Connect with us

በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከምርጫ ጋር ተያይዞ የመረጃ ነፃነት ህግ አተገባባርን ክትትል ማድረግ ጀመረ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

ዜና

በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ

“የፍርድ ቤትን የዋስትና ውሳኔ/ትዕዛዝ ወደ ጎን በመተው ተከሳሽን በእስር ማቆየት በሀገሪቱ ለሥርዓተ አልበኝነትና ….ለህገ-ወጥነት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል”

***

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸምን  እና ትኩረት በሚሹ ወቅታዊ ሁኔታዎች አስመልክቶ የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ

መግቢያ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 1142/2011 እና በመገናኛ ብዙሀንና መረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 በክፍል ሶስት ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ምክረ-ሃሳብ የመስጠት እና የማሳሰብ እንዲሁም መንግሰት በግልጸኝነት እና በተጠያቂነት መርህ መሰረት መስራቱን የመከታተልና የመቆጣጠር እንዲሁም በህገ መንግሥትና በሌሎች የሃገሪቱ ህጎች የተረጋገጡ የሰዎች መብቶችና ነጻነቶች በአስፈጻሚ አካላት እንዳይጣሱ የመከላከልና ተጥሶም ሲገኝ በአፋጣኝ እንዲታረሙ ህግን መሠረት ያደረገ ምክረ ሐሳብ የማቅረብ በዚህም በህግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ መልካም የመንግሥት አስተዳደርን የማረጋገጥ ሃለፊነት ተሰጥቶታል፡፡

በዚህ ህግ ማእቀፍ መሰረት ተቋሙ ለህግ የበላይነት መከበር የድርሻውን ለመወጣት በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት የባላፉት ስድስት ወራትን እንዲሁም ባላፉት አመታት ለመልካም አስተዳደር መንስኤ የሆነ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ በተለይ ዘንድሮ በሚካሄደው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመልካም አስተዳደር ጉዳይ አንዱ እና ዋንኛ የመፎካከሪያ አጀንዳ ማድረግ ይችሉ ዘንድ ማሳሰብን ጭምር ታሳቢ በማድረግ ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ ወይም ፕሬስ ሪሊዝ ማውጣት አስፍልጓል፡፡ 

በዚህ መሰረት የመልካም አስተዳደር ችግሮችና መንስኤዎችን እንዲሁም የመንግሰትን ትኩረት የሚሹ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ይህ መግለጫ ተዘጋጅቷል፡፡

  1. የመልካም አስተዳደር ወይም የአስተዳደር በደል መንስኤ ችግሮች

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስተዳደራዊ በደሎችን በመመርመር የመፍትሄ ሃሳብ የሚሰጥ ሲሆን ባላፉት አመታት ማለትም (ከ2011- 2013 ግማሽ ዓመት) ወደ ተቋሙ ከመጡ አቤቱታዎች መካከል 52 በመቶዉ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ የደረሱ አስተዳደራዊ በደሎች ሲሆኑ 34 በመቶ ከመሬት ወይም ከይዞታ ጋር የተያያዙ እና 13 በመቶ ከቀበሌ ቤቶች ኢፍትሀዊነት ጋር በተያያዙ የሚደርሱ አስተዳደረዊ በደሎች ናቸው፡፡ 

ስለዚህ አብዛኛው (52 በመቶ) የመልካም አስተዳደር ችግርች ወይም የአስተዳደር በደል መንስኤ በመንግሰት ተቋማት ወይም በመንግሰት አስፈጻሚ አካላት ተገቢ ወይም ፍትሃዊ አግልግሎት ባለመስጠት የተከሰቱ፤ 34 በመቶ መሬት ነክ ጉዳዮችና ለልማት ተነሺ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ ወይም በቂ ካሳ ካለመክፈል ጋር በተያያዘ የተከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ የመንግሰት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ከዜጎች ፍላጎት ጋር የተጣጣመ በግልጸኝነት በተጠያቂነት መርሆዎች እና ተቋማቱ ባወጡት የአገልግሎት አሰጣጥ  ስታንዳርድ መሰረት እየሰሩ ስለመሆናቸው አሰራራቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡

በመንግሰት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ከሚደረሱ የአስተዳደራዊ በደሎች በመቀጠል የአስተዳደር በደል መንስኤዎች ከመሬት እና ከካሳ ክፍያዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከመሬት  ጋር የሚነሱት ጉዳዮች ከመሬት የባለቤትነት መብት እና ዋስትና ማጣት ጋር ይያዛሉ፡፡ ምንም እንኳን በሀገራችን የመሬት ስሪት ስርዓት የፖሊሲ ጉዳይ ሳይሆን ህገ- መንግስታዊ ድንጋጌ በመሆኑ የዜጎች የመሬት ባለቤትነትና የዋስትና ጉዳይ አከራካሪ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከመሬት እና ለልማት ተነሺዎች ካሳ አከፋፈል ጋር ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንግሰት ፖሊሲዎቹን ህጎችን እና አሰራሮች  ጥናት ላይ ተመስርቶ ሊያጤነው ይገባል፡፡

  1. ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር

2.1. እርዳታ እና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በተመለከተ

የህወሀት ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ በፈፀመው ኢሰብአዊ ድርጊት መነሻነት መንግስት የወሰደው ህግ የማሰከበር እርምጃ በድል መጠናቀቁን ተከትሎ በክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር በማቋቋም ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሰብኣዊ እርዳታና ድጋፍ መደረጉ እንዲሁም የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በመንግስት በኩል የተሰሩ ስራዎችንና እየተደረገ ያለውን ጥረት ተቋማችን ከበሬታ ይሰጣቸዋል፡፡ 

በአንጻሩ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለይ የትምህርት፣  የጤና እና የጸጥታ ተቋማት እጅግ አንገብጋቢና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንደ መሆቸው መጠን በመንግስት የተለየ ትኩረት እንዲሠጣቸው ለማመላከት እንወዳለን፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ስድሰተኛው ሀገር አቀፍ እና የክልል ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ መንግስት ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት፡፡ በመሆኑም ለምርጫው በሚሰጠው ትከረት ሳቢያ ትግራይ ክልል እና በአማራ ክልል ጎንደር አካባቢ የሚገኙ እንዲሁም በመተከል እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የመንግስትን ሰብአዊ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ትኩረት እንዳይነፈጋቸው የሚመለከታቸው የመንግሰት አሰፈጻሚ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ ምክረ-ሃሳብ እናቀርባለን፡፡     

2.2. በፍርድ ቤት የሚሠጡ የዋስትና መብቶችን በተመለከተ

የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት ለተያዙ ሰዎች ከሚያረጋግጣቸው መሠረታዊ መብቶች መካከል  የዋስትና መብት አንዱ ነው፡፡ በህገ- መንግሥቱ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 6 ሥር  እና በሥራ ላይ ባለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ- ሥርዓት ህጉ በግልጽ እንደተመለከተው ማንኛውም የተያዘ ሰው በዋስ የመፈታት መብት ያለው ሲሆን በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ ፍርድ ቤት በተያዙ ሰዎች የሚቀርብለትን በዋስትና የመለቀቅ ጥያቄ ተቀብሎ ከመረመረ በሃላ ዋስትናውን ሊነፍግና ሊገድብ እንደሚችል ወይም በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ አስቀርቦ የመፍቻ ትዕዛዝ የመስጠት ሥልጣን አለው፡፡ 

በዚህም ሥልጣን ባለው የሥር ፍርድ ቤት የተሰጠን የዋስትና መብት በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ/ትዕዛዝ ሊታገድ እንደሚችል ተቋማችን ልብ ይለዋል፡፡ በፍርድ ቤት የተላለፈን የዋስትና ውሳኔን/ትዕዛዝን የማገድ፣ የመለወጥ ወይም የማሻሻል ሥልጣን የፍርድ ቤትና የፍርድ ቤት ብቻ ሲሆን ይህንን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተቀበለ ማንኛውም የሕግ አካል ወይም ህግ አስፈጻሚ በእጁ ላይ የሚገኝን የትኛውንም ተጠርጣሪ የመልቀቅ ግዴታ አለበት፡፡ በሥራ ላይ ባለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህግ በግልጽ እንደተመለከተው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የደረሰው ፖሊስም የዋስትናው ወረቀት እንደተፈረመና ሌሎችም ፎርማሊቲዎች እንደተሟሉ በአፋጣኝ ተከሳሽን የመልቀቅ ህጋዊ ግዴታ አለበት፡፡

የፍርድ ቤትን የዋስትና ውሳኔ/ትዕዛዝ ወደ ጎን በመተው ተከሳሽን በእስር ማቆየት በሀገሪቱ ለሥርዓተ አልበኝነት እና ባልተገባ መንገድ ፍትህን ለማግኘት ለሚደረግ ህገ-ወጥነት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም በተጨማሪ በእርግጥም  ግልጽ  የአስተዳደር በደል መሆኑን ተቋማችን በሚገባ ይገነዘባል፡፡

የሀገራችንን የፍርድ ቤት ውሎን አስመልክቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ከሚቀርቡልን ጥቆማዎችና ከምንሰማቸው እንግዳ መሳይ ክስተቶች መካከል ፍርድ ቤቶች ወይም ዳኞች ግራ ቀኙን ተመልክተው ተከሳሾች ተጠርጥረው የተያዙበትን ጉዳይ ካመዛዘኑ በኋላ የሚሰጧቸው የዋስትና መብቶች ተፈፃሚነት በአስፈጻሚ አካላት ወይም በፖሊስ መስተጓጎሉን ነው፡፡

ለዚህም ማሳያ ከሆኑት የፍርድ ቤት ውሎዎች መካከል በተለያየ ወቅት በሀገሪቱ አንዳንድ  አከባቢዎች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ ለደረሰው የህይወትና የንብረት ውድመት ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ያቀረቡትን የዋስትና መብት ከመረመሩ በኋላ ተጠርጣሪዎች የክስ ሂደታቸውን በውጪ ሆነው መከታተል ይችላሉ ሲሉ የአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት፣ የአዳማ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት፣ የሱሉልታ ከተማ ፍርድ ቤት የሰጧቸዉ ውሳኔዎች ተፈፃሚ አለመሆንን መጥቀስ ይቻላል ፡፡ 

በዚህም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጣቸውን የዋስትና መብት ተጠቅመው የተጠየቁትን የዋስትና ማስያዣ ቢያሟሉም ፖሊስ ግን የፍርድ ቤትን ትእዛዝ መፈጸም አለመቻሉ ወይም ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱንና የህግ የበላይነትን አደጋ ውስጥ ይጥላል፡፡ ስለዚህ የህግ የበላይነት መከበር የሚረጋገጠዉ  የህግ አውጪው የህግ አስፈጻሚው የህግ ተርጓሚው እና መላ ህዝቡ የሀገሪቱን ህጎች ማክበር እና ማስከበር ሲችሉ ብቻ ነውና በዚህ ረገድ እየተከሰቱ ያሉ የጠቀስናቸዉና ተመሳሳይ ችግሮች ከፍተኛ የማስተካከያ እርምጃ ሊደረግባቸዉ ይገባል ተቋማችንም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ አዝማሚያዎች ከወዲሁ ሊታረሙ እንደሚገባቸው በጽኑ ያምናል።

ማጠቃለያ

ዘንድሮ የሚካሂደው ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ መሆን የሚችለው ሁሉም የምርጫ ተዋናዮች መራጩን ህብረተሰብ ጨምሮ በሀሳብ የሚያምንና የተሻለውን ሀሳብ በመግዛት ድምጽ መስጠት ሲችል ነው፡፡ 

ይህ ሁኔታ የበለጠ ስኬታማ የሚሆነው የህግ የበላይነት በየትኛውም መመዘኛ ለድርድር መቅረብ ሳይችል ሲቀር እና  የመገናኛ ብዙሃን የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሃሳብ ለመራጩ ህብረተሰብ በፍትሀዊነት እና በእኩልነት ማድረስ ሲችሉ ነው እንዲሁም ምርጫን ለማስተግበር የወጡ ህጎችና አሰራሮችም በአግባቡ መተግበር ይገባቸዋል፡፡

የተፎካካሪ ፓርቲዎችም የመልካም አስተዳደር ነጻ የዳኝነት እና የፍትህ ስርዓት የመንግስት አገልገሎት አሰጣጥና የህግ የበላይነት መከበር የምርጫ እና የመፎካከሪያ አጀንዳቸው እንደሚያደርጉት እምነታችን የጸና ነው፡፡

                      የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም

                  የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top