Connect with us

#የአብን_ማሳሰቢያ!!

የአብን መግለጫ
አብን

ዜና

#የአብን_ማሳሰቢያ!!

#የአብን_ማሳሰቢያ!!

በአማራ ሕዝብ ላይ በወለጋ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የኦሮሚያ ብልጽግና አመራሮች የአደባባይ ፍረጃ ውጤት መሆኑን አብን ይገነዘባል!

ከየካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ አማራዎች ላይ ማንነትን መሰረት ባደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት ከ60 በላይ ወገኖቻችን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ታርደውና ተጨፍጭፈው ተገድለዋል፤ በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው ለችግር ተጋልጠው ይገኛሉ።

በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ለማሳየት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች በተደረገ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ የኦሮሚያ ብልጽግና አመራሮች የአማራን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፈርጀው «ነፍጠኛ ይውጣ!» የሚል ግልፅ ቅስቀሳ አድርገው አሁን እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ስጋታችንን ገልፀን ነበር ።

ይኼን ተከትሎም በወቅቱ ድርጅታችን አብን ለመንግስትና ለሚመለከታቸው አካላት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊፈፀም ስለሚችል ተገቢውን የሕግ ከለላ እንዲያደርግና የዘር ፍጅቱን በሚያነሳሱ አመራሮች ላይ ተገቢውን አስተማሪ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበን ነበር።

ሆኖም በተደጋጋሚ የሰጠነውን ማሳሰቢያ ትኩረት ባለመስጠቱና ሕዝባችን ሕጋዊ ከለላ ባለማግኘቱ መንግስታዊ መዋቅሩ ጭምር በቀጥታ የሚሳተፍበት ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመ ይገኛል።

በሕዝባችን ላይ ለተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በአደባባይ በሕዝባችን ላይ የዘር ማጥፋት እንዲፈፀም ያነሳሱ የኦሮሚያ ብልጽግና አመራሮች፣ ሕዝባችንን ከጥቃት መከላከል ባለመቻልና ባለመፈለግ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጸጥታ አካላት በተለይም የኦሮሚያ ክልል መንግስት እንዲሁም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ለማስቆም ፍላጎት ያላሳየውና ኃላፊነቱን ያልተወጣው የፌደራል መንግስት ኃላፊነቱን ይወስዳሉ።

ከአሁን ቀደም በማይካድራ፣ በመተከልና በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በሕዝባችን ላይ የተፈፀሙትን ጅምላ ጭፍጨፋዎች እንኳ መነሻ ያደረገ የዘላቂ መፍትኄ ፍለጋ ባለመደረጉና በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ ባለመወሰዱ፣ በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል እየታየ ያለው ለከት የለሽ ቸልተኝነት ዛሬ በወለጋና የተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳደረገ አብን ያምናል።

ስለሆነም ብልጽግና የሚመራው መንግስት በሕዝባችን ላይ የሚፈፀመውን ጅምላ ጭፍጨፋ ለማስቆም ፍላጎት የሌለውና መንግስታዊ መዋቅሩ በአማራ ጥላቻ የናወዘ መሆኑን በመረዳት እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቆም ሁሉም ኢትዮጽያውያን በጋራ እንድንቆም አብን ጥሪውን ያቀርባል።

አማራውን ማስያዥያ ያደረገው የጥላቻና የጽንፈኛ ፖለቲካን ግበዓተ መሬት መፈፀም ስላልተቻለ የአማራ ሕዝብ ጅምላ ሞት በቁጥር ሪፖርት ዙሪያ እየታጠረ የመጣና በኢትዬጵያ ውስጥ በስሜት ላይ ጫና የማይፈጥር መደበኛ ክስተት ለመሆን በቅቷል።

ከዚህ አዙሪት ለመውጣትና ለረጅም ዘመናት ሳይቋረጥ የቀጠለውን ተደጋጋሚና ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀል በዘላቂነት ለመከላከል በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ መላው ሕዝባችን በየአካባቢው፣ በየደረጃውና በየአደረጃጀቱ በፅኑ እንዲመክርበት አብን ጥሪውን ያቀርባል። አብን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣትም የበኩሉን የተጠናከረ ትግል እንደሚያደርግ ለመግለፅ ይወዳል።

በሕይወት መኖር ሳይቻል ሌላ ማኅበራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ህልምን ማሳካት እንደማይቻል የሚታወቅ ነው። በሰብዓዊ መብቶች ረገድ ከኢትዬጵያ መልክዓምድር መካከል አከባቢ፣ አቅጣጫና ዘር እየለዩ ትኩረት የሚያደርጉ ተቋማት እጅግ አሳፋሪ፣ ወገንተኛና በታሪክ የሚያስጠይቅ ስምሪታቸውን በአስቸኳይ እንዲያስተካክሉ አብን ያሳስባል።     

በመጨረሻም የዘር ፍጀት ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማር እያልን፤ ለመላው የአማራ ሕዝብም መጽናናትን እንመኛለን።

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top