Connect with us

በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ቀዳሚ ሪፖርት

በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርት
Photo: Social media

ዜና

በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ቀዳሚ ሪፖርት

በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርት

የድሬቲዩብ ማስታወሻ፡-በትግራይ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ በአክሱም ከተማ ስለመከሰቱ ሲነገር የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን ያካሄደውን የጥናት ሪፖርት ትላንት ለሊት ይፋ አድርጓል፡፡ ሪፖርቱ ስለተከሰተው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ጹሑፉ ትንሽ ዘለግ ያለ በመሆኑ ትግዕስት ከሌልዎት ባይጀምሩት ይመከራል፡፡

***

መግቢያ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በታኅሣሥ እና በጥር ወራት 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ይፋ ባደረጋቸው ሪፖርቶች፣ ኮሚሽኑ ገና በአካል ተገኝቶ ምርመራ ለማድረግ ባልቻለባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች በጦርነቱ ሂደት የሲቪል ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የአካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት መድረሱን፣ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ዘረፋ እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው መረጃዎች እንደደረሱት ጠቅሶ፣ በእነዚህ አካባቢዎች ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ እና የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ በመመርመር ላይ የሚገኝ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል።

እንዲሁም ኢሰመኮ በየካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ በአክሱም ስለተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጾ፣ በከተማዋ ላይ ተካሂዶ የነበረው ውጊያና ወታደራዊ ጥቃት ስላደረሰው ጉዳትና ኤርትራውያን ወታደሮች በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ መረጃዎች እንደደረሱትም አሳውቆ ነበር። 

በዚህም መሰረት፣ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ወደ አክሱም ለመጓዝ ያደረገው ጥረት በፀጥታ ሁኔታውና በተያያዥ ምክንያቶች ሳይሳካ ቢቆይም፣ ከየካቲት 20 እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በአክሱም ከተማ በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን፣ 45 የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዓይን እማኞችን እና የሃይማኖት መሪዎችን አነጋግሯል። እንዲሁም 20 ሰዎች የተሳተፉበት የቡድን ውይይት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር አድርጓል። በተጨማሪም ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል፣ ከአክሱም ሪፈራል ሆስፒታል፣ ከሚመለከታቸው የቀበሌ መስተዳደር አካላት እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት አገልጋዮች የተለያዩ የምስል፣ የድምጽ እና ሌሎች ሰነዶችን አሰባስቧል ።

ኮሚሽኑ የአክሱም ከተማ ከንቲባን እና ምክትል ከንቲባን በዚህ የምርመራ ጉቡኝት ወቅት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካም፤ ወደፊት በሚደረጉ የምርመራ ጉብኝቶች የሚመለከታቸውን ወታደራዊና ሲቪል ኃላፊዎች በሙሉ እንደሚያገኝ እምነት አለው። 

ኢሰመኮ በአክሱም የተፈጸመውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ ከአንድ መቶ በላይ የሞቱና ሌሎችም ብዛት ያላቸው የተጎጂ መረጃዎች የሰበሰበ ሲሆን፣ ፎቷቸው እና አድራሻቸው ገና በትክክል ያልታወቀ በርካታ ተጨማሪ የአክሱም ከተማ ተጎጂዎችን ለመለየት እና ከአክሱም ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኙ የገጠር ቦታዎች ተፈጸሙ ስለሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጨማሪ ክትትል በማድረግ ላይ ነው። ስለሆነም በዚህ የቀዳሚ (መጀመሪያ ደረጃ) ሪፖርት የተጠቀሱ አኃዞች አጠቃላይ የተጎጂዎችን ቁጥር የሚያመላክቱ ሳይሆን፣ ኮሚሽኑ እስከዚህ ምርመራና ሪፖርት ወቅት ድረስ ብቻ ለማረጋገጥ የቻለውን የሲቪል ሰዎች ጉዳት የሚጠቁም ነው።  

በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ጾታዊ ጥቃትንና ሁሉንም አይነት ጉዳቶች የማያጠቃልል ሲሆን፣ ሙሉ የምርመራ ስራው እንደተጠናቀቀ አጠቃላይ ግኝቱን እና ምክረ ሃሳቦቹን በይፋ ሪፖርት እንደሚያደርግ ኮሚሽኑ ይገልጻል። በዚህ ሪፖርት የተወሰኑ ሰዎች ትክክለኛ ስም እና ፎቶዎች በተጎጂ ቤተሰቦች ፈቃድ የተጠቀሰና የተመለከተ ሲሆን፤ በሌላ በኩል እንደነገሩ ሁኔታ የተጎጂዎችና ቤተሰቦችን የግል ሁኔታ ለመጠበቅ የተወሰኑ ሰዎች ስም ተቀይሮ ተጽፏል ወይም ሳይጠቀስ ታልፏል። በተወሰኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተፈጽመዋል የተባሉትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሚመለከት ከሚመለከታችው ወታደራዊ ክፍሎች የሚፈለጉ መረጃዎችና ማብራሪያዎች ገና ተሟልተው ያልተሰባሰቡ ስለሆነ፤ በዋናው ሪፖርት ውስጥ የሚጠቃለል ነው፡፡   

ስለ አክሱም ከተማ

አክሱም በትግራይ ክልል፣ ማዕከላዊ ዞን የምትገኝና ከክልሉ ዋና ከተማ ከመቀሌ በ190 ኪ.ሜ. ርቀት በስተሰሜን፣ ከአዲግራት በ132 ኪ.ሜ. በስተደቡብ ያለች ከተማ ነች። የሕዝብ ቁጥሯ ወደ 67 ሺህ የሚገመተው የአክሱም ከተማ በተለያዩ የቱሪስት መስህቦቿ የምትታወቅ ሲሆን፣ የአክሱም ሓውልቶች በዓለምአቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ ናቸው።  

ይህ ቀዳሚ ሪፖርት በሚዳሳስቸውና በተለይ ከኅዳር 9 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበሩት ቀናት፤ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ሸሽተው ከሌሎች  የክልሉ  አካባቢዎች የተፈናቀሉና ወደ አክሱም ከተማ የመጡ፤ እንዲሁም በየዓመቱ በኅዳር 21 ቀን የሚከበረውን  የጽዮን ማርያም የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ክብረ በዓል ለማክበር ከሌሎች ክልሎችም ጭምር የመጡ ሰዎች በከተማዋ ይገኙ ነበር።

በጦርነቱ ሁኔታ በሲቪሎች የደረሰው ጉዳት (ኅዳር 9 ቀን እስከ ኅዳር 15 ቀን

2013 ዓ.ም.)  

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ፤ በቀድሞው የክልሉ መንግስት ስር የአክሱም ከተማን ሲያስተዳድር የነበረው የአካባቢው መስተዳድር አካል ከኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከተማዋን ለቅቆ መውጣት ጀመረ። በእለቱ በአክሱም ከተማ እና ከከተማው በቅርብ ርቀት በነበሩ ቦታዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ ይሰማ የነበረ ሲሆን፣ እነዚህ አካባቢዎች በወታደራዊ የአየር ጥቃት ጭምር ሲናወጡ እንደነበር ነዋሪዎች ያስረዳሉ። የከባድ መሳርያና የተኩስ ድምጹ እስከ ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የዘለቀ ነበር።  

በዚህ ምክንያት “የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም ከሽረ እና ከሌሎች አከባቢዎች ሸሽተው በከተማዋ የተጠለሉ ሰዎች በድንጋጤ ተውጠው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ሸሹ።” ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የነበረው “የከባድ መሳሪያ ተኩስ እና የወታደራዊ አየር ጥቃቱ” በሲቪል ሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

ኁዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ሓፀቦ(ሞረር) ከአክሱም ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ቦታ 10 ሰዎች በወታደራዊ የአየር ጥቃቱ የተጎዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ፣ አምስቱ ወድያውኑ ሲሞቱ አንድ ቄስ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ነዋሪዎች እና ተጎጂዎቹ የህክምና እርዳታ ያገኙባቸው ሆስፒታል ባለሞያዎች ያስረዳሉ። “የሞቱት አምስት ሰዎች የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ማንነታችውን ለመለየት ሳይቻል ተቀብረዋል።” በተመሳሳይ ቀን በአክሱም ከተማ ዳሞ ሆቴል በመባል በሚታወቀው አከባቢ  ወ/ሮ ወይናረግ ረዳ የተባሉና በአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች የሚታወቁ እናት መኖሪያ ቤት በከባድ መሳሪያ ተመቶ፣ እሳቸውና እና ሶስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው ሞተዋል።   

እጃቸው፣ እግራቸው እና ሌሎች የሰውነት ክፍላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ አክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል እና አክሱም ሪፈራል ሆስፒታል የተወሰዱ ሰዎች በርካታ ናቸው። የህክምና ባለሙያዎች ለኢሰመኮ እንደገለጹት በኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ቅድስት ማርያም ሆስፒታል ጉዳት ደርሶባቸው ከመጡ ሰዎች መካከል አስሩ ሞተዋል። ከእነዚህ መካከል “አንድ ከ70 ዓመት በላይ እንደሚሆናቸው የሚገመቱ እናት አፋቸው እና መንጋጋቸው ሙሉ በሙሉ በመገንጠሉ አሰቃቂና ህክምና ለመስጠት አስቸጋሪ እንደነበርና  ለተሰወኑ ቀናት ምግብ በሕክምና ቱቦ እየተሰጣቸው ከቆዩ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን”  የሕክምና ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የተጎጂዋን ሁኔታ የሚያሳይ የምስል ማስረጃ  ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እና የኤርትራ ወታደሮች ከኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማዋ መታየት ጀመሩ። ሆኖም እስከ ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በዘለቀው ከፍተኛ ተኩስ ምክንያት ስጋት ስላደረባቸው አብዛኛዎቹ የቅድስት ማርያም ሆስፒታል እና የአክሱም ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ተቋማቱን ለቀው ለመሄድ መገዳደቸውን ይናገራሉ። ወደ ኋላ የቀሩት ሰራተኞች ሆስፒታሎቹ በተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና በኤርትራ ወታደሮች መዘረፋቸውን ይገልጻሉ። የቅድስት ማርያም ሆስፒታል ሰራተኞች ሲያስረዱ፣ “ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም.  የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና የኤርትራ ወታደሮች ወደ ሆስፒታሉ ገቡ።

ከሆስፒታሉ ፋርማሲ መድኃኒት እና የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች ዘርፈው የማይፈልጉትን ደግሞ አወደሙ።  በድንገተኛ ክፍል የነበረ አንድ ታካሚ በተኛበት ተኩሰው ገድለው እና የሆስፒታሉን መኪና ይዘው ሄዱ። የኤርትራ ወታደሮች የሆስፒታሉን ሰራተኞች አፀያፊ እና የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረጉ ስድቦች ይሳደቡ ነበር።” አክሱም ሪፈራል ሆስፒታል በተወሰኑ የመከላከያ ሰራዊት እና የኤርትራ ወታደሮች በተለያየ ወቅት አራት ጊዜ እንደተዘረፈ፡ እንዲሁም በሆስፒታሉ የኮረና ማዕከል ሁኖ ሲያገለግል በነበረ ሕንፃ በከፍተኛ ወጪ የተገዙ የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች፣  የታማሚ አልጋዎች እና ፍራሾች  ሳይቀር በኤርትራ ወታደሮች እንደተዘረፉ የአይን እማኞች ይናገራሉ። ማዕከሉ የደረሰበትን ጉዳት የሚያሳይ የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃ ለኮሚሽኑ ሰጥተዋል። 

የህክምና መድኃኒቶች ስለተዘረፉና ተገቢ ህክምና መስጠት አዳጋች በመሆኑ ምክንያት  “ብዙ ሰዎች በሕክምና ወይም መድኃኒት እጦት ጭምር እንደሞቱ” የህክምና ባለሞያዎቹ ያስረዳሉ። ለምሳሌ ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ቅድስት ማርያም ሆስፒታል የተወሰደች አንዲት አራስ እናት በወሊድ ምክንያት ብዙ ደም ፈሷት፣ በቂ የህክምና ባለሞያዎች ባለመኖርና  የሕክምና እርዳታ ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታ ስላልነበር ሕይወቷ አልፏል።

ከውቅሮ ማራይ ከሚባል ከአክሱም 17 ኪ.ሜ ከሚርቀው ቦታ “በከባድ መሳሪያ ጥቃት ተመትተው ወደ ቅድስት ማርያም ሆስፒታል ከመጡ ሶስት ሴቶች ውስጥ ሁለቱ ሴቶች ሕይዋታቸው ያለፈበትን ምክንያት የሕክምና ባለሙያዎቹ ሲያስረዱ፤ ፣ የስኳር በሽታ መድኃኒት በኤርተራ ወታደሮች በመዘረፉና ይህን መድኃኒት ባለማግኘታቸው ምክንያት የሞቱ ናቸው” በማለት ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከጤና ተቋማቱ ባገኘው የሰነድ ማስረጃ መሰረት፣ በሁለቱም ሆስፒታሎች ከኅዳር 9 እስከ ህዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ሰዎች ውስጥ፤ በልዩ ልዩ የሰውነታቸው ክፍል ላይ በደረሰባቸው ጉዳት፣ በደም መፍሰስ እና በተገቢው የህክምና እጦት ምክንያት 41 ሰዎች መሞታቸውን፤ እንዲሁም 126 ሰዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የሆነ የአካል ጉዳት (የአጥንት ስብራትና የጭንቅላት ላይ ጉዳት ጨምሮ) እንደደረሰባቸው ተመልክቷል።

የህምክና ባለሞያዎቹ ወደ ሆስፒታል ወይም ወደ ጤና ተቋም ሳይወሰዱ የሞቱ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምናሉ። ለምሳሌ ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. አንድ ለጊዜው ማንነቱ ያልተለየ ተጎጂ “ሳሙና ፋብሪካ” ተብሎ  በሚጠራ የአክሱም ከተማ አከባቢ “በጥይት ተመትቶ የፍሳሽ ማስተላለፍያ ቱቦ ውስጥ ተጥሎ እንደተገኘ” ማየታቸውን ገልጸዋል። 

አንድ በዓድዋ ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ቴሌኮሙኒኬሽን) የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ሰራተኛ ሁኖ ሲሰራ የነበረ ሰው ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም.ቤተሰቡን ለመጠየቅ ከአድዋ ወደ አክሱም በመኪና በመጓዝ ላይ እያለ ከአክሱም ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ዳየሱስ በተባለ ቦታ በወቅቱና በስፍራው ጦርነት ያልነበረ ቢሆንም በአካባቢው የነበረ የመከላከያ ሠራዊት አባል በመኪናው ላይ በከፈተው ተኩስ መኪናው ውስጥ እያለ በጥይት መመታቱን እንደነገራቸው በጊዜው ያከሙት የህክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል። ወደ ሆስፒታሉ ከደረሰ በኋላም “እርዱኝ” በማለት እየተማጸነ ሕይወቱ ማለፉንና ሲጓዝበት የነበረውን የቴሌኮሙኒኬሽን መኪና ተጎጂውን ሆስፒታል ካደረሰችው በኋላ በመከላከያ ሠራዊት አባላት መወሰዷን አክለው ይናገራሉ።

ኅዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም, “ቤተሰቡ ሬሳውን ከሆስፒታል ወስደው ሊቀብሩት ጉዞ ላይ እንዳሉ “በወቅቱ ሬሳ እንዳታነሱ፣ ሰው እንዳይሰበሰብ” ይባል ስለ ነበርና “የመከላከያ ወታደሮች መጥተው መተኮስ ስለጀመሩ” ሰዎች በድንጋጤ ሬሳውን ጥለው ሸሽተው፣ ተኩሱ ረገብ ሲል ሬሳውን አንስተው የተወሰኑት የቅርብ ቤተሰቦች ብቻ በተገኙበት  ቤተ ክርስትያን ወስደው ቀበሩት።”  

በሲቪል ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት

በአክሱም ከተማ በሲቪል ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ኮሚሽኑ ወደተወሰኑት አካባቢዎች በመዘዋወር ተመልክቷል። ለምሳሌ ብራና ሆቴል በተባለ የግለሰብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። የሆቴሉ ባለቤቶች እንደሚሉት “መከላከያ ሠራዊቱ ከብራና ሆቴል በቅርብ ርቀት የሚገኝ የአንድ የሕወሓት ጄኔራል ሆቴል ለመምታት አስበው በተሳሳተ መረጃ ምክንያት  ከሕወሓቱ ጀነራል ምንም ንክኪ የሌለውን ብራና ሆቴልን መትተዋል”። በጥይት የሆቴሉን የውጭ መስተዋቶች ሙሉ በሙሉ ሲያወድሙ ወደ ውስጥ በመዝለቅም አብዛኛውን የሆቴሉን ንብረቶች ከጥቅም ውጪ እንዲሆን አድርገውታል ብለዋል። ኮሚሽኑ ምርመራውን እስካካሄደበት ቀን ድረስ ሆቴሉ አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመረ ተመልክቷል። የሆቴሉ ባለቤቶች “ሆቴሉ በሚያሳዝን ሁኔታ እንደተመታ” የሚያረጋግጥ ደብዳቤ  ከአካባቢው ጊዚያዊ መስተዳድር አካላት የደረሳቸው ሲሆን ደበዳቤውና የደረሰውን ጉዳት የሚያመላክቱ የምስል ማስረጃዎች ለኮሚሽኑ አሳይተዋል። 

በተጨማሪም፣ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱት፤ የግለሰቦች “የልብስ ሱቆች (ቡቲክ) ፡ የሞባይል ሱቆች፡ የእርዳታ እህል፣  የምግብ ዘይት፣ እና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ንብረቶች በኤርትራ ወታደሮች እንደተዘረፉ” እንዲሁም በወቅቱ በተፈጠረው የጸጥታና ደህንነት ክፍተት ሌሎችም ሰዎች በዝርፊያው እንደተሳተፉ ይናገራሉ።

የኤርትራ ወታደሮች ከወሰዱዋቸው ንብረቶች ውስጥ የአክሱም ቤተ ክርስትያን ጳጳስ አቡነ መቃርዮስ ንብረት የሆነች ቶዮታ መኪና ወታደሮቹ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ሃገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ድረስ በመሄድ የወሰድዋት እና “የሃገረ ስብከቱ ንብረት የሆነች ኮድ 5  (ታርጋ ቁጥር 02223) መኪና 4 ጎማዎችንና አንድ የመኪናዋ ኮምፒተር በመፍታት እንደወሰዱ የቤተክርስትያኗ አገልጋዮች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። ሁኔታውን ለመከላከያ ሠራዊት አካላት ብናሳውቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም” ብለዋል።

የኤርትራ ወታደሮች በሲቪል ሰዎች ላይ ያደረሱት ጥቃት (ኅዳር 16 እስከ ኅዳር

21 ቀን 2013 ዓ.ም.)

ኢትየጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ከከተማዋ ሲወጡ እንደታዩ፡ ኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. አክሱም ላይ “ምንም የወታደር እንቅስቃሴ” በከተማዋ እንዳልነበረ የከተማው ነዋሪዎች ለኢሰመኮ አስረድተዋል። ኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ግን “ብዛት ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች በከተማዋ መታየት ጀመሩ። በሶስት የተለያዩ የከተማዋ ቦታዎች ማለትም በማይ ኩሖ፣ በሳሙና ፋብሪካ እና ፅልዓ በተባሉ ቦታዎች ሰፈሩ። ከኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ  ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ድምፅ በከተማዋ መሰማት ጀመረ።”  

ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች ተኩሱ ስለተጀመረበት ምክንያት እንዳማያውቁ ይናገራሉ።  የተወሰኑ ሰዎች ግን ስለ ሁኔታው የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቅሳሉ። አንዳንዱ “ተኩሱ የተነሳው የታጠቁ የአከባቢው ሚልሻዎች በኤርትራ ወታደሮች ላይ ተኩስ ከፍተው ስለነበር በዚህ የተቆጡት የኤርትራ ወታደሮች ሲቪል ሰዎችን መግደል” መጀመራቸውን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ “የኤርትራ ወታደሮቹ የአክሱም ፅዮን ቤተ ክርስትያንን ለመዝረፍ ስለፈለጉ እና የአከባቢው ሰውም ይህንን ስለተቃወመ ሲቪል ሰዎችን መግደል ጀመሩ” ይላሉ። ሌሎች የኮሚሽኑ መረጃ ምንጮች ደግሞ በአካባቢው የነበሩ ሚልሽያዎች ከተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን በኤርትራ ወታደሮች ላይ በሰነዘሩት ጥቃትና የኤርትራ ወታደሮች በአጸፋ በሰነዘሩት የበቀል እርምጃ በሲቪል ሰዎች ላይ በተለይም በአብዛኛው በወንዶች ላይ ያነጣጠረ ግድያና ጉዳት አደረሱ በማለት ይገልጻሉ፡፡

አንድ የአካባቢው ነዋሪ  ለኢሰመኮ ሲያስረዱ “ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ጥዋት ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን ልወጣ ስዘጋጅ ተኩስ ሰማሁ። ከዛም እድሜያቸው ከ 18 ዓመት በታች  የሚመስሉ አምስት ልጆች ማይ ኩሖ ወደ ተባለና በቤተክርስትያኑ አቅራቢያ በሚገኝ  ኮረብታ ስፍራ ላይ ቢላ እና በትር ይዘው ሲወጡ አየሁ፣ በመቀጠልም ብዛት ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች በዓድዋ መውጫ በሚባለው መንገድ በኩል ሲገቡ አየሁ” በማለት ገልጸዋል ። 

ኅዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም. የአካባቢው ሕዝብ በኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. የተገደሉትን ሰዎች ለመቅበር መውጣት ቢሞክርም የኤርትራ ወታደሮች “የእኛ ሰዎች ሳይቀበሩ የናንተ ሰዎች ሊቀበሩ አይችሉም በሚል ምክንያት በቀባሪዎች ላይ መተኮስ ስለጀመሩ ሕዝቡ ፈርቶ ወደ ቤቱ ሸሸ”። የተገደሉትን ሰዎች መቅበር የተፈቀደው ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ብቻ መሆኑንና “የሰዎች አስከሬን በየመንገዱ ወድቆ ለሦስት ቀናት ያክል ስለቆየ በእንስሳት የተበላ የሰውነት ክፍል እና ከመሽተቱ ብዛት ለማንሳት የሚያስቸግር አስከሬን እንደነበረ” ቀብሩን በማስተባበር ላይ የተሳተፉ  የአይን እማኞች ገልጸዋል። ለምሳሌ ምስክሮች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱት፤ አንድ የአክሱም ከተማ ነዋሪ መሆኑ የተረጋገጠ በአክሱም ካሌብ ት/ቤት አከባቢ የተገደለ ሰው (ስሙ በኮሚሽኑ ይገኛል ግን መጥቀስ አልተፈለገም) አስከሬኑ፣ በጅብ ስለተበላ ጭንቅላቱ እና እጁ ብቻ ነው የተገኘው።

ከእሱ ጋር ሌሎች ከፊል የሰውነት ክፍላቸው ብቻ የተቀበሩ ሰዎች አሉ። እንዲሁም በሌላ ቦታ ጭንቅላታቸው ብቻ የተገኘ ሌሎች አራት ሰዎች ነበሩ” ብለዋል። ነዋሪዎቹ በተጨማሪም እንደገለጹት፤ “የሰው ሬሳ በሲሚንቶ ከረጢት፡ በጆንያ እየተጠቀለለና በጋሪ ላይ እየተጫነ በአንድ መቃብር ውስጥ  በርካታ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው ሳያይዋቸው እና ተገቢው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሳይደረግላቸው በአከባቢው ማኅበረሰብ በአርባዕቱ እንስሳ፣ በእንዳሚካኤል፣ እንዳፔንጠሊየም፣ እንዳየሱስ እና በሌሎች ቤተክርስትያናት አንድ ላይ በጅምላ ተቀብረዋል” በማለት አስረድተዋል። ኮሚሽኑ ለመሄድ በቻለባቸው በአርባእተ እንስሳ ቤተክርስትያን እና እንዳሚካኤል ቤተክርስትያን በመገኘት የጅምላ የመቃብር ቦታዎችን ተመልክቶ የተወሰኑ የምስል ማስረጃዎችን አሰባስቧል።  

አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አክሱም ቅርንጫፍ ሰራተኛ እንደነበረ የተረጋገጠ ሰው (ስሙ በኮሚሽኑ የሚገኝ) ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ሙሉ ቀን እቤቱ ቆይቶ ከረፋዱ 11፡00 ሰዓት አከባቢ ምግብ ለመግዛት ወጥቶ “አብነት ሆቴል ፊት ለፊት ሲደርስ የኤርትራ ወታደሮች መጀመርያ እግሩ ላይ ቀጥሎ ደረቱ ላይ በጥይት መተው እንደገደሉት” በርካታ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ሟች ሳይቀበር አስፋልት ላይ እስከ ኅዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም. መቆየቱንና ታንክ እሬሳው ላይ ስለሄደበት “ከወገቡ በታች ተጨፍልቆ እጁና እግሩ ተቆራርጠው እንደነበር” የአስከሬኑን ሁኔታ ያዩ የአይን ምስክር ገልጸዋል።

የተጎጂ ቤተሰቦችና የአይን ምስክሮች ለኢሰመኮ እንዳስረዱት “ሙሉብርሃን ገብረመድህን(ወዲ ጎንየ)የተባለ የ38 ዓመት ሰው እርጉዝ ሚስቱ እና ልጆቹ ፊት እንዲሁም መኮንን ጠሚዓ የተባለ ሰው በልጆቹ ፊት ተገድለዋል፣ ጉዕሽ መኮነን የተባለ የ38 ዓመት የእንስሳት ሃኪም ልጁ እያለቀሰ ከቤት አውጥተው ገድለውታል፣ ቢትወደድ ታደሰ ከበደ የተባለ የ51 ዓመት ሰው በጥይት የተገደሉ ሰዎች ሬሳ ለማንሳት ሲሞክር ጉሮሮው እና ደረቱ ላይ ተመቶ ቤተሰቡን ለማሳወቅ ባለመቻሉ በአካባቢው ሰዎች ተቀብሯል። ሙሉጌታ ጥዓመ ወዲ ውቅሮ)የተባለ ወጣት ህዳር 20 ከጥዋቱ ሁለት ሰዓት አከባቢ የተገደሉት ሰዎች ለማንሳት ሲሞክር በሶስት ጥይት ተመቶ ሞቷል።” 

ሙሉጌታ ፍስሃ የተባለ ዕድሜው በግምት 14 ዓመት የሚሆን ልጅ እናቱ ወ/ሮ ተጫዊት በኤርትራ ወታደሮች ተገድለው  እያለቀሰ ወደ ወደቁበት ቦታ እየሮጠ ሲሄድ እሱንም ጨምረው እንደገደሉት የሟቾች የቅርብ ቤተሰብ ያስረዳሉ።

 “ኤፍሬም አለም የተባለ ወጣት የልጁ ክርስትና ቀን በመሆኑ ከጓደኞቹ ጋር ወደ ቤት እየሄደ እያለ እሱን እና ሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ተገድለው ከመካከላቸው አንዱ ብቻ ተርፏል። በሪሁ ገብረ ሩፋኤል የተባለ ወጣት የልጁ የአንድ ዓመት ልደት እያከበረ እያለ ከቤት አውጥተው ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር አንድ ላይ ገድለውታል።” 

አቶ ብርሃነ ገብረ እግዚአብሔር ኣብርሃ የተባሉ በግምት 70 ዓመት የሚሆናቸው አዛውንት ”ቤታቸው ውስጥ እያሉ የኤርትራ ወታደሮች መጥተው ከሁለት ልጆቻቸው ማለትም ሺሻይ ብርሃነ ገ/ብሔር እና መኮነን ብርሃ ገ/ብሔርን ከቤት አስወጥተው ባቅራቢያው ወዳለው የውሃ ታንከር በመውሰድ መሬት ላይ በማስተኛት ሦስቱም ጭንቅላታቸውን በጥይት በመምታት ሲገድሉዋቸው በቅርብ ርቀት በመሆን ኣይቻለሁ” በማለት አንድ ሌላ ነዋሪ ለኮሚሽኑ አስረድቷል።

 “አቶ ልሳነ ወርቅ የተባሉ ሰው ከልጃቸው ቢኒያም ልሳነ ወርቅ እና ከሴት ልጃቸው ባለቤት መምህር ግርማይ ጋር አንድ ላይ ቤቱ ውስጥ በኤርትራ  ወታደሮች እንደተገደሉ” የሟቾቹ ቤተሰቦች  ለኮምሽኑ ገልጸዋል።  

ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. የኤርትራ ወታደሮች “ሲያትል ሲኒማ” ተብሎ በሚታወቀው የአክሱም ከተማ አካባቢ  በሲቪል ሰዎች ላይ በአደረጉት ጥቃት፤ የሌላ ብሔር ተወላጆች መሆናቸውና ትግርኛ እንደማይችሉ ያረጋገጡትን 2 ሰዎች በመተው ከእነሱ ጋር አንድ ግቢ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን ሰዎችን ግን ከቤት በማስወጣት ገድለው እንዲሁም አንድ አቶ ተገን ባህታ የተባለና ቤቱ ውስጥ ተኝቶ የነበረን ሰው እዛው ገድለውት መሄዳቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል። እቤቱ ውስጥ የተገደለው የአቶ ተገን ባህታ ተኝቶበት ነበር የተባለውን ክፍልና  በደም ተነክሮ የነበረ ፍራሽ የኮሚሽኑ ቡድን ተመልክቷል።  

ኅዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም. የኤርትራ ወታደሮች “ብዛት ያላቸውን የአክሱም ወጣቶች ከተለያዩ ቦታዎች በመሰብሰብ ምሽላም እና ዜሮ ዜሮ ወደሚባሉ የአክሱም ሰፈሮች በመውሰድ ጉድጓድ ውስጥ አጉረው ካዋሏቸው በኋላ ‘ነገ ኤርትራ ውስጥም የማርያም በዓል ስለሚከበር ዛሬ አንገድላችሁም አሁን ሂዱ እና የሞቱትን ቅበሩ’” በማለት አመሻሽ ላይ እንደለቀቋቸው በዚህ ሁኔታ ተይዘው የነበሩ ወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። 

በዚሁ ቀን የኤርትራ ወታደሮች ወጣቶችን እያፈሱ በነበረበት ጊዜ፤ በአክሱም ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የማርያም ቤተክርስትያን ቅጥር ግቢ የነበረ ሃፍተማርያም ግዛቸው ግርማይ የተባለ ነዋሪ የኤርትራ ወታደሮቹ “ተነስ” ሲሉት “እግሬን እና እጄን በሽተኛ ነኝ መንቀሳቀስ አልችልም” ሲላቸው “እና እንግደልህ” የሚል ጥያቄ ሲጠይቁት “አዎ” የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው ተኩሰው ገደሉት” በማለት ምስክሮች አስረድተዋል፡፡

‹‹ህዳር 21 ቀን የማርያም ፅዮን ዓመታዊ ክብረ በዓል በቤተክርስትያኑ ቅጥር ግቢ ታስቦ ቢውልም፤ በከተማው የደረሰው ሀዘን ግን ክብረ በአሉን በዘገቡት ሚዲያዎች አልተነገረም›› በማለት ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ኮሚሽኑ በጥይት ተመትተው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችንም አነጋግሯል። አንድ ጉዳት የደረሰበት ሰው ሲያስረዳ፣ “ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. የኤርትራ ወታደሮች ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ገደማ እኔን እና ሌሎች ወንዶችን ከየቤታችን እና ከመንገድ ለቅመው መጋቢት ትምህርት ቤት አከባቢ ወሰዱን። እኔን በሦስት ጥይት ተኩሰው ቢመቱኝም ተረፍኩ። ሌሎች ከኔ ጋር የነበሩ ሰዎች ሞቱ።” ሲል ተናግሯል። ተጎጂው ለኮሚሽኑ ያቀረባቸውን የሟቾች ስም ዝርዝር ኮሚሽኑ ከተለያዩ ምንጮች ያረጋገጠ ሲሆን፣ ተጎጂው በአካሉ ላይ የደረሰውን ጉዳት የኮሚሽኑ ባለሞያዎች ተመልክተዋል። 

ሌላ ተጎጂ፣ ልጁ እንደተገደለ ስለተነገረው እሱን ፍለጋ ሲወጣ መንገድ ላይ የኤርትራ ወታደሮች አግኝተውት ከሱ ጋር የነበሩ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ እሱ ግን እግሩ ከተመታ በኋላ ስለወደቀ ሞቷል ብለው እንደተውት ገልጿል። 

አንድ ሌላ ተጎጂ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ከረፋዱ 10፡00 ሰዓት ገደማ የአክሱም ከተማ ሓውልቶች በሚገኝበት አከባቢ እየተንቀሳቀሰ እያለ “ከ15 በላይ የሚሆኑ የኤርትራ ወታደሮችን በመንገዱ ላይ እንደተመለከታቸውና” እነርሱም “ና” ብለው ሲጠሩት መሮጡን ገልጾ፣ “ብዙ ጊዜ ተኩሰውብኝ አንድ ግዜ ብቻ በቀኝ ጀርባየን መቱኝ፣ ደም እየፈሰሰኝም ቢሆን እሮጬ አመለጥኩ። በወቅቱ የጤና ተቋማት ስራ ላይ ስላልነበሩ ምንም ያገኙሁት የህክምና አገልግሎት የለም” በማለት ያስረዳ ሲሆን ። ተጎጂው የደረሰበትን አካል ጉዳት  ኮሚሽኑ ተመልክቷል። 

“ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ገደማ አክሱምን ለቅቄ ገጠር ወዳሉ ወላጆቼ ለመሄድ ወሰንኩኝ። ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያንን አቋርጬ እያለፍኩኝ ሳለ በመቃብር ቦታው ላይ አድፍጠው ሲጠብቁ የነበሩ የኤርትራ ወታደሮች ተኩሰው አንድ ጥይት ቀኝ እግሬን ሲመታኝ፣ አንድ ጥይት በግራ ሽንጤ ገብቶ በቀኝ በኩል የወጣ ሲሆን አንድ ጥይት የግራ እጄን መቶኛል። ደም ሲፈሰኝ ያዩ ሰዎች ወደ ቤት ተሸክመው አድርሰውኛል። 

ከሦስት ሳምንት በኋላ ወደ አክሱም ሆስፒታል ሄጄ ህክምና አግኝቻለሁ” በማለት ሌላው በሕይወት የተረፈ ተጎጂ ያስረዳል።  

በሲቪል ሰዎች ላይ ከደረሰው የሞት እና የአካል ጉዳት በተጨማሪ የሃይማኖት ተቋማትና የግለሰብ መኖርያ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች የንብረት ጉዳቶች ደርሰዋል። ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ገደማ እስከ ረፋዱ 11፡00 ሰዓት ቁጥራቸው ያልታወቁ የኤርትራ ወታደሮች በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ውስጥ ባለው የመቃብር አከባቢ ሆነው የቤተክርስትያኑን ሕንፃ ለማፍረስ  በትግርኛ “ህረሞ … ህረሞ … “ (በለው… በለው)እያሉ በጥይት ሲደበድቡት እንደዋሉ ቤተ ክርስትያኑ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ የዓይን እማኞች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል።

እንዲሁም “ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. የአክሱም ዩኒቨርስቲ የዶክተሮች መኖርያ ሕንፃ “ከሌሎች መኖርያዎች ተለይቶ በብዙ ጥይት “ሆን ተብሎ” እንዲደበደብ ተደረገ” በማለት ምስክሮች አስረድተዋል። ኮሚሽኑ በሁለቱም ቦታዎች የደረሰውን ጉዳት በምስል ይዟል።

ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በአክሱም ከተማ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባሎችና ኃላፊዎች በከተማው ውስጥ እያሉ ጥቃቱን ባለመከላከላቸው ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል በማለት ገልጸዋል። 

በሌላ በኩል ከዚህ ክስተት በኋላ ታኅሳስ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የኤርትራ ወታደሮች ወደ አክሱም ቅድስት ማርያም ፅዮን ቤተ ክርስትያን ገብተው ለመዝረፍ ያደረጉትን ሙከራ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ህዝቡ ተባብሮ እንደተከላከለው ምስክርነታቸው የሰጡ ነዋሪዎች እና የቤተ ክርስትያን አገልጋዮች አሉ።

ኮሚሽኑ በዚህ  ምርመራው ያሰባሰባቸው መረጃዎች በተለይ ከኅዳር 19 እስከ ኅዳር 21 በነበሩት ሁለት ቀናት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈጸመና በመቶዎች የሚቆጠሩ የአክሱም ከተማ እና አከባቢው ነዋሪዎች፣ከተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች ጦርነት ሸሽተው በከተማዋ የተጠለሉ ተፈናቃዮች፣ እንዲሁም የኅዳር ፅዮን ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ለማክበር ከተለያየ ቦታዎች የመጡ ሲቪል ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ያመላክታሉ። 

ኢሰመኮ በዚህ ዙር ምርመራው ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የተጎጂ ቤተሰቦች እና የአይን እማኞች እንዳስረዱት በርካታ ሲቪል ሰዎች ልጆቻቸው፣ ሚስቶቻቸው እና እናቶቻቸው ፊት ጭምር በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ ይናገራሉ። የኤርትራ ወታደሮች ቤት ለቤት እየዞሩ “ባልሽ የት አለ፣ ልጅሽ የት አለ፣ ወንድ ልጅ ካለ አውጪው” እያሉ በትግርኛ ይጠይቁ እንደነበርና ሲቪል ወንዶች “መሳርያ የለንም አልታጠቅንም እያሉ ቢማፀኑም ወንዶችን ከቤት እያስወጡ ሌሎች ደግሞ ቤት ውስጥ እያሉ ባሰቃቂ መንገድ ገድለዋቸዋል። 

የተጎጂዎች ቤተሰቦችና የአይን ምስክሮች አጥቂዎቹ የኤርትራ ወታደሮች መሆናቸውን በሚናገሩት የትግርኛ ቋንቋ ዘየ፣ በለበሱት የኤርትራ ወታደራዊ ዩኒፎርምና ጫማ፣ እንዲሁም አንዳንዶቹን ወታደሮች ፊታቸው ላይ ባላቸው ባህላዊ ምልክት ጭምር ማወቅ መቻላቸውን  ገልጸዋል።   

ይህ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተራ ወንጀል ሳይሆን በዓለምአቀፍ ድንጋጌዎችና መርኆች የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚጥስ፣ በግጭቱ ተሳታፊ ያልነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ጭምር ሆነ ተብሎ ያነጣጠረ (Intentionally directing attacks against the civilian population as such or against individual civilians not taking direct part in hostilities)፣ እና በሚሊተሪ አስፈላጊነት ሊገመገሙ የማይችሉ እና ሆን ተብሎ የተደረጉ በሲቪል ሰዎች ንብረቶች በሃይማኖት ተቋማትና በሆስፒታሎች ጭምር ዝርፊያና ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቱ ምናልባት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) ወይም የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆን ስለሚችል፤ በአጠቃላይ ክልሉ የተሟላ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምርመራ ስራ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ 

የሰዓት እላፊ ገደብ ጋር በተያያዘ የደረሰ ጉዳት   

በትግራይ ክልል በታወጀው የሰዓት እላፊ ምክንያት በአክሱም ከተማ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እንቅስቃሴን ያግዳል። ከሰዓት እላፊው ገደብ በኋላ በመንገድ ላይ በመታየታቸው ምክንያት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡  

ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም.  ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አከባቢ አቶ ተክላይ ስዩም የተባለ ሰው ወታደሮች ከተማ አከባቢ ሲንቀሳቀስ ስላገኙት እነሱን አይቶ እየሮጠ ወደ ቅድስት ማርያም ፅዮን ቤተ ክርስትያን ቢገባም ወታደሮቹ ተከታትለው ቤተ ክርስትያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሁለት ጥይት ገድለውታል። ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ማታ አከባቢም ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ሁለት ሰዎች ዘ-አርክ ሆቴል አከባቢ እና መጋቢት አንደኛ ደረጃ ት/ቤት አከባቢ እንደተገደሉ ኮሚሽኑ ጥቆማ ደርሶታል።       

ጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ከምሽቱ 12:30 ሰዓት አከባቢ አቶ በርሃ ረዳ ተፈሪ የተባለ የ35 ዓመት ወጣት ከጓደኛው ጋር ሁኖ ከስራ ወደ ቤቱ እየተመለሰ እያለ እቤቱ በር ሲደርስ በወቅቱ እዛው አከባቢ በነበሩ የመከላከያ ሰራዊት ዩኒፎርም በለበሱ ወታደሮች በተተኮሰበት አንድ ጥይት የአካል ጉዳት ደርሶበታል። አቶ በርሃ በፊቱ ላይ የደረሰበትን የመበላሸት ጉዳት ለማስተካከል በአክሱም ሪፈራል ሆስፒታል ስድስት ሰዓት በፈጀ ቀዶ ጥገና ጊዜያዊ ጥገና ከተሰራለት በኋላ ወደ መቐለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ተልኮ የመንጋጋ ቀዶ ጥገና ተሰርቶለታል። በጉዳቱ ምክንያት ሁለቱም ዓይኖቹ ያጣ ሲሆን አፍንጫው በመጎዳቱ ምክንያት የመተንፈስ ችግር እንዳለበትም ኮሚሽኑ በቃለ መጠየቅ ወቅት ተገንዝቧል። አቶ በርሃ ከመጎዳቱ በፊት እና ከጉዳት በኋላ የሚያሳይ ምስል ኮሚሽኑ ደርሶታል። 

ኮሚሽኑ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በጸጥታና ደህንነት አጠባበቅ ምክንያት በጸጥታ ኃይሎች የሚወሰደው እርምጃ አሁንም ለሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉድለት መድረስ ምክንያት መሆኑ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ 

ለምሳሌ የአክሱም ዩኒቨርስቲ  የጥበቃ ሰራተኞች ስራቸውን እንዲጀምሩ በተነገራቸው መሰረት ወደ ስራ ቢመለሱም በአካባቢው ከነበሩ ወታደሮች ጋር ተከስቶ በነበረ ውዝግብ ምክንያት የጸጥታ አባሎቹ በወሰዱት እርምጃ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. የጥበቃ ሰራተኞቹ አዛዥ የነበረው ሃለፎም ለገሰ የተባለ ሰራተኛ ጭንቅላቱ በጥይት ተመትቶ ሲገደል ሌሎች ሶስት የጥበቃ ሰራተኞች ደግሞ በዪኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ስራ ላይ እያሉ በመከላከያ ወታደሮች በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድበዋል።  

በአጠቃላይ የሰዓት እላፊ ገደብን ተላልፎ የተገኘ ሰውንም ቢሆን በተመጣጣኝ ኃይል በቁጥጥር ስር ማዋል ስለሚቻል፤ ለነገሩ ሁኔታ ፍጹም ተመጣጣኝ ያልሆነ ሕይወት የሚያጠፋ መሳሪያ (lethal weapon) በመጠቀም የተወሰዱት እርምጃዎች ፈጽሞ ተገቢ ባለመሆኑ በዚህ መልክ የተገደሉ ሰዎች ሁኔታ በተሟላው ሪፖርት የጸጥታ ኃይሉንም ምላሽ በማካተት የሚጣራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሲቪል ነዋሪዎች ደህንነት አጠባበቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡

ምክረ ሃሳብ

– የፌዴራል መንግስቱ በትግራይ ክልል የተከሰተውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በዓለምአቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋምና በብሔራዊው የሰብአዊ መብቶች ተቋም የጣምራ ምርመራ ቡድን (joint investigation team) አማካኝነት እንዲጣራ ባሳየው ቁርጠኝነት መሰረት፤ ለምርመራ ስራው ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርና የሚመለከታቸው አካሎች በሙሉ ለምርመራ ስራው ተገቢውን እገዛ እንዲያደርጉ፣

– የምርመራው ስራ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የተጎዱ ቤተሰቦችን የመጠገንና መልሶ የማቋቋም እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታ የማዳረስ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣

– በተለይ ለሕክምና ተቋሞች የበለጠ ትኩረት በመስጠት በአፋጣኝ መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣

– የጸጥታ ኃይሎች የሲቪል ሰዎችን ደኅንነትና ጸጥታ ለማስከበር የሚያከናውኑት

አስፈላጊ ስራ ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ።

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top