራዊ ቋንቋዎች ለሚያወጧቸው ድምጾች መከተቢያነት የተሻሉ እንደሆኑ እየታወቀ፣ አፍሪካዊ ፊደል በመጠቀም ሊገነባ የሚችል ሃገራዊና አፍሪካዊ ኩራት እንዳለ እየታወቀ፣  አፍሪካዊ ያልሆነና አፍሪካን በቅኝ ገዥነት ለመቆጣጠር የመጡና ኢትዮጵያውያን በጀግንነት በጋራ መክተው የመለሷቸውን፣ የጥቁር ዘርን የሚንቁ ነጮች ፊደላት በተግባር እንዲያውሉ የሚያደርግ የጽንፈኛ ብሄረተኞች ውሳኔ ተወሰነ።

በኢኮኖሚ መስኩ፣  በአንድ ሃገር ውስጥ የሚካሄድ የኢኮኖሚ ግንባታ በዛ ሃገር ውስጥ የሚገኘውን የተፈጥሮ  ሃብትና የአየር ጠባይ ግምት ውስጥ አስገብቶ ሲከናውን የሚኖረው ጠቀሜታ ይታወቃል። ሃብት አባካኝ አይሆንም፣ እድገት ያፋጥናል፣ የኢኮኖሚ ሃገራዊ የስራ ክፍፍል  ሃገራዊ  አንድነት  ማጠናከር ይችላል። በኢትዮጵያ ግን ይህ በዘመኑ ሃገሮች በሙሉ ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ የልማት ሞዴል ተግባራዊ እንዳይሆን ተደረገ።  

እየአንዳንዱ አካባቢ ራሱን  ከሌላው አካባቢ የሚለይ አስተዳደራዊ መዋቅር መዘርጋትና  ከሃገሪቱ ታሪካዊ ሰነደቅ አላማ ጋር የሚጻረር ስነደቅ አላማ ማውለብለብ ብቻ ሳይሆን  ከሌሎች አካባቢ ጋር የሚያስተሳስረው የኢኮኖሚ አደረጃጀት እንዳይኖረው ተደረገ። አላማው ልማት ሳይሆን ወደፊት ነጻ ሃገር ሲሆን ራሱን ችሎ እንዲቆም በሚል የፖለቲካ እሳቤ የተወሰነ ጉዳይ ነው።

ሁሉም ክልሎች ተፈጥሮ ሃብታቸውን  የአየር ጠባያቸውን  ግምት ውስጥ ያላስገባ የሁሉም የኢኮኖሚ ሴክተሮች ባለቤቶች  እንዲሆኑ የሚያደርግ የሃገር ሃብት አባካኝና ከፋፋይ የመሬት የውሃ የማእድን ሽሚያ ውስጥ እንዲገቡ ያደረገ የኢኮኖሚ  ፖሊሲ በሃገር ተዘረጋ።

በአለም ላይ ድንበር የማያውቁት የሰው ጉልበትና  ካፒታል በኢትዮጵያ ውስጥ ድንበር  ተበጅቶላቸው የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ የየጉራጌ፣ ጉልበትና የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ የጉራጌ፣ ካፒታል የሚል ስም ተሰጥቷቸው በሃገር ደረጃ እንዳይንቀሳቀሱ ተደረጉ። ፋይናንስ በዘር  ተመትሮ የኦሮሞ ባንክ፣ የትግሬ ባንክ፣ የአማራ ባንክ የሚል ስም እየተሰጣቸው ሰዎች  ገንዘባቸው በዘራቸው  ስም ከሚጠሩ   ባንኮች ውጭ  እንዳያስቀምጡ፣ ብድር እንዳያገኙ የሚያደርግ ከፋፋይ የፋይናንስ ፖሊስ ስራ ላይ እንዲውል ተፈቀደ።

አድዋ የሁሉም የሃገሪቱ ህዝብ የጋራ  ሃብት  ያደረጋቸው የታሪክ  ቅርሶች፣  ታሪኮች፣  ተውፊቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣  የየከባቢው ብቻ ሆነው እንዲታዩ ተደረገ። የኦሮሞ ታሪክ፣ የኦሮሞ  ባህል፣ የኦሮሞ ቋንቋ፣ የአማራ ታሪክ፣ የአማራ ባህል፣ የአማራ ቋንቋ፣  እንዲሁም የሌሎች ብሄረሰቦች የባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ የመላው ሃገሪቱ የጋራ ቅርስ  መሆኑ ቀርቶ፣ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ፣ የመተባበሪያ  ሳይሆን የመፋጠጫና የመጠፋፊያ እሴቶቻችን እንዲሆኑ ተደረገ። 

አድዋ ላይ ተገምዶ የነበረ ሃገራዊ በዝሃነታችን በዚህ መንገድ ሆን ተብሎ በተወሰዱ መንግስታዊ እርምጃዎች በደምና በአጥንት የተሰፋበት ውል እንዲተረተር ተደረገ።

እንግዲህ ኢትዮጵያውያን ቀደም ብዬ የገለጻኩትን ፈጣን ለሆነ፣ ሃገር ለማዘመኛ ለማበልጸጊያ ስንቅ የሚሆናቸውን በጋራ የገነቡትን እሴት በዚህ መንገድ አፍርሰው እንዴት  ወደ ፈጣን ልማትና እድገት መገስገስ ይችላሉ? ሌሎች የበለጸጉ ሃገሮች ከሚያሳድሩባቸው አላስፈላጊ ተጽእኖ ክብራቸውን ነጻነታቸውን መከላከል ይችላሉ? የኢትዮጵያን እውነታ በደንብ ለተመለክተው የኢትዮጵያ ህዝብ  በጋራ መበልጽግ ማደግ  ቀርቶ በጋራ በድህነት መኖር የማይችለበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን መገመት አያዳግተውም። ይህ የኢህአዴግ የስራ ውጤት ነው።

የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳዝነው የአለማችን ጉዞ በሁሉም መልኩ ትልልቅ ፈተናዎች ይዞ እየመጣ ባለበት ዘመን፣ የዘመናዊ የሳይንስና የቴክኖሎጂ እድገት በሚያስፈራ ፍጥነት በሚገሰግስበት፣ በተለይ ከመረጃና ከባዮ ቴክኖሎጂ ሳይንስ ጋር እየመጣ ያለው እውቀት በ19ኛው ምእተ አመት ከነበረው የነጮች የቅኝ ግዛት ወረራ የከፋ የማንነትና የህልውና አደጋ በራሳችን ላይና በመላው የጥቁር ዘር ይዞ በመጣበት አደገኛ ወቅት ላይ የጋራ የሆነ እሴታችን እየተባላን እንዲበላ መፍቀዳችን ነው።  

የወቅቱን የሳይንስና የእውቀት ባላቤት መሆን በማይችሉ ሃገሮች ላይ ይዞት የሚመጣው አደጋ እጅግ አስፈሪ በሆነበት ዘመን፤ በተለይ አፍሪካ እጅግ አሳሳቢ አደጋ ውስጥ የመውደቅ እድሏ ከማንኛም ሌላ አህጉር የከፋ ሆኖ በሚታይበት ወቅት፤ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ መነቃቃት ትንሳኤና ተሃድሶ የሞራልና የመንፈስ ስንቅ ትሆናለች የሚል ተስፋ የተጣለባት ኢትዮጵያ፤ እኳን አፍሪካን ማዳን ራሷን ማዳን የምትችልበትን ስንቅ በፍጥነት በልታ ለመጨረስ ስትጣደፍ ማየት ትልቅ የታሪክ ጣር ነው።

የመደመር እሳቤ ትርጉም የሚኖረው ይህን ሃገራዊ እና አህጉራዊ ኢትዮጵያዊ መነሻ ያለውን አሳዛኝ የታሪክ የቁልቁለት ጉዞ ለማስቆም የሚያስችል የፖለቲካ ፍልስፍና ሆኖ መውጣት ሲችል ነው። ኢትዮጵያ የምትፈለገው በዚህ መሰረታዊ ችግር ዙሪያ በሃገሪቱ ልሂቃን ብሄራዊ መግባባት ተደርሶ በአንድነታችን ያስከበረነውን ብዛሃነት አንድነቱን ያላሉትን ጉዳዮች ነቅሶ በማረም ነው። በእውቀት ማነስ ይሁን በሌላ ምክንያት የተወሰዱ እርምጃዎች የሚቀለበሱበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ይህን ሳናደርግ ከገባንበት ሃገራዊ ሆነ አህጉራዊ አደገኛ ቅርቃር መውጣት አንችልም።

በርካታ የአለም ሃገራት፣ አገር ሊያደርጋቸው የሚችል የጋራ እሴት አጥተው ፍጹም ልብ ወለድ ኩነቶችን እየፈጠሩ የህዝባቸው አንድነት ማስተሳሰሪያ  አድርገው አገር ሲገነቡ፣ ለስልጣኔና ልማት መኮርኮሪያ አድርገው ሲጠቀሙባቸው፣ እኛ ማንም አገር ያልታደለውን እውነተኛ የታላቅነትና የገናናነት ማንነት ልብሳችን አውልቀን ምንተህፍረታችንን በአለም አደባባይ ቆመን እንዴት የማንነት ክብር ይኖረናል። 

እራሳችንን በራሳችን አዋርደን ካበቃን በኋላ የትኛውን ልዩ ማንነታችን፣ ክብራችንና ኩራታችንን ነው ከሌሎች ሃይሎች ለመከላከል  ሃገራችንን በፍጥነት በዘመናዊ ስልጣኔ ለመገንባት የምንነሳው?

ጊዚያዊ ስልጣንን ጥቅምን እያሰላን መሰረታዊ የሆኑ የሃገሪቱን ችግሮች አለባብሰን ብናልፍ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለከፋ መውጫ ለማይኖረው መከራ መዳረጋችን አይቀርም። ሁሉም በጊዜ ሊነቃ ይገባዋል። አድዋ ላይ መስዋእትነት ከፍለን ካመጣነው ጎጥና ዘር እምነት ተሻጋሪ ጠንካራ አንድነት ውጭ  የኢትዮጵያን ህዝብ መከራ ማሳጠር እንደማንችል ሁሉ፣ ድምበር ዘለል ከሆነ የብዝሃዊት አፍሪካ የማንነት እሳቤ ውጭ አፍሪካን ከጥፋት ማዳን አንችልም።

  1. መደምደሚያ የመደመር – የፖለቲካ ፍልስፍና መሰረታውያን፣

– የትኛውም ሃገራዊ የሆነ፣ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃብት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃብት መሆኑን ከታሪካችን በሚገኝ ማሰረጃ የሚያሳይ መሆን ይችላል።

– የሃገሪቱ ቁሳዊ ሃብት የሁሉም ሃብት መሆኑን ታሪካችንን በማጣቀስ ማሳየት ይችላል።

– የሀገሪቱ፣ እንደ ሰንደቅ አላማ አይነቶች ሃገር ወካይ ምስሎች የሁሉም የጋራ ምስሎች መሆናቸውን ከታሪካችን በሚገኙ ተጨባጭ ማስረጃዎች በመነሳት ማሳየት ይችላል። ይህ ሰነድቅ አላማ ለምን የድርድር ጉዳይ መሆን እንደማይችል መግባባት ይገባል።

– መደመር ከፋፋይ የዘር ፌደራላዊ የዘር የፖለቲካ አደረጃጀት ሳይኖረን የብዛሃን ቋንቋ ተጠቃሚዎችና ተናጋሪዎች፣ የበርካታ ብሄራዊ ቋንቋ ባለቤቶች ራሳችን ማድረግ እንደምንችል በቀላሉ ማሳየት ይችላል።

– መደመር የግእዝ  ፊደል የብቸኛው የጥቁር ዘር ፊደል መሆኑን በመከራከሪያነት በማቅረብ  ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ፊደል እንዲሆን የጥቁር ዘር የማንነትና የኩራት ማጠንጠያ እንዲሆን ማድረግ ይችላል።

– መደመር የጉልበትን እና የካፒታልን ድንበር የለሽነት አውቆ የሃገሪቱ ጉልበትና ሃብት ራሱ በሚመቸው የሃገሪቱ ክፍል በነጻነት እንዲፈስ በማድረግ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ እንደምንችል ማሳየት ይችላል።

– መደምር ሁሉም ክልል የሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ባለቤት ለመሆን የሚያደርጉትን ሃብት አባካኝና መከፋፋፈልን የሚያፋጥን ጥረት አቁመው ለኢንዱስትሪ የሚመቹት በኢንዱስትሪ ላይ እንዲያተኩሩ፣ ለግብርና እና ለግብርና ኢንዱስትሪ የሚመቹት በግብርና እና በግብርና ኢንዱስትሪ ላይ እንዲያተኩሩ፣ ለእርሻና ለከብት እርባታ የሚያመቹት በእርሻና በከብት እርባታ እንዲያተኩሩ በማድረግ እርስ በርሱ በሚደጋገፍ የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይለያይ ተደረጎ የተሳሰረ የበለጸገ ሃገር መገንባት እንደሚቻል ማሳየት ይችላል።

– የፋይናንስ ዘርፉ ገንዝብን በዘር የሚያይበትን ዘረኛ የባንክ አደረጃጀት በማፍረስ ሃገራዊ የፋይናንስና የባንኪንግ ስርአት በመዘርጋት ቁጠባን ብድርን ለሁሉም በእኩልነት በሁሉም የሃገሪቱ ክልል እንዲደርሱ፤ ልማት በሁሉም አካባቢዎች እንዲፋጠን ማድረግ እንደሚቻል ማሳየት ይችላል።

– መደመር በሃገራችን የሚመረቱ ማናቸውም ሸቀጦች በስፋት በሃገር ውስጥ የሚሸጡበትን በራሳችን የውስጥ ገበያ እርስ በርሳችን የተሳሰርንበትን የሃገር ውስጥ የገበያ ስርአት መገንባት እንደሚቻል ማሳየት ይችላል።

– መደመር የትምህርት ስርአታችንን ከአድዋ ድል ቱሩፋቶች ጋር በማቆራኘት የሃገሪቱ አዲስ ትውልድ አንድነቱ ብዝሃነቱ ያስጠበቀለት ወደፊትም ኢትዮጵያ የበለጸገች ጠንካራ የተስፋ ሃገር እንድትሆንለት ዋስትናው የአድዋን ድል እሴቶች አጥብቆ በመያዝ እንደሆነ በማስተማር፣ የጃፓን እና የቻይና አይነት፣ ከራሳቸው በፊት የሃገራችውን እና የህዝባቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ቢሮክራቶች፣ የጦር መሪዎች፣ ዳኞች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ፕሮፊሽናል ሙያተኞች ማፍራት፣ በነዚህ የበቁ ሙያተኞች ነጻና ገለልተኛ ተቋማት መገንባት እንደሚቻል ማሳየት ይቻላል።

– መደመር ከየትኛውም የውጭ አካል የሚመጣን የባህል ወረራ በጋራ ለመመከት ሁሉም በቁርጠኛነት መስራት የሚችልበት፣ ሃገራዊ ለሆኑ ባህሎች ቋንቋዎች እምነቶች የጥበብና ስራዎች አይን ያወጣ የጎንዮሽ ተደጋጋፊነት፣ የህዝብ እና የመንግስት ድጋፍ እንዲኖራቸው በማድረግ መገለጽ የሚችል መሆን ይኖርበታል። የውጭን የባህል ወረራ በመቀነስ የውስጥ የባህል መደመርን ማሳደግ እንደሚቻል ማሳየት ይቻላል።   

– መደመር ከፋፋይነት ያላቸውን ማናቸውንም ህጎች መሰረዝ ማናቸውንም ከፋፋይነት ያላቸውን ተቋማት ማፍረስ የብዛሃነት ዋስትና በሆኑ እንድነትን የሚያጠንክሩ ህጎችና ተቋሞች መተካት ይጠይቃል።

– የመደመር ሃሳብ በዘር ላይ የተመሰረቱ ከፋፋይ የፖለቲካ ድርጅቶችን አይፈቅድም፣ በዘር ላይ የተመሰረቱ ወታደራዊና የደህንነትና ተቋማትን አይፈቅድም፣ መደመር በዜጎችና በማህበረሰቦች  መሃከል  ድልድል መገንባትን እንጂ ድልድይ የሚያፈርሱ አመለካከቶችንና ተግባራትን አይፈቅድም።

– መደመር በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል አንድ ዜጋ በየትኛውም አካል በነጻነት የመኖር፣ ሃብት የማፍራት፣ በማንቸውም ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የመሳተፍ መብቱን ማንም ሊያግደው የማይችል መሆኑን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ይህን መብት በሚገፍ ማንኛውም አካል የመላው ህዝብ ፍላጎት መገለጫ የሆነው የማእከላዊ መንግስት፣ የማንንም ፈቃድ ሳይጠይቅ ህግ የማስከበር ስልጣን ያለው አካል መሆኑን የተቀበለ ሊሆን ይችላል። 

ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸውን ምልከታዎችና ሌሎችንም ግምት ውስጥ ለማስገባት ያልተዘጋጀ የመደመር እሳቤ ሳይወለድ የሚጨነግፍ እንጂ የሚያብብና የሚያድግ አይሆንም። ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ አይሆንም።

የዚህ አይነቱ የመደመር ፍልስፍና ሃሳብ እውነተኛ የሲነርጂ እሳቤ በውስጡ የያያዘ ነው። የሚደመሩት ነገሮች ከተራ ድምራቸው በላይ ውጤት ያመጣሉ። ብዛሃነታችን የጥንካሬያችን እንጂ የድክመታችን ምንጭ አይሆንም። እስከ ዛሬ ልናመጣው ያልቻልነው ብልጽግና መልካም አስተዳደር፣ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት የምንችልበት መሰረት ነው። ይህ መሰረት ከተጣለ ሁለንተናዊ ችግሮቻችንን ለማቃለል፣ የእድገታችንን ፍጥነት እንዲጨምር አብይ በመጻሃፎቹ ያቀረባቸው፣ የሞራል፣ የስልጠና፣ የተቋማት ግንባታና፣ ሌሎችም በርካት መፍትሄዎች በቀላሉ በተግባር ሊያውላቸው የሚችል የሰው ሃይል ማግኘትና ውለው አድረውም አመርቂ ውጤት ማምጣት ያስችሉናል።

የዚህ አይነት ፍልስፍና የብሄራዊ መግባባት አጀንዳ እንዳይሆን ስምምነት እንዳይደረስበት የሚፈልጉ በርካታና ጠንካራ የውስጥና የውጭ ሃይሎች እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። ከዚህ አካሄድ ውጭ ያለው መንገድ የጥፋት መንገድ መሆኑን የተረዱ ሃይሎች ሁሉም እስኪሰባሰብ መጠበቅ የለባቸውም። ጉዳዩ የአካዳሚ ክርክር ወይም ጉንጭ አልፋ የመጠጥ ቤት ወይም የፌስ ቡክ ወይም የዩትዩብ ቀልድ አይደለም። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እጅግ ድንቅ የሆነ ታሪክ ባህል ያላቸው ዜጎች የማንነትና የህልውና ጉዳይ ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ በፍጥነት መምክር፣ በፍጥነት መደራጀት፣ በፍጥነት ስትራተጂ መንደፍ ይጠይቃል። እንደ አበደ ውሻ በተገኘው አጋጣሚ ወንዝ የማያሻግር ጩኸት በመጮህ የሚከናወን ስራ አይደለም። ብሩህ አይምሮ ያላቸውን፣ ለግል ጥቅማቸው ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም የሚያስቡ፣ የዛሬን ሳይሆን ነገን አሻግረው ማየት የሚችሉ የሁሉም ብሄርና ብሄረሰብ፣ የህዝብ ልጆችን የጋራ ምክክርና ድካም ይጠይቃል። ይህን የሚሰሩ አካላት ከትንሽ ጀመረው እያደጉ እንደሚሄዱ ከልባቸው አምነው መንቀሳቀስ መጀመር አለባቸው።

ይህ እይታ ከውስጥም ከወጭም በከፈተኛ ደረጃ የደለቡ ጠላቶች አሉት። የፈለገው የቀናነትና የአካታችነት ፍላጎት ቢኖርም ለመደመር ፈጽሞ ፍላጎት የማይኖራቸው ሃይሎች እንደሚኖሩ ማወቅ ይገባል። በፖለቲካ፣ መደመር የማይፈለገውን በመቀነስ የመደመርን አቅም ማበርታት እንደሚቻል ተገንዝቦ በቁርጠኛነት ወደፊት መጓዛ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ሌላ አማራጭ የለም። ሌላው አማራጭ የያዝነው አማራጭ ነው። ይህ አማራጭ የሲኦል አማራጭ ነው። በዚህ አማራጭ ሄደን መጥፋታችን ካልቀረ የመዳን እድል ሊሰጠን በሚችል አማራጭ ሄደን ለመትረፍ መሞከራችን ማናችንም አይጎዳም። ከተረፈን ያሰበነው ተሳክቷል ማለት ነው። ካልተረፍንም በሌላው አማራጭ በመሄድ ይገጥመን ከነበረ የከፋ እጣ ስለማናመጣ አዲሱን መንገድ ለመሞከር መድፈር ይገባናል።

እንዲህ አይነቱ የመደመር ፍልስፍና የወያኔን ዘመን በችግር የተሞላ የአመለካከት አተያይ ሰብሮ በአዲስ አተያይ ለመተካት ካልተሞከረ ነፍስ ሊዘራ አይችልም። በሁለቱ የ“መደመር” መጽሃፎች ማግኘት ያልቻልኩት ይህን የመደመር ግልጽና ጥርት ያለ አተያይ ነው።

አንዳርጋቸው ጽጌ

አዲስ አበባ

መጋቢት 2013

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top