Connect with us

በኑሮ ውድነት ተመትተን በወንበዴ የምንገደል ከተሜዎች፡፡

በኑሮ ውድነት ተመትተን በወንበዴ የምንገደል ከተሜዎች፡፡
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

በኑሮ ውድነት ተመትተን በወንበዴ የምንገደል ከተሜዎች፡፡

በኑሮ ውድነት ተመትተን በወንበዴ የምንገደል ከተሜዎች፡፡

ወንጀልና ህገ ወጥ ድርጊት የኢትዮጵያ ከተሞች መገለጫ ሆኗል፡፡

(በድሬ ቲዩብ ሪፖርተር)

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ የታወቀ ወጣት በወንጀለኞች ተገድሏል፡፡ አዲስ አበባ በጎዳናዋ ላይ የሰው ህይወት ይህንን በመሰለ መልኩ ሲጠፋ እንግዳ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፉን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የሚመሩት ግለሰብ አደባባይ ላይ ሞተው ተገኝተዋል፡፡ ታዋቂው ድምጻዊም ህይወቱን ያጣው መዲናይቱ ጎዳና ላይ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ከተሞች ሥራ አጥ የበዛባቸው ናቸው፡፡ ቤት እጥረቱ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ኑሮ ውድነት በከተሞች እጅግ ከፍቷል፡፡ ይሄ ሁሉ ተዳምሮ የተመታው የከተማ ነዋሪ በወንበዴ የሚገደል፣ በወንበዴ የሚደበደብ በቀማኛ የሚነጠቅ ሆኗል፡፡

የአዲስ አበባ ደንብ አስከባሪዎች ጎዳና ላይ ሚዛን አስቀምጦ ተመዘን የሚል ዳቦ ፈላጊን ሲያሳድዱ የአዲስ አበባ ሰው ሞባይሉን የሚነጥቅ ሌባ ያሳድደዋል፡፡ የከተማው ሰው አሳዳጁን የሚያሳድድለት አጥቷል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ምሽት መንቀሳቀስ እየከበደ የመጣባቸው ቦታዎች በዝተዋል፡፡ ቀንም ቢሆን የመኪና ስርቆቱ ጭምር ተፋፍሟል፡፡ ከንቲባ ታከለ ኡማ በሞተር የታገዘውን ዝርፊያ አብርደውት ቢሄዱም በየመንደሩ ያለው ቀምቶ አዳሪ ቁጥር ጨምሯል፡፡ የተሰረቀ ሞባይል ሊመለስ የሚችልበትና ሰራቂውን ማደን የሚቻልበት ቴክኖሎጂ ቢኖርም ምስጢር ነው፡፡ ፖሊስና ቴሌ ቴክኖሎጂውን ታግዘው ለሞባይል ቀፎ ሲባል የሚቀጠፍን ህይወት መታደግ አልቻሉም፡፡

ለምሳሌ የተሰረቀ ሞባይል ሌላ ሲምካርድ ሲገባበት የሚታወቅበት የተሰረቀ ሞባይል የሚገዛ ሰው በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት እድልና ቴክኖሎጂው አለ፡፡ ይሄንን መተግበር መቻልና ለህዝብ ይፋ አድርጎ አሰራሩን ተግባራዊ ማድረግ ቢቻል ነጥቆ ለመብላት የሚፈልገውን ቁጥር በእጅጉ መቀነስ ይቻል ነበር፡፡

በሌላ በኩል ኮሚውኒቲ ፖሊስ ተብለው በየሰፈሩ የተቀለሱ ጎጆዎች አሁን ወና ሆነዋል፡፡ ዝርፊያና ንጥቂያዎቹ ከጎሮኖ ወጥተው ታክሲ ተራና አደባባይ መፈጸም ጀምረዋል፡፡ እንዲህ ያለው ዓይን ያወጣ ውንብድና የአዲስ አበባ ብቻ መገለጫ አይደለም፡፡ ባህር ዳር ሀዋሳ አዳማና መሰል ከተሞች የነዋሪዎቹ ስቆቃ ተሰምተዋል፡፡

የአዲስ አበባው ወጣትና ቴዲ ቡናማው በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ለጋ በተመሳሳይ መልኩ ህይወትን ለማሸነፍ ስራ ላይ እያለ በጩቤ ወግተው ገደሉት፡፡ የብዙ ሰዎች እጣ ፈንታ ነው፡፡ ተዘርፎ የሚገባውና ተደብድቦ የሚደማው ብዙ ነው፡፡ ፖሊስ ጣቢያም ብሄድ ተስፋ የለውም ብሎ የወንጀል ድርጊትን በጸጋ የሚቀበለው ነዋሪ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በብዙ የሀገራችን ከተሞች ነዋሪዎች ያልሞቱት እንቅስቃሴያቸውን ስለገደቡ እንጂ ከተሞቹ ፍጹም ሰላማዊ ስለሆኑ አይደለም፡፡

በሰለጠነ ዘመን አታምሽና በግዜ ግባ መርህ ሆኗል፡፡ ጋምቤላ ከተማ ሰው እንኳን ምሽት ቀን መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ የተደራጀ ቡድን አደባባይ ላይ ሞባይሉን ይነጥቀዋል፡፡ ማጅራቱን ይመታዋል፡፡ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች እግራቸውን በመሰብሰብ ብቻ ነው ችግሩን ተቋቁመው እየኖሩ ያሉት፡፡ በከተማህ ወክ የማትሄድበት ልጆች አደባባይ የማይወጡበት ጎዳና ላይ ስልክ የማይወራበት ከተማ መኖር ምን ያህል መራር እንደሆነ ማሰብ ነው፡፡

የአደባባይ ንጥቂያ ዝርፊያና ግድያዎች አልባት ካላገኙ ውለው አድረው ወደ ቤት ለቤት መቀየራቸው አይቀርም፡፡ ሀገር ሲወድቅና ህግ ሲፈርስ እንዲህ ነው፡፡ ወንጀል ቅጡን ሲያጣ ቅጥ ያጣ የመከላከል እርምጃ ጭምር መውሰድ ያስገድዳል፡፡ ምርጫ ላይ ድምጽ ይነሳኛል ብሎ የጎዳናውን ወንበዴ መብት መስጠት ቀጥሎ የሚመጣውን መራር ያደርገዋል፡፡

መንግስት አሁን በቃ ሊል ይገባል፡፡ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ መንግስት ተራ ቀማኛን አደብ አስገዝቶ ዜጎቹን ካልታደገ እሱም የሚሰበስበው ግብር እንደ ወንበዴዎቹ ከደሃ የነጠቀው ሀብት መሆኑን ሊረዳ ይገባል፡፡

እናም የከተሞች ስቆቃ፣ የነዋሪዎች አበሳ የወንበዴዎች እንደልብ መሆን ይብቃ!!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

To Top