Connect with us

ጎንደር አመታዊውን የግዕዝ ጉባኤ እያስተናገደች ነው።

ጎንደር አመታዊውን የግዕዝ ጉባኤ እያስተናገደች ነው።
ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

ዜና

ጎንደር አመታዊውን የግዕዝ ጉባኤ እያስተናገደች ነው።

ጎንደር አመታዊውን የግዕዝ ጉባኤ እያስተናገደች ነው።

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ወመዘክርና የአብክመ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጥምረት አዘጋጅተውታል።

(በድሬ ቲዩብ ሪፖርተር)

በኢ.ፊ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋ ሥነ ቃልና ትርጉም ሥራ ልማት ዳይሮክተሬት መሪነት የሚዘጋጀው አመታዊው  የግዕዝ ጉባኤ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው። ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ለጥቂት አመታት ተቋርጦ ከነበረ በኋላ ዳግም ወልቂጤና መቀሌ ከተሞች በተከታታይ ተዘጋጅቶ የዚህን አመት ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ እያስተናገደችው ይገኛል።

“ግዕዝና ግብረ ገብነት” በሚል መሪ ቃል እየተዘጋጀ ያለው ሀገራዊ ጉባኤ በትናንትናው ዕለት መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲጀመር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር አስራት አፀደወይን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር  ሲከፍቱ የግዕዝን ቋንቋ ልቀትና የያዘውን ጥበብና ዕውቀት የተረዱት የምዕራባውያን ዩኒቨርሲቲዎች እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ሲከፍቱ በሀገሩ ትኩረት መነፈጉን አንስተዋል።

ዶክተር አሥራት አፀደወይን በቀደምት ኢትዮጵያዊያን ዕውቀትና ጥበብ በከበረችው ጎንደር ከተማ ስለሚገኘው ዩኒቨርሲቲያቸውም ከ2011 ጀምሮ በመጀመሪያ ዲግሪ የግዕዝን ቋንቋ እያስተማረ እንደሆነ ተናግረዋል። ቋንቋው ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በአጫጭር ሥልጠናዎች ሲሰጥ መቆየቱም ለጉባኤተኛው ገልጸዋል።

ጉባኤው ላይ ታድመው ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ሊቅ ዶክተር ሥርግው ገላው የጎንደር ህዝብ ለአራት መቶ አመታት የግዕዝ እውቀትና ትምህርት በመዲናይቱ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ላበረከተው አስተዋጽኦ ወደር የሌለው ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ አንስተው የበጎ ሰው ሽልማት የሚገባው ነው ሲሉም አመስግነዋል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የዕለቱ የክብር እንግዳና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ብዙነሽ መሠረት ናቸው። ጉባኤው በመጀመሪያ ቀን ውሎው በሊቃውንት ቅኔ ታጅቦና ደምቆ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ በአባ በአማን ግሩም “በተመረጡ የግዕዝ መዛግብት የሥነ ምግባር አስተምሮ እንደ ማሳያ” በዶክተር ሙሉቀን አንዷለም “የግዕዝ ቅኔ ለግብረ ገብነትና ሥነ ምግባር ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ” በሚሉ የጥናት ፅሑፎች ላይ የጠዋቱን መርሐ ግብር ውይይት አድርጓል።

ከሰዓት በኋላም በተመሳሳይ በመምህር ላዕከማርያም ብርሃኑ “የግዕዝ ሀብት ግብረ ገብነት ለሀገረ መንግሥት ሥረዓት ግንባታ ያለው ሚና በግዕዝ ቅኔ ማሳያነት” በሚል በመምህርት አዲሴ አያሌው ደግሞ “የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ሀብት ለግብረ ገብነትና ፍልስፍና ያለው ፋይዳ ከሀተታ ዘ ዘርዕ ያዕቆብ እና ከአንጋረ ምሳሌ ግዕዝ መጻሕፍት አንፃር” በሚል የጥናት ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል። በጠዋቱ መርሐ ግብር መምህር አሸናፊ ምህረት በከሰዓቱ ደግሞ ዶክተር ዮሐንስ አድገህ የመጀመሪያውን ቀን ውሎ ውይይት መርተዋል።

ይህ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲና በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቅንጅት የተዘጋጀው ጉባኤ በዛሬው ዕለትም ቀጥሎ ሲውል የባህር ዳር ዩኒቨርስቲው ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲው ሊቀ ህሩያን ተግባሩ አዳነ ዶክተር ሥርግው ገላውና ዶክተር ጥበበ አንተነህ የውይይት መነሻ የጥናት ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ጉባኤው በግዕዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጂም ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

(ፎቶዎቹን የተጠቀምነው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የፌስ ቡክ ገፅ ነው።)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top