Connect with us

529 ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ ተደረገ

529 ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ ተደረገ
ኢዜአ

ዜና

529 ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ ተደረገ

529 ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ ተደረገ

በምስራቅ ጎጃምና ሰሜን ወሎ ዞኖች በድብቅ ሊካሄድ የነበረ የ529 ያለ እድሜ  ጋብቻ እንዲቋረጥ መደረጉ ተገለጸ። በምስራቅ ጎጃም ዞን ሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች መምሪያ የሴቶች ማደራጃ እና ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ዳግማዊ ገበየሁ ለኢዜአ እንደተናገሩት ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ያለ እድሜያቸው እየተዳሩ ነው።

ችግሩን የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ለውጥ እየመጣ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በጉዳዩ ዙሪያም ትምህርት፣ ጤናና የፍትህ ተቋማት ተቀናጅተው ዘንድሮ ባደረጉት እንቅስቀሴ  ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ሊዳሩ የነበሩ 480 እድሜአቸው ያልደረሱ ልጆች ጋብቻ  ከወላጆቻቸው ጋር በመወያየት ማቋረጥ መቻሉን ገልጸዋል

ሆኖም መረጃ ፈጥኖ ባለመድረሱ  የ90 ህፃናት ጋብቻ መፈፀሙን ጠቅሰው፤ በህግ ለማስጠየቅ ቢሞከረም የማስረጃ ክፍተት የሚገባውን ያህል ተጠያቂ ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።

በቀጣይም የቅንጅት መጓደሉን ክፍተት በማስተካከል ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ጥረት እንደሚደረግ ቡድን መሪው ተናግረዋል።

በጎዛምን ወረዳ የቸር ተከል ቀበሌ አርሶ አደር ባወቀ ክብረት በሰጡት አስተያየት ”እኔ እንደ ባህሉ ልጄን ድሬ ዘመድ አዝማድ  ጠርቼ መደሰት እና ማስደሰት እፈልግ ነበር” ብለዋል።

ሊድሯት የነበረች ልጃቸው 18 ዓመት ያልሞላት በመሆኑ ባለሙያዎች በልጅቱ ጤናም ሆነ ስነ ልቦና ትጎዳለች ብለው በመከሯቸው መሰረት ጋብቻው እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን  ገልጸዋል።

የልጅቱም ፍላጎት እንዳልነበራት ጠቅሰው፤ ከዚህ በኋላ ግን ያለልጅቱ ፈቃድ ለመዳር አላስብም፤  ትምህርቷን በማስጨረስ በራሷ የመወሰን እድል ሰጥቻታለሁ ብለዋል።

በደባይ ጥላን ግን ወረዳ የአሰንዳቦ ቀበሌ አርሶ አደር ስማቸው ካሴ በበኩላቸው  የ11 ዓመቷን ህፃን የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሆና እያለ ሁለተኛ ድግስ ላለመደገስ  ብለው ከታላቅ ወንድሟ ጋር አብረው መዳሯን ተናግረዋል።

ተማሪ ናት ተብላ ሳትዳር ብትቀር በአካበቢው ወግና ባህል መሰረት ቁሞ ቀር የሚል ሃሜት እንዳይደርስባት በሚል ጋብቻውን መፈፀሙን ገልጸው ፤ ስህተት መሆኑን ጋብቻው ከተፈፀመ በኋላ ተፀፅቻለሁ ብለዋል።

በተመሳሳይ በሰሜንወሎ ዞን እድሜያቸው ለጋብቻ ሳይደርስ በድብቅ ሊዳሩ የነበሩ የ49 ህፃናት ጋብቻ መቋረጡን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ዐቃቤ ሕግ መምሪያ ሃላፊ አቶ አምባው መላኬ ናቸው።

ይህም ሆኖ  መመሪያን ተላልፈው የሶስት ህጻናት ጋብቻ  እንዲፈጸም ያደረጉ ወላጆች በፖሊስ ተጣርቶ ክስ በመመስረት እንዲቀጡ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ጋብቻውን የፈፀሙት የሴት ልጅ አባትና የወንድ ልጅ አባት ከሁለት ወር እስከ አንድ ዓመት ከሁለት ወራት  እስራት እና እስከ አንድ ሺህ ብር መቀጣታቸውን አመልክተዋል።

ጋብቻው እንዲሰረዝ ለተቆጣጣሪ አካላት መመሪያ መተላለፉን አቶ አምባው አስታውቀዋል።

በዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ቡድን መሪ አቶ እጅጉ በላይ ያለ እድሜ ጋብቻን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በየደረጃው በተዋቀረ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ጥምር ኮሚቴ፣ በሴቶች የልማት ቡድንና በልጃገረዶች ክለቦች አማካይኝነት እንደሆነ  አስረድተዋል።

በአካባቢው  ህፃንነት የመዳር  ልምድ እንዲቀር  እየተሰራ ቢሆንም አሁንም ችግሩ እንዳለ ጠቁመዋል።

ያለእድሜ ጋብቻ በህፃናት ስነ ልቦና ላይ የሚየደርሰው  ጫና ከባድ መሆኑን በመረዳትም የሚመለከታቸው አካላት ድርጊቱን ለመግታት እንዲያግዙ መልዕክት አስተላልፈዋል።(ኢዜአ)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top