Connect with us

ኮሮና የሚስፋፋባቸው ሁለት መንገዶች፤ ግዴለሽነትና የብልጽግና የድጋፍ ሰልፍ፡፡

ኮሮና የሚስፋፋባቸው ሁለት መንገዶች፤ ግዴለሽነትና የብልጽግና የድጋፍ ሰልፍ፡፡
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ኮሮና የሚስፋፋባቸው ሁለት መንገዶች፤ ግዴለሽነትና የብልጽግና የድጋፍ ሰልፍ፡፡

ኮሮና የሚስፋፋባቸው ሁለት መንገዶች፤ ግዴለሽነትና የብልጽግና የድጋፍ ሰልፍ፡፡

ጎበዝ ለምርጫ ቅስቀሳው ወጥተን ከቀረን ያኔ ማን ሊመርጣችሁ ነው?

(ስናፍቅሽ አዲስ -ድሬቲዩብ)

ባለስልጣናቱ ምን ሆነዋል? አንድ ጃፓናዊ ተያዘ ብለው መርካቶ ገብተው ተጠንቀቁ እያሉ በመኪና ሲቀሰቅሱ እንዳልነበረ ዛሬ መንገዱን ሁሉ መርካቶ አደረጉት፡፡ ጥንቃቄ ምን ያደርጋል? የሚለውን በተግባር ማሳየት ጀመሩ፡፡ ማስክ አውልቆ በቴሌቨዥን መታየት የፖለቲከኞቹ ጠባይ ሆነ፡፡ መተቃቀፍና በአንድ መጠጫ መጠጣት ጭምር ስንመለከት ከረምን፡፡ የሚያሳዝነው ግን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየቀኑ የሚያዘው ቁጥርና ጽኑ ማገገሚያ የሚገባው ዜጋ መጠን እየጨመረ እንደሆነ ይነግረናል፡፡

ችግሩ ያለው እነሱ ጋር፤ ችግሩ ያሳስበናል የሚሉንም እነሱ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ኮሮና የሚስፋፋባቸው ሁለት ዋና ዋና መንገዶች ብንባል አንዱ የእኛ መዘናጋት ቢሆንም አንዱ ደግሞ የብልጽግና ሰልፍ ነው፡፡

እግር ኳስን ያለ ደጋፊ የሚያሳየው መንግስት ጠባብ ጎዳናን ስታዲየም አድርጎ በሰው እያጨናነቀ ተደገፍኩኝ ብሎ ዜና ይሰራል፡፡ የብልጽግና የድጋፍ ሰልፎች ኮሮናን ለማዳረስ ምትክ የለሽ እንደሆነ መረዳት እውቀት አይጠይቅም፡፡

ኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጎን ነን ብለው ያለ ጥንቃቄ እንደ ጎርፍ በየመንገዱ ላይ የፈሰሱት ዜጎች ምን አፍሰው እንደሚገቡ ማሰብ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ኑሩልኝ እንጂ ይቅርብኝ አላሉም፡፡ እንደውም ለድጋፉ አመሰገኑ፡፡

ከሰኞ ጀምሮ ብሎ ትናንት ጤና ጥበቃ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የአማራ ብልጽግና ደብረ ማርቆስ ላይ ዋዜማውን ሽር ብትን እያለ በአስር ሺህ ዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን አደባባይ አስወጥቶ ነበር፡፡

የድጋፍ ሰልፎቹ በጎንደር ያላቸውን ድባብ ላይ በዚህ አስፈሪ ጊዜ እንኳን ካድሬው እንቅልፉ ምርጫ ድል አድርጎ ነገን እንዲሁ ኑሮው እንዳይጎድል ማድረግ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ሰው እንዴት የራሱ ኑሮ እንዳይጎድል ሀገርና ወገን መከራ ላይ ይጥላል?

ለምርጫ ቅስቀሳው የሚጠሩት ሰዎች ብዙዎች እናቶችና መንግስት እጅ የወደቁ ዜጎች ናቸው፡፡ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል መንግስትን ቢደግፍ እንኳን ጎዳና ላይ መውጣት አደጋ አለው ብሎ በማሰብ ቢያንስ ወስኖ ለመቅረት ይችላል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ምረጡኝ በሚል ቅስቀሳ ስም ይህንን ሁሉ ዜጋ አደባባይ እያወጡ ኮሮናን እንከላከል ርቀትን እንጠብቅ የሚል መልእክት ማስተላለፍ መቀለድ ነው፡፡ እንድንመርጣቸው የሚፈልጉት ሰዎች ከምርጫው በፊት ሊገድሉን አስበዋል እንዴ እስክንል ቅጥ የሌለው ስካር ውስጥ ናቸው፡፡

የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ርቀትን እንጠብቅ የሚለውን የጽሑፍ መልእክት በቴሌቨዥን የሚለጥፉልን ጥግግቱ ላብ እንኳን በማይጠየፍ ጭንቅንቅ ላይ ባለ ኩነት የቀጥታ ዘገባ ላይ ሆነው ነው፡፡

መጨባበጥን፣ መጠጋጋት፣ ማጠጋጋትን ከሚመሩን ፖለቲከኞች እያየን ችግሩ ባሰ ተብሎ ደግሞ ስለ ኮሮና እንመከራለን፡፡

የመተንፈሻ መሳሪያ እጥረት አለ፡፡ ጽኑ ህሙማኑ ቁጥራቸው ጨምሯል በዚያ ላይ የሚያዘው ምጣኔም ቢሆን የሥርጭቱን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳየን ነው፤ በዚህ ሁሉ መካከል አሳሳቢ እንደሆነ የተረዳው መንግስት በሁለት ልብ ሲያነክስ አይተናል፡፡ ተጠንቀቁ ግን ጎዳና ላይ ውጡ አይሰራም፡፡ አፍ አፍኖ መፈክርም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ለአወጣው ህግ የሚገዛ ፓርቲና መንግስት ቢኖረን ደስ ይለናል፡፡ ትኩረት ለኮሮና፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top